የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት በኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ላይ ታህሳስ 7 ቀን 2012 ዓ.ም ተወያይቶ ለዝርዝር ዕይታ ጉዳዩ ወደሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል:: ረቂቅ አዋጁ ከያዛቸው ጭብጦች መካከል ለአብነት ያህል ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችን በተመረቱበት ዕድሜ ከ100 ፐርሰንት እስከ 500 ፐርሰንት ኤክሳይዝ ታክስ እንዲጣልባቸው የደነገገ ሲሆን የሰው ጸጉር፣ ዊግ፣ የውሸት ጺምና ቅንድብ፣ ሌሎችም አርቴፊሻል ማጌጫዎች 40 በመቶ ታክስ የተጣለባቸው መሆኑ በረቂቅ አዋጁ ተደንግጓል:: በተጨማሪም ማንኛውም ቢራና የአልኮል አልባ መጠጦች ድብልቅ 40 በመቶ፣ በአገር ውስጥ በበቀለ ገብስ የተመረተ ቢራ 35 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ተጥሎባቸዋል::
የአዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ዓላማዎች መካከል የኤክሳይዝ ታክስ ከተጣለባቸው ምርቶች ሊሰበሰብ የሚገባው ገቢ በትክክል ተሰብስቦ የአገሪቱን የልማት ዕቅዶች ለማስፈጸሚያ እንዲውል ማድረግ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት ነው:: ለጤና ጎጂ በሆኑ ምርቶች በተለይም በትምባሆ ላይ የተጣለው የኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔ አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት የእነዚህ ምርቶች ፍጆታ ስላልቀነሰ ምጣኔውን ማሻሻል ይጠቀሳል:: በተጨማሪም ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች በአካባቢ ደህንነት ላይ የሚኖረው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ከተወሰነ ዓመት በላይ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ወደአገር እንዳይገቡ መከላከል፣ መንግሥት ለልማት ሥራዎች ማስፈጸሚያ የሚውል ተጨማሪ ገቢ ማግኘት እንዲችል በተጨማሪ ዕቃዎች እና በአንዳንድ አገልግሎቶች ላይ ኤክሳይዝ ታክስ መጣል የሚሉ ይገኙበታል::
የማሻሻያው ዐብይ ጭብጥ
በሥራ ላይ የሚገኘው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቁጥር 307/1995 ኤክሳይዝ ታክስ ስሌት መሠረት የሚያደርገው የማምረቻ ወጪ መሆኑን የሚደነግግ ሲሆን “የማምረቻ ወጪ” የሚለው ሐረግም በአዋጁ ትርጉም ተሰጥቶታል:: በዚህ ትርጉም መሠረት “የማምረቻ ወጪ” የሚባሉት ለምርት ተግባር በቀጥታ የሚውሉትን ጥሬ ዕቃዎችና የጉልበት ዋጋ፣ ቀጥተኛ ያልሆኑ ግብዓቶች ወጪ እና ኦቨር ሄድ ወጪ ሲሆን በማምረቻ ወጪ ላይ የሚታሰበው የእርጅና ቅናሽ አይጨምርም::
