ዛሬ ‹‹የኢትዮጵያ ፊልም ከየት ተነስቶ የት ደረሰ›› በሚለው ሃሳብ ዙሪያ ጥቂት ለማለት ወደናል። ይህን ጉዳይ ስናነሳ ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የሲኒማቶግራፊ ባለሙያ የሆኑትን አበበ ቀፀላን እንግዳችን በማድረግ ነው። በዚህ የሙያ ዘርፍ በሰነድም ሆነ በሌላ አግባብ ትክክለኛውን ታሪካዊ እውነት ለማወቅ የሂደቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆኑትን ባለሙያ ማግኘት መታደል ነው። በቅድሚያ ጊዜያቸውን ሰውተው በጉዳዩ ዙሪያ ለመነጋገር በመፍቀዳቸው ምስጋናችንን በዝግጅት ክፍሉ ስም ለማቅረብ እንወዳለን።
የኢትዮጵያ ፊልም ታሪክ ከየት ወዴት
ፊልም በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ያለው ቢመስልም እውነታው ግን ከዚያም ያለፈ ነው። ይህን እውነት ግልፅ የሚያደርጉልን ደግሞ ሲኒማቶግራፈር አበበ ናቸው። ፊልም በአገራችን ከ1916 እና 1917 ዓ.ም ጀምሮ ታሪኩ ወደኋላ የሚመዘዝ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜም ሲኒማ በማሳየት መጀመሩን ይነግሩናል። ምንም እንኳን ከጅምሩ በተበታተነና ባልተደራጀ መንገድ ቢሆንም አብዮት ፈንድቶ መንግሥት በሚቀየርበት በ1967 የባህል ሚኒስቴር እንዲቋቋም ተደርጎ ቅርፅ ለማስያዝ ተሞክሯል።
በአፄ ኃይለሥላሴ የንግስና ዘመን ይህን መሰል እንቅስቃሴዎችን ፈር ለማስያዝ የሚሞክር የባህል ሚኒስቴር አለመኖሩ የተደራጀ የፊልም እንቅስቃሴ እንዳይኖር አድርጎታል። ሆኖም በወታደራዊው መንግሥት ልዩ ትኩረት ስላገኘ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሊቋቋም ችሏል። በ1968 ዓ.ም የፊልም ማዳበሪያና መቆጣጠሪያ የሚል ክፍል በባህል ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ስር እንዲደራጅ ተደረገ።
ወታደራዊው ስርዓት በከተማ ትርፍ ቤቶችን በሚወርስበት ወቅት አምባሳደር ሲኒማ ቤት ከአቶ ተስፋዬ ቀጀላ ተወርሶ በኪራይ ቤቶች ስር እንዲተዳደር ተደረገ። ይህ ቤት ለሲኒማ ማዳበሪያና መቆጣጠሪያ ክፍል ተሰጥቶ በስድስት ሰዎች ሥራ ተጀመረ። ከእነዚህ ውስጥ አምስቱ ባለሙያዎች ፊልም የመሥራት ሚና ላይ በቀጥታ ሲሳተፉ አንደኛው ባለሙያ ደግሞ የማከፋፈል ሚና እንዲኖረው ተደርጓል።
በወቅቱ የነበረው ስርዓት ፊልም መፍጠር የሚችለውን በጎ ተፅዕኖ መረዳት በመቻሉ ቀጥተኛ ድጋፍ ማድረጉን ቀጠለበት። በመዋቅርና በመስሪያ ቤት ደረጃ ቅርፅ እንዲኖረው በማድረግም ዓመት ሳይሞላ በሚሰጠው በጀት ታግዞ ዘመናዊ የዶክመንተሪ ፊልም ሥራ ጀመረ። የፊልም ሙያን ሩሲያ ተምረው በመጡ አቶ ተፈሪ ብዙአየሁ የተባሉ ሰው ‹‹ምርት ሦስት ሺ ሁለት›› የሚል ፊልም በ16 ሚሊሜትር ካሜራ ተሠርቶ ለእይታ በቃ። ይሄ ሥራ በናይጄሪያ ሌጎስ ከተማ በተካሄደ የኪነ ጥበብ ፌስቲቫል ላይ ተሳታፊ መሆን የቻለ የመጀመሪያው ፊልም ነበር።
ከዚያ ቀደም ግን በግለሰቦች ጥረት አሁንም ድረስ በታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ፊልሞች ተሠርተዋል። ከእነዚህ ውስጥ ‹‹ሂሩት አባቷ ማነው›› በ1957 ዓ.ም ኢላላ ኢብሳ በሚባሉ ሰው የፊልም ስክሪፕቱ ተፅፎ በአገር ውስጥ ተዋንያንና በውጭ አገር የቀረፃና ሲኒማቶግራፊ ባለሙያዎች ጥረት ለእይታ የበቃ ሲሆን ‹‹ጉማ›› የተሰኘው ፊልም ደግሞ በ1960 ዎቹ ተሠርቶ በ1964 ለእይታ የቀረበ ነው። እንደ ሲኒማቶግራፈር አበበ ገለፃ እነዚህ ፊልሞች የግለሰብ እና የውጭ አገር ዜጎች ተፅዕኖ ያረፈባቸው ሲሆኑ የፊልም ማዳበሪያና መቆጣጠሪያ ከመመስረቱ በፊት ለእይታ የበቁ ናቸው።
የኢትዮጵያ የፊልም ሥራ ታሪክ ቀስ በቀስ እያደገ መምጣቱን የአዲስ አበባ ዩኒርሲቲ መምህሩ ይነግሩናል። በ1971 ዓ.ም በቅርፅም በይዘትም ዕድገት አሳይቶ ፊልም ማዳበሪያና መቆጣጠሪያ የሚለውን መጠሪያ አስቀርቶ ‹‹የኢትዮጵያ ፊልም ማዕከል›› የሚል ስያሜን አገኘ። ቀድሞ የነበሩትን ሠራተኞች ጨምሮ 40 የሚደርሱ ባለሙያዎችን ማሳተፍ ጀመረ። አደረጃጀቱም ጠንካራ ከመሆኑ ባሻገር በጥበቡ ዘርፍ ትልቅ እመርታን ማሳየት ችሎ ነበር።
በወቅቱ ፊልም የሚሠሩ ሰዎችን በአንድ መስሪያ ቤት ከማሰባሰብ ባሻገር እውቀታቸውን በየጊዜው እንዲያዳብሩ ከፍተኛ እገዛ ይደረግ ነበር። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው አደረጃጀቱን እንዳሻሻለ ስድስት ሰዎችን ለተሻለ የትምህርት ዕድል ወደ ኬንያ በመላክና በማስተማር በካሜራ፣በፊልም ኤዲቲንግ፣ በፕሮዳክሽን እንዲሁም በድምፅ እውቀት እንዲይዙ ተደረገ።
‹‹በጊዜው ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ አገራቸው የመጡት ባለሙያዎች ከጀርመን፣ ቡልጋሪያ፣ ቺኮዝላቫኪያ አገሮች ጋር በጥምር በመሆን የተለያዩ ፊልሞች መሠራት ጀመሩ›› የሚሉት ሲኒማቶግራፈር አበበ ፤ ይህ ጥረት ውጤት ማምጣት በመቻሉ አምስት የኮሚሽን መስሪያ ቤቶች ኮሚቴ ያለበት አባላት ተቋቁሞ ጥናት በማድረግ ‹‹የኢትዮጵያ ፊልም ማዕከል›› ወደ ኮርፖሬሽን እንዲያድግ ተወሰነ። ታህሳስ 11 ቀን 1979 ዓ.ም ‹‹የፊልም ኮርፖሬሽን›› በሚል በአዋጅ እንዲቋቋም መደረጉን ይናገራሉ።
