ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት የስልጣኔ ተምሳሌት እንደነበረች መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በተለይ በኪነ ህንፃ ጥበብ የነበሩት የታሪክ አሻራዎች አስደማሚ ከመሆናቸውም በዘለለ አንዳንዶቹ ዛሬም የማይሞከሩ እና በዚያን ዘመን እንዴት እንደተሰሩ ሚስጥር ሆነው የቆዩ ናቸው፡፡ ለዚህም የአክሱም ሃውልቶች፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የጎንደር ቤተመንግስት፣ የጢያ ትክል ድንጋዮች፤ የብራና ጽሁፎችና ሌሎችም ማሳያዎች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በነዚያ የከፍታ ዘመኗ ለአንዳንዶቹ አገራት የክፉ ጊዜ ደራሻቸው፣ ለከፊሎቹ ደግሞ መመኪያቸው ነበረች፡፡ ለምሳሌ በድርቅና በረሃብ ለተጎዱ ዜጎች ሰብኣዊና ቁሳዊ ድጋፍ አድርጋለች፤ ግጭቶችን ለማስቆም ጦር አዝምታ ተዋግታለች፤ የነፃነት ታጋዮችን አሰልጥና ከተበደሉ አገራት ጎን ቆማለች፤ ቅኝ ባለመገዛትም የጥቁሮች መመኪያ ሆናለች፡፡ ያም ሆኖ ግን ከነበርንበት ከፍታ ወደሌላ ከፍታ ከመውጣት ይልቅ ባለንበት በመቆየታችንና ብሎም ተንሸራተን በመውረዳችን ሌሎች አገራት ከኋላ ተነስተው ቀድመውን ሊሄዱ ችለዋል፡ ፡ ራሳችንን መመገብ እንኳን ተስኖን እጃችንን ለልመና እንድንዘረጋ አስገድዶናል።
በተለይ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣው ቴክኖሎጂ አለምን ሲቀይር እኛ ለቴክኖሎጂው ተገቢውን ቦታ ሳንሰጥ በመቆየታችን የሚፈለገውን እድገት ሳናስመዘግብ ቆይተናል፡፡ በዚህም የተነሳ ዛሬም ከድህነት ወለል በታች ከሚገኙ አገራት ተርታ መሰለፍ ግድ ሆኖብናል፡፡
አሁን ግን ይህንን የኋቋርነትና የድህነት ታሪካችንን ለመቀየር የሚያስችሉ ተስፋዎች ብቅ እያሉ ነው፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት በመንግስት፣ በባለሃብቱና በሃገር ወዳድ ዜጎች እየተዘረጉ ያሉ ዘርፈብዙ የእድገትና የብልፅግና መስመሮች ታሪካችንን የመቀየር አቅም ያላቸው እንደሆኑ ባለራዕይ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ መላው ዓለም ምስክርነት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ለዚህም አንዱ ማሳያ በዘንድሮ ዓመት ብቻ ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ጨምሮ ለተለያዩ ስኬታማ ኢትዮጵያውያን የተሰጠው ዓለም አቀፍ እውቅናና ሽልማት ትልቅ ማሳያ ነው፡፡
ከነዚህ ዓለምአቀፍ እውቅናዎችና ሽልማቶች ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ በዛሬው እለት ከትልቁ የቴክሎጂ ጎራ የተቀላቀለችበት የሳተላይት ቴክኖሎጂ ወደከፍታ ለሚደረገው ጉዞ ትልቁ መሰረት ነው፡፡
የሳተላይት ቴክኖሎጂ የእድገት ትልቁ መሰረተ ልማት ነው፡፡ በዚህ ዘመን የሳተላይት ቴክኖሎጂ ያልታከለበት ማንኛውም እንቅስቃሴ ስኬታማ ሊሆን አይችልም፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ አሁን ከደረሰችበት የእድገት ደረጃ አንጻር የሳተላይት ቴክኖሎጂ የግድ የሚያስፈልጋት ቢሆንም ዘርፉ ውስጥ ባለመግባቷ በከፍተኛ ወጪ ከሌሎች አገራት በግዢ ስትጠቀም ቆይታለች፡፡ በየዓመቱ ከ600 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪ ስታደርግ መቆየቷም እውነት ነው፡፡ ይህ ገንዘብ ለሌላ አገልግሎት ቢውል በርካታ ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችል ሲሆን ከቴክኖሎጂው በሚገኝ ትሩፋት የተሻለ እድገት ማስመዝገብ ይቻል እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የሳተላይት ቴክኖሎጂ በማደግ ላይ ላሉ አገራት የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት ግብርና ዋነኛው መሰረቷ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህን የግብርና ኢኮኖሚ ለማዘመንና ስኬታማ ለማድረግ የሳተላይት ቴክኖሎጂ የሚኖረው ፋይፋ የላቀ ነው፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ሳተላይት በግብርና ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታትና ምርትና ምርታነትን ለማሳደግ፣ የአየር ንብረትን ለመቆጣጠርና ለመሳሰሉት ተግባራት ያለው ፋይዳ የላቀ በመሆኑ አጠቃላይ ለአገራችን እድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ነው፡፡
ይሁን እንጂ ይህንን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ዕድገታችንን ለማፋጠንና ወደምንፈልገው ብልፅግና ለማምራት በርካታ ጥረቶች ይጠበቁብናል፡፡ በተለይ በዘርፉ የተሻለ እውቀት ለመገብየትና ስኬታማ ስራ ለመስራት ራስን በእውቀት መገንባት፣ የስራ ባህላችንን ማሳደግና በሁሉም የስራ መስኮች የተሻለ ስራ ለመስራት መጣር ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን አሁን የተጀመሩ የእድገትና የብልፅና ተስፋዎች እንዲጎመሩና ፍሬ እንዲያፈሩ ሰላማችንን ማስጠበቅ ትልቁ የቤት ስራ ነው፡፡
በማንኛውም መንገድ እድገት ሙሉ የሚሆነው ሰላም ሲሰፍን ነው፡፡ ሰላም ከሌለ ኢኮኖሚን ማሳደግ ቀርቶ ያለውንም ማስጠበቅ አይቻልም፡፡ ከዚያ ይልቅ ያለውን የማጥፋትና የማውደም፣ ብሎም ወደውድቀት ማምራት የግድ ነው፡፡ ከመሰላሉ መውደቅ የሚያስከትለው ኪሳራ የውድቀቶች ሁሉ መጨረሻ በመሆኑ ከዚህ አደጋ ለመዳን ከፊሎቻችን መሰላሉን አጥብቀን እንያዝ፤ ከፊሎቻችን ደግሞ ወደመሰላሉ የሚወጡትን ገፍተን ወደላይ ለማውጣት የበኩላችንን ድርሻ እንወጣ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2012