‹‹ከምን ይማራሉ ቢሉ፣ አንድም ‹‹ሀ›› ብሎ ከፊደል፤ አንድም ‹‹ዋ›› ብሎ ከመከራ›› ይባላል። ከደቡብ ጎንደር በአንድ ገጠር መንደር የተወለዱት አቶ ስንታየው አበጀ፣ ለትምህርት ያልታደለው የልጅነት እድሜያቸው እናታቸውን በህጻንነታቸው በሞት ማጣት ጋር ህመም ተደምሮ ከልጅነት እስከ ወጣትነት ያለውን አፍላ ጊዜያቸውን በብዙ መከራ እንዲያሳልፉ አድርጓቸዋል። ለ23 ዓመታትም በተለያዩ በሽታዎች ተሰቃይተው ያሳለፉት እኚህ ሰው፤ ገና በለጋነታቸው ነበር ሕመሙ እየጠናባቸው የሄደው። ከዚያም በ1981 ዓ.ም ከትውልድ ቀዬያቸው ወደ አዲስ አበባ ተጓዙ። አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ህመማቸውን ተቋቁመው ፈረንሳይ አከባቢ ሰው ቤት መስራት ቢጀምሩም፤ ብዙም ሳይቆዩ ህመማቸው ብሶ መስራት ሲደክማቸው በአሰሪዎቻቸው ‹‹መስራት ካልቻልክ ምን ታደርጋለህ ውጣ›› የሚል ትዕዛዝ ከሚሰሩበት ቤት ወደ ጎዳና ወጡ።
እንደምንም ራሳቸውን አጠንክረው ሌላ መጠጊያ ሲፈልጉም ወደ ንፋስ ስልክ አከባቢ ሌላ ቤት የመግባት እድል አገኙ። በዚህ ቤትም ሕመማቸውን ቻል አድርገው ሰርተው ራስን ለማሸነፍ ቢጥሩም በ1983 ዓ.ም ላይ ከነጭራሹ ራሳቸውን ማዘዝ በማይችሉበት ደረጃ (ፓራላይዝ ወደመሆን) ላይ ስለደረሱ በድጋሜ መስራት ስላልቻሉ ለጎዳና ሕይወት ተዳረጉ። አሁንም አንዲት እናት አንስተው ያስጠጓቸውና እንደምንም ሻል ሲላቸው ሌላ ቤት የመስራት እድል ቢያገኙም ደብቀው የማይዘልቁት ሕመም ጭራሹን አድክሟቸው ለሦስተኛ ጊዜ ለጎዳና ሕይወት ወጡ። በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳሉ ስቃያቸውን የተመለከተ አንድ ግለሰብ ፈረንሳይ 07 ቀበሌ ወደሚገኘው ቤቱ ወስዶ ያስጠጋቸዋል፤ እዛ እያሉም ባለቤቱ ቤት ገዝቶ ሲወጣ እርሳቸውን ቤቷ ውስጥ ትቷቸው ይሄዳል።
ይሁን እንጂ አቶ ስንታየው በወቅቱ መንቀሳቀስ ስለማይችሉ በዛችው የቀበሌ ቤት ውስጥ እንዳሉ የሚተኙበት ጀርባቸው እስከመላላጥ፤ ቁስላቸውም በጉንዳን እስከመወረር ይደርሳሉ። በዚህ ሁኔታ የሚያዩዋቸው ሁሉ ዕለት ተዕለት ከመደገፍ ይልቅ ሞታቸውን ይጠባበቁ ይመስል ‹‹አልሞተም እንዴ?›› እያሉ ሲዘባበቱባቸው ያደምጣሉ።
ይሄን ያደመጡትና በተኙበት አካላቸው ቆስሎ እየተበጣጠሰና በጉንዳን እየተበላ ያዩት አቶ ስንታየሁም ፈጣሪያቸውን እንዲህ አሉ፤ ‹‹ፈጣሪ ሆይ ከህጻንነቴ ጀምሮ ይህ ሁሉ መከራ የሚደራረብብኝ ምን አድርጌ ነው? አውቃለሁ አሁን ሰዎች በእኔ የሚያደርጉት እኔም በሰዎች ላይ ሳይ ሳደርገው የነበረው ነው፤ ሆኖም አንተ የሚሳንህ የለምና የ15 ቀን እድሜ ስጠኝና እንደ እኔ መንቀሳቀስ የማይችሉ፣ መልበስ መጉረስ የማይችሉ፣ መቀመጥ መነሳት የማይችሉ፣ ቤተሰብ ወገን የሌላቸውና ሰው አውጥቶ የሚጥላቸው ሰዎችን ገላቸውን አጥቤ፣ ምግብ አጉርሼ፣ ለሰውም ነግሬላቸው፣ የሞቱትንም ቀብሬና ለቆሙም ይሄን ስራ እንዲሰሩ ነግሬ እንድሞት አድለኝ?›› ብለው ፀለዩ። ይህ ደግሞ ፈጣሪ በሚሰጣቸው በ15 ቀን እድሜ ውስጥ በራሳቸው ጥረት የሚያደርጉት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የወደቁት እንዲነሱ፣ የታመሙት እንዲደገፉ፣ የተራቡት እንዲጎርሱ፣ የታረዙት እንዲለብሱና የሞቱትም እንዲቀበሩ ማስቻልን ያለመ ነው።
‹‹ለምኑ ይሰጣችኋል፤ አንኳኩ ይከፈትላችኋል›› እንዲልም፤ የለመኑትን የማይነሳ አምላክ ከዛ አስከፊ ሕመምና ዘግናኝ ሕይወት እንዲፈወሱ ጸበልን መዳኛ ምክንያት አድርጎላቸው ቃላቸውን እንዲፈጽሙ እድል ሰጣቸው። በዚህም በ1987 ዓ.ም በወርሃ ህዳር በሁለት ብር በገዟት 10 ሊትር ጄሪካን ውሃ እየቀዱ የወደቁ ስምንት ደካሞችን ገላና ልብስ በማጠብ ስራቸውን አንድ ብለው ጀመሩ። ለ15 ቀን የቀረበ የልመና ጥያቄ ዘልቆ ለዘጠኝ ወርም ብቻቸውን ሲሰሩ ቆዩ። በኋላ ላይ አንድ እንጨት ብቻውን እንደማይነድ ሁሉ አንድ ሰውም ብቻውን ሮጦ ለውጤት አይበቃምና፤ ቢያንስ የወደቀ ሰው ለማንሳት አጋዥ ማግኘት የግድ ሆነ። ሆኖም ፍላጎትና ህልማቸውን የሚረዳቸው ያጣሉ፤ ይልቁንም ከማገዝ ይልቅ አቃላዩ ይበዛባቸዋል። ሆኖም ከብዙ መካከል ጥቂት ልባም አይጠፋምና ሕልማቸውን የሚረዷቸው ሁለት ታዳጊ ወጣቶችን ያገኛሉ። ካንድ ብርቱ እንዲሉም የ15 ቀን እድሜ ተጠይቆ በአንድ ሰው የተጀመረው ስራ፤ እድሜም ሰውም ተጨምሮበት የወደቁትን የማንት ስራው ቀጠለ።
በዚህም ‹‹የወደቁት ይነሱ፤ የተረሱ ይታወሱ፤ የሞቱም በነጻነት ይቀበሩ፤ የቆሙ ሰዎችም ለአገር ውለታ የዋሉ እናት አባትና አዛውንቶችን ማንሳት፣ ማስታወስና መደገፍን ይማሩ፤›› የሚለውን የልመናቸው አንድ አካል የሆነውን ሀሳብና ምኞታቸውን አጠናክሮ ለመስራት እድል አገኙ። ‹‹የወደቁትን አንሱ የነዳያን መርጃ ማህበር››ንም እውን በማድረግ፤ ‹‹ዋ›› ብለው ከመከራቸው ባገኙት ትምህርት በፈጣሪያቸው በተሰጣቸው ምህረት ታግዘው፤ ዛሬ ላይ እርሳቸው ወድቀው ደጋፊ ያጡ፣ ቆስለው አስታማሚና አገላባጭ የተራቡ፣ ራሳቸውን መንከባከብና ማንቀሳቀስ ያልቻሉ፣ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው ግለሰቦችን ፈልገው ያለመጠየፍ በማንሳት ወደማዕከሉ በመውሰድ ይንከባከባሉ።
ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላም ዛሬ ላይ የወደቁትን አንሱ የነዳያን መርጃ ማህበር ባቋቋመው ዘመናዊ ማዕከልም 200 ያክል ነዳያን (ትናንት ባለሃብት፣ ሃኪም፣ መሃንዲስ፣ መምህር፣ ወታደርና ሌላም የነበሩ መሆኑን ልብ ይሏል) የሚረዱ ሲሆን፤ 150 ያክሉ አልጋ ይዘው በማዕከሉ ውስጥ እንክብካቤ የሚደረግላቸው፤ 50ዎቹ ደግሞ በተመላላሽ ተመጋቢነት የሚደገፉ ናቸው። እንዚህ ነዳያንም በማዕከሉ ከምግብ እስከ አልባሳት በወቅቱ ያገኛሉ፤ ሲታመሙ ይታከማሉ፤ ያላንዳች መጠየፍ በማዕከሉ እንክብካቤ ይደረግላቸዋል።
በማዕከሉ ውስጥ ከሚረዱት መካከል አቶ መኮንን ዓሉ አንዱ ናቸው። በቀድሞው ወሎ ጠቅላይ ግዛት አምባሰል አውራጃ የተወለዱት አቶ መኮንን፣ ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመን ጀምረው እስከ ደርግ ስርዓት ማብቂያ ድረስ ለ35 ዓመታት በወትድርና አገራቸውን ቢያገለግሉም፤ በድካማቸው ወቅት የሚደግፋቸውና የሚጦራቸው ቤተሰብ አላፈሩም። በደርግ ስርዓት ውድቀት ማግስት ግን ያገለገሏት አገርና ህዝብ ረስተዋቸው የአገልግሎት ጡረታቸውን ለማስከበር እንኳን ባለመቻላቸው፤ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ሰባራ ሳንቲም ሳይኖራቸው የጉበት በሽታ ያሰቃያቸው ጀመር። ከህመማቸው ጋር እየታገሉም በየግለሰቦች ቤት ጥበቃ እየሰሩ ሕይወትን ለማሸነፍ ቢጥሩም፤ ለሕመማቸው እጅ መስጠታቸው የግድ ሆነ። በሕመም የተጎዳ ሰርቶ የማይበላ ሰውነት ደግሞ ፈላጊ የለውምና ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ከጥበቃ ስራ ያገኟትን ጥቂት ሳንቲም ይዘው ከወደቁበት ቦታ አዝግመው ወደሚያውቃቸው አንድ ሐኪም ያመራሉ።
ሐኪሙም በሁኔታቸው አዝኖና የሕክምና መድሃኒት ሳይቀር በራሱ ገዝቶ ሰጥቷቸው ባሉበት ሁኔታ መንገድ ላይ ወድቀው ከሚቀሩ ለሶስት ቀን እንኳን እንጀራ በልተው ቢሄዱ በሚል ወደ የወደቁትን ያንሱ የነድያን መርጃ ማዕከል ይልካቸዋል። ጉዳታቸውን የተመለከተው ማዕከልም እኚህን ያገር ባለውለታ መልሶ መጣልን አልፈለገም። ይልቁንም በማዕከሉ ተጠልለው ሕክምናቸውን እንዲከታተሉ ያደርጋል። የሞት ቀናቸውን ሲጠባበቁ የነበሩት አቶ መኮንንም ከህመማቸው አገግመው በማዕከሉ ውስጥ እየተረዱ አራተኛ ዓመታቸውን ይዘዋል።
