‹‹ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ አፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች ቀዳሚው ይሆናል›› – የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፋሪስ ደሊል (ዶ/ር)

ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን ውስጥ ይገኛል። ሶስተኛ ትውልድ ከሚባሉት ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ነው። ወደ መማር ማስተማር ሥራው የገባው 547 ተማሪዎችን በማስተማር ነበር። ላለፉት 13 ዓመታት ባደረገው ጉዞ ከመሰረተ ልማት ግንባታ ጀምሮ ለመማር ማስተማር ምቹ የሆነ ውብ ገጽታ ያለው የትምህርት ተቋም መሆን ችሏል። ግቢውን የማስዋብ እና ተጨማሪ የግንባታ ሥራዎች አሁንም ቀጥለዋል።

ዩኒቨርሲቲው በስምንት ኮሌጆችና በአንድ ትምህርትቤት ሥር 51 የቅድመ መደበኛ፣ 14 የሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም አንድ የሶስተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች እየሰጠ ይገኛል። በእስካሁኑ ጉዞውም 21 ሺህ 494 ተማሪዎች አስመርቋል።

ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ተልዕኮውን እየተወጣ የሚገኘው በመማር ማስተማር፣ ምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን፣ የሚያስመርቃቸው ተማሪዎች ተቀጥረው እንዲሠሩና ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር እየሠራ ይገኛል።

የዛሬው ወቅታዊ እንግዳችን በለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገኘውን ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ እየመሩ የሚገኙት ፋሪስ ደሊል (ዶ/ር) ናቸው። በዩኒቨርሲቲው ታሪክ ሦስተኛው ፕሬዚዳንት ከሆኑት እንግዳችን ጋር ያደረግነው ቆይታ እንደሚከተለው ተሰናድቷል።

አዲስ ዘመን፡- ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከየት ተነስቶ የት ደረሰ ከሚለው እንጀምር?

ፋሪስ (ዶ/ር)፡- ዩኒቨርሲቲያችን የተቋቋመው በ2004 ዓ.ም ነው። በ13 ፕሮግራሞች 547 ተማሪዎችን ተቀብሎ ነው ወደ መማር ማስተማር የገባው። ትምህርቱም የተጀመረው አካባቢው ላይ በነበረው ነገር በመጠቀም ነበር። የመማር ማስተማር ሥራ የተጀመረው ዩኒቨርሲቲው አሁን በሚገኝበት ሕንፃ ውስጥ አልነበረም። በወልቂጤ ከተማ በሚገኘው ፖሊቴክኒክ ኮሌጅንና የከተማ አስተዳደሩን ቢሮዎች በመጠቀም ነበር በጊዜያዊነት የመማር ማስተማር ተልዕኮውን ሲወጣ የነበረው::

ጎን ለጎን አሁን በሚገኝበት ቦታ ላይ የመሠረተልማት ግንባታዎችን በማካሄድ አስፈላጊ ነገሮችን ካሟላ በኋላ የራሱን የትምህርት ተቋም መገንባት ችሏል። ዩኒቨርሲቲው አሁን ከሚገኝበት ከዋናው ግቢ በተጨማሪ ክላስተር ካምፓስ የሚባል ሶስት የኢንጂነሪንግ ፕሮግራሞች ያለው በወልቂጤ ከተማ ውስጥ አለው። የማስተማሪያ ሆስፒታልም አለው። ሆስፒታሉ ጉራጌ ባሕልና ልማት ማኅበር ለአካባቢው ሪፈራል ሆስፒታል መስራት ጀምሮ ብዙም ሳይገፋበት የነበረ ነው። ዩኒቨርሲቲው ተረክቦ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ወጪ በማድረግ ሰርቶ በማጠናቀቅ ለማስተማሪያም ለሕክምና አገልግሎትም በማዋል ጥቅም እንዲሰጥ አድርጓል።

የትምህርት ፕሮግራሙንም የተማሪዎች ቅበላ አቅሙንም በሂደት በማሳደግ አሁን የሚገኝበት ደረጃ ላይ ደርሷል። በአሁኑ ጊዜም ሲጀምር የነበሩት 13 የቅድመ መደበኛ የትምህርት ፕሮግራሞች ወደ 51 ከፍ ብለዋል። በሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪም 15 ፕሮግራሞች ተከፍተዋል። ዩኒቨርሲቲው አድማሱን እያሰፋ ይገኛል። በአሁኑ ጊዜ ወደ 11ሺ537 ተማሪዎችን በተለያየ የትምህርት ዘርፎች በማስተማር ላይ ነው::

ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ተደራሽነቱን ለማስፋት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው። አንዱ ተግባር በእረፍት ቀናት ቅዳሜና እሁድ ትምህርት የሚሰጥበትን ሁኔታ በማመቻቸት ፍላጎት ማሟላት ነው። በዚህም ወደ ሥራ ገብቶ በምሥራቅ ጉራጌ ዞን ቡታጅራ ከተማ ላይ ትምህርት እየሰጠ ይገኛል። በዚያው ከተማ ወደ አምስት ፕሮግራሞችን በመደበኛ የትምህርት ፕሮግራም ለመጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ ነው። በአጠቃላይ በ2018 ቀጣናው ላይ ፍላጎትን መሠረት ያደረጉ ትምህርት ለማካሄድ ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል::

አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ አገልግሎት ረገድ እየሠራቸው ያሉ ሥራዎች ምንድን ናቸው ?

ፋሪስ (ዶ/ር)፡- ዩኒቨርሲቲው ዋና ተልእኮው መማር ማስተማር ቢሆንም ጎን ለጎን በተለያየ መልኩ የማኅበረሰብ አገልግሎት በመስጠት፣ እንዲሁም ለፖሊሲ አውጭዎች የሚሆን ግብአት በጥናትና ምርምር ለይቶ በመደገፍ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል። በማኅበረሰብ አገልግሎት ለቀጣናውም፤ ለሀገርም ጥቅም በሚሰጡ ነገሮች ላይ ነው ትኩረት አድርጎ እየሠራ የሚገኘው።

አንዱና ትልቁ የማኅበረሰብ አገልግሎት ብዬ ከምጠቅሳቸው በጤናው ዘርፍ ለማኅበረሰቡ እየሰጠ ያለው አገልግሎት ነው። በዞን ደረጃ የሪፈራል አገልግሎት እየሰጠ ያለው በዩኒቨርሲቲው ስር የሚገኘው ሆስፒታል ነው። የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ከማድረግ አልፎ በአጎራባች ለሚገኙት ጭምር የጤና አገልግሎትን በጥራትና በስፋት ተደራሽ ለማድረግ በሚችለው አቅም ጥረት እያደረገ ነው። የጤና ተቋሙ ማስተማሪያም ጭምር በመሆኑ ባለሙያዎችን ያፈራል። ይሄ ወደፊት የሚሰጠው የጤና አገልግሎት ጥራት እየተሻሻለ እንዲሄድ ያግዛል።

ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ጥራት ላይም ልዩ ትኩረት ይሰጣል። የትምህርት ጥራት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት ታች ላይ መሰራት እንዳለበት ያምናል። ይህን እምነቱን በሥራ ላይ ለማዋል ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ጋር በመሆን የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤቶች የመምህራንን የማስተማር ብቃት ለማሻሻል የአጭር ጊዜ የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት ያግዛል። ተማሪዎች ላይ ደግሞ የትርፍ ጊዜ ትምህርት (ቲቶሪያል) በመስጠት ክፍተታቸውን ይሞላል።

በዚህም ዘንድሮ ወደ 39 ትምህርትቤቶችን በማሳተፍ በተመረጡ 20 ማዕከላት የዩኒቨርሲቲው መምህራን በእረፍት ጊዜያቸው ቅዳሜና እሁድ እንዲያስተምሩ ተደርጓል። በተለይም የ12ኛ ብሄራዊ መልቀቂያ ተፈታኞች ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል። ፍላጎቱም ከፍተኛ በመሆኑ የአገልግለቱን አድማስ በማስፋት ተጠናክሮ ይቀጥላል። የትምህርትቤቶችን የትምህርት ክፍሎችና ቤተሙከራዎቻቸውን በማደራጀት ያግዛል።

ዩኒቨርሲቲው ሲጠቀምባቸው የነበሩ እንደ ኮምፒውተርና የመጻፊያ ሰሌዳ የመሳሰሉትን በስጦታ በማበርከት እንዲጠቀሙበት ያደርጋል። ትምህርትቤቶችን በማቋቋምም የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብና የአካባቢው ልጆች ተመጣጣኝ በሆነ ክፍያ እንዲማሩ እያደረገ ነው። ወልቂጤና ዩኒቨርሲቲው በሚገኝበት ቡሬ ላይ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ሁለት ትምህርትቤቶችን አቋቁሟል።

በግብርናው ዘርፍም እንዲሁ በስፋት እያገዘ ይገኛል። አካባቢው በእንሰት ልማት ይታወቃል። እንሰት የተለያየ ዝርያ አለው። አንዱ ዝርያም በባሕላዊ መንገድ ማኅበረሰቡ ለጤና አገልግሎት የሚጠቀምበት ነው። እነዚህ የተለያየ ዝርያ ያላቸው የእንሰት አይነቶች ሁሉም ጥቅም ላይ እየዋሉ አይደሉም። አንዳንዶቹ ዝርያቸው ለመጥፋት እየተቃረበ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው አንድ የእንሰት ጥናትና ምርምር ማዕከል አቋቁሟል። የማዕከሉ ዋና ተግባርም ዝርያ ጠብቆ የማቆየት ሥራ መሥራት ነው።

ከእንሰት ለምግብነት የሚውል ቆጮና ቡላ ይዘጋጃል። ተረፈምርቱ ደግሞ ለቃጫ ይውላል። እንሰትን ፍቆ ቆጮና ቡላ ለማዘጋጀት በአድካሚ ሂደት ውስጥ የሚያልፍ በመሆኑና ሥራውንም የሚሠሩት ሴቶች በመሆናቸው ድካማቸውን ለመቀነስ ዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂ በማፍለቅ እያገዘ ይገኛል። የፈጠራ ችሎታ ካላቸውና በገንዘብ ከሚደግፉ አካላት ጋር በመተባበር በኤሌክትሪክና በነዳጅ የሚሠራ የእንሰት ማሽን ወይንም መሳሪያ በአራት ወረዳዎች ውስጥ በማኅበር ተደራጅተው ለሚሠሩ ወጣቶች አበርክቷል። የማሽን አጠቃቀሙንም ለማኅበራቱ አባላት ስልጠና ተሰጥቷል። በቀጣይ በሌሎችም አካባቢዎች ተደራሽ የማድረግ እንዲሁም ማሽኑን ተጠቅመው ያገኙትን ጥቅምና ማሽኑም መሻሻል ካለበት ለማሻሻል ግብረመልስ የመውሰድ ሥራም ይሠራል::

የሌማት ትሩፋት ሥራንም ለማገዝ ዝርያቸው የተሻሻለ በጎችን ለአርሶአደሩ በመስጠት በእንስሳት እርባታው ላይም እየሠራ ይገኛል። የአካባቢውን የውሃ ሀብት ለአሣ እርባታ ለማዋልም ጥናትና ምርምር ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። የአሣ ጫጩቶችን ከሰበታ በማስመጣት ሙከራዎችም ተጀምረዋል። ውጤታማነቱ ሲረጋገጥ አካባቢው ላይ አሣ ከማምረት ባለፈ እሴት ተጨምሮ የሚቀርብበት ሁኔታ ይፈጠራል የሚል እምነት ተይዞ ነው እየተሠራ ያለው::

አካባቢው ለቡናና ለፍራፍሬ ምርትም ምቹ ነው። በስፋት ባለመታወቁ ነው እንጂ የወልቂጤ ቡና እጅግ ተፈላጊ ነው። ዩኒቨርሲቲው በቡና እና በፍራፍሬ ላይ የጥናትና ምርምር ሥራውን በማጠናከር የአካባቢውን አቅም ለማሳየትም ጥረት እያደረገ ነው። በማዕከሉ የተቋቋመው የቡና እና የፍራፍሬ ጥናት ማዕከል ችግኝ በማፍላትና በማሰራጨት በስፋት እየሠራ ነው። በዘንድሮ ዓመትም ወደ 40ሺ የቡና ችግኝ የማፍላት ሥራ ተሠርቷል። ለማሰራጨትም ደርሷል። በአረንጓዴ አሻራም ዩኒቨርሲቲው አሻራውን በማኖር እያደረገ ባለው ጥረት በአንድ ወረዳ ላይ ዩኒቨርሲቲው ተለይቶ የተሰጠውን የተጎዳ መሬት በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በማልማት በደን አልብሶ መልሶ አስረክቧል። በ2016 ዓ.ም ደግሞ እንደጋኝ ወረዳ ላይ የተጎዳ መሬት በተመሳሳይ እያለማ ይገኛል። በአጠቃላይ በግብርናው ሥራ ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ ተግባራትን በማከናወን በዩኒቨርሲቲው በኩል ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ ነው።

በአቅም ማነስ በፍትህ መብታቸውን ማስከበር ላልቻሉ ወገኖች የዩኒቨርሲቲው የሕግ ክፍል ነፃ የሕግ አገልግሎት በመስጠት እያገዘ ይገኛል። ለነዚህ ሥራዎቹም በተለያየ ጊዜ የተበረከቱለት የምስጋና የዋንጫና የምስክር ወረቀት ማረጋገጫዎቹ ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- ትምህርት ሚኒስቴር አፕላይድ ሳይንስ የትምህርት ተቋም እንዲሆኑ ከመረጣቸው ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ነው። ወደ አፕላይድ ሳይንስ ተቋምነት ለመሸጋገር እያደረጋችሁት ያለው ዝግጅት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል ?

ፋሪስ (ዶ/ር)፡- አጠቃላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሪፎርም በ2013 ዓ.ም ሲጀመር በትምህርት ሚኒስቴር በኩል የትምህርት ተቋማት በተልእኮና በትምህርት መስክ እንዲለዩ የተደረገ ጥናት ነው። ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አፕላይድ ሳይንስ የትምህርት ተቋም እንደመሆኑ እንዴት አድርጎ ነው የተሟላ የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ የሚሆነው የሚለውን የሚያመላክት ፍኖተካርታ ቀርጿል።

አፕላይድ ሳይንስ ሲባል ያለማንም ድጋፍና ያለተጨማሪ ስልጠና የተሟላ ክህሎት ያለው የበቃ ተማሪ ወይንም የሰው ኃይል ማፍራት ማለት ነው። ከዚህ አንፃር በእስካሁኑ ሂደት ዩኒቨርሲቲው ያለበት ሁኔታ ምን ይመስላል የሚል በዝርዝር ጥናት ተደርጓል።

በሁለተኛ ደግሞ ዩኒቨርሲቲው ካለበት ጥቅል ባህሪ በትኩረት ወደ ተለየ ተቋም እንዴት ነው የሚሄደው የሚለውን ስትራቴጂ ተነድፏል። በስትራቴጂው መሠረትም አጠቃላይ ፕሮግራሞችን የመፈተሽ ሥራ እየተሠራ ነው። ፕሮግራም ፍተሻ ሲባል፤ ተጠቃሚዎች ወይንም አስተምረን ባስመረቅናቸው ተማሪዎች ላይ የሚስተዋለውን ክፍተት ወይንም ውስንነት በጋራ የመለየት ሥራ ነው የሚሠራው።

ለትምህርት አገልግሎት የሚውሉትን ቤተሙከራዎች ማሟላት፣ የማስተማር ሥነዘዴዎች ማዘመን፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂን ማጠናከር፣ ሰርቶ ማሳያዎች ከትምህርት ዘርፎች ጋር እንዲያያዙ ማድረግና ተያያዥ ነገሮች እንዲጠናከሩ ማድረግ ናቸው። ፕሮግራሞቹ ተፈትሸው ከተለዩ በኋላ የፕሮግራም ክለሳ ሊኖር ይችላል። በዚህ ጊዜ ደግሞ የሚቀናጁ ወይንም ሀገራዊ ጥቅም እንደሌላቸው ከታመነባቸው የሚዘጉ ፕሮግራሞች ይኖራሉ::

አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ተልዕኮውን ከመወጣት ባለፈ ቀጣሪ ተቋማት ወይንም አምራች ኢንዱስትሪዎችን በግቢው በመጋበዝ ከእጩ ተመራቂዎች ጋር የሚገናኙበትን መድረክ አመቻችቷል። ይህ ተግባሩን እንዴት ይገልጹታል?

ፋሪስ (ዶ/ር)፡- ዩኒቨርሲቲው ፈላጊና ተፈላጊን ወይንም ቀጣሪና ተቀጣሪን ለማገናኘት ያመቻቸው የሥራና የሙያ አውደርዕይ ለሁለቱም ወገኖች ጠቃሚ ናቸው። ፈላጊው አምራች ኢንደስትሪው የበቃ ባለሙያ፣ ምሩቁ ደግሞ ሥራ ይፈልጋል። ሁለቱን የማገናኘት ተልዕኮ ነው ያለው። የጋራ ግንኙነት ሲፈጠር አምራች ኢንደስትሪዎቹ ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያሉትን የትምህርት ፕሮግራሞችና በምን ሁኔታ እንደሚሰጥ ያለውን ጥንካሬና ክፍተት፣ በአጠቃላይ የዩኒቨርሲቲውን አቅም ለማወቅ ዕድል ይሰጣል። አምራች ኢንደስትሪዎቹ በደንብ ፈትሸው የሚፈልጉትን ባለሙያ ለማግኘት ያስችላቸዋል። ምሩቃኑም ያለውጣ ውረድ በግቢያቸው ውስጥ አምራች ኢንደስትሪዎችን ስለሚያገኟቸው ሥራ የማግኘት ዕድላቸው ይሰፋል። ዩኒቨርሲቲውም የምሩቃን መዳረሻዎች የት አካባቢ ነው የሚለውን ግንዛቤ ለመያዝ ያስችለዋል። ይሄ ጥሩ ጅምርና የሚበረታታ ተደርጎ ይወሰዳል። በዘላቂነት ግን ዩኒቨርሲቲው የሚወስደው የቤት ሥራ አለ። አምራች ኢንደስትሪው የሚፈልገውን ታሳቢ ያደረገ ፕሮግራም ለመቅረጽ ያስችለዋል። በጋራ ተቀናጅቶ መሥራቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።

ዩኒቨርሲቲው በንድፈሀሳብም በተግባርም ተማሪዎችን የማብቃት አቅም ቢኖረውም አምራች ኢንደስትሪዎች ደግሞ የእለት ተእለት ተግባራቸው በተግባር ላይ ያተኮረ በመሆኑ ተቀራርቦ መሥራቱ ምሩቃን ተማሪዎች ያሉባቸውን ክፍተቶች ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች ለማፍራት ያግዛል። የትምህርት ፕሮግራሙም ቢሆን የተሟላና የተሳካ ይሆናል። ከሥርዓተ ትምህርት ቀረፃ እስከ ትግበራው ከአምራች ኢንደስትሪዎች ጋር በቅንጅት መሥራቱ ተመራጭ ነው የሚሆነው::

አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር የያዛቸውን ሰፊ እቅዶቹን ከግብ ለማድረስ የተረጋጋና ሰላም የሆነ አካባቢ ከመፍጠር አንፃር እየሠራቸው ያሉት ሥራዎች ምን ይመስላሉ ?

ፋሪስ (ዶ/ር)፡- ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች የሚመረጥ ዩኒቨርሲቲ ነው ብዬ በድፍረት መናገር እችላለሁ። የዚህ መነሻ ዋናው በዙሪያው የሚኖረው ማኅበረሰብ ነው። በቀጣናው የሚኖረው ማኅበረሰብ ሰላም ወዳድ ማኅበረሰብ ነው። በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚማሩትን ተማሪዎች ከልጆቹ ለይቶ አያያቸውም። ዩኒቨርሲቲውም ያለሰላም ስኬት እንደሌለ የሚያምን በመሆኑ ለሰላም ጠንቅ የሆኑ ነገሮችን ቀድሞ በመከላከል የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራል። ተማሪዎች ከቤተሰባቸው ቀጥሎ ዩኒቨርሲቲው እንደቤተሰብ ሊጠብቃቸው፣ ሊቆጣጠራቸውና ሊከታተላቸው ኃላፊነት አለበት። በመሆኑም አቅም በፈቀደ ለተማሪዎች ሁለንተናዊ ምቾት ይሠራል። ተነጋግሮ ችግሮችን በጋራ የመፍታት ባሕል መዳበር ስላለበት ከተለያዩ አቅርቦቶች ጋር ተያይዞ ተማሪዎች የመልካም አስተዳደር ችግሮች ቢያጋጥሟቸው በምክክርና በውይይት እንዲፈቱ ይደረጋል። በትምህርት የሚያበቃቸው ተማሪዎች በሥነምግባራቸውም የተመሰገኑ እንዲሆኑ ጥረት ያደርጋል::

ዩኒቨርሲቲ ትንሿ ኢትዮጵያ የሚገኝባት ተቋም እንደመሆኑ አንድነትና አብሮነት የሚጠናከርበት ነው። ይህንን ለማምጣትም ተማሪዎች ጠንካራ የሆነ የተማሪ ሕብረት አደረጃጀትና የሰላም ፎረም አላቸው። የተማሪ ሕብረት ሲቋቋምም ብዝሀነትን ያማከለ እንዲሆን ነው የተደረገው። የተማሪዎች ሕብረት በዩኒቨርሲቲው በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገለት ለሰላም አበክሮ ኢንዲሠራም ይደረጋል። የሰላም እሴትን በመጠበቅ ረገድ ኃላፊነቱ ተማሪዎች ብቻ አይደሉም። መምህራንም ኃላፊነት አለባቸው። አልፎ ተርፎ ቀጣናውም ሰላማዊ እንዲሆን የዩኒቨርሲቲው የማኅበራዊ ሳይንስ ምሁራን በጥናትና ምርምር ችግሮችን ለይተው ከነመፍትሄው በማቅረብ የተለያዩ የውይይት መድረኮችንም በማዘጋጀት ከአካባቢው ከሚመለከታቸው አመራሮች ጋር በጋራ ይሠራል። በአጠቃላይ ዩኒቨርሲቲው ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመሆን የሰላም እሴት እንዲገነባ የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል::

ችግሮች ሲፈጠሩም አካባቢው ላይ የባሕላዊ የግጭት መፍቻ የዳኝነት ሥርአት አለ። ዩኒቨርሲቲው ውስጥ የቋንቋ ባሕልና ሀገር በቀል እውቀት ዳይሬክቶሬት አለ። ዳሬክቶሬቱ ሀገር በቀል እውቀት እንዲጎለብት በጥናትና ምርምር የማጠናከር ሥራዎች ይሰራል::

አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲው ተልዕኮውንና ርዕዩን ለማሳካት የሰው ኃይሉን ለማብቃትና በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያከናውናቸው ሥራዎች ምንድን ናቸው ?

ፋሪስ (ዶ/ር)፡- ለዩኒቨርሲቲው ስኬት የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አይተኬ ሚና እንዳለው ይታወቃል። የግቢው ቅጥር ግቢን ውበት ከመጠበቅ ጀምሮ ከታች እስከ ላይ ያለው ሠራተኛ የሚጫወተው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም። ለዚህ ማኅበረሰብ አቅም በፈቀደ መጠን መሥራት ይጠበቃል። ለሠራተኛው ከተሠራው ሥራ አንዱ የሕፃናት ማቆያ ይጠቀሳል። እናቶች ተረጋግተው ሥራቸውን እንዲወጡ አስችሏቸዋል። በግሌም የምደሰትበት ሥራ ነው። ሌላው ዩኒቨርሲቲው ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ሁለት ትምህርትቤቶችን ገንብቷል። የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ልጆቹን ያለሰጋት ለማስተማር ትልቅ ጥቅም እየሰጠ ነው።

የትምህርትቤቱ ማኅበረሰብ በዩኒቨርሲቲው የጤና ትምህርት መስጫ 80 በመቶ ተሸፍኖለት የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኝም ተደርጓል። የመኖሪያቤት ችግርን ለመቅረፍም ባደረገው እንቅስቃሴ ወደ 370 ዘመናዊ ሕንፃ ገንብቶ የተወሰኑ ሰዎች መኖሪያቤት አግኝተዋል። እኔም አብሬያቸው ነው የምኖረው። አንድ መምህር ስለሚኖርበት ቤትና ኑሮ የሚያስብና የሚጨነቅ ከሆነ በተዘዋዋሪ በመማር ማስተማሩ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም። የመኖሪያቤት ዕድሉን ያገኙ መምህራን ተረጋግተው መኖር መቻላቸው እንዲህ ያለውን ችግር ያስቀራል::

እንደ ወተት፣ ስጋ፣ እንቁላል፣ አትክልት ያሉ ለምግብነት የሚውሉ አገልግሎቶችንም በአቅራቢያ እንዲኖር የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ እየሠሩ ይገኛሉ። ዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል በመስጠትም እያበቃ ነው። ወደፊትም የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርት ዕድል ይሰጣል። ብዙዎቹ ማለት ይቻላል በተለይ የአስተዳደር ሰራተኞች ዩኒቨርሲቲው ባመቻቸላቸው የትምህርት ዕድል የተማሩ ናቸው። ከብዙ በጥቂቱ ዩኒቨርሲቲው የሚሰጣቸው ጥቅሞች እነዚህን ይመስላሉ። በዚህ በሚደረገው ድጋፍም የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ደስተኛ ሆኖ ይሠራል የሚል እምነት አለኝ::

አዲስ ዘመን፡- ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በቀጣይ ዓመታት እንዴት ያለ ደረጃ ላይ ይቀመጣል ብለው ያምናሉ ?

ፋሪስ (ዶ/ር)፡– አጠቃላይ የዩኒቨርሲቲውን ርዕይና ተልእኮ አስቀምጠናል። አፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ እንደ ኢትዮጵያ ሲጀመር በወቅቱ አፕላይድ ናችሁ ተብለው የጀመሩት ዩኒቨርሲቲዎች 15 ናቸው። በወቅቱም ወደ ሥራ ስንገባ የ10 ዓመት ዕቅድ ነበር የተያዘው። በ2022 ዓ.ም ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ አፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች ቀዳሚ ሆኖ ማየት የሚል ርዕይ ይዘን ነው እየሠራን ያለነው። ይሳካል ወይ ተብሎ ለሚነሳው ጥያቄ አዎ እናሳካለን ብዬ ነው በሙሉ ልብ የምናገረው። የምንገመገምበትና የምንለካበት መሥፈርት እንዳለ የምናምን ቢሆንም ሙሉ እምነት አለኝ ለማለት የምደፍረው እስካሁን በመጣንበት ሂደት ያለውን እንቅስቃሴ በማየት ነው። በአሁኑ ጊዜ ዩኒቨርሲቲያችን ዲጂታል በማስፋፋት፣ የስማርት የትምህርት ክፍሎች በማደራጀት፣ ትውልዱ ወቅቱ ከሚጠይቀው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር እንዲራመድ ማድረግ ችለናል። ከእቅዳችንም ቀድመናል ነው የምለው።

በተለያየ ጊዜ በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ በመሳተፍም ዩኒቨርሲቲው እራሱን ይፈትሻል። ዩኒቨርሲቲዎችንና የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችን በተለያየ ጊዜ የሚያወዳድረው የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት በሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ያደረገው ተሳትፎ ይጠቀሳል። የሽልማት ድርጅቱ ባዘጋጃቸው 2013፣ 2014፣ 2015 በተከታታይ ዓመታት ተሳትፈናል። በሶስቱ የውድደሮች ላይ ያገኘነው ውጤት የተለያየ ነበር። በየዓመቱ በውድድሩ ላይ የምናደርገው ተሳትፎ ሥራችንን ለማሻሻል አግዞናል። እነዚህ ሁሉ ናቸው በ2022 ዓ.ም ከፊት እንቀድማለን ብለን ለመናገር የምንደፍረው።

የተጀመሩትን አቀናጅቶ ዘላቂነት እንዲኖረው ከማድረግና ሥርዓት ከመገንባት አንጻርም ሥራዎች እየተሠሩ ነው። በኔ እምነት ሥርዓት ከተገነባ እኔ ባልኖርም የተለያየ ሰው ዩኒቨርሲቲውን ቢመራውም የተዘረጋው ሥርዓት ነው ዩኒቨርሲቲውን የሚመራው። ሥርዓት ግንባታ ላይ አተኩረን ሰርተናል። ለምሳሌ የዩኒቨርሲቲውን ሕገ ደንብ (ሴኔት ሌጅስትሌሽን) ከወቅቱ ጋር የተገናዘበ እንዲሆን ከልሰናል። ሕገደቡን በአግባቡ ከጠበቅነውና መሥፈርት ላይ መመሪያዎችን አውጥተን ተግባራዊ ካደረግነውና በሥርዓት ከተመራ ሰው ተኮር አይሆንም። ይሄንን ነው ተስፋ የምናደርገው። ዩኒቨርሲቲው እስካሁን የተጓዘበት የሚዋዥቅ አይደለም። በጊዜው እያደገ የመጣ በመሆኑ በሥርዓት ሲመራ ደግሞ የማያቋርጥ እድገት እያስመዘገበ ይሄዳል::

ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ መሆንም ይጠበቅበታል። ራስ ገዝ ለመሆን አንዱ የገቢ አቅሙን ማሳደግ ነው። ኢንተርፕራይዛችን አድጎ የሚያመነጨውን ገቢ ማሳደግ ከቻለ ዩኒቨርሲቲያችን እንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን እንደአኅጉርም ተወዳዳዳሪ ለመሆን ብዙ ዓመት አይፈጅበትም የሚል እምነት አለኝ::

አዲስ ዘመን፡- ጊዜ ወስደው ለጥያቄዎቻችን ለሰጡን ማብራሪያ በጣም አመሰግናለሁ!

ፋሪስ (ዶ/ር)፡- እኔም እድሉን ስላገኘሁ አመሰግናለሁ

በለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You