ከስምንት ዓመት በፊት ባጋጠመኝ የጤና እክል እጅ እግሬ በመስነፉ የተሽከርካሪ ወንበር ዊልቸር ተጠቃሚ ሆኛለሁ። ሕመሙ ከፈጠረብኝ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጫና ይልቅ ዛሬ ድረስ ይበልጥ ዕለት ዕለት የሚያሳምመኝ መንገዱም ሕንጻውም ለአካል ጉዳተኛ ምቹ አለመሆኑ ነው። ፈተናው ከምኖርበት የጋራ መኖሪያ ቤት ይጀምራል። ያለ ሰው ርዳታ መግባትም መውጣትም አልችልም።
መንገዱም ሆነ ሕንጻው አካል ጉዳተኛውን ታሳቢ ያደረገ ስላልሆነ ከቤት አለመውጣትን እመርጣለሁ። አንዳንድ ሕንጻዎች ለአካል ጉዳተኞች መግቢያ አዘጋጅተናል ለማለት ብቻ ለይስሙላ ያሰሩት ይመስላል። ጠባብ ቀጥ ያሉ አቀበቶችና በቀኝም በግራም ድጋፍ የሌላቸው ናቸው። አዲሱ ኢቢሲ ሕንጻ ለቃለ መጠይቅ ሄጄ ሾፌሩ በዊልቸር መግቢያው እየገፋ ሊያወጣኝ ሲል እንደ ተራራ ቀጥ ያለ አቀበት ስለነበር ስለከበደው ወደኋላ ተመልሶ ለሌላ ጉዳት ከመዳረግ ለትንሽ ነው የተረፍሁት። ሌላ ሰው እንዳያግዘው መውጫዋ ጠባብ ነች። ለዛውም በቀኝም በግራም መደገፊያ የላትም። አንድ ጓማዋ ወደ ጎን ሸርተት ብትል የለሁም። የኮሪደር ልማቱ ግን ለዘመናት ተዘንግቶ የኖረውን አካል ጉዳተኛ ታሳቢ እያደረገ ስለሆነ በልኩ እውቅና ሊሰጠው ይገባል።
በተረፈ ሆስፒታሎችና ዩኒቨርሲቲዎች ሳይቀር ለአካል ጉዳተኛ የተመቹ አይደሉም። በሥራ ምክንያት ከታዘብኋቸው ሕንጻዎች ከፍ ብዬ ከገለጽሁት በተጨማሪ የቀድሞው ኢቢሲ፣ፋና፣ የኢትዮ ቴሌኮም ቅርንጫፎች፣ እንደ ዘፍመሽ ያሉ ሞሎች፣ ሱፐር ማርኬቶች፣ ወዘተረፈ እንደኔ ላለ አካል ጉዳተኛ ፈተና ናቸው። የቀድሞው ኢቢሲ ሕንጻ እንዲሁ ለቃለ መጠይቅ ሄጄ በስድስት ጋዜጠኛ በወሳንሳ ተይዤ ነው ስቱዲዮ የገባሁት ስወጣም እንደዚሁ። በዚህ የተነሳ ሳልወድ እንቅስቃሴዬን ለመገደብ፤ ቤቴ ተዘግቼ ለመዋል ተገድጃለሁ። እነዚህን ተቋማት ያነሳሁት ምሳሌና አርዓያ መሆን ሲገባቸው ሆነው ስላላገኘኋቸው ነው።
ከአምስት ዓመት በፊት ከሕመሜ እንዳገገምሁ አቋርጨው የነበረውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማንዴላ ሕንጻ 4ኛ ፎቅ ላይ እከታተለው የነበረውን የጋዜጠኝነት ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት ለመቀጠል ብፈልግም ሕንጻው አሳንሰር ወይም ሊፍት ስላልነበረው ለሁለት ዓመት ያህል የደከምሁበት ትምህርት ያለ ውጤት መና ቀርቷል። የሚገርመው ሕመሙ ከፈጠረብኝ የሥነ ልቦናና የአካል ችግር ይልቅ ዛሬ ድረስ እየጎዳኝ ያለው እንደ አካል ጉዳተኛ ለመንቀሳቀስ በየዕለቱ የሚገጥመኝ ፈተና ነው። በዚህ ቁዘማና ድባብ ውስጥ ሆኜ ነው በየዓመቱ December 3 ወይም ሕዳር 24 የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን እያሰብሁ ያለሁት።
ዘንድሮም በሀዋሳ በሀገር አቀፍ ደረጃ ‘’የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚና በማጉላት አካታችና ዘላቂ ልማትን እናረጋግጥ!’’ በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል። ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ እንዲሉ አበው መሪነቱ ቀርቶብን በቀላሉ ወጥተን በገባን። ይህ መሪ ቃል የቤት ሥራቸውን በጊዜ ለሰሩ ሀገራት እንጂ እንደኛ ላለ ሀገር ከፈረሱ ጋሪው ዓይነት ነው። ሌላው የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ እንዲህ ዓመት እየጠበቀ አጀንዳ መሆኑን ሳይ አዝናለሁ። ከ20 ሚሊየን በላይ አካል ጉዳተኞች ያሏት ሀገር ለምን ዓመት ጠብቃ አስባ ለመዋል ላይ ታች ትላለች የሚል ጥያቄ ያጭራል። ለምን ዓመቱን ሙሉ አጀንዳ ማድረግ አልተቻለም። ተቋማትስ ለምን የዋናው ዕቅዳቸው አካል አላደረጉትም ስል እጠይቃለሁ።
አካል ጉዳት ማለት የአእምሮ፣ የስሜት ህዋሳት እና የአካል መጎዳት ሲሆን ግለሰቡን በማህበረሰቡ ውስጥ እኩል ተሳትፎ እንዳያደርግ የሚገድብ ሁኔታ ነው፡፡ አካል ጉዳተኝነት ማለት በተፈጥሮ ወይም በሰው ሠራሽ ምክንያቶች ማየት ፣ መናገር፣ መስማት የማይችል ወይም በእግሩ ላይ ወይም በአእምሮ ዝግመት የሚሰቃይ ሰው ነው። አካል ጉዳተኞችን ማካተትን በሚመለከቱ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ድጋፍን ማሰባሰብ፣ ስለ አካል ጉዳተኞች ግንዛቤ የማሳደግ ሥራን ማበረታታት እንዲሁም ትኩረትን ወደ ሁሉን አቀፍ እና ተደራሽ ማህበረሰብ ጥቅሞች ማዳረስ አስፈላጊ ነው።
የዓለም ባንክ እና የዓለም ጤና ድርጅት ባወጡት ቆየት ያለ መረጃ መሠረት ከዓለም ሕዝብ 15 በመቶ ያህሉ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ወደ 17.6 በመቶው የሕብረተሰብ ክፍል የአካል ጉዳተኛ ነው። በኢትዮጵያ ወደ 20 ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎች ከተለያየ ዓይነት የአካል ጉዳት ጋር እንደሚኖሩ ይታመናል።
በኢትዮጵያ ለአካል ጉዳተኞች የሚመጥን መሠረተ ልማት አውታር ግንባታ አለመኖር እና አገልግሎት አሰጣጥ ጉድለት በርካቶችን ለከፍተኛ እንግልት እና የጤና ችግር እንደዳረጋቸው ይነገራል። ሆኖም በጦርነት የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች እንክብካቤ የሚያገኙበት የተሐድሶ እና ስልጠና ማዕከል ማቋቋሚያ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለመንግሥት መቅረቡም ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ለአካል ጉዳተኞች የሚመጥን መሠረተ ልማት አውታር ግንባታ አለመኖር እና አገልግሎት አሰጣጥ ጉድለት በርካቶችን ለከፍተኛ እንግልት እና የጤና ችግር እንደዳረጋቸው ይነገራል። በርግጥም በመንገድ ላይ የቁም እና የወለል ምልክቶች እጦት፤ ወደ ሕንጻዎች አካል ጉዳተኞችን የሚደግፉ መወጣጫዎች እጦት፤ ተመጣጣኝ መጸዳጃ አገልግሎቶች አለመኖር፤ በመጓጓዣ አገልግሎቶች ዘርፍ ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት አለመደረጉ ችግሮቹን የሚያባብሱ ጉዳዮች መሆኑንም የአካል ጉዳተኞች በተደጋጋሚ ጊዜያት በምሬት ሲናገሩ ይደመጣል።
በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኛ ዜጎች በሀገሪቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የነበራቸው ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት እጅግ አነስተኛ እንደነበረም ተገልጿል ይለናል ዶቼ ቬለ። የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር ለዘርፉ ችግር መፍትሔ ለማምጣት ይረዳሉ ያላቸውን የአደረጃጀት እና ሕግ የማውጣት ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን አስታውቋል። በጦርነት የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች እንክብካቤ የሚያገኙበት የተሐድሶ እና ስልጠና ማዕከል ማቋቋሚያ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለመንግሥት መቅረቡም ተገልጿል።
የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) መንግሥት የብዙሃኑን የአካል ጉዳተኞች የመብት ጥሰት ለመከላከል እና እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንዲቻል የተጠቃለለ የአካል ጉዳተኞች ሕግ ረቂቅ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ሚንስትሯ የኢትዮጵያ ጀግኖች የጦር አካል ጉዳተኞች ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያገኙ የሚያስችል የተሐድሶ እና ስልጠና ማዕከል ማቋቋሚያ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለመንግሥት መቅረቡን ተናግረዋል። የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከፊት ለፊት ብሩህ ተስፋ ያለ ቢሆንም ቀሪው ሥራ ሰፊ በመሆኑ ለበለጠ ጥረት መዘጋጀት ይኖርብናል ብለዋል።
በጤናው መስክ የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሠሩ ያሉ ተግባራትን ያስረዳው የጤና ሚኒስቴር በተለይ በቅርቡ አካል ጉዳተኞች በጤና የትምህርት መስክ ያላቸውን ተሳትፎ በሚመለከት የገጠመውን ችግር በማንሳት መፍትሔ ለማስቀመጥ እየሠራ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ወይንሸት ሙሉሰው በበኩላቸው የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ትኩረት ሳይሰጠው ለረጅም ዓመታት የቆየ መሆኑን በማንሳት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግሥት እና በተለያዩ አካላት የተጀመሩ ሥራዎች ተስፋ ማሳየታቸውን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ «ሃያ ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎች ከተለያየ ዓይነት የአካል ጉዳት ጋር እንደሚኖሩ ይታመናል» ብለዋል የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)። በጎጂ ልማድ እና በተዛባ አመለካከት እንዲሁም በሕግጋት ክፍተት እና በመልካም አስተዳደር እጦት የተነሳ በአካል ጉዳተኞች ላይ ወድቆ የቆየው ችግር ዘርፈ ብዙ እና ውስብስብ ነበር ተብሏል። በዚህም ምክንያት ዘርፈ ብዙ ለሆኑ ችግሮች ሰለባ ሆነው መቆየታቸው ገልጸዋል።
መንግሥት በለውጡ ማሕቀፍ ለአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ትኩረት በመስጠት ከአካል ጉዳተኛ ማኅበራት እና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ተጨባጭና ውጤታማ ሥራዎችን እየሠራ ነው ተብሏል።
የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚንስቴሩ ተቋማዊ መዋቅር ውስጥ ካሉ «በጣም ጥቂት» የሥራ ክፍሎች የአካል ጉዳተኞች የሥራ ክፍል አንዱ ሆኖ በዋና ሥራ አስፈፃሚ እንዲመራ መደረጉን የትኩረቱ ማሳያ መሆኑን ሚንስትር ኤርጎጌ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