‹‹እዚህ ማዕከል ባልገባ ኖሮ ሞት ነው የሚጠብቀኝ›› የሚሉት አቶ መኮንን፤ ለአገርና ህዝብ ሲሉ ከእድሜያቸው 35 ዓመታትን የገበሩበትንና በህመምና በችግር ስላሳለፏቸው የመከራ ጊዜያት ሲናገሩ በጥልቅ የሃዘን ስሜት ውስጥ ሆነው በእንባ ጅረት ታጅበው ነው። ሆኖም እኚህ አባት ውለታዬ ተረሳ፣ በድካም፣ በችግርና ሕመሜ ሜዳ ስወድቅ አልተጎበኘሁም ብለው ትናንት የተዋደቁላትን አገርና ህዝብ አላኮረፉም፤ አልረገሙም። ይልቁንም እነዚህ የበጎ ምግባር ዓርዓያዎች ከዚሁ ህዝብና አገር በተለያየ አግባብ የወጡ ናቸውና በእነርሱ እንደተካሱ ስለሚያምኑ፤ ለአገርና ህዝብ ሰላም፤ ለመንግስትም መጽናት ቀን ከሌት ይማጸናሉ፤ ‹‹አገራችንን ዳርና ዳሯን እሳት፤ መሃሏን ገነት አድርጎ ይጠብቅልን›› ሲሉ ላደመጣቸውም ዛሬም በአገራቸው ተስፋ እንዳልቆረጡ፤ ይልቁንም ለትውልዱ አብዝተው ይጨነቃሉ። እንዲህ ከሞት የታደጋቸውን በጎ ሰው ብቻ ሳይሆን፤ ጠጋ ብሎ የጠየቃቸውንም ‹‹በእኛ ቦታ ከመውደቅ ሰውሮ የተባረከና የተቀደሰ እንጀራ፤ እድሜንም ከጤና እንዲሰጣቸው እመኛለሁ፤›› ከሚል ልባዊ ምኞት ከልብ መርቀው ይሸኛሉ።
ሌላዋ በማዕከሉ ጥላ ስር እንክብካቤን የሚያገኙት ወይዘሮ ንጋቷ ወንድሙ፣ የትላንት ማንነታቸውን ከዛሬው ጋር አነጻጽረው መግለጽ ቢቸግራቸው፣ ‹‹ዛሬ ቢያወሩት ወዴትና ወዴት ነው›› በማለት በሀሳብ የኋሊት ሲመለሱ ፊታቸው የሃዘን ጥላ ሲጥልበት፤ ዓይናቸው እንባን ያዘንባል። ከሀሳባቸው መለስ ሲሉም በደብረብርሃን አከባቢ በነበረች መንደራቸው ሳሉ ከማጀት እስከ ማሳ የነበራቸውን የሃብት ልክ፤ የእርሳቸውንም የስራ ፍቅርና ተሳትፎ ይተርካሉ። ማሳቸው ጾም ሳያድር፣ ቤታቸው ሳይጎድል፣ ጎተራቸው እንደሞላ ከዓመት ዓመት ሲሸጋገሩ፤ እርሳቸውም ከቤት ውስጥ ስራ አልፈው ወንዶቹ ሲያርሱ እርሳቸው ቆፍረው፤ ሲያጭዱም አብረው አጭደው ጊዜያቸውን አሳልፈዋል።
ይሁን እንጂ እንደ ሀብቱ ለልጅ፤ እንደ ጉብዝናቸው ወቅትም በጉልምስናቸው ጤናን፤ እንደ ሀብት መሰብሰባቸውም አያያዙን አልታደሉ ሆነና የመጦሪያቸው ጊዜያቸው እንደ ጉብዝናቸው አላምር አለ። ጤና ጠፋ፤ ንብረት አለቀ፤ አቅም ሲደክም፣ ሃብት ሲጠፋና ጤና ሲታወክ ደጋፊ ጠፋ። ሕመሙ ጸና፣ በራሳቸው አቅም መንቀሳቀስ አቃታቸው፤ የሰው እጅ ማየት በሰው እጅ መንቀሳቀስ የግድ ሆነ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሲንገላቱ ወደ ማዕከሉ የመግባት እድሉን አገኙ። ዛሬ ማዕከሉ እየተንከባከባቸው፣ የሕክምና ክትትል እያደረገላቸውና እየጦራቸው ሲሆን፤ እርሳቸውም በጎዎች ያደረጉላቸውን በማሰብ በእናትነት ልባቸው አገርና ህዝባቸውን በጸሎት እያሰቡና በጎዎችንም እየመረቁ ይገኛሉ። ‹‹የቆምነው እድንጦር፣ የወደቁትም እንዲነሱ፣ የተረሱትም እንዲታወሱ፣ የሞቱትም እንዲቀበሩ፤ ፈጣሪ ኢትዮጵያንም ሰዎቿንም በቸርነቱ ያስብልን፤ ከወደቅንበት ያነሱንንም ፈጣሪ ብድራቱን ያቆይንል፤.›››› ሲሉም የመልካም ምኞታቸውን፤ ተማጽኖና መልዕክታቸውን ለፈጣሪም፤ ለሰውም ያቀርባሉ።
ምንም እንኳን በዚሁ በአዲስ አበባ ተወልደው ያደጉ ተድረውም ወልደው የከበዱ ቢሆንም፤ ወይዘሮ ዘውድነሽ በቀለም ከብዙ እንግልትና ውጣ ውረድ በኋላ ከኪዳነ ምህረት ደጅ ወድቀው በመገኘታቸው የማዕከሉ ጥላ ከታደጋቸው እናቶች አንዷ ናቸው። ወይዘሮ ዘውድነሽ ዛሬ ላይ እንደልብ መናገርና ሀሳባቸውን መግለጽ ባይችሉም፤ በተቆራረጠ ሀሳባቸው የቁጭት ሳግ እየተናነቃቸውና ፊታቸው በእንባ እየታጠበ ለዚህ ያበቃቸውን እንዲህ አወጉን። ወይዘሮዋ፣ በትዳር ሕይወታቸው ሰባት ልጆችን አፍርተዋል። ሆኖም ቤት ሲጎድል ኑሮ ሲከፋ የተሻለ መኖርን የማይሻ የለምና ከባለቤታቸው ጋር መክረው ቤታቸውን ሊያቀኑ የጎደለ ማጀታቸውን ሊሞሉ ወደ አረብ አገር ያመራሉ። በቆይታቸው የሚያገኟትን ገንዘብ እየላኩ ባለቤታቸው ቤት ይሰራሉ፤ ንብረትም ያፈራሉ።
ቤት ሲሞላ፣ ጎጆ ሲቀና የሰው አገር በቃ ይሉና በሞላ ቤታቸው መኖርን ናፍቀው ይመለሳሉ። ይሁን እንጂ ያሰቡት ቀርቶ ያላሰቡት ይጠብቃቸዋል። በሰው አገር ለፍተው ባገኙት ገንዘብ በተሰራው ቤታቸው ውስጥ ባለቤታቸው ሰራተኛቸውን አግብተው ኑሮን አደላድለዋል። ይሄን መቀበል ያቃታቸው ወይዘሮ ዘውድነሽም፣ አዕምሯቸውም ስነ ልቡናቸውም ይጎዳል። ለደስታ የተዘጋጀው አካላቸው ሕመምን፤ ለፈገግታ የተዘጋጀው ገጽታቸው ሐዘንን፤ የሞቀ ቤት የሻተው አካላቸውም ከሰው ቤት ጥገኝነትን ያስተናግዳሉ። ነገሮች እየከበዱ ህመሙም እየጸናባቸው ይሄዳል። በደም ግፊትም ይሰቃዩ ጀመር፤ ልጅም ባልም የረሷቸው እናት በበጎ አድራጊ ግለሰብ እጅ ወደቁ። በጎነትም ደጋፊ ይሻልና ግለሰቧ አቅም ቢያጥራቸው ጎዳና እንዳይወድቁ በሚል ለሌላ የድርጅት ይሰጧቸዋል። ሆኖም ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት ኪዳነምህረት ደጅ ወድቀው ይገኙና ወደዚህ ማዕከል ይገባሉ።
የእነዚህንና ሌሎች በማዕከሉ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ታሪክ በማስታወስ መልዕክት የሚያስተላልፉት የማህበሩ መስራች አቶ ስንታየሁ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ዓለማችን በሁለት ተከፍላለች፤ ገሚሱ እናትና አባቱን አውጥቶ ይጥላል፤ ገሚሱ ደግሞ ባዕድ አንስቶ ይንከባከባል። ይህ ግን በሰውነት ሚዛን ሊታይ በሰው ስብዕና ልክ መንቀሳቀስን ይጠይቃል። እናም ሰው ሆኖ በሰው ሚዛን መራመድ መስራትና ማሰብ ተገቢ ይሆናል። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ስለማያውቁ፣ አቅማቸው ስለደከመና ሕመምም ስለጎዳቸው በየጎዳናው ተጎሳቁለው፤ የአዕምሮ ህሙማንና ሌሎችም መጫወቻ ሲሆኑ ማየት ያሳምማል።
እነዚህ ሰዎች እናት፣ አባት ናቸው። አገርን ጠብቀውና አስከብረው ለትውልድ ያስተላለፉም ናቸው። በዚህ መልኩ ወድቀው ሲቀሩ ደግሞ ለትውልድ እርግማንን ያወርሳሉ። ይሁን እንጂ ትውልዱ የእነዚህን እናትና አባቶች ብሎም የአገር ባለውለታዎች ማንሳት አንድም የሞራል ግዴታ፤ ሁለትም የፈጣሪ ትዕዛዝ፤ ሶስትም ከእርግማን ይልቅ ምርቃትን ማትረፊያው መሆኑን አለመገንዘቡ በርካታ አስታዋሽና ደጋፊ ያጡ ነድያን በየቦታው ወድቀው እንዲታዩ አድርጓል። ይህ ደግሞ ቆሞ ሂያጅ የሆነው ትውልድ አለመማር ውጤት ሲሆን፤ የእነዚህን እናት አባቶች ወላጅነት፤ የሚኖርባትን አገር በነጻነት አስረካቢነት ውለታ ባልዘነጉ ነበር።
‹‹የሚሞት ሽማግሌ አይርገምህ፤ የሚያባራ ዝናብ አይምታህ›› ይሉት ብሂልን የሚያነሱት አቶ ስንታየሁ ታዲያ፤ ‹‹እንዴት እናት አባት ሜዳ ላይ ወድቆ ይቀራል?›› ሲሉ ትውልዱን ይጠይቀሉ። ዛሬ ላይ ትውልዱ ያልተገቡ ምጽዋቶችን መስጠቱ፣ ከድሃ ይልቅ ብድር የሚመልሰውን ሃብታም ደግሶ መጋበዙ ለታይታ ካልሆነ ለክፉ ቀን ስንቅ የማይሆነው መሆኑን በመግለጽም፤ እነዚህን አስታዋሽና ደጋፊ ያጡ ወገኖችን ቢጎበኙ፣ ቢያስታምሙ፣ ቢያበሉ፣ ፕሮግራሞቻቸውንም ከእነርሱ ጋር ቢያሳልፉ፣ ቢንከባከቡና ሲሞቱም ቢቀብሩ ለስጋም ሆነ ለነፍስ ስንቅ የሚሆናቸው እንደሆነም ይመክራሉ። ማህበሩ በማዕከሉ በሚሰጠው አገልግሎት ህብረተሰቡ እያደረገ ላለው ድጋፍ አመስግነውም፤ ድጋፉ ለእናቶችና አባቶችን ውለታ ማሰቢያ እንደመሆኑ እርስ በእርስ በመዋደድ ስሜት ሁሉም በአቅሙ እንዲሳተፍ መልዕክት አስተላልፈዋል። ቸር እንሰንብት፤ ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!
አዲስ ዘመን አርብ ታህሳስ 10/2012
ወንድወሰን ሽመልስ