
ሀገራችን የጀመረቻቸው የለውጥ እና የተሐድሶ ትግበራዎች ይበል የሚያሰኙ ናቸው:: በተለይ በፅዱ ከተማ እና በአረንጓዴ ምድር በኩል እያሳየቻቸው ያሉ እመርታዎች የሚወደሱ በመሆን በቀዳሚነት ይነሳሉ:: ለዚህ ሀገራዊ እና ሕዝባዊ የለውጥ ጉዞ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ተቀርጸው ወደሥራ መግባታቸው ደግሞ በበለጠ ለትግበራው ጉልበት የሚሰጥ በመሆን ይጠቀሳል:: ይሄን የለውጥ ሂደት ተከትሎ ከሰሞኑ በፕላስቲክ ምርቶች ላይ የፀደቀ አዋጅ ተሰምቷል::
በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የፀደቀው የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ ሥርዓት ቅጣቶችን እና ሕግጋቶችን ያወጀ ሲሆን ለጀመርነው የዘመናዊነት ርምጃ ወሳኝ መሆኑ ይነሳል:: በስድስት ክፍሎች እና በሃያ ስምንት አንቀጾች የተቀነበበው አዋጅ በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ዙሪያ የቀጣይዋን ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የወሰነ ሆኖ ተነስቷል::
እንደሚታወቀው የፕላስቲክ ምርቶች ጉዳታቸው የከፋ ነው:: በአፈር ውስጥ እስከመቶ ዓመት በመቆየት ቀጣይነት ያለው ጉዳትን በማድረግ በአስከፊነታቸው ይታወቃሉ:: እንደባለሙያዎች ገለጻ አፈርን ወደመርዛማነት በመቀየር ምርታማነትን በመቀነስ ብሎም መሬትን በማምከን ጉዳቱ ከፍ ያለ እንደሆነ ይገለጻል:: ለአብነት የአዲስ አበባን አንዳንድ ቦታዎች ብንመለከት የጉዳቱን አስከፊነት መረዳት እንችላለን:: በርካታ የፕላስቲክ ምርቶች በየቦታው ወድቀው መንገድ ሲያቆሽሹ ልናይ እንችላለን:: በተጨማሪም የውሃ መውረጃ ቱቦዎችን በመድፈን ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ከማድረግ የከተማን ውበትን እስከማጥፋት የሚደርሱ መሆናቸው ይገለጻል::
እንደሀገር ከሚወገደው ቆሻሻ ውስጥ ከሁለት መቶ እስከ ሁለት መቶ ሀምሳ ሺህ ቶን ያህሉ የፕላስቲክ ምርት መሆኑን ዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ:: የሀዋሳን ሐይቅ ጨምሮ ሌሎች ሐይቆችም በነዚህ የፕላስቲክ ምርቶች ምክንያት ስጋት ላይ ከወዳደቁ ሰንብተዋል:: ችግሮችን ከማውራት እና ከማሽሞንሞን ወጥቶ ዘላቂ መፍትሔ የሚመጣበትን መንገድ መትለም እንደሀገር መልካም ነው:: በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የፀደቀው አዋጅም ችግሮችን በመቅረፍ ዘላቂ የጤና እና የዘመናዊነት ዋስትና የሚያመጣ መሆኑ እሙን ነው::
እንደሚታወቀው አፈር ሕይወት ነው:: የሀገራችን ሕልውና ከሆኑት ውስጥ ቀዳሚው ግብርና ነው:: ግብርናው ደግሞ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈልጋል:: የፕላስቲክ ምርቶች ጎጂነታቸው ሁሉም ቦታ ቢሆንም በተለየ መልኩ ግን ግብርናው ላይ ተፅኗቸው የገዘፈ ነው:: እንደአየር ብክለት ሁሉ የፕላስቲክ ምርቶች የመሬት ብክለትን በማስከተል ተወዳዳሪ የላቸውም:: ከአካባቢ ከፅዳት፣ ከማኅበራዊ ጤና፣ ከሥነ ምኅዳር ስጋት እንዲሁም ከአካባቢ ጥበቃ አኳያ የተወሰደው ርምጃ ወሳኝነት ያለው ነው::
ከአስከፊነታቸው አኳያ አዋጁ ቅጣትንም አፅድቋል:: ለአንድ ጊዜ አገልግሎት የሚውልን የፕላስቲክ ከረጢት ይዞ የተገኘ ግለሰብ ከሁለት ሺህ ብር እስከ አምስት ሺህ ብር እንዲቀጣ ደንግጓል:: ከዚህ ባለፈ የፕላስቲክ ምርቶችን ያመረተ፣ ወደሀገር ውስጥ ያስገባ፣ ለገበያ ያቀረበ ወይም ሲሸጥ የተገኘ ግለሰብ አሊያም ድርጅት ከሃምሳ ሺህ ኢትዮጵያ ብር እስከ ሁለት መቶ ሺህ ብር እንደሚቀጣ በተጨማሪም የአምስት ዓመት ጽኑ እስራት እንደሚጠብቀው አዋጁ ደንግጓል::
በጉዳዩ ላይ ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ሰፊ እና ተደራሽ የሆኑ እንቅስቃሴዎች አስፈላጊ መሆናቸው ታምኖበት እየተሠራ እንደሚገኝ ሲገለጽ አዋጁ ከአንድ ብሩ ፕላስቲክ ውጪ ሌሎች የፕላስቲክ ምርቶችን እንደማይጨምር ነው የተገለጸው:: አዋጆች ተፈጻሚ ከመሆናቸው በፊት ሁሉም ጋ ደርሰው ጥቅማቸው መታወቅ እንዳለበት አምናለሁ:: ሕዝብ በተረዳው መልኩ ሲሆን ነገሮች የበለጠ የተሳለጡ የመሆን ዕድላቸው የሰፋ በመሆኑ ለአተገባበሩም ቀላል ይሆናሉ::
ማኅበረሰቡ የአዋጁን ዓላማ እስኪገነዘብ ድረስ ብዙ ሥራዎች መሠራት ይኖርባቸዋል:: አዋጅ አውጥቶ ተፈጻሚነቱን ከማረጋገጥ በፊት በብዙ መድረኮች እና ሚዲያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች አስፈላጊ መሆናቸው ይታመናል:: አዲስ አበባን እንደስሟ ውብ እና ፅዱ የማድረግ እንቅስቃሴ ከሕግ፣ ከሥርዓት፣ ከአዋጅ እና ከተፈጻሚነት ጋር የሚያያዝ ነው::
ከኮሪዶር ልማት እና ከፅዱ ከተማ እሳቤ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ፖሊሲዎች በመተግበር ላይ ይገኛሉ:: በተለይ ከቆሻሻ አወጋገድ ጋር በተገናኘ ማኅበረሰብን የሚያነቁ ሥራዎች ተሠርተዋል:: ፅዱ ከተማን እየተመኘን የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓቶቻችንን ካላዘመንን አስቸጋሪ ነው:: የሚወጡ ሕጎች ሁሉን የሚጠቅሙ፣ ሁሉንም ተጠያቂ የሚያደርጉ፣ ከሕዝብ ለሕዝብ ናቸው:: ነገሮችን በዚህ መልኩ መረዳት የተሻለ ይሆናል::
ሀገር የጋራ ቤታችን ናት:: የጋራ ቤት ደግሞ በጋራ የሚፀዳ፣ የሚለማ፣ የሚጠበቅ መሆኑ አይካድም:: በዚህም አዋጁ ማንኛውም ሰው ከመኖሪያ ቤቱ ጀምሮ እስከ ሃያ ሜትር ድረስ ላለው አካባቢ ኃላፊነት እንዳለበት ያስገነዝባል:: ዘመናዊነት ትስስር ነው:: ሥልጣኔ ከአንዱ ወደአንዱ የሚተላለፍ የሃሳብ፣ የቅንጅት፣ የተግባር ውሕድ ነው:: እየተሠሩ ያሉ ከተማ ተኮር ሥራዎች የአንድና ሁለት ሰዎች ኃላፊነቶች ሳይሆኑ የመላው ሕዝብ ኃላፊነቶች እንደሆኑ መረዳት አይከብድም:: እንደቤታችን አካባቢያችንን ማፅዳት ከቻልን፣ ደረቅ እና ርጥብ ቆሻሻዎችን ለይተን ማስወገድ ከቻልን፣ በከተማችን ለሚሆነው ሁሉ የያገባኛል መንፈስን ካሰረጽን ይሄ ነው ዘመናዊነት::
ፅዱ ከተማ የፅዱ አስተሳሰብ ውጤት ነው:: ፅዱ አስተሳሰብ በአብሮነት ውስጥ የሚፈጠር መንፈስ ነው:: በዓለም ላይ ያሉ ብዙዎቻችን ለመኖሪያነትም ሆነ ለመዝናኛነት የምንመርጣቸው ከተሞች በፅዱ አስተሳሰብ በኅብረት የተሠሩ ናቸው:: በአስተሳሰባችን ዘምነን እጅ ለእጅ ተያዘን በጋራ መሥራት ከቻልን ብዙ ለውጦችን ማስተናገድ እንችላለን::
ዘመናዊነትን እና ሥልጣኔን ከፅዱ ከተማነት እና ከመሰል እንቅስቃሴዎች ጋር አስታርቃ በመጓዝ ላይ ላለች ሀገር አዋጁ ይበል የሚያሰኝ መሆኑ አያጠያይቅም:: በተለይ ሕግ እና ሥርዓት አልበኝነት ለሰፈነበት ተለምዷዊ አኗኗራችን መፍትሔ በመሆን የሚነሳ ጉዳይ ነው:: ትርፍ አልባ ነባር ልምምዶቻችን ለጀመርነው የዘመናዊነት ጉዞ እንቅፋት ስለሆኑ መገራት ግድ ይላቸዋል::
አመርቂ ውጤቶች በቆራጥ ውሳኔ እና በሕዝባዊ ተሳትፎ የሚገኙ ናቸው:: ፖሊሲዎች እና አዋጆች ደግሞ ሕጎችን በማስፈጸም ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው:: ዘመናዊነት የነበረውን አካሄድ በማቅናት፣ በመግራት እና ዘመኑን በዋጀ አካሄድ በመተካት የሚመጣ እንጂ ልክ ባልሆነ ባልታረቀ አኗኗር የሚታሰብ አይደለም::
አዋጁ ሁሉንም የሚመለከት ነው:: እንደመንግሥት ኃላፊነትን መወጣት ሊኖር ይችላል እንደዜጋም ግዴታን ማወቅ ይኖራል:: የፕላስቲክ ምርቶችን መጠቀም ሕገወጥ ነው ከሚለው አዋጅ ጎን ለጎን ምርቶቹን የሚተኩ ሌሎች ጉዳት አልባ አገልግሎት ሰጪ ከረጢቶች መተዋወቅ ግድ ይላል::
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም፡፡
በትረ ሙሴ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም