ብዙዎቻችን በተለይም የእኔ ዘመን ትውልድ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ያለን እሳቤና አመለካከት ከአባቶቻችንና ከአያቶቻችን በእጅጉ የተራራቀ ነው። ኢትዮጵያን አናውቃትም፤ አወቅናት ካልንም የምንናውቀው ረሐቧን፣ እርዛቷን፣ ድህነቷንና ጉስቁልናዋን ብቻ ነው።
የምናውቀው ከሁሉም ቀድማ የዕውቀት ብርሃን ያየችውን፣ ከራሷ አልፋ ስልጣኔን ለዓለም ያስተዋወቀችውን ከእርሻ እስከ ማረሻ ፣ ከግብርና እስከ ህክምና፣ ከሥርዓተ ጽህፈት እስከ ሥርዓተ መንግሥት፣ ከዜማ እስከ ፍልስፍና የሁሉም ስልጣኔ እርሾ የሆነችውን፣ ነፃነቷን ሳታስደፍር ለብዙ ሺ ዘመናት ታፍራና ተከብራ የኖረችውን ታላቋን ኢትዮጵያ አይደለም።
እንዲያውም ዕድሜ ለክፋትና ለውድቀት መሪዎቻችን፤ ቀሽሞቹን ሰምተን በቀሽሙ የብሔር ፖለቲካ ከታላቅነታችን የቀነጨርነው እኛ የዚህ ዘመን ትውልድ “ውበቷ አይታያችሁ፣ ሚስጥሯ አይገለጽላችሁ” ተብለን የተረገምን ይመስል የአገራችንን ታላቅነት አውቀን በታሪካችን ልንኮራና ታሪክ ልንሰራ ይቅርና አባቶቻችን በሠሩልን የትም የማይገኝ አኩሪ የነፃነት ታሪክም የማንስማማና “በቅኝ ግዛት ተገዝተን ቢሆን ኖሮ እንሰለጥን ነበር!” የምንል ስልጣኔን የማናውቅ ስልጡን መሐይማን ነን።
ይሁንና ታሪኳንና ማንነቷን ጠንቅቀው የሚያውቁ ልጆቿ ኢትዮጵያን በስስት ይመለከቷታል፤ እንደ አፄ ቴዎድሮስ ህይወታቸውን እስከ መስጠት ድረስ በፍፁም ፍቅር ያፈቅሯታል፣ እንደ አብዲሳ አጋ እንኳንስ ምድሯ ድረስ መጥተውባቸው ቀርቶ በማያውቁት በጠላት ምድርም በረሃ ገብተው ይዋጉላታል፤ ሰንደቋን በጠላት አደባባይ ላይ በክብር ከፍ አድርገው እያውለበለቡ ይዘምሩላታል። ፍቅሯ የገባቸው፣ ሚስጥሯ የተገለፀላቸው ልጆቿ ሁሌም ከፍ ከፍ ያደርጓታል፤ እርሷም እንደዚሁ ከፍ ከፍ ታደርጋቸዋለች። እናም ታላቅ ነገርን ፈፅመው መቼም ላትወርድ ታላቅ የክብር ማማ ላይ አስቀምጠዋታል።
ታላቅነቷን የተገነዘቡ የኢትዮጵያ ፍቅር የገባቸው ልጆቿ ዛሬም ኢትዮጵያን ከፍ አድርገው ይመለከቷታል፣ ታላቅ ነገርንም ይመኙላታል፣ ያደርጉላታልም። ከፍ ያለውን ምርጫ በመምረጥ፣ ትልቅ ነገርን ለአገራቸው በማድረግ፣ ዛሬም እንደ ጥንቱ ለታላቋ አገራቸው ታላቅ ታሪክን ይጽፋሉ። ከአያሌ ዓመታት በኋላ ከሰሞኑ ታላቋን አገር እንደገና ታላቅ የታሪክ ማማ ላይ ያስቀመጧት የዘመኔ ጀግና ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያደረጉትም ይህንኑ ነው። ገና መንበረ ሥልጣኑን ከተረከቡበት የመጀመሪያዋ ቅጽበት ጀምሮ ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ስሟ እንኳን ተረስቶ የቆየችውን ታላቋን ባለ ታሪክ አገር “ኢትዮጵያ…ኢትዮጵያ…ኢትዮጵያ…” እያሉ ባለ ግርማ ሞገሱን ስም በአደባባይ ከፍ አድርገው፣ ከፍ አድርገው ብቻ ሳይሆን ደግመው ደጋግመው በፍቅር ጠሩት።
ታላቋን አገር ለመምራት ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ሲመረጡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ አባላት ፊት ቃለ መሐላ በፈፀሙበት ወቅት ከአርባ አንድ ጊዜ በላይ ኢትዮጵያን በፍቅርና በክብር ደጋግመው በጠሩበት ንግግራቸው ዶክተር አብይ አንድ ትንቢት የሚመስል ነገር ተናግረው ነበር። “ኢትዮጵያ ማህፀነ ለምለም ናት። ከፍ ባለ የአገር ፍቅር መንፈስ ሰርክ የሚተጉ ልጆች አፍርታለች። ልጆቿም ወደ ቀድሞ ክብሯ እንድትመለስ፣ የህዝቧ ሰላምና ፍትህ እንዲጠበቅ፣ ብልጽግና ያለ አድልዎ ለመላው ዜጎቿ ይዳረስ ዘንድ አጥብቀው ይመኛሉ፤ ይደክማሉ” ብለው ነበር።
እነሆ ታላቂቷ አገራቸው ወደ ቀድሞ ክብሯ እንድትመለስ ከፍ ባለ የአገር ፍቅር መንፈስ ሰርክ ከሚተጉ፣ የሀገራቸውን ታላቅነት አጥብቀው ከሚመኙና ከሚደክሙ ልጆቿ መካከል አንደኛው እርሳቸው ራሳቸው ሆኑና ትንቢታቸው ተሳክቶ ከዘመናት በኋላ የሚወዷት አገራቸው በዓለም መድረክ ላይ ዳግም እንደገና ከፍ ብላላቸዋለች። ለአገራቸው ከፍ ማለት በፍቅር የሚደክሙ የኢትዮጵያ ልጆች እነርሱም በተራቸው ከፍ ማለታቸው አይቀርምና ዶክተር አብይ አህመድም ከትንሿ በሻሻ ተነስተው በታላቁ የዓለማችን መድረክ ኖርዌይ ኦስሎ ላይ በኩራት ከፍ ብለው ሊቆሙ ችለዋል።
ለመሆኑ ዶክተሩን ለዚህ ታላቅ ክብር ያበቃቸው ነገር ምንድነው?
አዎ ሰው ሆኖ መፈጠርና ሰው ሆኖ መኖር የተለያዩ ነገሮች ናቸው። በእርግጥ በአፈጣጠራችን ሁላችንም ሰዎች ነን። በእኔ እምነት ግን ሰው ለመሆን ሰው ሆኖ መፈጠር ብቻ በቂ አይደለም ባይ ነኝ። እንዲያውም ሰው ሆኖ የመፈጠር ዋናው ምስጢር የሰውነት ዋናው መለኪያ ሰው ሆኖ ከመፈጠር ባሻገር ሰው ሆኖ መኖር ነው። እዚህ ላይ ታዲያ ሰው ሆኖ መኖር ማለት ምን ማለት ነው? የሰውን ልጅ ሰው ሆኖ ለመኖር የሚያበቁ መሰረታዊ የሰውነት ባህርያትስ ምንድናቸው? የሚሉትን አንኳር ጥያቄዎች መጠየቅና መመለስ ወደ ጉዳያችን ጭብጥ ያንደረድረናል።
በእኔ ዕምነት ሰውን ሰው ሆኖ ለመኖር ከሚያበቁት መሰረታዊ ባህርያት መካካል ዋነኛው ለራስ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም መኖር የሚለው ነው። ይህም በተለያየ መንገድ የሚገለጽ ሲሆን፤ አገራችን ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ሰው ሆኖ መኖር የቻሉ ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሰሞኑን የፈፀሙት ተግባርም የዚሁ ሰው ሆኖ የመኖር ባህሪ ዓይነተኛ መገለጫ ነው። እርሱም ከራስ አልፎ ለሰው መኖር መቻል ነው።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በግል ህይወታቸው በሁሉም ረገድ የተሟላ ህይወትን የሚመሩ ሰው ናቸው። የተማሩና በወጣትነታቸው የዶክተርነት ማዕረግ ያላቸው፣ ተኩለው ተድረው፣ ወልደው ወግ ማዕረግ ያዩ፣ በቂ የመተዳደሪያ ጥሪት ያላቸው፣ ብሎም በዓለም ላይ የመጨረሻው የታላቅነት ማማ ተደርጎ የሚወሰደው አገርን የመምራትና የማስተዳደር ደረጃ ላይ የደረሱ ምንም ያልጎደለባቸው ስኬታማ ሰው ናቸው። ይሁን እንጂ “እኔን ከተመቸኝ” ብለው ዝም አላሉም።
ትናንት
ከዚህ ቀደም እንዳየናቸው ምንም እንኳን እርሳቸው የሚኖሩት በታላቁ ቤተ መንግሥት ቢሆንም ትንሿ የእማሆይ ጎጆ የሚያሳስባቸው ሰው ናቸው። ከታላቁ የሥልጣን ማማ ወርደው በደሳሳዋ የእማሆይ አዱኛ ቤት ተገኝተው፤ በድህነት የተጎሳቆለውን የአቅመ ደካማዋን አሮጊት ኑሮ በአካል ተገኝተው የተመለከቱ፤ ለዘመናት ዝናብና ወጀቡን ታግሳ አልፋ ከእማሆይ ጋር አብራ አርጅታ ጣሪያውን መሸከም አቅቷት የዘመመችውን ጎጆ ለማቃናት ዶማቸውን ይዘው ግንባር ቀደም ሆነው የተሰለፉ፤ ከራስ አልፎ ለሰው መኖርን በተግባር ያሳዩ ሰው ናቸው።
እማሆይም ኢትዮጵያን ያህል ታላቅ አገር በልቡ ተሸክሞ አገሩን ወደ ቀደመ ታላቅነቷና ክብሯ ለመመለስ ሌት ተቀን ፋታ ከሌለው ህይወቱ ቀንሶ ለእርሳቸው ሊኖር ከደሳሳ ጎጇቸው አጎንብሶ የገባውን ታላቅ ሰው “ያን ሁሉ የችግር ጊዜያት አሳልፌ ዛሬ አንተን ማን አመጣልኝ፤ ወይ አምላኬ በደስታ መሞቴ ነው” ብለው በደስታ ተሞልተው አመስግነዋቸው ነበር።
አብዩ ሰው ለራስ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም በመኖር ሰው ሆኖ መኖርን በተግባር አሳዩ። ይህም ሰው የቱንም ያህል ታላቅ ቢሆንና ሁሉም ነገር ያለው ቢሆን ከራሱ አልፎ ለሌሎች የሚኖር ካልሆነ ሰው ሆኖ ቢፈጠርም፤ ሰው ሆኖ መኖር ካልቻለ ታላቅ መባል ይቅርና ሰው ተብሎ ሊጠራበት የሚችል አቅም የሌለው መሆኑን የሚያረጋግጥ ከመሆኑም ባሻገር ሁሉም ሰው በዚህ መንገድ እንዲጓዝ የሚያነሳሳ ታላቅ አርአያነት ያለው የሰውነት ተግባር መፈፀማቸውን ያመላከተ ነበር።
ዛሬ
ዛሬስ? ዛሬም ጠቅላይ ሚንስትሩን ለዚህ ታላቅ ስኬት ያበቃቸው ዋነኛው ነገር ይኸው ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የመኖር ፍላጎታቸው፣ ሰው “ሆኖ” መኖርን የተለማመደው ታላቅ ባህሪያቸው ነው። “መሪ ከመሆንህ በፊት ስኬት ማለት ራስህን ለማሳደግ የምታከናውነው ማንኛውም ተግባር ነው፤ መሪ ከሆንክ በኋላ ደግሞ ስኬት የሚባለው ሌሎችን ለማሳደግ የምትሠራው ማንኛውም ሥራ ነው”። ይህ ግሩም አባባል በአንድ ወቅት የጀኔራል ኤሌክትሪክ ሊቀመንበርና ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበረው ታዋቂው አሜሪካዊ መሐንዲስ፣ ደራሲና የቢዝነስ ባለሙያ ጃክ ዌልች የተናገረው ነበር።
ጃክ ዌልች እ.ኤ.አ. ከ1981 እስከ 2001 ዝነኛውን የአሜሪካ ሞተር አምራች ኩባንያ ጀኔራል ኤሌክትሪክን ባስተዳደረባቸው ሃያ ዓመታ የኩባንያውን አጠቃላይ ገቢ በአራት ሺ እጥፍ እንዲጨምር ማድረግ ችሏል። ጃክ ዌልች በግሉ ከቢሊዬነሮች ተርታ የሚሰለፍ ሲሆን፤ የሀብት መጠኑም እስከ አውሮፓውያኑ 2006 ድረስ 720 ሚሊየን ዶላር ደርሶ የነበረ መሆኑን ከዊኪፒዲያ ድረ ገጽ የተገኘ መረጃ ያመላክታል። በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ትልቅ ደረጃ ላይ ከደረሱ ስኬታማ የዓለማችን መሪዎች መካከል አንዱ ሆኖ የሚጠቀሰው መሐንዲስ፤ ደራሲና የቢዝነስ ባለሙያው ጃክ ዌልች በጡረታ ከተሰናበተ በኋላም በታሪክ 417 ሚሊየን ዶላር የጡረታ ክፍያ የተከፈለው ብቸኛው ሰው ሆኖ ተመዝግቧል።
ወደ ዶክተር አብይ ህይወት ስንመጣ የዓለም የሰላም የኖቤል ሽልማትን ሊያሸንፉ የቻሉበትና ለዚህ የእርሳቸውንና የአገራቸውን ስም በዓለም አደባባይ ከፍ አድርገው ላስጠሩበት ለዚህ ታላቅ ክብር የበቁበት ምክንያት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም ለመኖር ካላቸው ፍላጎት ባሻገር በጠቅላይ ሚንስትርነት የአመራር ዘመናቸውም ጃክ ዌልች እንዳለው “ሌሎችን ለማሳደግ ባደረጉት ጥረትና ባከናወኑት ተግባር ነው”።
የኖቤል የሰላም ኮሚቴው ያለውም ይህንኑ ነበር። የኖርዌይ የኖቤል የሰላም ኮሚቴ መሪ አስተባባሪ ቤሪት ሬይስ አንደርሰን ሽልማቱ ለጠቅላይ ሚንስትሩ የተሰጠበት በሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች መሆኑን አብራርተዋል። አስተባባሪዋ “የዘንድሮው የሰላም ኖቤል ሽልማት ለእርስዎ የሚገባዎ በሦስት ምክንያቶች ነው፤ አንደኛ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማስፈን ባደረጉት ጥረት፣ ሁለተኛ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሰላም እንዲወርድ በማድረግዎ፣ ሦስተኛ ከዚያም አልፈው በምስራቅና ሰሜን ምስራቅ አፍሪካ በአጠቃላይ በቀጠናው ላይ ሰላምና ዕርቅን ብሎም አንድነትንና ትብብርን ለመፍጠር በጀመሩት ሥራ ነው”።
ይህም ጠቅላይ ሚንስትሩ ከራሳቸውና ከራሳቸው አገር አልፈው ለጎረቤቶቻቸው በአጠቃላይ በመላው ዓለም ለሚኖሩ የሰው ልጆች ያላቸውን መልካም ራዕይ በተለይም “ሰው ሆኖ ለመኖር” ያላቸውን ታላቅ ፍላጎት የሚያሳይ ነው። ሰው ማለትም ይኼ ነው። ከራሱ አልፎ ለሌሎች ሲያስብ ራሱን ብቻ ሳይሆን አገሩንም የሚያስጠራ፤ መሰረቱ ደግሞ ለአገሩ ያለው ታላቅ ፍቅር! ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ቀላል፣ የኢትዮጵያ ታላቅነትም ተረት ተረት ለሚመስለን ለእኔ ዘመን ትውልድም እውነታውን ለማሳወቅ ትልቅ አጋጣሚ ነው።
በታላቅ የአገር ፍቅር ታላቅ ክብርን የተጎናፀፉት ታላቁ ሰው አገራቸውን አስከብረው በዚያውም ራሳቸው ከብረው ወደ አገር ቤት ከተመለሱ በኋላ በተደረገላቸው የደስታ መግለጫ የአቀባበል መርሐ ግብር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያስረገጡትም ይህንኑ ነው።
“ትናንትናና ከትናንትና ወዲያ በኦስሎና ስቶክሆልም በነበረን ቆይታ የማናውቃትን ኢትየጵያ ለማወቅ ዕድል አግኝተናል!” አሉ ዶክተር አብይ፤ “ለካ እኛ ኢትዮጵያውያን አላውቅነውም እንጅ ትልቅ ታሪክ ያላት የተከበረች ታላቅ አገር ነው ያለችን!”። …‹‹አጋጣሚውን ተጠቅመው ነገሥታት፣ መሪዎች፣ የፓርላማ አባላት፣ ምሁራንና ሳይቲስቶች ስለ እኛ አገር ታሪክና ትልቅነት ሲናገሩ፣ አገራችን ስላልገባችን በሚገባት ልክ እያገለገልናት እንዳልሆነ ተሰምቶን ነው የተመለስነው!” አይገርምም!
አዎ! አገራችን ስላልገባችን ነው እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት እኛ የሰለጠንን መስሎን ነው የራሳችንን ጥለን የሰውን የምናንጠለጥለው፣ የራሱን ናቂ ሩቅ ናፋቂዎቹ አገራችንን ፍፁም ለማናውቃት ይቅርና ብዙ ታሪኳንና ማንነቷን ለማወቅ ለደከሙላትና አውቀናታል ብለው ለሚያስቡትም ኢትዮጵያ ሚስጥር ናት! ያውቋት ይመስላቸዋል እንጂ ፈፅመው አያውቋትም።
በውብ ተፈጥሮ ያጌጠች፣ የራሷ ፊደልና የዘመን አቆጣጠር ያላት፣ የታላላቅ ቁሳዊና መንፈሳዊ ቅርሶች ባለቤት፣ የሰው ዘር መገኛ፣ ቀደምት የስልጣኔ ምንጭ፣ በቅዱሳን መጽሐፍት ተደጋግማ የተጠቀሰች ታላቅ አገር ናት ኢትዮጵያ! ስልጣኔን ቀድመው ለዓለም ያስተማሩ ጥበበኛ ልጆቿ የአዕምሮ ውጤት የሆኑትና ዓለምን ያስደነቁት እነ አክሱም፣ ላሊበላ ፋሲልና ጀጎል በመሳሰሉትና ሌሎችም ተዘርዝረው በማያልቁ ቁሳዊ፣ መንፈሳዊና ባህላዊ ሀብቶቿ ለዓለም የስልጣኔን እርሾ የጣለች ታላቅ አገር ናት።
ጥንት ድሮ ገና ያኔ መንግሥታት ሳይመሰረቱ፣ የዛሬው “ስልጡኖቹ” አውሮፓና መላው ዓለም በድንኳን በነበሩበት ሰዓት የታሪክና የአውሮፓ ስልጣኔ አባት በመባል የሚታወቁት ታላላቆቹ ግሪካውያን እነ ሄሮዶተስ እና ሆሜር ገነትን እስከሚያጠጣው ምንጯ ግዮን ድረስ መጥተው ህዝቦቿንና ምድሯን ጎብኝተው “በጦርነት ካልሆነ በስቀር በበሽታ የማይሞቱ፣ ረጃጅሞችና መልካቸው የሚያምር፣ አማልክት የሚሰግዱላቸው ውብ ህዝቦች ያሉባት ምድር” ብለው የመሰከሩላት አገር ኢትዮጵያ ናት።
ጥንት ስለ ሰብዓዊነቷና ስለደግነቷ “አትንኳት” የተባለች፣ ኋላም በዘመናዊው ዓለም ትዕዛዙን ጥሰው በክብሯ በመጡባት ላይ ደግሞ በአስደናቂ ጀግንነት ጠላቷን አንበርክካ አንፀባራቂ ድልን የተቀዳጀች አኩሪ ታሪክ ያላት አገር ኢትዮጵያ ናት። ሁኔታዎች ተመቻችተውለት በአንፃራዊነት በጉልበት በልጦ በመገኘቱ እንደሚጠፋ እንስሳ በኃላፊ ጠፊ ጡንቻው ተመክቶ፣ በሳጥናኤላዊ “የእኔ እበልጣለሁ” ትዕቢት በሰው ልጆችና በሰውነት ላይ ይቅር የማይባል ወንጀል በፈፀመው አምባገነን ወራሪ ላይ ድልን የተቀዳጀች፤ ማንም ያልቻለውን ዘመን አይሽሬ ድል በሚወዷት ልጆቿ እጅ የጻፈች፣ ሰው ሁሉ እኩል መሆኑን ያሳየች የዓለም የነፃነትና የእኩልነት ተምሳሌት የሆነች ታላቅ አገር ኢትዮጵያ ናት!
እንደ ጥንቱ ሁሉ በዚህኛው ዘመንም እነ አዶልፍ ፓርልሳክ ከምስራቅ አውሮፓ ድረስ መጥተው፣ ከጀግኖች አባቶቻችን ጋር ጦር ሜዳ ዘምተው፣ ታንክ በምድር እየተሽከረከረ ዕሳት እየተፋባቸው፣ ከሰማይ በአውሮፕላን መርዝ እየዘነበባቸው ታሪክና ጀብዷን የጻፉላት ታላቋ አገር ኢትዮጵያ ናት ።
ዛሬስ ? ዛሬም በሚወዷት ልጆቿ በእነ አብይ አህመድ አማካኝነት በታላቁ የዓለም መድረክ ላይ በክብር ከፍ ብላ የቆመች፣ ሁለት ቢሊዮን የሚጠጋ የዓለም ህዝብ በቀጥታ በቴሌቪዥን በሚከታተለው በታላቁ የሰላም የኖቤል ሽልማት መርሐ ግብር ላይ ልጆቿ ብቻ ሳይሆኑ ባዕዳንም ታላቅነቷን የመሰከሩላት ታላቅ አገር ናት ኢትዮጵያ! እንዲያውም ሚስጥሩ ሲጠቃለል ቤሪት ሬይስ አንደርሰን ‹‹ኢትዮጵያ ኃያል ነን ብለው በኃይል ሊወሯት የሞከሩትን የምዕራባውያንን ጡንቻ ክብር እንጅ እጅ መስጠት በማይወዱት በጀግኖች ልጆቿ ክንድ የመከተች፣ በዚህም በዘመኗ ሁሉ ነፃቷን አስጠብቃ በክብር የኖረች፣ ልዩ ታሪክ ያላት” እንዳሉት ታላቅ አገር መሆኗ ተመስክሮላታል።
እናማ ታላቅነቷ ከልጆቿም አልፎ ለመላው የሰው ዘር መመኪያ መሆኑ “የመጀመሪያው የሰው ዘር የተገኘው ከኢትዮጵያ ምድር ነው፤ በዚህም እኛ ሁላችንም መላው ዓለምም ኢትዮጵያን ነን ማለት ይቻላል” የሚለው የቤሪት ሬይስ አንደርሰን ምስክርነት ከመቼውም ጊዜ በላይ የኢትዮጵያን ታላቅነት ለማወቅ መልካም አጋጣሚ ነውና ባለማወቅ ኢትዮጵያን የምናቃልል ሁሉ ከስንፍናችን ለመላቀቅ ጊዜው አሁን ነው በማለት ልሰናበታችሁ ወደድኩ። ታላቅ ነበርን፣ ታላቅም እንሆናለን! ኢትዮጵያ ታላቅ ናት ለዘላለም ትኑር!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታህሳስ 8/2012
ይበል ካሳ