የሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ (በተለምዶ ሞዴስ) በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል ብቻም ሳይሆን በከተሞችም አካባቢ የሴቶች የብቻ ችግር ሆኖ ኖሯል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሞዴስ ገዝቶ የኢኮኖሚ አቅም ችግር ላለባቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሴት ተማሪዎች (ወጣቶች) በማደል ድጋፍ ለማድረግ የሚሞክሩ በጎ ፈቃደኛ ወገኖች እና ተቋማት መኖራቸው ይታወሳል።
የአርቲስት ቴዲ አፍሮ ባለቤት፤ አርቲስት አምለሰት ሙጪ ለተማሪዎችና ለወጣቶች ሞዴስ አሰባስባ በማደል ስታደርግ የቆየችውን አስተዋጽኦ በአርአያነቱ አንዘነጋውም። በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከ ኡማ ሰሞኑን በፌስቡክ ገፃቸው ይፋ እንዳደረጉት የከተማ አስተዳደሩ ለሴቶች የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ ዋጋ መናር ምክንያት የሆኑ የህግና የአስተዳደር ጉዳዮችን በመፈተሽ እንዲሁም ቀጥተኛ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው በተለይም ለተማሪዎች መድረስ የሚችል ተግባራዊ ሥራ በቅርቡ ይጀምራል ማለታቸው ተስፋ ሰጪ ዕርምጃ ሆኗል።
እነዚህ ድጋፎች ታዳጊ ሴቶች በወር አበባ ምክንያት ከትምህርት እስከ መቅረት የሚያደርሱ ችግሮችን ለመፍታትና የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎን ማሳደግ ላይ የሚሠሩ ሥራዎች አካል ናቸው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሲ ኤን ኤን የዘንድሮ ጀግና የኢንጂነር ፍሬወይኒን መብራህቱ ልምድና ተሞክሮ ብዙ የተራመደና በአርአያነቱ ከፍ ብሎ ሊወደስ የሚገባው ነው።
ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ ሰኞ ህዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም የዓለም መገናኛ ብዙሃን ግንባር ዜናዎች አንዱ የሆነው የኢንጅነር ፍሬወይኒ መብራህቱ የሲኤንኤን ሽልማት አሸናፊ መሆን ነበር። ታዳጊ ሴቶች በወር አበባ ምክንያት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ መፍትሔ የዘየደችው ኢንጂነር ፍሬወይኒ መብራህቱ የ”2019 CNN Heroes” ሽልማትን ማሸነፏ ብዙ ወገኖችን አስደስቷል። ፍሬወይኒ መብራህቱ ሲ ኤን ኤን ከመረጣቸው 10 ግለሰቦች መካከል የተደረገውን ፉክክር በአንደኝነት ደረጃ በድል ተወጥታለች።
ፍሬወይኒ በአሜሪካ ሀገር የኬሚካል ኢንጅነሪንግ ትምህርቷን የተከታተለች ሲሆን፤ በድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውሉ የሴቶች የፅዳት መጠበቂያዎችን ዲዛይን ያደረገች እና የፈጠረች ናት።
“ማሪያም ሳባ” የተሰኘ የፅዳት መጠበቂያ ምርት የሚያመርት ፋብሪካ በመቐለ ያቋቋመችው ፍሬወይኒ መብራህቱ ፤በዚህሥራዋም ነው የሲ ኤን ኤን የ2019 ጀግና በመሆን የተመረጠችው።
ከህይወት ልምዷ በመነሳት የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ማምረቻ ያቋቋመች ሲሆን፥ በፈረንጆቹ 2006 በድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውል የንፅህና መጠበቂያ የባለቤትነት ማረጋገጫ በኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተሰጥቷታል።
ይህ የንፅህና መጠበቂያ ማምረቻ ፋብሪካ ለ42 የአካባቢው ሴቶች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፤ በየዓመቱ የወር አበባ መጠበቂያን ጨምሮ 600 ሺህ የንፅህና መጠበቂያ እና 300 ሺህ የውስጥ ሱሪዎችን ያመርታል።
ፋብሪካው ሴቶች በኢኮኖሚው ራሳቸውን እንዲችሉ ወሳኝ ነው ያለችው ፍሬወይኒ መብርሃቱ፤ ለሴት ሠራተኞቿ ነፃ ሥልጠና፣ የቴክኒክ ሥልጠና ክፍያ እና ሌሎች ዕድሎችን ይጠቀማሉ ብላለች።
ከዚህ ባለፈ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የንፅሕና መጠበቂያ መጠቀም እንዳለባቸው በማስተማር የወር አበባ መጠበቂያ ድጋፍ ታደርግላቸዋለች።
በፋብሪካው ከሚመረቱ የሴቶች ንፅሕና መጠበቂያ 80 በመቶውን ለሴቶች በነፃ ለሚያከፋፍሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንደምትሸጥም ተነግሯል።
የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት መረጃ እንደሚያመላክተው 75 በመቶ የሚሆኑ ኢትጵያውያን ሴቶች የወር አበባ ሲከሰትባቸው የንፅህና መጠበቂያ አይጠቀሙም።
ማሪያም ሳባ በተባለው የንፅሕና መጠበቂያ ፋብሪካ የሚመረተው ይህ የሴቶች ንፅሕና መጠበቂያ ሙሉ በሙሉ የሚታጠብ እና ፈሳሽን መጥጦ ያመያዝ አቅም ያለው መሆኑ ይታወቃል።
ፍሬወይኒ በዚሁ የሽልማት ውድድር ከ10ሩ አንዷ በመሆኗ 10 ሺ ዶላር፤ ከ10ሩ አንደኛ በመሆኗ ደግሞ 100 ሺ ዶላር አግኝታለች። በተጨማሪም ሲኤን ኤን (CNN) መርጦ ለሚሸልማቸው ድጋፍ ከሚሰጡ መንግሥታዊ ካልሆኑ ዕርዳታ ድርጅቶች ጋር ትገናኛለች። ምናልባት ይኸም አጋጣሚ ፍሬወይኒ ለምታከናውነው ሥራ አጋዥ የፋይናንስ ድጋፍ ልታገኝ የምትችልበት ዕድል ሊፈጥር እንደሚችል ይገመታል።
የፍሬወይኒ የበጎ እሳቤ ትሩፋት
ቢቢሲ በቅርቡ ስለፍሬወይኒ መብራህቱ በሠራው ዘገባ እንደሚከተለው አስተዋውቋታል። “በወር አበባ መጠበቂያ እጦት ችግር አንድም ሴት ከትምህርት ገበታ መቅረት የለባትም” የሚል አቋም ያላት ፍሬወይኒ “የወር አበባ በየወሩ የሚመጣ ስለሆነ ይህን ችግር ለመፍታት ማድረግ ስላለብኝ አንድ ነገር በየወሩ የሚያስታውሰኝ ነገር ነበረኝ” ትላለች።
ወይዘሮ ፍሬወይኒን በየወሩ የሚቀሰቅሳት ጉዳይ ለመጀመሪያ ጊዜ የወር አበባ ያየችበትን ዕድሜ ስታስታውስ ነው። “የትኛዋ ሴት ናት ለመጀመርያ ጊዜ የወር አበባ ስላየችበት ቀን ሳትሸማቀቅ የምታወራው?” በማለትም ትጠይቃለች።
“ኅብረተሰባችን ስለ ወር አበባ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ታላላቅ እህቶቼና ወላጆቼም የማያወሩት ጉዳይ ስለ ነበር እኔም የወር አበባ ምን እንደሆነ ሳላውቅ ነው ያደግኩት” ስትል በልጅነቷ የነበረውን ሁኔታ መለስ ብላ ታስታውሳለች።
የወር አበባ ያየችበትን የመጀመሪያ ቀን በማስታወስም “የወር አበባዋን ያየች ሴት ባልጋለች ይባል ስለነበረ ምን ሆኜ ይሆን ይህ ነገር የተከሰተው ብዬ ነበር” ትላለች።
ፍረወይኒ ዘመናዊ የንጽህና መጠበቂያ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየችው ለትምህርት በሄደችበት አሜሪካ አገር እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ1983 ነበር።
“ለትምህርት ወደ አሜሪካ እንደሄድኩ ታላቅ እህቴ መጀመርያ የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ (ሞዴስ) እንድገዛ ወደ ሱፐር ማርኬት ወሰደችኝ። ያኔ ነበር አገር ቤት ትቼያቸው የመጣሁት ሴቶችስ መች ይሆን ይህንኑ ዓይነት አማራጭ የሚያገኙት የሚል ሃሳብ አእምሮዬ ላይ የቀረው” በማለት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ሴቶች የሚቀርብ የንፅሕና መጠበቂያ በርካሽ ዋጋ ማቅረብ የሚል ሃሳብ የተጠነሰሰው አሜሪካ ሳለች ነው።
በ1983 ዓ.ም የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ ሁኔታዎች ተቀይረው እንደሆነ በማለት ወደ ሀገሯ ብትመለስም ልጅ ሆና ነውር ሲባል ትሰማና ታይ የነበረው ነገር አሁንም ጥዩፍ እንደሆነ፣ መገለል እንዳለ አስተዋለች።
ወይዘሮ ፍሬወይኒ “ሰዎችን ስጠይቅ ለምንድነው ስለዚህ ጉዳይ የምትጠይቂኝ ይሉኝ ነበር” በማለት የወር አበባ አሁንም እንደ ነውር እንደሚቆጠር ታስረዳለች።
ማንኛዋም ሴት የወር አበባ በምታይባቸው ቀናት የምታሳልፋቸው ጊዜያት ከባድ መሆናቸውን የምትጠቅሰው ፍሬወይኒ “በገጠር አካባቢዎች ጉድጓድ ቆፍረን እንቀመጣለን አሉኝ። ያኔ የሚፈሰው ደም ልክ እንደተከፈተ የውሃ ቧንቧ መቆጣጠር የማይቻል መሆኑን ሳስብ ከእግር ጥፍሬ እስከ ራሴ መጥፎ ስሜት ነበር የተሰማኝ” ትላለች።
በአቅም ማነስ ምክንያት በርካታ ሴቶች የወር አበባቸውን በሚያዩበት ወቅት አንሶላ ቀድደው፣ እራፊ ጨርቅ ነው የሚጠቀሙት።
ከዚህ በከፋ ደረጃ ግን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ እስከ አሁን የሙታንታንና የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያን ጥቅም የማያውቁ ሴቶች መኖራቸውን ታስታውሳለች። ይህንን የሴቶች ችግር ከእኛ ሴቶች ውጪ ተረድቶት መፍታት የሚችል ሰው የለም በማለትም ታስረዳለች።
ላለፉት 10 ዓመታት ‹‹ማርያም ሰባ›› ብላ በልጃቸው በሰየሙት ድርጀት ስም የሚታጠብ ሞዴስ በማምረት በዝቅተኛ ዋጋ በትግራይ እና አፋር ገጠር አካባቢዎች ለሚገኙ ሴቶች ስታቀርብ ቆይታለች።
ማርያም ሰባ የሴቶች ንፅሕና መጠበቂያ ታጥቦ መልሶ አገልግሎት ላይ የሚውል ሲሆን፤ ከ18 ወራት እስከ ሁለት ዓመት ማገልገል ይችላል።
በምቾትና ፈሳሽ በመያዝ አቅም አንዴ ጥቅም ላይ ውሎ ከሚወገደው የንጽሕና መጠበቂያ የሚለየው ነገር እንደሌለ የሚናገሩት ወ/ሮ ፍሬወይኒ ግማሹ ጥሬ ዕቃ በአገር ውስጥ ከሚመረት ጨርቅና ጥጥ እንደሚጠቀሙ ይገልጻሉ።
ከንጽሕና መጠበቂያ ጨርቁ ጋር አብሮ የሚለበስ ሙታንታም ይሠራል። ተቋሙ ንጽሕና መጠበቂያውን ማምረት ሲጀምር በዓመት 200 ሺህ ያመርት የነበረ ሲሆን፤ አሁን ወደ አንድ ሚሊዮን ማሳደግ ተችሏል።
2014 የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ከባለቤቱ ጋር ወደ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ የመጣው ዶክተር ልዊስ ዎል የማርያም ሰባን ፋብሪካ ማገዝ እንዳለበት አምኖ ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ሰባት ወር ወስዶበታል።
ከዚህ በኋላ ግን “ዲግኒቲ ፔሬድ” የሚል ፕሮጀክት በመጀመር የድርጅቱን ምርቶች በመግዛት 150 ሺህ የሚደርሱ ሴቶች ተጠቃሚዎች እንዲሆኑና በወር አበባ ዙርያ ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ለመፍታት የሚረዳ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን እየሰጠ ይገኛል።
ድርጅቱ ሴቶችና ወንዶች ስለ ወር አበባ ማወቅ ያላቸው እውቀት ከፍ እንዲል ሥልጠና የሚሰጥ ሲሆን፤ በትግራይ ከ800 ሺ በላይ ሴቶች ይህን ንጽሕና መጠበቂያ እንዲያገኙ በማድረግ ትምህርታቸው ያቋረጡ ሴቶች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ማድረጋቸውን ይናገራሉ።
“ይህ መሠረታዊ ችግር ካልተፈታ ሴት ልጅ ልትደርስበት የሚገባ ቦታ መድረስ አትችልም” የምትለው ወ/ሮ ፍሬወይኒ ሥራውን ለመጀመር የባንኮችን ደጅ በጠናችበት ወቅት የገጠማትን ታስታውሳለች።
ባንኮችን ለማሳመን ሁለት ዓመት እንደወሰደባት የምትናገረው ወ/ሮ ፍሬወይኒ “እኔ ደፍሬ ካልጀመርኩት የወር አበባ ለዘላለም የሚያሳፍር ነገር ሆኖ ይቀራል” በሚል ቆራጥነት በእቅዷ በመግፋት እንዳሳካችው ትገልጻለች።
“ማንም በልጁ አይጨክንም፤ ይህ ፕሮጀክት ለእኔ ልጄ ነበር። እስከ መጨረሻው መውሰድ አለብኝ ብዬ የሚገጥሙኝን ፈተናዎች በጽናት ተወጥቻለሁ። የሴት ልጅ ውበቷ ደግሞ ጥንካሬዋ ነው” ትላለች።
አክላም የወር አበባን በሚመለከት ያለውን ግንዛቤና አመለካከት ለመቀየር ግን አሁንም ትልቅ ሥራ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው በማለት የችግሩን ግዝፈት ትናገራለች።
እንደማሳረጊያ
ጥንት ለአባቶቻችን ጀግንነት ማለት በጦር ሜዳ ጠላትን አርበድብዶ ድል ማድረግ ነበር። ዛሬ ግን የጀግንነት ትርጉሙ ሰፋ ብሏል። ለዚህ ዘመን ትውልድ ጀግና ማለት ድህነትን ማሸነፍ፣ በተሰማሩበት መስክ ውጤታማ ወይንም ስኬታማ መሆን ነው። የኢንጅነር ፍሬወይኒን ስኬት ለዚህ አባባል ጥሩ አብነት አድርጎ መጥቀስ ይቻላል።
በዚህ በሰለጠነ ዓለም እስከ ዛሬ ድረስ የወር አበባ አንዱ የሴት ልጅ ተፈጥሯዊ ክስተት እንደሆነ የማይቀበሉ ኃይማኖቶችና ባህሎች ያላቸው አገራት ጥቂት አይደሉም።
በበርካታ የአፍሪካ አገራትም ሆነ በሌሎች ሴቶች የወር አበባ በሚያዩበት ወቅት ከኃይማኖታዊ ክንዋኔዎች ተከልክለው ነፃነታቸው በኃይማኖታዊው ወይም ባህላዊው ትምህርት እንዲገዛ ይደረጋል።
ህንድ የወር አበባ እንደነውር ከሚቆጠርበት አገራት አንዷ ነች። 70 ከመቶ በህንድ የሚገኙ የገጠር ሴቶች በግንዛቤ ችግር፣ በድህነትና ሀፍረት የወር አበባ በሚያዩበት ወቅት ንጽሕናቸውን በአግባቡ ስለማይጠብቁ ለሞትና ለበሽታ የተጋለጡ ናቸው።
የጋና ሴቶች የወር አበባ በሚያዩበት ወቅት ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ እንዳይሻገሩት የሚከለከል ‹‹ኢፊን›› የሚባል ወንዝ አለ። ለምን ቢባል በወር አበባ ጊዜ ሴቷ ስለምትረክስ ወንዙ ላይ የሚመለኩ አማልክትን ታረክሳለች ተብሎ ስለሚታመን ነው ።
እ.ኤ.አ በ2018 ዩኒሴፍ ባወጣው መረጃ መሠረት በዓለም ላይ ሁለት ነጥብ ሦስት ቢሊየን ሰዎች መሠረታዊ የንጽሕና መጠበቂያ አቅርቦት የላቸውም። በታዳጊ አገሮች ከሚኖሩ ጠቅላላ ዜጎች መካከል የእጅ መታጠቢያ መሰል ቀላል መሠረተ ልማት የሚያገኙት እንኳን 27 በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው።
የግል ንጽሕና ለመጠበቅ መሠረታዊ የውሃ አቅርቦት በሌለበት ሁኔታ ደግሞ ሴቶች በወር አበባ ጊዜ የሚያስፈልገውን ጠበቅ ያለ ንጽሕና ለማሟላት ይቸገራሉ። ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገራት የሚገኙ ግማሽ ያህሉ ትምህርት ቤቶች የንጹሕ የመጠጥ ውሃ እና ለሴቶች ወሳኝ የሆኑ የንጽሕና መጠበቂያ አቅርቦት ብርቃቸው ነው። የውሃ መስመር ዝርጋታ ብርቃቸው በሆኑ የገጠር ት/ቤቶች የሚማሩ ሴቶች በየሰዓቱ መታጠብና ሞዴስ መቀያየር የቅንጦት ያህል ሆኖባቸው ኖረዋል። ከዚህ አሳዛኝ ችግር ጋር ተያይዞ በየወሩ ሰባት ቀናትና ከዚያ በላይ ከትምህርት ገበታቸው ለመቅረት ይገደዳሉ። ት/ቤት እያሉም በድንገት ደም ፈሷቸው ከሆነም መሳቂያ መሳለቂያ ስለሚሆኑ አፍረው ከእነጭራሹ ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ እህቶች ብዙ ናቸው።
ዩኒሴፍ እንደሚለው በኢትዮጵያ 75 በመቶ ሴቶች በቂ የንጽሕና መጠበቂያ አያገኙም፤ ከአጠቃላይ ሴት ተማሪዎች ደግሞ 50 በመቶ የሚሆኑትን ከዚሁ ችግር ጋር ተያይዞ ከትምህርታቸው ይስተጓጎላሉ።
ከውጭ ሀገር የሚገቡ የሞዴስ ምርቶች ዋጋ አቅምን ያላገናዘበ መሆን በተለይ የኢኮኖሚ አቅማቸው ደከም ለሚሉ ብዙሃን ሴቶች ፈተና ሆኖ ቆይቷል። ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ሞዴሶች እንደቅንጦት ዕቃ ተቆጥረው እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ከ67 እስከ 123 በመቶ ግብር ይጣልባቸው ነበር።
ተጠቃሚዎች የዋጋውን እጥፍ እንዲከፍሉ፣ ወጪውም ከብዙሃኑ የመክፈል አቅም በላይ ስለነበር ይህ እንዲስተካከል የበጎ አሳቢ ወገኖች ንቅናቄ ሲካሄድ መቆየቱም የሚታወቅ ነው። በቅርቡ መንግሥት ችግሩን በመረዳት በሞዴስ ምርቶች ላይ ተጥሎ የነበረውን የተጋነነ የግብር ሥርዓት እንዲስተካከል መወሰኑ ሌላ የምሥራች ሆኖ ከርሟል። በተጨማሪም እንደፍሬወይኒ መብራህቱ ዓይነት በጎ አሳቢዎችና የፈጠራ ባለቤቶች ትጋት ደግሞ ሴቶችን በማገዝ ረገድ የሚታይና የሚዳሰስ ለውጥ ማምጣት ችሏል።
የኢንጂነር ፍሬወይኒ መብራህቱ የሲ ኤን ኤን ታላቅ ሽልማት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ሰሞኑን በኦስሎ የተቀበሉትን የሠላም ኖቤል ሽልማት የሚያስታውስ ነው። ሁለቱም የጥረት ውጤት መሆናቸው፣ ያስገኙት ፋይዳም ብዙኃኑን ተጠቃሚ የሚያደርግ የመሆኑ ጉዳይ ላይ በእጅጉ ያመሳስላቸዋል። (ማጣቀሻዎች፡- ቢቢሲ አማርኛ፣ ቪኦኤ አማርኛ፣ ፋና፣ ሪፖርተር ጋዜጣ….)
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታህሳስ 8/2012
ፍሬው አበበ