ይሁን እንጂ ይህን “የማምረቻ ወጪ” የሚለውን ሐረግ ትርጉም ተገቢ ባልሆነ መንገድ በመጠቀም የኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልባቸውን ምርቶች የሚያመርቱ አንዳንድ ባለሀብቶች ተገቢውን ታክስ አይከፍሉም:: ከዚህም በተጨማሪ የታክሱ ባለሥልጣን ባለሙያዎች አንዳንድ ጊዜ የማምረቻ ወጪ ሊባሉ የሚችሉትን ወጪዎች ከማምረቻ ውስጥ በማውጣት አልፎ አልፎ ደግሞ የማምረቻ ወጪ ያልሆኑትን በማካተት የግብር ውሳኔ የሚሰጡ በመሆኑ ታክስ ከፋዮች ለከፍተኛ እንግልት የተዳረጉ ከመሆኑም በላይ መንግሥትም ተገቢውን ታክስ እንዳይሰበስብ ምክንያት ሲሆን ይታያል::
ይህንን ችግር ለማቃለል በረቂቅ አዋጁ የታክሱ ስሌት መሠረት የፋብሪካ መሸጫ ዋጋ እንዲሆን ተደርጓል:: የስሌቱ መሠረት የፋብሪካ መሸጫ ዋጋ እንዲሆን መደረጉ ለሁሉም የታክስ ዓይነቶች ወጥ የሆነ ስሌት መሠረት እንዲኖር በማድረግ አፈጻጸሙ ግልጽ እንዲሆን ያስችላል::
የታክሱ ስሌት መሠረት የፋብሪካ ዋጋ መሆኑ በታክስ ከፋዮች ላይ ጫናን ሊያስከትል ስለሚችል ጫናውን ለማቃለል በአንዳንድ ምርቶች ላይ የማስከፊያ ምጣኔው ማስተካከያ ተደርጎበታል::
በሥራ ላይ ያለው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ በአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃዎች ለሚመረቱ ምርቶች የሚሰጥ ድጋፍ አልነበረውም:: ይህ ባለመደረጉ ባለኢንዱስትሪዎች ጥሬ ዕቃዎችን ከውጭ አገር በማስገባት ላይ እንዲያተኩሩ አድርጓል:: ይህንን ለማስቀረት እንዲሁም የአገራችንን አርሶአደር ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ቢራ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች በአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃ (ገብስ፣ብቅል፣ ጌሾ ወዘተ) ተጠቅመው ምርታቸውን የሚያመርቱ ከሆነ ከሌላው ዝቅ ባለ የኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔ ታክሱን እንዲከፍሉ በረቂቅ አዋጅ ውስጥ ሐሳብ መቅረቡን አዋጁን ለማብራራት ለፓርላማው የቀረበው ሰነድ ያስረዳል::
የኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔ
በሥራ ላይ ባለው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ አገር ውስጥ በሚመረቱና ወደ አገር በሚገቡ 19 ዕቃዎች ላይ የኤክሳይዝ ታክስ ተጥሏል:: ከእነዚህ ዕቃዎች ውስጥ ለመኖሪያ ቤት አገልግሎት የሚውሉ የሣህን ማጠቢያ መሣሪያዎች፣ የቪዲዮ ዴክ፣ የጠረጴዛ፣ የግድግዳ እና የእጅ ሰዓቶች፣ አሻንጉሊቶችና መጫወቻዎች፣ ላይ ሲሰበሰብ የቆየው የኤክሳይዝ ታክስ አሁን በደረስንበት ደረጃ የቅንጦት ዕቃ ናቸው ሊባል የማይችሉ ይልቁንም ለህብረሰተቡ አስፈላጊ ሆነው በመገኘታቸው ከዝርዝሩ እንዲወጡ ተደርጓል::
በሌላ በኩል በተመሳሳይ ዕቃዎች ላይ የኤክሳይዝ ታክስ ተጥሎ ሳለ በዝርዝሩ ውስጥ ሳይካተቱ የቀሩ አገሪቱ ያላትን ወሳኝ የውጭ ምንዛሪ የምታፈስባቸው ሆነው ሳለ አስፈላጊ ያልሆኑና አጠቃቀማቸው ሊገደብ የሚገባ እንደቸኮሌት፣ አርተፊሻል ጸጉር፣ ፐርል፣ ወዘተ የመሳሰሉ ዕቃዎች በዝርዝርሩ ውስጥ ተካተው የኤክሳይዝ ታክስ እንዲጣልባቸው ሆኗል::
በአካባቢ ደህንነት (Environment) ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ አንዱና ዋናው የተሸከርካሪዎች የሚያመነጩት ካርቦን መሆኑ ይታወቃል:: በተለይም አሮጌ ተሽከርካሪዎች በከፍተኛ ደረጃ ካርቦን የሚያመነጩ በመሆኑ በአካባቢ ደህንነት ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ከፍተኛ ነው:: ከዚህም በተጨማሪ ያረጁ ተሽከርካሪዎች የመለዋወጫና የነዳጅ ፍጆታ ከፍተኛ በመሆኑ እነኚህ ተሽከርካሪዎች ለሚጠቀሙበት ነዳጅና መለዋወጫ አገሪቱ የምታወጣው የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ በሕይወትና በንብረት ላይ ለሚደርሰው የትራፊክ አደጋ ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው:: በእነዚህ ምክንያቶች የእነዚህ ዓይነት ተሽከርካሪዎች ወደአገራችን እንዳይገቡ ማድረግ የሚያስችል ሕግ ማውጣት የሚቻል ቢሆንም የዚህ ዓይነቱ እርምጃ በዓለም የንግድ ድርጅት ስምምነቶች የተከለከለ በመሆኑ አገሪቷ የድርጅቱ አባል ለመሆን በምታደርገው ጥረት ላይ እንቅፋት እንዳይፈጥር የተሻለ አማራጭ ሆኖ የተገኘው እንዳይገቡ የመከልከል ያህል ውጤት የሚኖረው የኤክሳይዝ ታክስ መጣል ነው:: በዚህም መሠረት ያገለገሉ ተሸከርካሪዎች ወጪያቸው እንዲንር በማድረግ ወደ አገር እንዳይገቡ የሚያስችል የኤክሳይዝ ታክስ በረቂቅ አዋጁ መደንገጉን ሰነዱ ያብራራል::
እንደ አብነት
አዲሱ ኤክሳይዝ ታክስ ከውጭ በሚገቡ መኪኖች ላይ ከ100% እስከ 500% ታክስ ለመጣል አቅዷል። ይህም ማለት:-
ከ0 – 1 ዓመት ያገለገሉ = 100%
ከ1 -2 ዓመት ያገለገሉ = 150%
ከ2 – 4 ዓመት ያገለገሉ = 200%
ከ4 -7 ዓመት ያገለገሉ = 300%
ከ7 ዓመት በላይ ያገለገሉ = 500% ኤክሳይስ ታክስ የሚጥል ሲሆን የሚሰላውም እንደሚከተለው ይሆናል::.
ለምሳሌ የ2012 ሞዴል Toyota Corolla ዋጋው 6ሺህ ዶላር ቢሆን ($6000*40 ብር= 240,000 ብር)
የመኪናው ማጓጓዥ 50ሺህ ብር፣ ኢንሹራስ 1ሺህ ብር ቢከፈል:-
240,000+50,000 (የትራንስፖርት ወጪ) + 1000(ኢንሹራንስ) = 291,000 (ጠቅላላ የግዥ ወጪ)
የጉምሩክ ቀረጥ= 291,000*35% = 101,850
ኤክሳይዝ ታክስ = (ጠቅላላ የግዥ ወጪ + የጉምሩክ ክፍያ)*500%
ኤክሳይዝ ታክስ = (291,000+101,850)*500% = 1,964,250
የመኪናው ወጪ የኤክሳይዝ ታክስን ጨምሮ= 1,964,250 ብር.
የተጨማሪ እሴት ታክስ = 1,964,250*0.15 = 294,637
የመኪናው ዋጋ ኤክሳይዝ ታክስና ቫትን ጨምሮ = 2,258,887
ሱር ታክስ = 2,258,887*0.10 = 225,887
ጠቅላላ ሱር ታክስን ጨምሮ = 2,484,776
ዊዝሆልዲንግ ታክስ= duty paying value *.03 (291,000*0.03) = 8,730
ጠቅላላ ዊዝሆልዲንግ ታክስን ጨምሮ = 2,493,506 ብር
በዚህ ስሌት መሠረት 240 ሺ ብር የተገዛች መኪና ወደ ኢትዮጵያ ገብታ ዋጋዋ የሻጩን ትርፍ ሳያጠቃልል 2 ሚሊዮን 493 ሺ 506 ብር ትሆናለች ማለት ነው። ሻጩ 10 በመቶ ብቻ የትርፍ ህዳግ ይዞ መኪናውን ቢሸጠው 249 ሺ 350 ብር ከ60 ሳንቲም ያስጨምራል:: ጠቅላላው የመኪናው መሸጫ ዋጋ 2 ሚሊዮን 742 ሺ 856 ብር ከ60 ሳንቲም ይሆናል ማለት ነው::
ከዚህ በፊት በነበረው የኤክሳይስ ታክስ ህግ ይኸችው መኪና ዋጋ 801,128.4 ብር የነበረ ሲሆን አሁን በረቀቀው የኤክሳይስ ታክስ ግን ዋጋው የነጋዴውን ትርፍ ሳይጨምር 2,493,506 የደረሰ ሲሆን ይህም ማለት የ 1,692,377 ልዩነት ይኖረዋል ማለት ነው። (Asmish Ethiopia – Negarit)
ኤክሳይዝ ታክስ ምንድነው?
የኤክሳይዝ ታክስ ቀጥተኛ ያልሆኑ ታክሶች ተብለው ከሚታወቁ በዕቃ እና አገልግሎት ላይ ከሚጣሉ ታክሶች ምድብ ውስጥ የሚገኝ ታክስ ነው:: የኤክሳይዝ ታክስ ዋና ዓላማዎች ለመንግሥት ተጨማሪ ገቢ ማስገኘት፣ በኅብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ምርቶች ፍጆታ መቀነስ፣ ከፍተኛ ሀብት ያላቸው ሰዎች ከሚጠቀሙባቸው የቅንጦት ዕቃዎች ላይ ገቢ በመሰብሰብ በድህነት አረንቋ የሚገኙ ዜጎችን ሕይወት ማሻሻል እና በአካባቢ ደህንነት ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ምርቶች አጠቃቀም መቀነስ ናቸው::
ኤክሳይዝ ታክስ የቅንጦት ዕቃዎች ሆነው ዋጋቸው ጨመረም፤ አልጨመረም መሠረታዊ በመሆናቸው ምክንያት የገበያ ፍላጎታቸው በማይቀንስ ዕቃዎች ላይ፣ እንዲሁም የሕብረተሰቡን ጤንነት የሚጎዱና ማህበራዊ ችግር የሚያስከትሉ ዕቃዎችን አጠቃቀም ለመቀነስ ሲባል የተጣለ ታክስ ነው::
ታክሱ በሀገር ውስጥ በሚመረቱና ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ በአንዳንድ የተመረጡ ዕቃዎች ላይ ብቻ የተጣለ ነው::
በዓለማችን ለመጀመሪያ ጊዜ ኤክሳይዝ ታክስ የተጀመረው በእንግሊዝ ፓርላሜንት በ1643 ሲሆን በወቅቱ የመንግስት ገቢን ከፍ ለማድረግ ታስቦ የተጣለ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ:: በኢትዮጵያም ታክሱ ከረጅም ጊዜያት ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን የመንግስትን የገቢ አቅም በማሳደጉ ረገድ የበኩሉን ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል::
ዓላማው ማህበራዊ ችግር የሚያስከትሉና የህብረተሰቡን ጤንነት የሚጎዱ ምርቶችን መቀነስ እንዲሁም የቅንጦት የሆኑ የፍጆታ እቃዎች ላይ ተፅዕኖ ማሳደር ነው:: የተሻለ ገቢ ያላቸው ሰዎች በሚጠቀሙባቸው እቃዎች እና የመግዛት ፍላጎታቸው በማይቀንስባቸው ምርቶች ላይ ታክሱ ይጣላል፤ ምክንያቱም ለአገር ተጨማሪ ገቢ ያስገኛልና::
የቅንጦት እቃዎች ከሠው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎት በላይ የሆኑ ናቸው:: ለምሳሌ ውድ የሆኑ መጠጦች፣ ሲጋራ፣ ሽቶ የመሳሰሉትን ያካትታል:: የህብረተሰቡን ፍላጎት በማይገድቡ እቃዎች ላይ ሲባል እቃዎቹ ኤክሳይዝ ታክስ ስለተጣለባቸው በተጠቃሚዎች ላይ ብዙም የዋጋ ልዩነት የማያመጡ፤ ነገር ግን ለመንግስት ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ ለማለት ነው:: ይህ የታክስ ዓይነት ለህብረተሰቡ ጤንነት አደጋ የሆኑ የትምባሆ እና ሌሎች ምርቶች ላይ ዋጋቸው እንዲጨምርና የተጠቃሚዎቹ ቁጥር እንዲቀንስ ታስቦ የሚጣል ነው:: ከዚህ በተጨማሪም የሀገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታታት እንዲሁም ከውጪ የሚገቡ እቃዎች ሀገር ውስጥ የተመረቱትን ከገበያ ውጭ እንዳያደርጓቸው ታስቦ ይጣልባቸዋል። (የገቢዎች ሚ/ር)
እንደማሳረጊያ
ከኤክሳይዝ ታክስ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ጋር ተያይዞ በተለይም ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ እንደምርት ዘመናቸው ከ100 እስከ 500 ፐርሰንት ኤክሳይዝ ታክስ መጣሉ በተመለከተ ሁለት ዓይነት ተቃራኒ አስተሳሰቦች በመንጸባረቅ ላይ ናቸው::
አንዱ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች በብዛት እንዲገቡ መፍቀድ በአሁኑ ሰዓት ያለውን ሰፊ የትራንስፖርት ችግር ከመቅረፍ አኳያ ሊኖረው የሚችለውን ውጤት ግምት ውስጥ የሚያስገባ ነው:: አዲሱ ኤክሳይዝ ታክስ በግልጽ እንደተደነገገው ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ታክስ መናር ዋና ምክንያቱ እንዳይገቡ ከመዝጋት ያልተናነሰ ውጤት ያለው መሆኑ በሌላ በኩል የአዲስ ተሽከርካሪዎች ምርቶች ዋጋቸው ወደድ የሚል መሆኑ በቀጣይ የትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ግዥ መቀዛቀዝ ሊያስከትል የሚችል እርምጃ እንዳይሆን የሚሰጉ ወገኖች አሉ::
በሌላ በኩል ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች በብዛት ወደአገር ውስጥ መግባት መኪኖቹ አሮጌ በመሆናቸው በከፍተኛ ደረጃ ነዳጅ የሚጠቀሙ መሆኑና በየጊዜው ለጥገና የሚያስወጡት ወጪ አገሪቷን አላስፈላጊ የውጭ ምንዛሪ ጫና እየዳረገ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ይህን ችግር ለመቀነስ ከፍተኛ የኤክሳይዝ ታክስ መጠን መጣሉ አግባብነት የሚያስረዱ ወገኖች አሉ::
ጉዳዩ የተመራለት የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ቋሚ ኮሚቴ ይህንና መሰል ተቃራኒ እሳቤዎች ከሕዝብ ጥቅም አንጻር መርምሮ እና አጥንቶ የውሳኔ ሀሳብ ያሳልፋል፣ በቀጣይም ፓርላማው ጉዳዩን በአጽንኦት ተመልክቶ ያጸድቀዋል ብዬ እገም ታለሁ::
ይህ ዓምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ አስተያየታቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሑፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 11/2012
ፍሬው አበበ