በጊዜው የፊልም ኮርፖሬሽን ተግባር ከተለያዩ አገራት ፊልሞችን ማስመጣትና ማሳየት፣ መሥራት፣ ማምረት እንዲሁም የተሠሩ ፊልሞችን ወደ ውጪ መላክ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በአገር ውስጥ በባህል እና በተለያዩ ዘርፎች ኢትዮጵያዊነትን የሚያሳዩ ዶክመንተሪ ፊልሞችን እንዲሠራ ስልጣን ተሰጥቶታል።
የወቅቱ ስርዓት ለፊልም ሙያ በእጅጉ ትኩረት መስጠቱን የሚያሳየው ሌላኛው ጉዳይ ላቋቋመው ኮርፖሬሽን የሚያደርገው ድጋፍ ነው። የፊልም ባለሙያዎች በእውቀት የደረጁ እንዲሆኑ ወደ ተሻሉ አገራት በመላክ ከማስተማሩና እውቀት ከማስጨበጡ ባለፈ 49 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በጀት ነበረው። ገንዘቡ ከወቅቱ ጉልበት አንፃር ሲመዘን በጣም ከፍተኛ መሆኑን ማንም ሰው መገንዘብ ይችላል። ከዚህ በጀት ውስጥ 19 ሚሊዮን ብሩ ለእቃ ግዢ (የካፒታል) የሚውል ሲሆን 40 ዶክመንተሪ፣5 ልብ ወለድ ፊልም እና 25 ሲኒማ ቤቶችን ለመገንባት እንዲውል ታስቦ የተበጀተ ነበር።
ሲኒማቶግራፈር አበበ እንደሚናገሩት የወቅቱ አመራሮች በዘርፉ ላይ ትልቅ አመኔታ አላቸው። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ እርሳቸውን ጨምሮ በውጭ አገር ተምረው የሚመጡ ባለሙያዎችን በማግባባት ቅጥር ፈፅመው ኮርፖሬሽኑን ጠንካራ ለማድረግ መጣጣራቸው ነው። በጊዜው ኮርፖሬሽኑ በማስተርስ ደረጃ ከራሺያ ተምረው የመጡ 12 ባለሙያዎች ነበሩት። እነዚህ ባለሙያዎች በራሳቸው ጥረት የፊልም ሙያን የተማሩ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ሦስት ባለሙያዎች ብቻ ናቸው አሁን በህይወት የሚገኙት። ግማሾቹ በወቅቱ በቀይ ሽብር ሲገደሉ አንዳንዶቹ ደግሞ በተፈጥሮ ህመም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
የኮርፖሬሽኑ ተፅዕኖ
ኮርፖሬሽኑ በይፋ ከተመሰረተ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ከጀርባም ከፊትም ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት ‹‹በህይወት ዙሪያ›› የተሰኘ አዲስ ፊልም (ጥቁርና ነጭ) በመሥራት ለእይታ ማቅረብ ቻለ። ሥራው በ16 ሚሊሜትር የተቀረፀ እና እጥበቱም አገር ውስጥ የተሠራ ነው። በዚህ ፊልም ላይ ሲኒማቶግራፈር በመሆን አቶ አበበ ቀፀላ በቀዳሚነት በመሳተፍ አሻራቸውን አኑረዋል።
ከዚህ ቀጥሎ የፊልም ኮርፖሬሽን ሠርቶት ለእይታ የበቃው እውቅ ፊልም ‹‹አስቴር›› የሚል ርዕስ የተሰጠው የመጀመሪያው ባለቀለም ፊልም ነው። በዚህ ሥራ ላይ ታሪኩን እያጫወቱን ያሉት ሲኒማቶግራፈር አበበ ከፍተኛ ድርሻ ተጫውተዋል። ይህ ፊልም ደረጃውን በጠበቀ በ35 ሚሊሜትር ካሜራ የተሠራ ነው። ዋናውን ሥራ ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ ባለሙያዎች በመሥራት ለእይታ ማቅረብ መቻላቸው ከፊልም አፍቃሪያን ትልቅ አድናቆትን እንዲቸራቸው አስችሎም ነበር። ይህም ለኢትዮጵያ ሲኒማ ግዙፍ መሰረት የጣለ መሆኑም ይነገርለታል። አስቴር በ1984 ዓ.ም ለእይታ ሲበቃና ሁሉም ሲኒማ ቤቶች ለተመልካች ሲያቀርቡት በኢንዱስትሪው ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ ትልቅ እንደነበር ያስታውሳሉ። በ500 ሺህ ብር አጠቃላይ ወጪ ተሠርቶ አንድ ሚሊዮን ብር ገቢና የ500 ሺህ ብር ትርፍ ማስገኘት ችሏል። በጊዜው የኢትዮጵያ ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር 29 ሲኒማ ቤቶችን ያስተዳድር ነበር።
የፊልም ኮርፖሬሽን መፍረስ
የፊልም ኮርፖሬሽን ከሁለት አስርት ዓመታት በዘለቀ መልኩ የተለያዩ ሥራዎችን ለኢትዮጵያ ሲኒማ መሰረት ከመጣል ጀምሮ ሲሠራ ቢቆይም በ1990ዎቹ መግቢያ እንዲፈርስ ተደርጓል። ይህ ደግሞ ስር ነቀል ለውጥ እያመጣ ወደ ኢንዱስትሪነት እየተንደረደረ የነበረበትን መንገድ እንዲገታ አደረገው። ባለሙያዎቹም ወደ ተለያዩ መስሪያ ቤቶች ተበተኑ።
በጊዜው ሲኒማቶግራፈር አበበ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የፕሮዳክሽን መምሪያ ኃላፊ እንዲሆኑ ተደረገ። እርሳቸው እንደሚሉት የኢትዮጵያ ፊልም ኮርፖሬሽን አነሳስ መልካም የሚባል እና ጥሩ መሰረት የጣለ ሆኖ ለፊልም ባለሙያዎችም መልካም ስነምግባርን አላብሶ በሙያቸው የተጉ እንዲሆኑ ያስቻለ ነበር። ይህ ሂደት ቢቀጥል ኖሮ አሁን የሚታየው የተበታተነና ወጥነት የጎደለው ሂደት አይኖርም የሚል እምነት አላቸው።
በወቅቱ በፊልም ተዋናይነት የሚሳተፉና አንቱ የተባሉ ባለሙያዎችን ማፍራት መቻሉን ሲኒማቶግራፈሩ ይናገራሉ። ከዚህ ውስጥ በምሳሌነት ሲያነሱ በአስቴር ፊልም ላይ በመሪ ተዋናይነት የሠራው ተፈሪ አለሙን ጨምሮ አብራር አብዱ፣ ጥላሁን ጉግሳ እና ኤልሳቤት መላኩ ይጠቅሳሉ። በቅርቡ የኢትዮጵያ ሲኒማ ከየት ወዴት በሚል በአምባሳደር ሲኒማ ቤት ለአራት ቀን በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይም እርሳቸው ከጠቀሷቸው ተዋንያን መካከል አንዱ አብራር አብዱ ንፅፅር ሲሠራ ከጥራትም ሆነ ከሙያ ስነምግባር አንፃር የቀድሞው እጅጉን የተሻለ እንደነበር አንስቷል።
ያስከተለው ችግር
የኢትዮጵያ ሲኒማ ቀድሞ በተጀመረው መሰረት ላይ መቀጠል ቢችል አሁን ያለው የአደረጃጀትና የወጥነት መጓደል እንደማያጋጥመው ብዙዎቹ ባለሙያዎች ይናገራሉ። የሲኒማቶግራፊ ባለሙያው አበበም ይሄንኑ ሃሳብ ይጋራሉ።እርሳቸው እንደሚሉት በኢትዮጵያ የሲኒማ ትንሳኤ የፈነጠቀው የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ ግዛት ነፃ ሳይወጡ አስቀድሞ ነው። በምሳሌነት በ1957 የተሠራው ሂሩት አባቷ ማነው የሚለውን ያነሳሉ። ቀዳሚው የፊልም ጅማሮ አሁን ግን እንደ ፈረስ ጭራ ወደ ኋላ እየሄደ መሆኑ ያስቆጫቸዋል።
‹‹የተወሰኑ ግለሰቦች ይህን ሙያ ለማዳከም ተንቀሳቅሰዋል›› የሚሉት ሲኒማቶ ግራፈሩ ጥረታ ቸው ተሳክቶላቸው እንዳፈረሱት ይናገራሉ። በተለይ አሁን ላይ የፊልም አሠራር ስነ ምግባር እንደተጣሰም ነው የሚገልጹት።አሁን የድምፅጽና የምስል ጥራቱ እጅግ ዝቅ ያለ መሆኑን በምሳሌነት ያነሳሉ። ወደቀድሞው ደረጃው ለመመለስ ተቋም እንደሚያስፈልግም ምክረ ሃሳብ ይሰጣሉ።
የኢትዮጵያ ሲኒማ ከየት ወዴት በሚል በተዘጋጀው ውይይት ላይ ቀድሞ የነበረውን አደረጃጀት መመለስ አስፈላጊ መሆኑን ከባለሙያዎች በአስተያየት መልክ ተነስቷል። የፊልም ባለሙያው ሲኒማቶግራፈር አበበም የቀድሞውን አደረጃጀት መመለስና ከእንደገና ስርዓቱን በተገቢው መንገድ ማሻሻል ወሳኝነት እንዳለው ለመወያያ ሃሳብ እንዲሆን ባቀረቡት ጥናት ላይ ጥቆማ አድርገዋል። በእርሳቸው ቀጥተኛ አባባል ‹‹የፈረሰው ተቋም ከተገነባ ስለ ኢትዮጵያ ሲኒማ እድገት መነጋገር ይቻላል፡፡››
አሁን ምን ላይ ነን
አሁን ላይ የሚሠሩ ፊልሞች ከጥቂቶቹ በስተቀር ዓለም አቀፍ ይዘት የጎደላቸውና ለውድድር ብቁ ያልሆኑ ናቸው። ይህን ሃሳብ የሚያነሱት ሲኒማቶ ግራፈሩ ፊልሞቹ የይዘት እና የጥራት ችግር አለባቸው ይላሉ። በሙያው በቂ ግንዛቤ የሌለው ማንኛውም ሰው በፊልም ሙያ ውስጥ እየገባ መሆኑ ያሳስባቸዋል። ‹‹ፊልም ለመሥራትና የሚፈለገውን መልዕክት ለማስተላለፍ የግዴታ ተሰጦውና እውቀቱ ያስፈልጋል›› በማለት ይህን ለማግኘት የራስ ጥረትን ጨምሮ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ያስፈልጋል የሚል ሃሳብ ያስቀምጣሉ።
ከላይ የተነሱትን ችግሮች ለመቅረፍ ትምህርት ቤቶችን ማሳደግና የፈረሰውን የቀድሞ ተቋም መመለስ እንደሚያስፈልግ ሲኒማቶግራፈር አበበ ቀፀላ በምክረ ሃሳባቸው ላይ አስቀምጠዋል። ይህ መሆን ከቻለ ምስቅልቅሉንና ብልሽቱን ከማስተካከል ባለፈ የኢትዮጵያን ሲኒማ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን ማስቻል ቀላል መሆኑን አመላክተዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 12/2012
ዳግም ከበደ