አዲስ አበባ፡- የመዲናዋን የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ያሳድጋሉ የተባሉ 100 ኤሌክትሪክ አውቶቡሶች ግዥ ተከናውኖ ወደብ ላይ መድረሳቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ። በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 16 ባቡሮች ወደ አገልግሎት እንዲገቡ መደረጉንም ተጠቁሟል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ያብባል አዲስ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ የትራንስፖርት ዘርፍ ያለው የብዙሃን ትራንስፖርት አቅም በተሟላ ሁኔታ ከመጠቀም አኳያ ችግር አለበት። ችግሩን ለመፍታት የከተማ አውቶቡስ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅትን በአደረጃጀት፣ በአሰራር፣ በመመሪያ፣ በሰው ኃይልና በሌሎችም ግብዓቶች ሲሻሻል በመሆኑ ሪፎርም እየተደረገ ነው።
የከተማ አውቶቡስ ድርጅት ያሉትን አውቶቡሶች ወደ ስምሪት ውስጥ እንዲያስገባና አገልግሎቱ እንዲሻሻል የማድረግ ስራ መስራቱን የገለጹት ቢሮ ኃላፊው፤ በ2017 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ካሉት በተጨማሪ 149 አውቶቡሶች ወደ ስምሪት እንዲገቡ አድርጓል። በቀን 900 ሺህ በላይ ሕዝብ እንዲያጓጉዝ በማድረግ አገልግሎት አሰጣጡ እንዲሻሻል ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
የሕዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጠው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ድርጅት ባለፈው ዓመት በየቀኑ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩት 13 ባቡሮች መሆናቸውን አውስተው፤ በዚህ ዓመት የነበረውን የመለዋወጫ የእቃ እጥረት ችግር በመፍታት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 16 ባቡሮች ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ተደርጓል። ይህም ለዘርፉ አገልግሎት መሻሻል ከፍተኛ የሆነ አቅም እንዳለው አቶ ያብባል አስታውቀዋል።
እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፤ የአደረጃጀት ማሻሻያ እየተደረገበት ያለው የአውቶቡስ ብዙኃን ትራንስፖርት ድርጅት ላይ የግል ባለሀብቱ ተሳትፎ ዝቅተኛ ነው። ተሳትፎውን ለማሳደግ የመንግሥት ኦፕሬተሮች ያሉበት የግል ዘርፉ ኦፕሬተሮችን ለመፍጠር እየተሰራ ነው። በዘርፉ ያለውን በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል ልዩነት የማጥበብ ስራ መስራት ሲሆን፤ ከተማ አስተዳደሩ ቀደም ብሎ ግዥ የፈጸመባቸው 100 የኤሌክትሪክ አውቶብሶች ወደብ ላይ ደርሰዋል። ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው በሶስት አራት ወር ውስጥ ተገጣጥመው ወደ አገልግሎት የሚገቡበት ሁኔታ ይፈጠራል። ይህም የትራንስፖርት የአቅርቦት ችግሩን ለመፍታት የከተማ አስተዳደሩ የወሰደው እርምጃ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከተማ አስተዳደሩ 100 ሚሆኑ ኤሌክትሪክ አውቶቡሶች ይዞ የሚሰራ የግል ባለሀብት ኦፕሬተር የመፍጠር እንቅስቃሴ ይደረጋል። በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው የግል ባለሀብቶችን ማበረታቻ እየሰጠ ተሳትፎአቸው እያደገ መሄድ አለበት የሚል ሃሳብ ተይዞ እየተሰራበት መሆኑን አቶ ያብባል ገልጸዋል።
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም