ሰሞኑን በስፋት የውይይት አጀንዳ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል መንግስት በተወሰኑ ምርቶች ላይ ሊጥል ያሰበው ታክስ አንዱ ነው። ይህ የታክስ አይነት በሙያዊ አጠራሩ ኤክሳይስ ታክስ ተብሎ ይጠራል።
የኤክሳይዝ ታክስ ቀጥተኛ ያልሆኑ ታክሶች ተብለው ከሚታወቁ በዕቃ እና አገልግሎት ላይ ከሚጣሉ ታክሶች ምድብ ውስጥ የሚገኝ ታክስ ነው። የኤክሳይዝ ታክስ ዋና ዓላማዎች ለመንግሥት ተጨማሪ ገቢ ማስገኘት፣ በኅብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ምርቶች ፍጆታ መቀነስ፣ ከፍተኛ ሀብት ያላቸው ሰዎች ከሚጠቀሙባቸው የቅንጦት ዕቃዎች ላይ ገቢ በመሰብሰብ በድህነት አረንቋ የሚገኙ ዜጎችን ሕይወት ማሻሻል እና በአካባቢ ደህንነት ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ምርቶች አጠቃቀም መቀነስ ናቸው።
ኤክሳይዝ ታክስ የቅንጦት ዕቃዎች ሆነው ዋጋቸው ጨመረም፤ አልጨመረም መሠረታዊ በመሆናቸው ምክንያት የገበያ ፍላጎታቸው በማይቀንስ ዕቃዎች ላይ፣ እንዲሁም የሕብረተሰቡን ጤንነት የሚጎዱና ማህበራዊ ችግር የሚያስከትሉ ዕቃዎችን አጠቃቀም ለመቀነስ ሲባል የተጣለ ታክስ ነው።
ታክሱ በሀገር ውስጥ በሚመረቱና ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ በአንዳንድ የተመረጡ ዕቃዎች ላይ ብቻ የተጣለ ነው።
ዓላማው ማህበራዊ ችግር የሚያስከትሉና የህብረተሰቡን ጤንነት የሚጎዱ ምርቶችን መቀነስ እንዲሁም የቅንጦት የሆኑ የፍጆታ እቃዎች ላይ ተፅዕኖ ማሳደር ነው። የተሻለ ገቢ ያላቸው ሰዎች በሚጠቀሙባቸው እቃዎች እና የመግዛት ፍላጎታቸው በማይቀንስባቸው ምርቶች ላይ ታክሱ ይጣላል፤ ምክንያቱም ለአገር ተጨማሪ ገቢ ያስገኛልና።
የቅንጦት እቃዎች ከሠው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎት በላይ የሆኑ ናቸው። ለምሳሌ ውድ የሆኑ መጠጦች፣ ሲጋራ፣ ሽቶ የመሳሰሉትን ያካትታል። የህብረተሰቡን ፍላጎት በማይገድቡ እቃዎች ላይ ሲባል እቃዎቹ ኤክሳይዝ ታክስ ስለተጣለባቸው በተጠቃሚዎች ላይ ብዙም የዋጋ ልዩነት የማያመጡ፤ ነገር ግን ለመንግስት ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ ለማለት ነው። ይህ የታክስ ዓይነት ለህብረተሰቡ ጤንነት አደጋ የሆኑ የትምባሆ እና ሌሎች ምርቶች ላይ ዋጋቸው እንዲጨምርና የተጠቃሚዎቹ ቁጥር እንዲቀንስ ታስቦ የሚጣል ነው። ከዚህ በተጨማሪም የሀገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታታት እንዲሁም ከውጪ የሚገቡ እቃዎች ሀገር ውስጥ የተመረቱትን ከገበያ ውጭ እንዳያደርጓቸው ታስቦ እንደሚጣልባቸው ከገቢዎች ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
የቅንጦት የሆኑና ሀገሪቱን ተጨማሪ ዶላር የሚያስወጡ ምርቶች ላይ ታክስ መጨመሩ ይበል የሚያሰኝ ነው። ሆኖም ግን በየዕለቱ የምንጠቀምባቸው ስኳርና ዘይት የመሳሰሉ ምርቶች በዚህ ውስጥ መካተታቸው ብዙዎቻችንን እንድንሰጋ አድርጎናል።
የኤክሳይስ ታክሱ ረቂቅ አዋጅ ወደ ተወካዮች ምክር ቤት ሄዶ የውይይት አጀንዳ ከሆነ በኋላ በብዙዎቻችን ዘንድ ስጋት ከፈጠሩ ጉዳዮች አንዱ በዕለት ተዕለት በምንጠቀምባቸው ምርቶች ላይ ተጨማሪ ታክስ መጣሉ የኑሮ ውድነቱን እንዳያባብሰው ፍርሃት በብዙዎች ዘንድ ፈጥሯል። በተለይም በስኳር እና በዘይት ላይ የኤክሳይስ ታክስ መጣሉ ወትሮም ልጓም ያጣውን የሀገራችንን ገበያ ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይወስደው ያሰጋል። ምን አልባት ስኳርና ዘይት በአደጉት ሀገራት መሰረታዊ የሚባሉ ፍጆታ ዕቃዎች ስላልሆኑና በጠናም ላይ የሚያስከትሉትን ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት ተጨማሪ ታክስ ሊጣልባቸው ይቻላል። በእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ስኳርና ዘይት ድሃው በየዕለቱ የሚጠቀምባቸው ፤በገበያውም ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸውና እንደለብም የማይገኙ ናቸው።
አንዲት እናት ልጅዎችዎን ወደ ትምህርት ቤት የምትልከው ከገበያው ጋር ሸምታ በምታገኘው ጥቂት ስኳር ሻይ አፍልታና ዳቦ ገዝታ ነው። ይህም ለብዙ እናቶች የማይቻል ፈተና ሆኖ ከኑሮ ጋር ትንቅንቅ ላይ እንደሚገኙ እየታወቀ በስኳር እና ዘይት ላይ ተጨማሪ ታክስ ለመጣል በዕቅድ መያዙ ኑሯችንን የበለጠ የሚያመሰቃቅለው ነው።
የዘይትም ጉዳይ ቢሆን ለብዙዎቻችን የኑሮ ፈተና ነው። የዘይት አቅርቦት ውስን ከመሆኑና ዋጋውም የማይቀመስ መሆኑ ለጤና ጉዳት አለው እየተባልን እንኳን እንደአቅማችም ከገበያ እየገዛን በመጠቀም ላይ እንገኛለን። ይህ ሁኔታ ባለበት ምድር ላይ በዘይት ላይ ተጨማሪ ታክስ ለመጣ ማሰቡ ችግሩን በውል ካለመረዳት የመነጨ ይመስላል። ወይንም ደግሞ እንደብዙዎች ግምት ኤክሳይስ ታክሱ የሚጣለው ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ከሆነ በቅድሚያ ስኳርና ዘይት የመሳሰሉ ምርቶችን በቅድሚያ በሀገር ውስጥ በብዛት እንዲመረቱ ማድረግ ይገባል። ካልሆነ ለድሃው ተጨማሪ ሸክም ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 11/2012
እስማኤል አረቦ