ወትሮም በስንዴ ምርታቸው የሚታወቁት የምዕራብ አርሲና የባሌ ዞኖች የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል ግኝት የሆኑ የተለያዩ የሰብል ዝርያዎችን በመጠቀም አበረታች ውጤት እያገኙ ነው።
የምርምር ማዕከሉ ግኝቶቹን ከሚያስፋፋባቸው ስድስት ወረዳዎች አንዷ የአጋርፋ ወረዳ ነች። በወረዳዋ አሊ ቀበሌ በ7 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ የተዘራው የቡላላ ስንዴ ለአካባቢው አርሶ አደሮች የአይን ማረፊያ ሆኗል፤ አዲስ ተስፋንም ፈንጥቋል።
በመስክ ምልከታው ወቅት ያገኘነው አርሶ አደር አብዱል ሀኪም አማን የቡላላ ስንዴን በኩታ ገጠም እርሻ ተደራጅተው ከዘሩ አርሶ አደሮች አንዱ ነው። አርሶ አደሩ ቀደም ሲልም የሲናና ግብርና ምርምር የሚያስተዋውቃቸውን አዳዲስ የሰብል ዝርያዎች እየወሰደ በመዝራት ተጠቃሚ መሆኑን አስታውሷል። አሁንም ለፓስታና መኮረኒ የሚውለውን አዲስ የስንዴ ዘር በኩታ ገጠም ተደራጅቶ ሲያመርት የቀደመው የለም።
በምርምር
ማዕከሉ ድጋፍና ክትትል ከዘራው የቡላላ ስንዴ በሄክታር ከ60 እስከ 70 ኩንታል እንደሚያገኝም ተስፋ አድርጓል።
አብዱል ሐኪም ወደ ፊት የቡላላ ስንዴን በሰፊው አምርቶ ለፓስታና መኮረኒ ፋብሪካዎች በመሸጥ የመጠቀም ዕቅድ
እንዳለው ገልጧል።
አብዱል መና ዮና ሙያዊ ድጋፍና ክትትል የሚያደርግ የአጋርፋ ወረዳ የግብርና ልማት ሠራተኛ ነው። እርሱ እንደሚያስረዳው፤ ኩታ ገጠም እርሻ የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን በመጠቀም የአርሶ አደሩን ምርታማነት የማሳደግ አመቺነት አለው። የሲናና ግብርና ማዕከል ግኝት የሆነውን የቡላላ ስንዴ ዘር ለማስፋፋት የተሰራው ሥራ በአካባቢው አርሶ አደሮች ላይ መነቃቃትን ፈጥሯል።
ይህ አዲስ ዝርያ ለሁሉም አርሶ አደሮች እንዲዳረስም ምርቱ ተሰብስቦ ወደጎተራ ከገባ በኋላ ለምግብነት ከመዋሉ በፊት ዝርያው ለሌሎች አርሶ አደሮች የሚሰራጭ መሆኑን ተናግሯል።
በኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሲናና ግብርና ማዕከል ዳይሬክተር አቶ መሃመድ በሪሶ እንደገለጹት፤ ማዕከሉ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን ለአካባቢው አርሶ አደሮች በማስተዋወቅ ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ግብ ይዞ እየሰራ ነው፡ እስከ አሁንም 78 የምርምር ውጤቶችን ጥቅም ላይ አውሏል።
በዘንድሮው የመኸር ወቅትም የተለያዩ የሰብል ዝርያዎችን በ239 ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ላይ እያስፋፋ ይገኛል። እየተከናወነ ያለው የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን የማስፋፋት ሂደት በሁለተኛው የግብርና ዕድገት መርሀ ግብር የሚከናወን ነው። ‹‹ቡላላ›› የፓስታና የመኮረኒ ስንዴ ዘር ማስፋፋትም የዚሁ መርሐ ግብር አካል ነው። ይህን የስንዴ ዝርያ በማስፋፋት አርሶ አደሩ ለፓስታና መኮረኒ ፋብሪካዎች ምርቱን በማቅረብ ተጠቃሚ ይሆናል።
ሀገሪቱ ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ ለምታደርገው ሽግግርም እንደ ‹‹ቡላላ›› ስንዴ አይነት ሰብሎች የፋብሪካ ግብዓት በመሆን አስተዋጽዖ እንደሚያበረክቱ ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ዕድገት ፕሮግራም አስተባባሪ ዶክተር ዳኛቸው ሉሌ እንዳስረዱት፤ የግብርና ዕድገት መርሀ ግብር የግብርና ምርምር ውጤቶችን የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ የሚሰራ ነው።
አርሶ አደሮችን በኩታ ገጠም እርሻ በማደራጀት በሰፋፊ መሬቶች ላይ አዳዲሶቹን የሰብል ዝርያዎች የማስተዋወቅና የማስፋፋት ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል። ቴክኖ ሎጂን ከማውጣት አንጻር ላለፉት ሶስት ዓመታት በርካታ ሥራዎች ሰርተዋል።
ዶክተሩ፣ የግብርና ዕድገት ፕሮግራም በአቅም ውሱንነት ምክንያት የወጡ ቴክኖሎጂዎች እንዳይ ስተጓጎሉ ድጋፍ በማድረግ አዳዲስ ዝርያዎችን ለምርጥ ዘርና ለተለያዩ ዘር አባዥ ድርጅቶች እንደሚያቀርብ ጠቅሰዋል።
እንዲህ አይነት የምርምር ውጤቶችን በመደገፍና አርሶ አደሩን በመደጎም የስንዴ ምርታማነትን በማሳደግ መንግሥት ስንዴን ከውጭ ለማስገባት የሚያወጣውን ምንዛሪ ማዳን እንደሚቻልም ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 30/2012
ኢያሱ መሰለ