መንግሥት የህዝብን ጥያቄዎች ለመመለስ ቃል መግባት ቢችልም እሠራለሁ በሚል የመሰረት ድንጋይ አስቀምጦ እንዳላየ ማለፍ ግን የለበትም፡፡ ምክንያቱም ህዝብን ማታለል ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ አመኔታን ይሸረሽራል፡፡ የህዝብ ተቀባይነትን ያሳጣል፡፡ ይህ እየታወቀ መንግሥት የ2007ዓ.ም ምርጫ ተገን በማድረግና ከዚህም ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመንገዶች፣ የባቡሮች፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ ሆስፒታሎችና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ማብሰሪያ የመሰረት ድንጋዮች ቢያስቀምጥም ወዲያው ሊሠራቸው አልቻለም፡፡
እንዲያውም ይባስ ብሎ የተወሰኑት ፕሮጀክቶች የማይሠሩበት ጊዜ ከመርዘሙ የተነሳ የመሰረት ድንጋዮቹ በሳር ተሸፍነዋል፡፡ እስካሁንም ከነጭራሹ ግንባታቸው ያልተጀመሩ አሉ፡፡ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅትም ይሆን ከምርጫ በኋላ የተለያዩ የመሰረተ ልማቶችን ለመገንባት በህዝብ ፊት የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠላቸው ግንባታዎች የውሃ ሽታ ሆነው ቀርተዋል፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ሳይሰሩ ረጅም ዓመታት በመፍጀታቸውም የህዝብ ቁጣ ጭምር መፍጠራቸው አልቀረም፡፡ መንግሥትም የህዝብን ቁጣ ለማብረድ ምክንያቶችን ቢደረድር አሳማኝ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም አንድ መንግሥት እሠራለሁ ብሎ መሰረት ድንጋይ አስቀምጦ የገንዘብ እጥረት አጋጠመኝና ሌላ መንስኤዎችን ቢደረድር ውሃ የሚያነሳ አይሆንም፡፡
‹‹የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ›› ተብሎ ባደገ ማህበረሰብ ውስጥ ደግሞ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጦ ዓመታትን ሳይሠሩ ምክንያት መደርደር አሳማኝም፣ተገቢም አይደለም፡፡ የመንግሥት ባህሪም መገለጫ ፈጽሞ መሆን የለበትም፡፡ እውነታው ይህ ቢሆንም መንግሥት በ2007 ዓ.ም መጨረሻ የመጀመሪያውን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን አጠናቆ ወደ ሁለተኛው የእቅድ ዘመን የተሻገረው ሠፋፊ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ግብ አስቀምጦ ነበር። ይሄንኑ ግብ ከዳር ለማድረስም በዕቅድ ዘመኑ ዋዜማ ላይ በፌዴራል መንግሥት አማካኝነት በተለያዩ ዘርፎች ግንባታዎችን ለማከናወን በርካታ የመሠረት ድንጋዮች አስቀምጧል።
ሆኖም ከአራት ዓመታት በፊት ከተጣሉት የመሠረት ድንጋዮች የተወሰኑት ዘግይቶ ግንባታቸው የተጀመረ ሲሆን፤ አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች አሁንም ድረስ ከመሠረት ድንጋይ አልዘለሉም። ለአብነት ያህል በባቡር መሠረተ ልማት በአንደኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ታቅደው ወደ ሁለተኛው የእቅድ ዘመን ከተላለፉት ውስጥ የአምቦ- ጅማ- በደሌ የባቡር መስመር ይገኝበታል፡፡ ይህ የባቡር ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋዩ በ2007 ዓ.ም በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ቢቀመጥም፤ ግንባታው ግን እስከአሁን ድረስ አልተጀመረም።
የሚመለከታቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ፕሮጀክቶቹ የዘገዩት በአቅም ውስንነት ነው የሚል ምላሽ ቢሰጡም ውሃ የሚያነሳ ምክንያት አይደለም። ምክንያቱም የመሥሪያ ቤቶቹ በጀት ሳይዙና ሥራ ተቋራጮችን ሳይለይ የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ ህዝብን እንደማታለል ነው የሚቆጠረው፡፡
ይህ ብቻ አይደለም በ2007 ዓ.ም በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አማካኝነት የመሠረት ድንጋዩ የተቀመጠውና አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር የሚፈጀው ከ50ሺ በላይ ሰዎችን የመያዝ አቅም ያለው የድሬዳዋ ዘመናዊ ስታዲየም ግንባታም እስከአሁን ድረስ ሥራው አልተጀመረም። በኮልፌ፣ አቃቂ ቃሊቲና ቦሌ ክፍለ ከተሞች ሦስት ቢሊዮን ብር ወጪ የሚጠይቁና አንድ ሺ 500 አልጋ ያላቸው ሆስፒታሎች ግንባታን ለማከናወን በ2007 የመሠረት ድንጋይ ቢጣልም እስከአሁን ሥራቸው አልተጀመረም። የተጀመሩትም ቢሆን እጅግ ዘግይተው ነው፡፡
እንዲሁም በደቡብ ክልል ሆሳእና ከተማ የተቀናጀ የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ፤ ፀረ ተባይና አይጥ ማጥፊያ መድኃኒት ማምረቻ ፋብሪካ ይገነባል ተብሎ የመሰረተ ድንጋይ የተጣለው በግንቦት 12 ቀን 2007 ዓ.ም ነበር፡፡ የፋብሪካው ግንባታ በ2008 ዓ.ም ተጀምሮ በ2010 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ መሰረተ ድንጋይ በተጣለበት መርሀ ግብር ላይ ይፋ ቢደረግም የውሃ ሽታ ሆነ ቀርቷል፡፡ እነዚህና መሰል የመሰረት ልማት ግንባታዎች መዘግየትና አለመጀመርም በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ቅሬታና ቁጣን ፈጥሯል፡፡
ስለዚህ መንግሥት የማይሠራውን ሥራ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ብቻ ሲባል ቃል መግባትና የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ ተገቢ አይደለም፡፡ ስለሆነም ማንኛውንም የህዝብ ጥያቄ ለመመለስ ቅድሚያ ፋይናንሱን፣ አሰራሩንና ተግባራዊ ሥራ ለመጀመር የሚወስደውን ጊዜና ወጪ አስልቶና ወስኖ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም አንድ አገርና ህዝብን የሚመራና የሚያስተዳድር መንግሥት ዋናው የሥልጣን ምንጭ ለሆነው ህዝብ ተአማኒ ሊሆን ይገባል፤ ግዴታውና ኃላፊነቱም ጭምር ነው፡፡ ስለሆነም የማይሠራውን የመሰረተ ልማት የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ ተገቢ አይደለም፡፡ አንዱ የመልካም አስተዳደር ችግር ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ብሎ የማይፈጽመውን ነገር ቃል መግባትም ሆነ የማይሠራውን የመሰረተ ልማት ፕሮጀክት የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ ተቀባይነት የሌለውና ህዝብን ማታለል በመሆኑ ፈጽሞ መደገም የሌለበት ተግባር ነው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25/2011