በቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪው እና በሌሎች የተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የምትታወቀው የሀዋሳ ከተማ፣ በዘርፎቹ ይበልጥ እንድትፈለግ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች እንዳሏት ይታወቃል። የከተማዋ ሠላምና ፀጥታ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሠማሩ የሚያስችል አንዱ ዋና ምቹ ሁኔታ ሲሆን፣ ሕዝቡ ይህን ሠላም በመጠበቅ በኩል እያከናወነ ያለው ተግባር ከተማዋን ከኢንቨስትመንት ባሻገርም ተመራጭ እንድትሆን እያስቻላት ይገኛል።
ከተማዋ በኢንቨስተሮች ተመራጭ እንድትሆን ካደረጓት ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች መካከል ወጣት የሰው ኃይሏ፣ ምቹ የአየርና የየብስ ትራንስፖርቷ፣ የአየር ፀባይዋ፣ እንደ ሀዋሳ ሐይቅ ባሉ ልዩ ልዩ የተፈጥሮ ሀብቶች መታደሏ ይጠቀሳሉ።
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታደሰ ፍቅሬ በተለይ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በከተማዋ ብዙ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማቅረብ ባለሀብቶችን ለመሳብ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስታውቀዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ የ2017 በጀት ዓመት በሀዋሳ ከተማ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች (በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት፣ በከተማ ግብርናና በሌሎች ዘርፎች) ይሠማራሉ ተብለው 45 ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ይጠበቃሉ ተብሎ ታቅዷል። እነዚህ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች አራት ቢሊዮን ብር ካፒታል የሚያስመዘግቡ እንዲሁም ለሁለት ሺ 500 ሰዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ስለመሆናቸውም ታቅዶ እየተሠራ ነው።
እቅዱ ሲዘጋጅ ብዙ ምቹ ሁኔታዎች ታሳቢ መደረጋቸውንም አቶ ታደሰ ይገልጻሉ። በሀዋሳ ከተማ ኢንቨስት ለሚያደርጉ ባለሀብቶች አንዱ ታሳቢ የተደረገው ትልቁ ምቹ ሁኔታ ከተማዋ ሠላም የሰፈነባት መሆኗ ነው ይላሉ። ከተማዋ ያለው ሠላም ከሀገር ውጭም ሆነ ከሀገር ውስጥ ወደ ከተማዋ የሚመጡ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨትመንት መስኮች እንዲሠማሩ ምቹ ሁኔታ መሆኑን ይጠቁማሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ መሠረተ ልማቶችን ከማሟላት አንጻር ከአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ርቀት በ25 ደቂቃ ብቻ የትኛውንም ምርት በአየር ትራንስፖርት ወደ አዲስ አበባ ማመላለስ የሚቻልበት ሁኔታ ከተማዋ አላት። ከአዲስ አበባ ኬንያ የሚዘልቀው ትልቅ የመንገድ ትራንስፖርት በሀዋሳ ከተማ የሚያልፍ መሆኑ፣ ከሌሎች ክልሎች መሠረተ ልማቶች አንጻር ከተማዋ ስትታይ መብራት፣ ቴሌኮም፣ ውሃና የመሳሰሉት የመሠረተ ልማቶች በሚገባ የተሟላላት መሆኗም ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንድትሆን ያደርጓታል። ለተለያዩ ኢንቨስትመንት ሥራዎች ሊውል የሚችል መሬት ዝግጁ ተደርገዋል።
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ፤ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም 14 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ ገብተዋል። ባለሀብቶቹ አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ናቸው፤ ለአንድ ሺ400 ሰዎችም የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።
አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ወደ ከተማዋ መሳቡ እንደተጠበቀ ሆኖ ቀደም ሲል ለኢንቨስትመንት መሬት ወስደው ባላለሙ ላይም ሕግ የማስከበር እርምጃ መወሰዱን ኃላፊው አስታውቀዋል። በመሆኑም 24 ፕሮጀክቶች በተለያዩ ጊዜያት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ወደ ልማት መግባት ባለመቻላቸው በኢንቨስትመንት አዋጁ መሠረት ፕሮጀክቶቹን የመሰረዝ ሥራ መሠራቱን አስታውቀዋል። 24 ፕሮጀክቶች ሙሉ ለሙሉ መሰረዛቸውንና በእነሱ ተይዞ የነበረ 15 ነጥብ ሰባት ሄክታር መሬትም ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ መደረጉን ገልጸዋል። ይህንንም መሬት ለሌሎች አልሚ ባለሀብቶች ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል። በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ይገልጻሉ።
በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ወቅት ባለሀብቱን ተግዳሮቶች የሚገጥሙበት ሁኔታ እንዳለም አቶ ታደሰ ጠቅሰው፣ ከእነዚህ ተግዳሮቶች መካከል አንዳንዶቹ ብድር ለማግኘት ማነቆ ሆነው መቆየታቸውን ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ባለሀብቱ ወደ ኢንቨስትመንቱ ሥራ ለመግባት ሲመጣ 30 በመቶ ያህሉን ከራሱ እና 70 በመቶውን ከብድር ለማግኘት አቅዶ በመሆኑ ይህን ብድር በማግኘት በኩል ለረጅም ጊዜ ሲቸገር ቆይቷል። በቅርቡ መንግሥት ወደ ሙሉ ትግበራ ያስገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለአምራች ዘርፉ ምቹ ሁኔታዎችን ይዞ መጥቷል፤ በዚህም ችግሮች በመጠኑም ቢሆን እየተቀረፉ መጥተዋል፤ መሠረታዊ የሆነው ብድር ማግኘት ላይ ያለው ችግር ግን ተቀርፏል ብሎ መውሰድ እንደማይቻል አመላክተዋል።
የጥሬ እቃ አቅርቦት እጥረት ሌላው ተግዳሮት መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህም በተለይ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶች ከውጭ ሀገራት የሚመጡ ጥሬ እቃዎችን ለማስመጣት እየገጠማቸው ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ተግዳሮት መሆኑን ጠቁመዋል። ይህም ባለሀብቱ ወደ ሥራ ሊገባ የሚችልበትን ዕድል እያጠበበው መሆኑን ይገልጻሉ።
ክልሎችን አቋርጠው በሚመጡ የጥሬ እቃዎች አቅርቦት ላይም ተግዳሮት እየገጠመ መሆኑን ጠቁመው፣ እነዚህን ችግሮች ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን እንደሚፈቱ ይጠበቃል ብለዋል። በከተማ አስተዳደሩ የሚፈቱ ችግሮች ከባለድርሻ አካላት ከመብራት ኃይል፣ ከቴሌኮም እና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በቅንጅት ለመፍታት እየተሠራ መሆኑን ያስረዳሉ።
አቶ ታደሰ አንዳንድ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ስላሉበት ሁኔታም ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት በዓሣ ልማት ላይ ለመሠማራት ከፈለጉ ባለሀብቶች ጋር መሬት ርክክብ ተደርጎ የግንባታ ሥራ መጀመሩን አስታውሰው፣ ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ ወደ ሥራ መግባቱን አመልክተዋል። ፕሮጀክቱ በተጀመረው ፍጥነት ልክ ከተጓዘ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግንባታው ተጠናቅቆ ዓሣ ወደ ማምረት ሥራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ የመድኃኒት ፋብሪካ ለማቋቋም የተያዘው ፕሮጀክት የአፈር ምርመራ፣ ጥናት እና ውሃ ቁፋሮ ሥራ ጊዜ እንደወሰደበት ጠቅሰው፣ ይህም ፕሮጀክት አሁን የቅድመ ዝግጅት ሥራውን እየሠራ መሆኑን ይገልጻሉ። ‹‹ፕሮጀክቶቹ በሚፈለገው ልክ አልሄዱም፤ ትንሽ ወደኋላ ቀርተውብናል በሚል ከፕሮጀክቶቹ ባለቤቶች ጋር በመወያየት በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባሉ የሚል እምነት አለኝ›› ይላሉ።
በእንቁላል ምርት ብቻ ይታወቅ የነበረው ‹‹ሱፐር ኦቫ›› የተሰኘ ከኢትዮጵያውያን ጋር በሽርክና የተቋቋመ ድርጅት እያከናወነ ያለውን ሥራም ጠቅሰዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ድርጅቱ በቀን 65ሺ እንቁላል ያመርታል፤ እንደ ሀገርም ትልቅ የተሞክሮ ማዕከልና ምርታማነት የተገኘበት ነው።
ጎን ለጎንም በከተማዋ ዙሪያም ሆነ በከተማ ውስጥ ላሉ ነዋሪዎች 37 የሚደርሱ እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን እያቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ደግሞ ተጨማሪ የዶሮ መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ አቋቁሞ መኖ እያመረተ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ የዶሮ መኖ ዶሮ ማርባት ለሚፈልጉ የከተማዋ ነዋሪዎችም ሆነ በከተማ አቅራቢያ ላሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ትልቅ ዕድል ይዞ መምጣቱን አስረድተዋል።
አቶ ታደሰ፤ ሌሎች ከዚህ በፊት ብዙም ባልተሠራባቸው በሐይቅ ዙሪያና በሐይቅ ዳርቻ አካባቢ ለመዝናኛ የሚሆኑ ትላልቅ ሪዞርቶችን ለመገንባት በሂደት ላይ ያሉ ባለሀብቶች እንዳሉም ይናገራሉ። በዚህ ልማት ቀደም ብለው የገቡ ባለሀብቶች ውጤታማነት እየተመለከቱ ሌሎች ባለሀብቶች የሀገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ባለሀብቶች መሬት እየጠየቁ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
በሌላ በኩል እስካሁን ለአዳዲስ ባለሀብቶች መሬት ከማስተላለፍ አንጻር ችግሮች ይስተዋሉ እንደነበር አቶ ታደሰ አስታውሰዋል። ቀደም ሲል መሬት ወሰደው ያላለሙ ባለሀብቶች ወደ ልማቱ እንዲገቡ ለማድረግ ብዙ ጊዜ መፍጀቱን ይገልጻሉ። በዚህ በጀት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት በተለይ 15 ነጥብ 7 ሄክታር መሬት ወደ ባንክ ለማስገባት የእነርሱን መብት በማይጥስና ለሌሎች አስተማሪ የሆነ እርምጃ ለመውሰድ ሲባል የተሠራው ሥራ ብዙ ጊዜ መውሰዱን አስታውቀዋል።
በሁለተኛው ሩብ ዓመት አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ተጠይቀው ፕሮፖዛላቸው ተለይቶ ምላሽ ያልተሰጠባቸው እንዳሉ ጠቅሰው፤ ይህንንም ከክልሉ መንግሥት ጋር በመቀናጀት አዋጭነቱን በማየት መሬት የማስተላለፍ ሥራ እንደሚሠራ አስታውቀዋል። በቀጣዩ ዓመት ለአዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ሰፋፊ መሬቶች ለማስተላለፍ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ መሬት ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ለባለሀብቱ የሚሆን ማበረታቻ ማዘጋጀትንም ይፈልጋል። ይህን የተመለከተ አሠራር በፌዴራል መንግሥት በ2015 ዓ.ም የተዘጋጀ የማበረታቻ ሰነድ አለ፤ ይህም ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል። እንደ ክልልም ሆነ እንደ ከተማ አስተዳደር ተጨማሪ የግብር እፎይታ ጊዜ እንዲኖር በማድረግ፣ የሊዝ መነሻ ክፍያዎችን በመቀነስና በመሳሰሉት ማበረታቻዎች ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እየተሠራ ነው።
እንደ ሀገር ከፖሊሲ አንጻር ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄን ተግባራዊ በማድረግ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ መሬት ለማቅረብም ሆነ ሌሎች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ በዚህ ዘርፍ መሠማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች ይህን ትልቅ ዕድል ሊጠቀሙበት ይገባል ብለዋል።
የጽሕፈት ቤት ኃላፊው እንዳብራሩት፤ ባለሀብቱ ኢንቨስት አድርጎ ወደ ሥራ ሲገባ እንደ ሀገር የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት፣ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በማስቀረትና የውጭ ምንዛሪ ወጪን በመቀነስ ትልቅ ጠቀሜታ አለው። ለሀዋሳ ከተማና ለአካባቢው ማኅበረሰብም ትልቅ ፋይዳ ይኖራዋል። የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ገቢን በማሳደግና ከተማዋን በማስዋብ ረገድም ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል።
አንድ ባለሀብት ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም ለአካባቢው ማኅበረሰብ ትምህርት ቤቶችን፣ የጤና ተቋማትን በመገንባት ትልልቅ ሥራ ሊሠራ ይችላል። ከዚህም አኳያ ብዙ እየተሠራም ነው። በቅርቡ ቤጄኤይ የቢራ ፋብሪካ የሀዋሳ ቅርንጫፍ ለአንድ ትምህርት ቤት ስምንት የሚሆኑ የመማሪያ ክፍሎችን ገንብቶ ከነሙሉ ቁሳቁሳቸው ያስረከበበትን ሁኔታ ለእዚህ በአብነት ጠቅሰዋል። ይህ ሁኔታ የባለሀብቱን ፕሮጀክት ሕዝቡም የኔ ነው ብሎ እንዲቀበለውና እንዲደግፍ ያስችላል ብለዋል።
ኃላፊው እንዳብራሩት፤ በተያዘው 2017 በጀት ዓመት ሀዋሳ ከተማ የበለጠ የኢንቨስትመንት መዳረሻ የምትሆንበት ሥራ ለመሥራት ከተማ አስተዳደሩም የክልሉ መንግሥትም የኢንቨስትመንት እምቅ አቅምን ለማስተዋወቅ እየተሠራ ነው። ለባለሀብቶች በቴክኖሎጂ የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ተደርጎ ወደ ትግበራ ተገብቷል።
አንድ ባለሀብት ወደ ሀዋሳ ከተማ ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት መምጣት ሳያስፈልገው በየትኛው ሀገር ሆኖ በተዘጋጀው ፕላትፎርም አማካኝነት በኦንላይን አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ሥራዎች ተጀምረዋል። ይህም ሀዋሳ ከተማ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን ትልቅ በር ይከፍታል። በዘርፉ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል።
‹‹በሀዋሳ ከተማ ለባለሀብቱ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል ብለን ስናነሳ ሠላምን ለመጠበቅ እየተከናወን ባለው ተግባር ከቴክኖሎጂ ባሻገር የከተማዋ ነዋሪዎችም የከተማዋን ሠላምና ፀጥታ እንደ ዓይን ብሌናቸው ይጠብቃሉ። ከካሜራ የተሰወረ ከሕዝቡ ሊሰወር አይችልም፤ የከተማዋን የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ሕዝቡ የኔ ፕሮጀክቶች ናቸው፤ እኔ ነኝ የምጠብቃቸው ብሎ ጥበቃ ያደርግላቸዋል፤ ሠላም በማስጠበቅ በኩል ትልቁን ድርሻ ያለው ሕዝቡ ነው›› ሲሉም አስገንዝበዋል።
ኃላፊው እንዳስታወቁት፤ በቴክኖሎጂም ረገድ በሀዋሳ ከተማ ሲሲቲቪ ካሜራዎች የሌሉበት የለም፤ ካሜራዎቹ ሃያ አራት ሰዓት አገልግሎት ይሰጣሉ። ፕሮጀክቶችም በየትኛዎቹ ቦታዎች የራሳቸው ካሜራ አላቸው፤ ይህም መንግሥት ከገጠመው ካሜራ ጋር የተቀናጀ በመሆኑ የትኛውም ኮሪደር ላይ በየትኛውም አካባቢ ችግር ፈጥሮ ማምለጥ የሚቻልበት ዕድል እስካሁን አልገጠመም። ካሜራዎች መገጠማቸው ወንጀል እንዳይፈጸም ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ተፈጽመው ከሆነም የፈጸመውን አካል የመያዝ ዕድሉ ሰፊ እንዲሆን ያስችላሉ። ይህም ባለሀብቱም ዜጎችን ያለስጋት እንዲሠሩ እንዳስቻላቸው ነው።
በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዓለም አቀፍ ስታንዳርድ የሚያሟሉ ሼዶች ይገኛሉ፤ በቅርብ ርቀት ባለው የይርጋለም ኢንዱስትሪ ፓርክም እንዲሁ ሼዶች አሉ። ለኢንቨስትመንት አገልግሎት ሊውል የሚችል 103 ሄክታር የለማ መሬት ተዘጋጅቷል። ከዚህ መካከል 35 ሄክታሩ ለኢንዱስትሪ፣ 55 ሄክታሩ ለከተማ ግብርና የተቀረው ደግሞ ለሆቴሎችና ለቱሪዝም ማዕከላትም ሆነ ለየትኛውም ፕሮጀክት የተዘጋጀ ነው። ከሼዶች ባሻገር ሼዶችን መገንባት የሚያስችል በመሠረተ ልማት የተሟላ መሬት ዝግጁ ተደርጓል፤ የትኛውም ባለሀብት ወደ ከተማዋ መጥቶ ማልማት የሚችልበት ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።
‹‹የሀዋሳን የኢንቨስትመንት አቅም ገና ያልተነካ ብዙ ያልተሠራበት በመሆኑ የትኛውም ባለሀብት ኢንቨስት ቢያደርግ ምርታማ እና ውጤታማ የሚያደርገው ምቹ ሁኔታዎች አሉ›› የሚሉት አቶ ታደሰ፤ ከተማዋ ለአዲስ አበባ ሆነ ዙሪያዋ እንዲሁም ለተለያዩ ክልሎች በቅርበት ላይ መገኘቷ የገበያ መዳረሻዋን እንደሚያሰፋውም ይገልጻሉ።
የትኛውንም አይነት ኢንዱስትሪ ማቋቋም ለሚፈልግ አካል ለጥሬ እቃ አቅርቦትም ቢሆን ከጎረቤትና ሌሎች ክልሎች ማግኘት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው፤ በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ይታዩ የነበሩ ችግሮችን ለማቅለል ባለሀብቱ የግድ ከተማዋ ድረስ መምጣት እንደማያስፈልገው አስታውቀዋል። ባለበት ሆኖ በኦንላይን አገልግሎት የሚያገኝበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አመላክተዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም