ዋስትና መብት ነው
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
ዋስትና በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ብርቱ ጥበቃ ከተደረገላቸው መሰረታዊ መብቶች ውስጥ አንዱ ነው። የዋስትና መብት “ማንኛውም ሰው በሕግ ከተፈቀደው ሥርዓት ውጭ ሊያዝ፣ ክስ ሊቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰር አይችልም” ከሚለው ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚቀዳ ነው። በዚህ መነሻ የዋስትና መብት እናቱ የነፃነት መብት ስለመሆኑ ነው የሕግ የቀለም ቀንዶች ካሰፈሯቸው ስንክሳሮች መረዳት የሚቻለው።
የተያዙ እና የተከሰሱ ሰዎች በዋስትና የመፈታት መብት አላቸው። ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች የቀረበባቸው ክስና ምክንያቶቹ በዝርዝር ወዲያውኑ በሚገባቸው ቋንቋ ሊነገራቸው ይገባል። ከዚያም በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ አለባቸው።
ፍርድ ቤት ከመቅረባቸው አስቀድሞም ሆነ ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ ታዲያ በዋስትና የመፈታት መብት አላቸው። በተመሳሳይ በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች ክስ ከቀረበባቸው በኋላ በመደበኛ ፍርድ ቤት ለሕዝብ ግልጽ በሆነ ችሎት የመሰማት መብት ያላቸው ሲሆን፤ በዋስትና የመፈታትም መብት አላቸው።
አብዛኞቹ መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች በመርህ ደረጃ ዕውቅና የተሰጣቸውና ጥበቃም የተደረገላቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ፍፁማዊ መብቶች ባለመሆናቸው በሕግ በሚቀመጡ ልዩ ሁኔታዎች መገደባቸው አይቀሬ ነው። የዋስትና መብትም እንዲሁ ገደብ የሚጣልበት ወይም ሊከለከል የሚችል መብት ነው። እነዚህም በሕጉ የተቀመጡ ዋስትናን የሚያስከለክሉ የመርህና የሁኔታ ምክንያቶች ናቸው።
ዋስትና የሚከለከልባቸው የሕግ ሁኔታዎች
በ1954 ዓ.ም. ወጥቶ እስከ አሁንም ድረስ በሥራ ላይ የሚገኘው የአገራችን የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ከወንጀል ጉዳይ ጋር በተያያዘ ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግና ፍርድ ቤት ሊከተሏቸው የሚገቡ የሥነ-ሥርዓት መርሆና ቅደም ተከተሎችን የያዘ ሕግ ነው። በሕጉ ውስጥ ከተቀመጡት ጉዳዮች ውስጥ ደግሞ አንዱ ዋስትናን የተመለከተው ነው።
አንድ ሰው ወንጀል ፈፅሞ እጅ ከፍንጅ ተይዞ ሊታሰር ይችላል። ፖሊስ ወንጀል ስለመፈፀሙ ወይም እየተፈፀመ ስለመሆኑ አቤቱታ ከደረሰው በኋላ ወንጀል ፈፅሟል በሚል የተጠረጠረው ሰው መጥሪያ ተልኮለት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሊቀርብ ይችላል። የፖሊስ መጥሪያ ተልኮለት ወደፖሊስ ጣቢያ ያልቀረበውን ሰው አልያም ሌላ ተጠርጣሪን ፖሊስ የሥነ-ሥርዓት ሕጉን ተከትሎ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማውጣት ሊያስረው ይችላል።
ስለ ዋስትና መብት ሲነሳ ታዲያ ከሁሉም አስቀድሞ የሚፈፀመው ተጠርጣሪውን ፖሊስ በዋስትና የሚፈታበት ሥነ-ሥርዓት ነው። በሥነ-ሥርዓት ሕጉ አንቀፅ 28 ላይ እንደተመለከተው ደግሞ የተያዘው ሰው ቃሉን ከሰጠ በኋላ (ቃሉን ያለመስጠት መብትም አለው) ፖሊስ የዋስትና ወረቀት አስፈርሞ ከእስራት ሊፈታው ይችላል።
ፖሊስ ተጠርጣሪውን የዋስትና ወረቀት አስፈርሞ የሚፈታው በሦስት ምክንያቶች ነው። የመጀመሪያው ተጠርጣሪው የተያዘበት ወንጀል በፅኑ እስራት ወይም ይህንኑ በመሰለ ተለዋጭ ቅጣት የማያስቀጣ ሲሆን ነው። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ተፈፀመ የተባለው ወንጀል የተፈፀመ ስለመሆኑ የሚያጠራጥር ከሆነ ነው። ሦስተኛው ምክንያት ተጠርጣሪው የተጠረጠረበትን ወንጀል ለመሥራቱ የሚያጠራጥር ሲሆን ነው።
ይህ ድንጋጌ ዛሬም ሆነ በተለይም ቀደም ባሉት ጊዜያት አልፎ አልፎ በፖሊስ ተቋማት ውስጥ የዜጎችን መብቶች ለመጣስ ዓይነተኛ መሣሪያ ሆነው ከሚያገለግሉ ሕጎች ውስጥ አንዱ ነው። አንዳንድ ሥነ-ምግባር የጎደላቸው እና የሕግ ዕውቀት ያጠራቸው የፖሊስ አባላት በቁጥጥራቸው ሥር የሚገኘውን ተጠርጣሪ በድንጋጌው የተጠቀሱት ምክንያቶች ከተሟሉ የዋስትና መብቱን ማክበር ሲገባቸው ያለአግባብ አስረው ሲያቆዩ ይስተዋላል። በሌላ በኩል ድንጋጌውን ያለአግባብ በመተርጎም በፖሊስ ዋስትና ሊለቀቅ የማይገባውን ተጠርጣሪ በዋስትና የሚፈቱበት አጋጣሚም ቀላል አይደለም።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በወንጀል ፍትህ ፖሊሲው፣ በፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ እና በሌሎችም ሕጎች እንዲሁም የፍትህ አካላቱ በጋራ ባስቀመጧቸው ቢፒአርን የመሳሰሉ የአሠራር ሥርዓቶች በመታገዝ የወንጀል ምርመራዎችን ዓቃቤ ሕግ እየመራ ይገኛል። ምርመራዎችም በፖሊስና በዓቃቤ ሕግ በጋራ በመከናወን ላይ ናቸው። ዓቃቤ ሕግም የምርመራ አካሄዶችን ሕጋዊነት በቅርበት እየተከታተለ በመሆኑ የሥነ-ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 28 የመብት መጨቆኛ እንዲሁም ያልተገባ ጥቅም ማግኛ መሣሪያ መሆኑ እየቀነሰ መጥቷል። የጊዜ ቀጠሮ ችሎቶችም የምርመራ ሕጋዊነትን ይከታተላሉ።
በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በግልጽ ሰፍሮ እንደምናነበው የታሰሩና የተያዙ ሰዎች በዋስ የመፈታት መብት ቢኖራቸውም ቅሉ፤ በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች ግን ፍርድ ቤት ዋስትናን ሊከለክላቸው ይችላል። በሕግ የተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች የሚባሉት በአንድ በኩል ሕግ ራሱ እነዚህ እነዚህ ወንጀሎች ዋስትና ያስከለክላሉ በሚል በመርህ ደረጃ የዋስት መብትን የሚነፈግባቸው ምክንያቶች ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ወንጀሉ በመርህ ደረጃ ዋስትና ባያስከለክልም ሕጉ እነዚህ እነዚህ ሁኔታዎች ከተሟሉ ዋስትናን ለመከልከል ምክንያት ይሆናል በሚል ያስቀምጣል።
በአገራችን በመርህ ደረጃ የዋስትና ክልከላ የሚያስቀምጥ የመጀመሪያው ሕግ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ነው። በሕጉ መሰረት ማንኛውም የተያዘ ሰው የተከሰሰበት ወንጀል የሞት ቅጣትን ወይም 15 ዓመት ወይም በላይ የሆነ ፅኑ እሥራት የሚያስቀጣ ከሆነ እና ወንጀል የተፈፀመበት ሰው በደረሰበት ጉዳት ከሞተ የዋስትና መብት ይከለከላል።
ከዚህ ድንጋጌ ለመረዳት እንደሚቻለው ወንጀሉ የሞት ቅጣትን ወይም 15 ዓመት ወይም በላይ የሆነ ፅኑ እሥራትን የሚያስቀጣ መሆኑ ብቻ ዋስትና አያስከለክልም። በዚህ ወንጀል ምክንያት ሰው ከሞተ ጭምር ነው የዋስትና መብት የሚነፈገው።
እዚህ ድንጋጌ ላይ “15 ዓመት ወይም በላይ” በሚል የተቀመጠው አገላለጽ የሚያመለክተው የመነሻ ቅጣትን ነው ወይንስ የቅጣቱን ጣሪያ የሚለው አከራካሪ ነው። ለምሳሌ አንድ ወንጀል ከ10 እስከ 25 ዓመት የሚያስቀጣ ቢሆንና በወንጀሉ ምክንያት የሞተ ሰው ቢኖር 15 ዓመት ወይም በላይ በሚለው አገላለጽ መሰረት የመነሻው ነው ወይስ የመጨረሻው ቅጣት የሚታየው የሚለው አከራካሪ ነው።
ያም ሆኖ በተለያዩ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ውሳኔዎች ከተሰጡ ውሳኔዎችና የሥር ፍርድ ቤቶችም በስፋት ከያዙት የአተረጓጎም አካሄድ ለመረዳት እንደሚቻለው ለወንጀሉ የተቀመጠው የመጨረሻው ጣሪያ 15 ዓመትና ከዚያ በላይ ከሆነ እና ወንጀል የተፈፀመበት ሰው በደረሰበት ጉዳት ከሞተ የዋስትና መብት ለመንፈግ ምክንያት ይሆናል።
የዋስትና ክልከላን የሚያስቀምጥ ሌላው ሕግ የተሻሻለው የፀረ ሙስና ልዩ የሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 434/1997 ነው። በአዋጁ መሰረት በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው ወንጀሉ ከ10 ዓመት በላይ ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ በዋስትና ሊለቀቅ አይችልም።
ይህንን አዋጅ ያሻሻለው አዋጅ ቁጥር 882/2007 በበኩሉ በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው ወንጀሉ ከ10 ዓመት በላይ ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ በዋስትና ሊለቀቅ አይችልም ከሚለው በተጨማሪ ከአራት ዓመት በላይ ከአስር ዓመት በታች የሚያስቀጡ ተደራራቢ ወንጀሎች ሲኖሩም እየተደመሩ ድምራቸው ከአስር ዓመት በላይ የሚያስቀጣ ከሆነ ዋስትና እንደሚነፈግ ደንግጓል።
በመርህ ደረጃ የዋስትና መብት የተነፈገበት ሌላው ሕግ በ1996 ዓ.ም. አደገኛ ቦዘኔነትን ለመቆጣጠር በሚል የወጣው አዋጅ ቁጥር 384/1996 ነው። አዋጁ በአደገኛ ቦዘኔነት ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው በዋስትና እንደማይለቀቅ ደንግጓል።
ዋስትና የሚከለከልባቸው የሁኔታ ምክንያቶች
የታሠሩና የተያዙ ሰዎች በዋስ የመፈታት መብት አላቸው። ይሁንና በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች ፍርድ ቤት ዋስትናን ሊከለክላቸው ይችላል። በሕግ የተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች የሚባሉት ደግሞ ሕጉ ራሱ በመርህ ደረጃ የዋስትና መብት የሚነፍግባቸው እና ከላይ በዝርዝር የተመለከትናቸው ምክንያቶች ናቸው። በተጨማሪም ወንጀሉ በመርህ ደረጃ ዋስትና ባያስከለክልም ሕጉ እነዚህ እነዚህ ሁኔታዎች ከተሟሉ ዋስትናን ለመከልከል ምክንያት ይሆናል በሚል የሚያስቀምጣቸው የሁኔታ ምክንያቶችም አሉ።
የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ዋስትናን ለመንፈግ ሦስት የሁኔታ ምክንያቶችን ያስቀምጣል። የመጀመሪያው ተጠርጣሪው በዋስትና ከተፈታ በኋላ በቀጣይ ቀጠሮዎች ላይ የዋስትና ግዴታውን አክብሮ በችሎት በመቅረብ ጉዳዩን የማይከታተል የሚመስል ከሆነ ነው። ሁለተኛው ምክንያት ተጠርጣሪው ቢለቀቅ ሌላ ወንጀል ይፈፅም ይሆናል ተብሎ ሲገመት ነው። በዋስትና ከተፈታ በኋላ ማስረጃዎችን ያጠፋል በተለይም ምስክሮችን በማባበል፣ በመግዛት፣ በማስፈራራት ወይም በሌላ ምክንያት ያሸሻል ተብሎ ሲገመትም ዋስትና የሚከለከልበት ሦስተኛው የሁኔታ ምክንያት ነው።
የዋስትና መብት በሕጉ በልዩ ሁኔታ በሚገለፅ አግባብ በመርህ ደረጃ ሲከለከል አከራካሪ ሁኔታ ሊኖር አይችልም። ምክንያቱም ተጠርጣሪው የተያዘበት ወይም የተከሰሰበት ወንጀል በባህርዩ ዋስትና የሚያስከለክል ነው ተብሎ በሕጉ እስከተቀመጠ ድረስ ክርክር አይነሳም።
ይሁንና የተደረገው ወንጀል በመርህ ደረጃ ዋስትናን የማያስከለክል ቢሆንም እነዚህን ሦስት የሁኔታ ምክንያቶች መሰረት በማድረግ የዋስትና መብት በሚነፈግበት ወቅት ብርቱ ክርክር መነሳቱ አይቀርም። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በሕጉ የተቀመጡት ሦስቱም የሁኔታ ምክንያቶች ግምትን መሰረት ያደረጉና ማስረጃ የሚያስፈልጋቸው ብሎም ማስረጃዎቹም ሊመዘኑ የሚገባቸው መሆኑ ነው። ከሁሉም በላይ ሕጉ ሦስቱን ሁኔታዎች ከመዘርዘር ውጭ ለሁኔታዎቹ ምክንያት ይሆናሉ የሚባሉትን ጉዳዮች አላመላከተም። ለማሳያነት ተከሳሹ የዋስትና ግዴታውን አክብሮ ላይቀርብ ይችላል የሚለውን ግምት ለመያዝ ምን ምን ዓይነት ምክንያቶችን ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል የሚለው በሕጉ በግልጽ አልተቀመጠም።
ዋስትናን ለመከልከል ከሚቀርቡት ሦስት ምክንያቶች ውስጥ ሁለቱ ተጠርጣሪው በዋስትና ከተፈታ በኋላ የዋስትና ግዴታውን አክብሮ በችሎት በመቅረብ ጉዳዩን የማይከታተል የሚመስል ከሆነ እና ቢለቀቅ ሌላ ወንጀል ይፈፅም ይሆናል ተብሎ ሲገመት ነው። ፍርድ ቤት ታዲያ እነዚህን ግምቶች እንዲይዝና የተከሳሹን ዋስትና እንዲነፍግ በዓቃቤ ሕግ በኩል ብዙውን ጊዜ ከሚቀርቡ መከራከሪያዎች ውስጥ የመጀመሪያው ተከሳሹ ቀደም ሲል በሌላ ወንጀል የተቀጣ (የወንጀል ሪከርድ ያለበት) አለበት የሚል ነው።
ተከሳሹ ቀድሞ በሌላ ወንጀል የተቀጣ ስለሆነ አሁን በተከሰሰበት ወንጀል በዋስትና ቢወጣ ተመልሶ እንደማይቀርብ፤ እንዲያውም ቢለቀቅ ሌላ ወንጀል እንደሚፈፅም ግምት መውሰድ ይቻላል የሚለው ይህ የዋስትና መቃወሚያ ተጠርጣሪው በተከሰሰበት ወንጀል ፍርድ እስከሚያገኝ ድረስ ንፁህ ሆኖ የመገመት ሕገ መንግሥታዊ መብቱን ይፃረራል በሚል ሲነቀፍ ይስተዋላል። በተለይም ዓቃቤ ሕግ ዋስትናን ለማስከልከል የወንጀል ሪከርድ ሰነድ በማስረጃነት በሚያቀርብበት ወቅት ተከሳሹን በተመለከተ በዳኞች ሕሊና ውስጥ አሉታዊ ምስል እንዲቀረጽ ምክንያት ስለሚሆን ይህንን ክርክር በማንሳት ዋስትናን ለማስነፈግ መከራከር ሲነቀፍ ይስተዋላል።
የተጠርጣሪው የዋስትና መብት እንዲከለከል በዓቃቤ ሕግ በኩል በብዛት የሚቀርበው ሌላው የሁኔታ ምክንያት ተከሳሹ የቀረቡበትን የወንጀል ክሶች ብዛት በምክንያትነት ማንሳት ነው። በዚህም መሰረት ተከሳሹ በዋስትና ቢለቀቅ ንፁህ ሆኖ የመገመት መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ምናልባት ጥፋተኛ ሆኖ ቢቀጣ ከባድ ቅጣት እንደሚጣልበት ከወዲሁ አመዛዝኖ ቅጣቱን በመሸሽ ተመልሶ በችሎት ሊቀርብ እንደማይችል ጠቅሶ ዓቃቤ ሕግ ዋስትናን ይቃወማል። ይህ የሁኔታ ምክንያት ዋስትና ለመከልከል ቅቡልነት ያለው መሆኑ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የተሰጠበት ነው።
ዓቃቤ ሕግ ተጠርጣሪው በዋስትና ከተፈታ በኋላ የዋስትና ግዴታውን አክብሮ በችሎት በመቅረብ ጉዳዩን ሊከታተል አይችልም የሚል ግምት ተወስዶ ዋስትና እንዲከለከል መከራከሪያ የሚያቀርብበት ሌላው ምክንያት ተከሳሹ ቋሚ የመኖሪያ አድራሻ የለውም የሚል ነው። በዚህ አግባብ ተጠርጣሪው ቋሚ የመኖሪያ አድራሻ ስለሌለው የዋስትና ግዴታውን ሊያከብር አይችልም የሚል ግምት እንዲወሰድና ዋስትና እንዲከለከል ማድረግ በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ ሲነቀፍ ይደመጣል።
እርግጥ ነው አንድ ሰው የገንዘብ፣ የንብረት አልያም የሰው ዋስ አስይዞ በዋስትና ሲለቀቅ በቀጣይ ቀጠሮዎች ዋስትናውን አክብሮ በችሎት እንደሚቀርብ ግምታዊ እምነት ተጥሎበት ነው። ይሁንና ዋስትናውን አክብሮ ካልቀረበ በሕጉ መሰረት በቀጣይ ቀጠሮ ታስሮ እንዲቀርብ ይደረጋል። ይህ የሚፈፀመው ደግሞ ፖሊስ ተከሳሹ ባስመዘገበው አድራሻ መሰረት አፈላልጎ ወይም ተከታትሎ አስሮ ሲያቀርበው ነው። ከዚህ ውጭ ግን ተከሳሹ ቋሚ አድራሻ ካላስመዘገበ በዋስትና የተለቀቀበት ጉዳይ ከዳር ሳይደርስ፤ ፍትህም ሳይረጋገጥ መዝገቡም ተቋርጦ ማለት ነው።
በዚህ መነሻ ቋሚ የመኖሪያ አድራሻ አለመኖር ተከሳሽ በዋስትና ቢለቀቅ የዋስትና ግዴታውን አክብሮ አይቀርብም የሚል ምክንያታዊ ግምት ለመውሰድ አንዱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል መረዳት ያስፈልጋል። ያም ሆኖ ሌሎች ተጨማሪ የሁኔታ ምክንያቶች ባልተገኙበት ሁኔታ በአድራሻ ምክንያት ብቻ ግዙፍ የሆነውን የዋስትና መብት መከልከል አግባብነት አይኖረውም። እናም ምክንያታዊ ግምት ለመውሰድ ሌሎች ሁኔታዎችንም መመዘን የሚያስገፈልግ ሲሆን፤ ግምት ለመውሰድ የማይቻል ከሆነም ደግሞ ተጠርጣሪው ከአገር እንዳይወጣ እገዳ መጣልና ሌሎች መሰል ዋስትናን ከመከልከል በመለስ ያሉ ሕጋዊ እርምጃዎችን መውሰድ ቅቡልነት ያለው ነው።
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎትም ዋስትና ከሚከለከልባቸው የሁኔታ ምክንያቶች ጋር በተያያዘ የሥነ-ሥርዓት ሕጉን የአተረጓጎም መርሆ በተመለከተ በርከት ያሉ ውሳኔዎችን አሳልፏል። ችሎቱ በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ በርካታ ውሳኔዎችን በመወሰኑ ምክንያት ነቀፌታ የሚሰነዘርበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በሁሉም ውሳኔዎቹ ላይ ፍርድ ቤቶች የተከሳሾችን ዋስትና ለመከልከል የሚይዙት ግምት በበቂና በሕጋዊ ምክንያቶች ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል። በቂና ሕጋዊ በሚል የሚወሰዱት ምክንያቶች ደግሞ ከተለያዩ ከባቢያዊ ሁኔታዎችና ከጉዳዮች ልዩ ባህርይ አንፃር እየተመዘኑ ግንዛቤ የሚወሰድባቸው መሆናቸውንም በውሳኔዎቹ አመላክቷል።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታህሳስ 8/2012
በገብረ ክርስቶስ