የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን በዚህ ዓመት የካቲት ወር መጨረሻ ላይ ማከናወን ለሚጀምረው የአፍሪካ አትሌቲክስ ቱር፣ ውድድሩን እንዲያዘጋጁ ከመረጣቸው ስድስት አገራት አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን አሳውቋል።
ይህንን አይነት ውድድር ለማዘጋጀት ከተፈለገበት ዋና ዋና ምክንያቶች መካከልም አፍሪካውያን አትሌቶችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያገለለ የመጣውን የዲያመንድ ሊግ ውድድር ጫናን ለመቋቋም በማሰብ መሆኑ ታውቋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙም ትኩረት የማይሰጣቸውና አፍሪካውያን አትሌቶች ውጤታማ የሆኑባቸውን የርቀት አይነቶችን ከፍ ባለ የጥራትና የፉክክር ደረጃ ለማዘጋጀት እንደሆነም ተገለጿል።
ከየካቲት 24 እስከ ግንቦት 24/2012 ዓ.ም በእያንዳንዱ አዘጋጅ አገር ለአንድ አንድ ቀናት የሚከናወነውን ይህንን የቱር ውድድር፡ ኮንጎ ብራዛቪል፣ ጂቡቲ፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካና ካሜሩን፡ ከኢትዮጵያ በተጫማሪ እንደሚያዘጋጁት ኮንፌዴሬሽኑ አስታውቋል። የውድድሮቹ ትክክለኛ ቀናትና የየዕለቱ የውድድር አይነቶችም በቀጣዮቹ ጊዜያት ይፋ እንደሚሆኑ የሚጠበቅ ሲሆን ጅቡቲ ብቻ ውድድሩን የካቲት መጨረሻ ላይ እንደምታስተናግድ ተረጋግጧል።
የዓለም አትሌቲክስ በ2020 የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች 3 ሺ ሜትር መሰናክል፣ 5 ሺ ሜትር፣ዲስከስ ውርወራ፣ ርዝመት ዝላይና ሁለት መቶ ሜትር ውድድሮችን መቀነሱ ይታወቃል። የአፍሪካ ቱር ውድድር አፍሪካውያን አትሌቶች በዳይመንድ ሊግ ያጡትን የውድድር ዕድል በመካስ ከፍ ባለ ደረጃ እንዲወዳደሩና ገንዘብ እንዲያገኙ እንደሚያስችል የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሐማድ ማልቦም ካልካባ ለዢኑዋ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ውድድሮቹን ከሚያዘጋጁት ከተሞች መካከል አዲስ አበባ፣ ናይሮቢ፣ ፕሪቶሪያና ያውንዴ ግንባር ቀደሞቹ ሲሆኑ የመካከለኛ ርቀት ተወዳዳሪው ኮከብ አትሌት አያልነህ ሱሌይማን አገር የሆነችው ጅቡቲ ውድድሩን ለማዘጋጀት የተመረጠች ያልተጠበቀች አገር መሆኗን ካልካባ ተናግረዋል። ኮንጎም 2015 ላይ የመላ አፍሪካን ጨዋታዎች ባዘጋጀችበት ብራዛቪል ከተማ ውድድሩን ታሰናዳለች።
የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ላይ በየአንዳንዱ ውድድር ያሸነፈ አትሌት አስር ሺ ዶላር ተሸላሚ ሲሆን አጠቃላይ አሸናፊ የሚሆነው አትሌት መጨረሻ ላይ ሃምሳ ሺ ዶላር ተሸላሚ ይሆናል። የአፍሪካ ቱር ውድድር በዚህ ረገድ የዓለም አትሌቲክስን ለመፎካከር በየአንዳንዱ ውድድር አሸናፊ ለሚሆነው አትሌት አምስት ሺ ዶላር ለመሸለም የተዘጋጀ ሲሆን በሂደት የሽልማት መጠኑን እየጨመረ ለመሄድ ማሰቡ ታውቋል። ውድድሩ አፍሪካውያን አትሌቶች ለ2020 ቶኪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት እንደሚረዳቸውም ኮንፌዴሬሽኑ ያለውን እምነት ገልጿል።
የአፍሪካ ቱር ውድድርን ለማካሄድ 2018 ላይ ሐሳቡ የመነጨ ሲሆን፣ በወቅቱ የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ናይጄሪያና ኮንጎ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ጋር በመተባበር በአምስት ከተሞች ለማካሄድ ነበር የታሰበው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 11/2012
ቦጋለ አበበ