መንግሥት ባለፉት ጊዜያት በብሔራዊ ማኅበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ፣ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮንቬንሽን፣ ብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች የድርጊት መርሀ ግብር ፣ የአካላዊ ተሐድሶ ስትራቴጂ፣ ለአካል ጉዳተኞች ከቀረጥ ነፃ ተሽከርካሪ የማስገባት መመሪያ እንዲወጣ በማድረግ በርካታ አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ሲያደርግ እንደቆየም ተገልጿል።
በጤናው ዘርፍ በተመሳሳይ የተለያዩ ሥራዎች በመሠራት ላይ መሆናቸው ተጠቅሷል። የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ ሁሉን አቀፍ ጥራት ያለው አካል ጉዳተኞችን ያማከለ አገልግሎት እና የተሐድሶ ህክምና አገልግሎትን ተደራሽነት ለማሳደግ ከተለያዩ አካላት ጋር እየተሠራ ነው ብሏል።
በተለይ የተሐድሶ ሕክምናን ከማስፋት አንፃር ትኩረት በመስጠት ሀገራዊ ስትራቴጂ በመቅረፅ ጥረቶች ተደርገዋል። «የአካል ተሐድሶ ማዕከላት (Physical Rehabilitation Center) የምንላቸው በአሁን ሰዓት እንደ ሀገር ሃያ አራት ተቋማት ይገኛሉ»። ከእነዚህም ውስጥ አስራ አራት በግል እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ የሚገኙ ሲሆን አስሩ በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ የመንግሥት ተቋማት የሚገኙ ናቸው።
ተቋማትን ከማደራጀት ባለፈ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድም የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው ተብሏል። የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ በበኩላቸው የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ትኩረት ሳይሰጠው ለረጅም ዓመታት የቆየ መሆኑን በማንሳት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግሥት እና በተለያዩ አካላት የተጀመሩ ሥራዎች ተስፋ ማሳየታቸውን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ አካል ጉዳተኛ መሆን ምን ማለት ነው፤ በትምህርትም ሆነ በሥራ ዓለም ምን ዓይነት ውጣ ውረድ ይገጥማቸዋል፤ ሲል ቢቢሲ ይጠይቃል። እንደ ዕድል ሆኖ በቤተሰቤም ሆነ ባደግኩበት ሰፈር በአካል ጉዳተኛነቴ የደረሰብኝ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ አልነበረም። እንዲያውም አካል ጉዳተኛ መሆኔንም አላውቀውም የሚለው አንዱዓለም ከበደ አንድ እጁና ሁለት እግሮቹ ጉዳተኛ ናቸው። ከሚያከናውናቸው ተግባሮችና በአካባቢው ከነበረው ተቀባይነት የተነሳ አካል ጉዳተኝነቱን የዘነጋው አንዱዓለም፤ ብዙ አካል ጉዳተኛ ጓደኞቹ ግን ስለሚገጥሟቸው የተለያዩ ችግሮች እንደሚነግሩት ይገልጻል።
መላኩ ተክሌ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ልማት ማዕከል በመባል የሚታወቀው መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ነው። መላኩ አካል ጉዳተኛ ሲሆን ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር ክራንች ይጠቀማል። የሚሠራበት ድርጅት አካል ጉዳተኞች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች እንዲሳተፉ ለማድረግ የሚተጋ ነው። ከሥራዎቻቸው መካከል አካል ጉዳተኞችን የሚያካትት ትምህርት፣ ጤና፣ መተዳደሪያና የማህበረሰብ ልማት ይገኙበታል። ድርጅቱ በአጠቃላይ ወደ 48 ሠራተኞች አሉት። ከሠራተኞቹ መካከል ደግሞ 20ዎቹ አካል ጉዳተኛ ከእነሱም ውስጥ 19ኙ ሴቶች ናቸው።
የአካቶ ትምህርት ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆነችው እመቤት ግርማ ‘’ሴት አካል ጉዳተኞች በሁሉም መስኮች እኩል መካተታቸውን ለማረጋገጥ እንጥራለን። ይህም ደግሞ በሚሰጡ ሥልጠናዎችም ሆነ በማንኛውም አገልግሎት ቢያንስ 50 በመቶ ሴቶች እንዲሆኑ ይጠየቃል’’ ትላለች። እንደ ኢትዮጵያ እያደጉ ባሉ ሀገራት ውስጥ አካል ጉዳተኛ ለሆነ ሰው ብዙ አዳጋች ነገሮች አሉ የምትለው እመቤት፤ ፈተናዎቹ ለሴት አካል ጉዳተኞች እጥፍ እንደሚሆኑ ትጠቁማለች።
ትምህርት ካለማግኘት አንስቶ እስከ ሥራው ዓለም ድረስ ለአካል ጉዳተኞች ብዙ የሚከብዱ ነገሮችን ታነሳለች። ለአካል ጉዳተኞች ተብለው የሚዘጋጁ የትምህርት ማሟያ መጻሕፍት አቅርቦትና የትምህርት ዕድል የማግኘት አጋጣሚው በጣም ጠባብ በመሆኑ በትምህርታቸው ገፍተው የሚሄዱ የአካል ጉዳተኞች ቁጥር እየመነመነ እንደሚመጣም ታስረዳለች።
በቅርቡ በእንግሊዟ ለንደን ከተማ ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳት ጉባኤ ተካሂዶ ነበር። በጉባኤው ላይ ከተነሱ ነጥቦች አንዱ የአካል ጉዳተኞች ቁጥር አለመታወቁ ተጠቅሷል። አቶ መላኩ ተክሌ እንደሚሉት ከዓመታት በፊት በወጣው የተባበሩት መንግሥታት የአካል ጉዳተኞች ሪፖርት መሠረት፤ በዓለም ላይ ካሉት 1 ቢሊዮን አካል ጉዳተኞች መካከል 15 በመቶዎቹ በታዳጊ ሀገራት ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 15 በመቶ የሚሆኑት በኢትዮጵያ ይገኛሉ።
‘’በማህበረሰቡ ዘንድ በቂ መረጃ የለም’’ የምትለው እመቤት፤ ብዙ አካል ጉዳተኞች ከልጅነታቸው ጀምሮ እንደሚገለሉ ታክላለች። በየቤቱ ተደብቀው የሚያድጉ አካል ጉዳተኛ ልጆች ከማህበረሰቡ ጋር ከተቀላቀሉ በኋላ መድሎና መገለል ይደርስባቸዋል። ብዙ ሁኔታዎችም አልጋ በአልጋ አይሆኑላቸውም። እነዚህ ችግሮች ሁሉንም አካል ጉዳተኞችን የሚያጋጥሙ ቢሆኑም በሴቶች ላይ ግን ይብሳል። ከቤት መውጣት አይፈቀድላቸውም እንደውም እርባና እንደሌላቸው ይቆጠራሉ። እነዚህን ተግዳሮቶች ቢያልፉ እንኳን አካባቢያቸው ምቹ አይሆንም ትላለች።
ባለሙያዎች ከዚህ በተጨማሪም አካል ጉዳተኞች ለራሳቸው ያላቸው ዝቅተኛ አመለካከትም ይጨመርበታል ይላሉ። “አቅማቸውን እንዲጠራጠሩ ይደረጋሉ” የምትለው እመቤት ለአካል ጉዳተኞች በቂ መረጃ አለመኖሩም ችግር መሆኑን ትገልጻለች። አቶ ረታ ጌታችው በእንግሊዝ ሀገር ሊድስ ከተማ የማስተርስ ዲግሪውን በአካል ጉዳት ላይ እየሠራ ሲሆን እሱም ‘’ይህች ዓለም የአካል ጉዳት ለሌለባቸው ሰዎች ምቹ ሆና የተሠራች ናት’’ ይላል።
አቶ ረታ አካል ጉዳተኛ ባይሆንም ለአካል ጉዳተኞች ጉዳይ በቂ ቦታ አለመሰጠቱ ኢ-ፍትሐዊ ነው ይላል። ከመረጃ አንስቶ እስከ መንገድና የሀገር ኢኮኖሚ ድረስ አካል ጉዳተኞችን የማካተት ሥራ መሠራት አለበት ይላል። አክሎም አካል ጉዳተኞች ያሉበት ቦታ በበቂ ሁኔታ አይታወቅም ይላል። በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው መገለል ለማስረዳት አካል ጉዳተኛ ልጅ እንዳላቸው ለማሳወቅ እንኳን የሚያሳፍራቸው ወላጆች እንዳሉ ይገልፃል። እነሱም ላይ አልፈርድም። ምክንያቱም ከዚህ ቀደም አካል ጉዳተኛ ልጅ እንዳላቸው ያሳውቁ ሰዎች ብዙ ችግር ሲደርስባቸው አይተዋል ይላል።
ሻሎም ! አሜን።በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም