በአገሪቱ የኑሮ ውድነት በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱ ነጋሪ የማያሻ ጉዳይ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ መሰረታዊ የተባሉ ምርቶችን በተወሰነ መልኩ በድጎማ ከመንግስት ቢያገኝም የፍላጎቱን ያህል ግን አይደለም፡፡ ነጋዴዎች የምርት ዋጋን በየጊዜው እንዲጨምሩ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች መካከል የታክስ መጨመር ዋነኛው ነው፡፡
መንግስት የቅንጦት እቃዎች በሚላቸው ምርቶች ላይ ከፍተኛ ቀረጥ በመጣል ወደ አገር ውስጥ ማስገባትን ላለማበረታታት ጥረት እያደረገ ቢገኝም የተፈለገውን ውጤት ባለማምጣቱ አዳዲስ አዋጆች እንዲወጡ አስገድዷል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት ስድስተኛ መደበኛ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅን ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡ በረቂቅ አዋጁ ዙሪያ የምክር ቤቱ አባላት አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን፤ በተለይ የቅንጦት እቃ ባልሆኑትና መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ የተጣለው ታክስ አግባብ ባለመሆኑ በድጋሚ መታየት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በረቂቅ አዋጁ ስኳርና የስኳር ውጤቶች፣ ዘይት፣ የተሰፉ ልብሶች እንዲሁም የታሸጉ የውሃ ምርች እና አልኮል ነክ ባልሆኑ ለስላሳ መጠጦች ላይ የታክስ መጠኑን ቅናሽ አድርጎ ቀርቧል። ይህ ቅናሽ የሚያበረታታና ደሃውን የህብረተሰብ ክፍል የሚደጉም በመሆኑ የምክር ቤት አባላቱ እንዳሉት በድጋሚ መታየት አለበት።
የኑሮ ውድነት የህብረተሰቡን ጀርባ እያጎበጠ ባለበት ወቅት መሰረታዊ በሚባሉ ምርቶች ላይ ከዚህ ቀደም ተጥሎ የቆየውን የኤክሳይዝ ታክስ መጠን መቀነስ ኃላፊነት ከሚሰማው መንግስት የሚጠበቅ ተግባር ነው። ይህንን አለማድረግ ግን ድሃውን የህብረተሰብ ክፍል መዘንጋት ይሆናል።
የስኳርና የዘይት ምርቶች በየጊዜው እጥረት አለባቸው እየተባለ በሚነገርበት ወቅት እንዲሁም የሀገር ውስጥ አምራቾች እነዚህን ምርቾች በበቂ ሁኔታ ማምረት ባልቻሉበት ሁኔታ፤ ምርቶቹ ከውጭ ሲገቡ የሚጣለው ኤክሳይስ ታክስ በዋጋ ላይ የሚኖረው ጫና ከፍተኛ ነው።
በመሆኑም በአዋጁ ላይ መጠነኛ ቅናሽ ተደርጎበት መቅረቡ የሚያበረታታ ቢሆንም፤ ጉዳዩ የተመራለት ቋሚ ኮሚቴ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማወያየት ጭምር አዋጁ ደሀ ተኮር ሆኖ እንዲጸድቅ ማድረግ ይጠበቅበታል።
በተለይም ከምግብ ዘይት ጋር ተያይዞ በሀገር ውስጥ ያሉ የዘይት አምራቾች ከአጠቃላይ አገራዊ ፍላጎት መሸፈን የሚችሉት አምስት በመቶ ብቻ መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም ፍላጎቱን ለማሟላት ከፍተኛ መጠን ያለው የምግብ ዘይት ከውጭ ሀገራት በመንግስት ድጎማ ጭምር ይገባል።
ይህ ድጎማ መንግስትን የሚያስመሰግነው ቢሆንም፤ ፍላጎቱን በሀገር ውስጥ ምርት ለማሟላት የሚደረገውን ጥረት ይበልጥ ማጠናከር ግን የግድ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። እስከዚያው ግን በዘይት ላይ የተጣለው የታክስ መጠን ትርጉም ባለው መልክ አሁንም ሊቀንስ ይገባል። አዋጁም ድሃውን የህብረተሰብ ክፍል ማዕከል አድርጎ መውጣት ይኖርበታል፡፡
በረቂቅ አዋጁ ታክስ እንዲጣልባቸው ከተቀመጡት ውስጥ እንደ ቴሌቪዥን ካሜራ፣ የሳተላይት መቀበያና መሰል የመገናኛ ብዙሀን መገልገያ እቃዎችም ይገኙበታል፡፡ በእነዚህ እቃዎች ላይ ከዚህ በፊት የነበረው የታክስ መጠን እስከ 40 በመቶ የሚደርስ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ወደ 10 በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጎ በአዋጁ ቀርቧል።
መንግስት መገናኛ ብዙሀንን ለማበረታታትና ነፃ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ እየሰራ ባለበት ወቅት እንዲህ አይነት ማበረታቻ ማድረጉ ዘርፉን ይበልጥ ያጎለብተዋል፤ ያበረታታዋልም። ስለሆነም የመንግስት ውሳኔና ትኩረት የሚያስመሰግን ነው።
ምርቶች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ማበረታታቱ ተገቢ መሆኑ አይካድም። ይሁንና ይህ መደረግ ያለበት የሀገራችንንና የህዝቧን አቅም ባገናዘበ መልኩ ሊሆን ይገባል። ከዚህ አንጻር በአሮጌ ተሽከርካሪዎች ላይ ሊጣል የታሰበውም ኤክሳይዝ ታክስ እጅግ የተጋነነ ቢመስልም ዘርፉን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ያለው ፋይዳ የላቀ መሆኑ ይታመናል። ከዚህ ጎን ለጎንም መንግስት የሀገር ውስጥ አምራቾችንና መገጣጠሚያዎችን ማበረታታት የሚችሉ ተግባራትን ማከናወን ይጠበቅበታል። በዚህ መንገድ ረቂቅ አዋጁ ደሃ ተኮር ሆኖ እንዲጸድቅ ማድረግ ይቻላል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2012