ይህ ዕድሜ ጠገብ “አዲስ ዘመን ጋዜጣ” ባለፉት ዐሠርት የዕድሜ ጉዞው ውስጥ ከምጥን ዜና እስከ ዝርዝር ሀተታ ለንባብ ያበቃቸው ጽሑፎች በወጉ ቢጠኑና ቢመረመሩ ከዘመን ማሳ ላይ እጅግ ብዙ ቁምነገሮችን ማጨድ ይቻላል። የዛሬን መነፅር እንዳጠለቅን አትኩረን ወደ ኋላ ብንመለከት “ሆቼ ጉድ!” አሰኝተው የሚያስፈግጉን እጅግ በርካታ ሃሳቦችንና የንግድ ማስታወቂያዎችን መተዋወቅ ይቻላል። ጽናቱን ሰጥቶን ቀደምት የጋዜጣውን ዕትሞች ለመመርመር አቅም ይኑረን እንጂ የሃሰሳው ገበታ ይራቆታል ተብሎ የሚታማ አይደለም።
ለሦስት ዐሠርት ተኩል ዓመታት ያህል መደበኛ ጋዜጠኛ ሳልሆን ጋዜጠኛ አድርገው በሙያው ውስጥ ላዳበሉኝ ለዚህ ጋዜጣ መሪዎችና ቤተሰቦች ምስጋናዬን ባቀርብ ተገቢ ይመስለኛል። እየተማርኩ እንዳስተምር ያደረገኝ ይህ ጋዜጣ በግሌ “የሰለጠንኩበት ኮሌጄ ነበር” ብዬ ብመሰክር ለአንባቢዬ ግርታ ቢፈጥርም ለእኔ ግን የፀና እውነታ ነው። የማዕዱ ተጋሪና ተባባሪ በሆንኩባቸው ረጅም ዓመታት የተማረኩትና የደረስኩበት ድምዳሜም ይሄው ነው።
በምስጋና አጅቤ የተንደረደርኩበት ታሪካዊው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ በጥር 30 ቀን 1933 ዓ.ም በ36ኛው ዕትሙ አንድ አጭር ጽሑፍ፤ ግን የጠለቀ ትምህርት ያለው ባህላዊና ቅቡል ልማድ ለንባብ አብቅቶ ነበር። ይህንኑ አጭር ጽሑፍ የዛሬ ሣምንት ታኅሣሥ 1 ቀን 2012 ዓ.ም የወጣው ይሄው ጋዜጣ ለትውስታና ለትዝታ እንዲበጅ በማሰብ ከስምንት ዐሠርት ዓመታት በኋላ አስነብቦን ነበር።
,በዚህ ጸሐፊ እምነት ጽሑፉ “በትናንቱ ሀገራዊና ባህላዊ ልምምድ” ፈገግ እንድንል ታስቦ የቀረበ ብቻ አይመስለኝም። በግሌ መልዕክቱ ጥልቅ ትርጉም ስለሰጠኝ ቀልቤን ዘርፎታል። የተረዳሁትንም እውነታ ከዛሬው አንዳንድ ሀገራዊ እውነታችን ጋር ሳመሳክረው የትርጉሙ ጥልቀት መካሪና ዘካሪም እንደሆነ ተረድቻለሁ። ሳምንት እንደ ቅምሻ፤ በዛሬ ዕትም ደግሞ እንደ ጉርሻ የሚቆጠረውን ያንን አጭር ጽሑፍ ነዎሩ ብዬ ዳግም በብዕሬ ክብር ሰጥቼ ቃል ከነጥብ ሳላጓድል እንደሚከተለው እጠቅሰዋለሁ።
የጅብ አፍ፤
“በሀገራችን አንድ ሰው ከብት ሲጠፋበት አግኝቶ ላሳደረለት ሰው የሚከፍለው “የጅብ አፍ” የሚባል ገንዘብ አለ። የሚከፈለው ገንዘብ “የጅብ አፍ” ተብሎ የተሰየመበት ትርጓሜው እንዲህ ነው። ባጭሩ የጠፋችውን ከብት ያ የጅብ አፍ የሚከፈለው ሰው ባያገኘው ኖሮ ጅብ በልቷት ጠፍታ የምትቀር ስለነበረች ከጅብ አፍ አውጥቶ ጠፍቶ ከመቅረት ስላዳናት ላገኛት ሰው ስለውለታው ይህ የጅብ አፍ የሚባል ገንዘብ ይሰጠዋል።”
“ይህም ልማድና ደንብ ከአበው ጀምሮ እስከ እኛ ዘመን ስለደረሰ የሰው ከብት ከጅብ አፍ ጠብቆ ላዳነ ሰው ለድካሙና ለጠባቂነቱ “የጅብ አፍ” ይቀበላል። ይህንንም ብይን የሚበይኑ ዳኞች ለደከመው ምስጋና ከዋጋው ጋር የሚገባው መሆኑን ስለተረዱትና በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ለደከመና ለሠራ ውለታውን መመለስ የማያስወቅስ ስለሆነ ነው።”
ይህ ሥርዓት በዛሬይቱ ኢትዮጵያ በአንዱ ጎጥ ወይንም አካባቢ ይኑር አይኑር እርግጠኛ አይደለሁም። ካለም ለሽበቱ ክብር ነዎሩ ቢሰኝ፣ ዘመን ወለድ ሥልጣኔም በታሪክ መዝገብ ውስጥ ሸሽጎት ከሆነም መልካም የጡረታ ዘመን ብሎ መመረቁ አግባብ ብቻ ሳይሆን ላበረከተው የረጅም ዘመን አገልግሎት በኒሻን ሽልማት ማድመቁ እንኳ ቢቀር የቃል ምስጋና ግን ሊነፈገው አይገባም። ትምህርቱና ልማዱ በነበር ታሪክነቱ ብቻ ሳይሆን ለዛሬውም ጀምበር ቢሆን ለብዙ ጉዳይ ማጣቀሻ ሊሆን የሚችል አቅም እንዳለው ግን ማረጋገጥ አይከብድም።
አንድምታው ይህንን ይመስላል፤
የተለያዩ ዓይነት የመሪዎችን ባህርያት ያመላክታሉ ብለው ስለገመቱ የዘርፉ ምሁራን የአንድን መሪ ስብዕናና የአመራር ዘይቤ በጨዋታ መልክ እያዋዙ ከእንስሳት ባህርያት ጋር በተለዋጭ ዘይቤ እያነፃፀሩ ያስተማሩበትን አንድ አብነት “የአመራር ጥበብ” በሚለው መጽሐፌ ውስጥ በዝርዝር ጠቅሼ አመላክቻለሁ። ክቡሩ የሰው ልጅ ከእንስሳት ባህርይ ጋር እንደምን ሊነፃፀር ይችላል? የሚል ቅሬታ እንደማያስከትል ተስፋ በማድረግ። የመሪው ደካማም ሆነ ጠንካራ ባህርያት በመጽሐፌ ውስጥ እንደሚከተለው ተዘርዝሯል።
አንበሳ፤ ሁልጊዜ አሸናፊ መሆን አለብኝ በሚል ፍልስፍና የተቃኘ ስብዕና ያለው ነው። አህያ፤ እልኸኛና ግትር፣ ሃሳቧን ለመቀየር የምትቸገር እንስሳ መሆኗን የምታረጋግጠው በተግባሯ ነው። ጥንቸል፤ ውጥረት፣ ግጭት፣ ያልተረጋጋ ሁኔታ ሲፈጠር በአካባቢው አትገኝም፤ ፈርጥጣ ትጠፋለች። ጦጣ፤ ውጥረት አይሎ ሁኔታዎች ሲጦዙ የምታልፈው በብልጠትና በዘዴ ነው። ዝሆን፤ በግዝፈቱ ባህርይ ለውሳኔ አሰጣጥና አተገባበር በእጅጉ ያስቸግራል። ሠጎን፤ እውነታውን በፅናት ከመጋፈጥ ይልቅ ራሷን በአሸዋ ውስጥ ቀብራ ክፉውን ጊዜ ማሳለፍ ታውቅበታለች። ቀጭኔ፤ ከሁሉ በላይ ነኝ ተቀዳሚ መርሆዋ ነው። ዔሊ፤ “ጎመን በጤና፣ ተቻኩሎ የት ይደረሳል፣ በመሮጥ ብቻስ ይቀደማል ወይ?” ባይ ነች።
ድመት፤ ተልፈስፋሽና አላዛኝ ፍጡር ስለሆነች አቋም የላትም። እንቁራሪት፤ “ዝምታ ሁሌም ወርቅ አይደለም” ባይ ነች። ፒኮክ፤ በውበቷ አማላይነት ነገሮችን ሁሉ ለማስፈጸም ትፈልጋለች። እባብ፤ “ገላዬ ልስልስ፤ ምላሴ ተናዳፊ ነው” በሚለው ባህርይ ይኩራራል። አውራሪስ፤ “ጉልበት ካለ፤ ሁሉም አለ” ባይ ነው። ጉማሬ፤ “የተጋትኩትን እያቀረሸሁ አስበረግጋለሁ” እያለ ይፎገላል። በቀቀን፤ ባህርይዋ ያልሆነውን የሌሎችን ቋንቋ በመኮረጅ ታስተጋባለች። ዓሣ፤ ሙልጭልጭ ነው። እስስት፤ ተለዋዋጭ ባህርይዋ መለያዋ ነው። ዓይጠ መጎጥ፤ ሁሌም የምትንቀሳቀሰው ተለዋጭ ጎሬ አዘጋጅታ ነው። ጅብ፤ “ሁሉም ለእኔ፣ ከእኔ ውጪ ለማንም ሊሆን አይችልም” ባይ ስግብግብ የዱር አውሬ ነው።
የእንስሳቱ ባህርያት በተፈጥሮ የታደሉት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የፍጡራን ቁንጮ ለሆነው የሰው ልጅ፤ በተለይም መሪ ለተሰኘውና ብዙዎችን ተመሪዎች አስከትሎ ፊት ቀደም ለሆነ ተግባሩ ስለሚጠቅመው ራሱን ለማየት የትምህርቱ ፋይዳ ከፍ ያለ ነው። “ከእኔ ባህርይ ጋር ቢያንስ ትንሽ የሚቀራረበው የየትኛው እንስሳ ባህርይ ነው” ብሎ መጠየቅም ብልህነት እንጂ ወደ መዋዕለ ሕፃናት ደረጃ መውረድ አይደለም። ከእንስሳቱ መካከል በተለየ ሁኔታ ወደ አያ ጅቦ – “የጅብ አፍ” ጉዳያችን መለስ ብለን ጉዳያችንን እንደምድም።
ጠፍ ከብትን ከመባዘን ጠብቆ ከጅብ አፍ በማዳን ሽልማት እንደሚቀበል “የአምና ካቻምና ዘመን ሰው” ሀገርንም እንደዚሁ “ከጅብ አፍ” የሚያድኗት መሪዎች በመከራ ዘመን ብቅ ብለው የታዳጊነታቸው ብርሃን ባይፈነጥቅ ኖሮ እኛ ሕዝበ አዳም ኢትዮጵያዊያን ኑሯችን ሁሉ ምድራዊ ገሃነም እንደሆነ ዕድሜያችንን ለመግፋት እንገደድ ነበር። በዚህ ጉዳይ ሩቅ ሳናማትር፣ ካርታ ሳናነብ፣ የሀገራትን ስም ሳንደረድር በራሳችን ቀዬ፣ በጉዳዮቻችን ዙሪያ ብዙ ማለት ቢቻልም ከብዙው መካከል ጥቂቱን ብቻ እየጠቋቆምን ግርድፍ ቅኝት እናደርጋለን።
የሩቅ ዓመታቱን ትርክት ወደ ኋላ ገፋ አድርገን በቅርብ ዓመታቱ ሀገራዊ ጉዳዮቻችን ዙሪያ እንኳ ጥቂት እንቆዝም ብንል ብዙ ትንታኔ መስጠት አይገድም። ጉዳዩ እንዲህ ነው። ለበርካታ ዓመታት “ከእኛ ወዲያ ላሳር” በሚሉ መሪዎች ተቀጥቅጠንና ገብረን ኖረናል። ብሶታችንን እንዳንተነፍስ ማንቁርታችን ታፍኖ፣ እንዳንጮህ አንደበታችን ተዘግቶ፣ እንዳንንፈራገጥ እግር ተወርች የፊጥኝ ታስረን ለዓመታትና ለዘመናት በእንባና በትካዜ ኖረናል።
ሞኣ አንበሳ በሞኣ ሶሻሊዝም፣ ሞኣ ሶሻሊዝም በሞኣ ኢህአዴግ እየተተካ ስንዳመጥና ስንፈጭ ኖረናል፤ (ሞኣ ማለት አሸናፊ ማለት ነው።) ሚሊዮኖች “ከሞኣ” አምባገነኖች እየሸሹ በባዕድ ምድር ስደተኛና መጻተኛ ሆነዋል። የተረፉት ሚሊዮኖች በወህኒ እየማቀቁ “ሀገር በቃኝ” ብለዋል። የተቀሩት ሚሊዮኖች ደግሞ ፍትሕ ፊት ነስቷቸው በአደባባይ ተለጉመው፣ በቤታቸው እንባቸውን እያዘሩ ኖረዋል። ጊዜና ዕድል ከፍ ባደረጋቸው “ሞኣዊያን” ሥር የተኮለኮሉት ጥንቸሎች፣ ጦጣዎች፣ ዝሆኖች፣ ዔሊዎች፣ እንቁራሪቶች፣ በቀቀኖች፣ ፒኮኮች፣ እባቦችና አውራሪሶች ወዘተ… የየሥርዓቱ የበኩር ልጅነት መብት እየተሰጣቸው “ሁሉ በእጄ፤ ሁሉ በደጄ”ን መዝሙር እየዘመሩ በዋና ቤተኛነት ተንደላቀው በቀዳሚም ሆነ በተለዋጭ ሀገራቸው ተንሰራፍተው ሲፋንኑ ኖረዋል። ምስኪን ባለሀገሮች ደግሞ “የዳቦ ያለህ!” እያሉ ለዕለት እንጀራ “በአባታችን ሆይ” ጸሎት አምላካቸውን ሲማጠኑና ሲያጉተመትሙ ዘመን አሸብተዋል።
ለመባዘንና ለመንከራተት፣ ለእንባና ለእንግልት የተዳረጉ ሀገር አልባ፣ መብተ-ንፉግ መጻተኞች፤ “ያልታደልሽ እንዴት አደርሽ!”፤ በተሰኘችው ምድራቸው ባይተዋር ሆነው ኖረዋል። ኖረዋል ከማለት ይልቅ እየሞቱ ቀን በመቁጠር ነፍሳቸውን በጨርቃቸው ቋጥረው ለመኖር ተገደዋል ማለቱ ይቀል ይመስላል።
ይህ የዛሬው ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ለግፉዓን ዜጎች ከአንበሶች ጡጫ፣ ከጅቦች ቡጭቂያ፣ ከዝሆኖች እርግጫ፣ ከእባቦች ንድፊያ፣ ለማዳን ተስፋ የፈነጠቀ ይመስላል። የምልክቶቹ ነፀብራቅ የሚያመልክተው ይህንን የሩቅ ብርሃን እንደሆነ ለመረዳትም በፈራ ተባ አጮልቀን እየተመለከትንና እየመረመርን ነው። የእስከአሁኑ የለውጡ አካሄድ ፍፅምና ተላብሷል ለማለት ግን አፍን ይይዛል። የለውጡ ብርሃን የአንዳንድ ቡድኖችንና ግለሰቦችን ዓይን እያጥበረበረ ሲያደነባብረ እያስተዋልን ነው። ይሄው የለውጥ ነፋስ የአንዳንዶችን ገበና እየገለበ እርቃናቸውን ሲያቆማቸው እያስተዋልን በእነርሱ እፍረት እኛ ምስኪኖች ተሸማቀናል። የፖለቲካ ለውጡ ሱናሚ “የተለበጠውንና የተለሰነውን የፈሪሳዊያን መቃብር እየከፈተ” የክፋት በድናቸው ሲከረፋ አይተን “አጀብ!” ብለን በእነርሱ የግፍ ድርጊት እኛን ምስኪን የለውጥ ተሰፈኞች አስነጥሶናል።
ይህ የለውጥ ዕርምጃ ያስፈነደቃቸው፣ ያመከናቸው፣ የፈወሳቸው፣ ያስደነበራቸው፣ ያንጓለላቸው፣ ያሳበዳ ቸው፣ ያሞላቀቃቸው፣ ያራቆታቸው፣ ያከበራቸው፣ ያዘመራቸው፣ ለሙሾ ረገዳ የዳረጋቸው፣ ያወፈፋቸው፣ ያኮሰሳቸው፣ ያነገሣቸው፣ አቤት የውጤቱ ብዛት! ከፋም ለማም የለውጡ ማሳ እንክርዳድ አልባ ነው ባይባልም “የነጣው አዝመራ” ጅማሮ አስጎምጂ እንደሆነ ግን ዓይኑና ልቡናው የበራለት ቅን ዜጋ ለመመስከር የሚያመነታ አይሆንም።
የዚህን ለውጥ ካፒቴን በማድነቅና ስል ዛሬው ሀገራዊና አህጉራዊ የለውጥ አዋላጅ ጥረቱ ዋጋ በመስጠት ሰሞኑን ለሀገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር ግዙፏ ዓለማችን በግዙፉ ተቋም በኩል የሰላም ተምሳሌት በማድረግ በርግብ ባህርይ መስላ የመሸለሟ ዜና ገና ተወርቶ አላለቀም። ለምን ተሸለመ ብለው እኛን ባለሀገሮቹን የሚጠይቁን ባእዳን ካሉ መልሳችን “ከጅብ አፍ ስላዳኑን ነው” ብለን በጋራ መልስ እንሰጣለን። የእኛን የጋራ ምስክርነት ለመጋራት ለሚያመነቱ ወይንም ለሚጠራጠሩ ወገኖቻችን ዴሞክራሲ ደጉ ስላለላቸው የሙግት ፋይል ሊከፍቱ ይችላሉ፤ ፋይል ከፍተውም ከሆነ ሰላማዊ ክርክራቸውን ሊያጧጡፉ ይችላሉ።
ለውጡ በብዙ ተግዳሮቶች መደነቃቀፍ ቢገጥመውም ከጉዞው ግን የተገታ አይመስልም። በለውጡ ዙሪያ በርካታ የጎራና የቋንቋ መደበላለቅ እያስተዋልን ቢሆንም ጅምሩን ወደሚያጨነግፍ ደረጃ ይደርሳል የሚል ግምትም ሆነ እምነት የለንም። ይህንን ምስክርነት ለመስጠት ማን ፊትአውራሪ አደረጋችሁ ለሚል ተሟጋች መልሳችን “ሀገር የጋራ፤ ፖለቲካ የግል” በሚለው መከራከሪያችን እኛም እንሟገታለን።
ሀገሬን ከመባዘንና ከመንከራተት አድኖ በኅብረ ብዙሕነት ኢትዮጵያዊ ጃንጥላ ሥር ለማዳን እየሞከረ ያለው ይህ ለውጥ ወደ ተሻለ ደረጃ እንደሚያደርሰን ጅምሩ ተስፋ እየፈነጠቀልን ነው። በበቀደሙ የጠቅላዩ “የጅብ አፍ” ሽልማት ለማረጋገጥ የሞከርነውም ይህ ለውጥ እንደማይጨነግፍ ነው። ከለውጡ ውስጥ ሊወለድ ስላለው በረከት ለአላህና ለእግዜር የአደራ ስዕለት ያፀናን ቢሆንም ለወር ተራው ጥበቃም እኛ ተስፈኛ ዜጎች የምንሰንፍ አይደለንም። የፖለቲከኞችና የአክቲቪስት ነን ባዮች ሸብ እረብና ሸር ግን በብዙ ጉዳዮች ረገድ እያሳሰበ እንቅልፍ እንደነሳን ባንመሰክር ደግ አይሆንም።
የለውጥ ወጋገኑን የለመደው ዓይናችን ድንገት ቢዳምን ወይንም ቢጨልም ምን ውጤት ሊከተል እንደሚችል ከተረዳን ሰንብተናል። የበለዓምን ሟርት መተዳደሪያቸው ያደረጉ ዜጎችና ቡድኖች “ሀገር ትፈራርሳለች!” ከሚለው ንግርት አንደበታቸውን ቢዘጉ ደስታችን ወደር የለውም። ነጋ ጠባ ሀገር ላይ ማሟረት ሟርቱ ወደሟርተኛው እንደሚመለስ የሚያውቁ ቢያሳውቋቸው ትንሽ ተንፈስ የምንል ይመስለናል። የስምንት ዐሠርት ዓመታቱ ባለሽበት አጭር ታሪክ ይህንን ያህል እያጫወተ ካጓጓዘን ዘንዳ ሃሳባችንን ከንባብ ገታ አድርገን ከራሳችን ጋር እንድናወጋ ዕድል ለመስጠት ብዕሬን ወደ “ሰገባው” ከትቼ እሰናበታለሁ። ሰላም ይሁን!!!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታህሳስ 8/2012
በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