ለውጡን ያልተቀበሉ የግንባታውን ዘርፍ የሚመሩ ባለሥልጣን ለጋዜጠኞች ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክተው መግለጫ እየሰጡ ነው።
አንድ ጋዜጠኛ ከለውጡ በፊት አንድ ሚዲያ ላይ ቀርበው “ከሩቅ ሆነህ ስታየው የአገር ሀብት ማለት በሌሎች ቁጥጥር ሥር ያለ የብዙኋኑ ጥሪት ነው። በአንተ እጅ ውስጥ ሲገባ ግን ወዲያውኑ ባለመብትና ባለድርሻ የምትሆንበት የራስህ ሰፊ ኪስ ይሆናል። ‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል› ብሎ ተረት ቀርቷል። አሁን የሚተረተው ‹ሲዘንብ ያላቆረ ሲያባራ ይጠማል› ተብሎ ነው። በታሪክ አጋጣሚ የሚዘንብበት ቦታ ላይ ስትቀመጥ በቅድሚያ በመጠኑ የራስህን አካውንት ትሞላልህ። ከዚያ የዘመድ አዝማድ አካውንትን ተውሰህ መደቀን ነው።” ብለው ተናግረዋል። ምን ማለትዎ ነው? ሲል ጠየቃቸው።
በቁጣ ካፉ ቅብል አድርገው ንግግር ማድረግ ጀመሩ። እናንተ ጋዜጠኞች አድርባዮች ናችሁ። ጠቅላይ ሚንስትሩ ሥልጣን የያዙ ሰሞን ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢ በሚሉት ቃላት ምትክ “ሌብነት” የሚል ቃል መጠቀማቸውን ትልቅ ነገር አድርጋችሁ በየሚዲያዎቻችሁ ለሰዓታት ትንታኔ ስትሰጡበት ሰነበታችሁ። በሌብነት የተጠረጠሩ አንዳንድ ባለስልጣናት በቁጥጥር ሥር ሲውሉ ደግሞ እየፈነደቃችሁ ገና የፍርድ ውሳኔ ያላገኙትን ሰዎች ወንጀለኛ አድርጋችሁ አቀረባችሁ። ሰንበትብት ብሎ ሌባውን ሁሉ እናጉር ካልን አገሩ ሁሉ እሥር ቤት ሊሆን ነው ተብሎ ለትናንሽ ሌቦች ምህረት መደረጉ ሲነገርም አጨበጨባችሁ።
ሳትጠይቁኝ አዕምሯችሁ ውስጥ ምን እንደሚመላለስ አውቃለሁ። የማጠናቀቅ ጉጉታችንን በሥራ ሳይሆን በዜና የመግለጽ አባዜ ተጠናውቶን ጅምር ላይ ያለ ህንፃ ሳይቀር 10 በመቶ ተጠናቋል የሚል ዜና ብናሰራም … ግንባታ ላይ ነን። ደግሞ ዋናው ነገር አንድን ሜጋ ፕሮጀክት መጀመር ነው ወሳኙ ነገር። እርግጥ ነው አንዳንዶች “የመጨረስ እንጂ የመጀመር ችግር የለባቸውም” እያሉ ይሳለቁብናል።
ያልተጀመረ ነገር እንዴት ሊቋጭ ይችላል? እንዲህ የሚሉን “የጀመርነውን ጨርሰን ሪባን እንቆርጣለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም” መባሉን ያልሰሙ ናቸው። ግባችን ቀጣዩ ትውልድ መጀመርን ያህል ትልቅ ጣጣ ተቀርፎለት ትኩረቱን አባቶቹ የጀመሯቸውን ፕሮጀክቶች መጨረስ ላይ ብቻ እንዲያደርግ በማድረግ አገሪቱን ከድህነት መንጭቆ ማውጣት ላይ ነው።
እዚህ አገር በተያዘለት ጊዜ የሚጠናቀቀው ድንኳን ተከላ ብቻ እንደሆነ አድርገው የሚያስወሩ እንዳሉ እናውቃለን። የጀመርነው ነገር አልሆን ካለም አቁመነው ሌላ ነገር እንጀምራለን። ለምሳሌ የስኳር ፍላጎታችንን በተወሰነ መልኩ ያሟላልናል በሚል ተስፋ ስንገነባው የቆየነው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ አልሆን ስላለን ስኳር ማምረት ሥራውን እርግፍ አደርጎ ወደ ስንዴ ምርት ፊቱን እንዲያዞር አድርገናል። ዋናው ነገር የማያቋርጥ የግንባታ ሂደት ላይ መሆናችን ነው። ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም።
ታላቅነት ፈፅሞ አለመውደቅ ሳይሆን በወደቁ ቁጥር መነሳት መቻል ነው። ውድቀት ብርቃችን አይደለም። የሚያበቃልን ስንወድቅ ሳይሆን ተስፋ ስንቆርጥ ነው። ከሦስት ሳምንት በፊት ትራንስፓረንሲ ኢንሺየቲቭ የተባለ ተቋም ያወጣው ሪፖርት በኢትዮጵያ መንግሥት በጀት የሚካሄዱ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በታሰበው ጊዜና በተቀመጠላቸው በጀት እየተጠናቀቁ አይደለም ብሏል።
ሪፖርቱ ግንባታ ላይ መሆናችንን ከግምት ያላስገባና በሁለት ምክንያቶች አስገራሚ ነው። እጅግ የተገረምነው ተቋሙ በፌደራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር የሚመራ ሆኖ ሳለ እንደ ተቃዋሚ ፓርቲ ጣቱን በእኛ ላይ መቀሰሩ ነው። በሺ የሚቆጠሩ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ መሆናችን እየታወቀ በስምንት ፕሮጀክቶች ላይ ባደረገው ጥናት እንዲህ ያለ ድምዳሜ ላይ መድረሱም አስገርሞናል።
ትራንፓረንሲ ኢንሺየቲቭ በተባለው ተቋም ተቀጥሮ ጥናት ያደረገው ኮስት ኢትዮጵያ የተባለው ድርጅት ዘርፉ ለሙስና ተጋላጭ መሆኑ ለፕሮጀክቶቹ በወቅቱ አለመጠናቀቁ መንግሥትን ለተጨማሪ የጊዜና የገንዘብ ኪሳራ እየዳረገው ነው ማለቱ የዘርፉን ልዩ ባህሪ ከግምት ያስገባ ባለመሆኑ አልተዋጠልንም።
ተካሄደ በተባለው ጥናት ከተዳሰሱ የመንግሥት ፕሮጀክቶች መካከል የሐዋሳና የጂንካ አየር ማረፊያዎች፣ በአዲስ አበባ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የአደይ አበባ ስታዲየም በዲዛይን ሥራው ወቅት መካተት ያለባቸው ነገሮች ባለመካተታቸው በተያዘላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቁ ሆኗል መባሉ ከምንመራበት መርህ ጋር የማይጣጣም በመሆኑ አንቀበለ ውም።
ዲዛይን እያደረግን እንገነባለን፤ እየገነባን ዲዛይን እናደርጋለን። በእኛ አገር ሁኔታ የዲዛይን ለውጥ ማድረግ ተራማጅነት እንጂ ድክመት አይደለም። እንደሚታወቀው የዲዛይን ማሻሻያ ማድረግ በሰበር ዜና የሚነገር የምስራች ነው። የህዳሴውን ግድብ ጨምሮ በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የዲዛይን ማሻሻያና ለውጥ ተደርጎላቸዋል።
የጥናቱ ዋና አላማ ፕሮጀክቶቹ ያሉበትን ሁኔታ ህዝብ እንዲያውቀው ለማድረግና ፕሮጀክቶቹን የሚከታተሉ ባለድርሻ አካላት ትኩረት እንዲሰጡት ለማድረግ ነው ይባል እንጂ እኛ ድብቅ ዓላማ እንዳለው ደርሰንበታል። በውይይቱ ተሳተፉ የተባሉት ባለድርሻ አካላት ሰጡት በተባለው አስተያየት “መንግሥት በግንባታው ዘርፍ ላይ የሚያወጣቸው ጨረታዎች ግልፅነት የጎደላቸው ናቸው፤ በታቀዱ ፕሮጀክቶች ዙሪያ መረጃ የመስጠት ጉድለት ይስተዋላል፤ ማለታቸውም የዘርፉን ልዩ ባህሪ ከግምት ያላስገባ ነው።
መጀመሪያ ትራንፓረንሲ ኢንሺየቲቭ የተባለው ተቋም ጥናቱን ያካሄደለትን ኮስት ኢትዮጵያ የተባለ ድርጀት በግልጽ ጨረታ አወዳድሮ ስለመቅጠሩ ሳያጣሩ ግንባታ ላይ ያለነውን እኛን መውቀሳቸው ትዝብት ላይ ይጥላቸዋል። መርሐችን “እየገነባን እንማራለን፤ እየተማርን እንገነባለን” የሚል መሆኑን አትርሱ።
ብዙ ፕሮጀክቶች ዋነኛ ሥራቸው ከተጠናቀቀ በኋላ በጥቃቅን ሥራዎች አለመከናወን ቆመው መቅረታቸው ሐቅ ነው። ችግሩ የተከሰተው ለግንባታ ተቋራጮች የሚቀርበውን ጀሶ እንጀራ ሻጮች በመሻማታቸው እጥረት በመፈጠሩ ነው። በዘርፉ ለዓመታት ልምድ እንዳለው ሰው የምነግራችሁ ዝርፊያንና ግንባታን መነጣጠል አስቸጋሪ ነው። የሚሻለን አንድ ሰው ለራሱና ለቤተሰቡ የሚበቃውን ያህል ብቻ እንዲመዘብር በሥርዓተ ትምህርታችን ውስጥ በልክ መዝረፍን የተመለከተ አንድ ምዕራፍ ማካተት ነው። ምክንያቱም የአገሪቱ ዕዳ ቢቆለል አገሪቱ እንጂ መዝባሪዎች ባለዕዳ አይሆኑም። ነገር ግን ‹‹የግለሰቦች መብት ሳይከበር የቡድኖች መብት ሊከበር አይችልም›› እንደሚባለው የግለሰቦች አቅም ሳይገነባ አገር አትገነባም !
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ታህሳስ አራት ቀን ባካሄደው 77ኛ መደበኛ ስብሰባው የመንግሥት ፕሮጀክቶች አስተዳደርና አመራር ረቂቅ አዋጅ ላይ መክሯል። የአዋጁ ዋና ዓላማ የመንግሥት አካላት በመንግሥት ፕሮጀክቶች ውስጥ ያላቸውን ኃላፊነት በግልፅ በማመላከት ተጠያቂነትንና ግልፀኝነትን በማስፈን የፕሮጀክቶችን ውጤታማነት ማጎልበት መሆኑን ገልጿል። ይባስ ብሎ በሀገሪቱ ወጥ የሆነ የመንግሥት ፕሮጀክቶች አስተዳደርና አመራር ሥርዓት ባለመኖሩ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ ወጪና ጥራት ባለመጠናቀቃቸው የሀገሪቱን ውስን ሀብት ለከፍተኛ ብክነት እየዳረጉ ይገኛል ብሏል።
ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችል ወጥ የሆነ የፌዴራል መንግሥት ፕሮጀክቶች አስተዳደርና አመራር ሥርዓትን በሕግ ለመደንገግ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ልኳል። እንዲህ ያሉ ነገሮች አዲስ አይደሉም። ኢህአዴግ አምና 11ኛ ጉባኤውን ባጠናቀቀ ማግስት ‹‹የተደራጀ ሌብነትና ዘረፋ የማይታለፉ ቀይ መስመሮቼ ናቸው›› ቢልም አሁንም ድረስ የመሮጫ ትራኮች ሆነው ቀጥለዋል።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ብድር የሚሰጠው አገር በቀል የኢኮኖሚ መርሐ ግብር ለማገዝ፣ የውጭ ምንዛሬ ዕጥረትን ለመቅረፍ፣ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ባለሀብቶች ለማዛወር፣ የግብር አሰባሰብ አቅምን ለማጠናከርና የወጪ አስተዳድርን ለማሻሻል፣ የፋይናንስ ዘርፉን ለማሻሻል ተግባራት ጭምር እንደሚውል እያወቃችሁ ለመሠረተ ልማት ግንባታ የሚውለው ገንዘብ ብቻ ይባክናል ብላችሁ መጨነቃችሁ አግባብ አይደለም። በግንባታው ዘርፍ የሚባክን ገንዘብ ቢኖር እንኳን በተቀሩት ዘርፎች በድምሩ ከሚባክነው የሚያንስ ነው። የተበደርነውን እያወደምን፤ ሌላ እየተበደርን፤ ብድር ከነወለዱ እየከፈልን እንቀጥላለን … ምክንያቱም ግንባታ ላይ ነን !
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታህሳስ 8/2012
የትናየት ፈሩ