የእሥራኤል የጦር አውሮፕላኖች ዋና ከተማዋ ደማስቆን ጨምሮ በሶሪያ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ማድረሳቸውን የሀገሪቱ ሚዲያ ዘገባዎች ያሳያሉ። መቀመጫውን በእንግሊዝ ያደረገ የሶሪያ ሰብዓዊ መብት ታዛቢ እንደገለፀው ከሆነ፤ እሥራኤል ወታደራዊ ኢላማ የተደረገባቸው 100 የአውሮፕላን ጥቃቶች አካሂዳለች። እንደ ሀገሪቱ ሚዲያ ዘገባዎች አንድ ከኬሚካል መሣሪያ ማምረቻ ጋር ግንኙነት አለው ተብሎ የተጠረጠረ የምርምር ማዕከልም ከተመቱት ተቋሞች አንዱ ሲሆን፤ እሥራኤል የአሳድ አገዛዝ መገልበጡን ተከትሎ ‹‹መሣሪዎቹ በጽንፈኞች እጅ እንዳይገቡ›› ለማድረግ የተወሰደ እርምጃ እንደሆነ ገልፃለች ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ሰኞ ዕለት የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ፕሬዚዳንት በሽር አልአሳድ መውደቅን ተከትሎ በክስተቱ ላይ ለመነጋገር እና በቀጣዮቹ ቀናት መግለጫ ለመስጠት ተሰባስበው ነበር። ‹‹እንደምገምተው ምክር ቤቱ ከፋም ለማም ግዛታዊ ደህንትን ለመጠበቅ እና የሶሪያን አንድነት፤ እንዲሁም የሲቪሎችን ደህንነት ለማረጋገጥ፣ ሰብዓዊ እርዳታ ለመስጠትና ለተጎዳው ሕዝብ ለመድረስ በአንድነት ይሠራል›› ሲሉ በተመድ የሩሲያ አምባሳደር ቫሲሊ ነበንዚያ ለሪፖርተሮች ተናግረዋል።
የሶሪያ ሰብዓዊ መብት ታዛቢ እንደገለፁት፤ ባለፉት ሁለት ቀናት በደማስቆ የኢራን ሳይንቲስቶች ለሮኬት ማምረቻ ይጠቀሙበታል የተባለ ቦታን ጨምሮ በሶሪያ ከመቶዎች በላይ የእሥራኤል አየር ጥቃቶች ተካሂደዋል። ቦታው የተመታው የተመድ ኬሚካል ተቆጣጣሪ በሶሪያ ያሉ ባለሥልጣናትን የሚጠረጠሩ የኬሚካል መሣሪያዎች ክምችቶች ከአደጋ ነፃ በሆነ ቦታ መቀመጣቸውን እንዲያረጋግጡ ካስጠነቀቀ በኋላ ነው።
እንደ ተመድ ኬሚካል ተቆጣጣሪ የኬሚካል መሣሪያዎች ክልከላ ድርጅት ከሆነ የኬሚካል ጦር መሣሪያ የሚጠቀመው ኬሚካል ውስጡ ባሉ መርዛማ ባህርያት ሰዎችን ለሞትና ለአካል ጉዳት የሚያደርስ ነው። ኬሚካል መሣሪያዎችን ከትክክለኛ ወታደራዊ ዒላማ ውጭ ሲጠቀሙ መገኘት በዓለም አቀፉ የሰብዓዊ ሕግ የተከለከለ ነው። የእነዚህ መሣሪያዎች ውጤትም የጎንዮሽ ጠባሳው የከፋ ነው።
በሶሪያ የትና ምን ያህል የኬሚካል መሣሪያዎች እንዳሉ የማይታወቅ ሲሆን፤ የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዚዳት በሽር አልአሳድ ሲያከማቹ እንደነበርና በዚህ ዙሪያ ግን የተሟላ መረጃ አለመገኘቱ ተገልጿል።
ሶሪያ በ2013 ከ”የኬሚካል መሣሪያዎች ተከላካይ ድርጅት” (OPCW) ኬሚካል መሣሪያዎች ምስክር ወረቀት አግኝታ ነበር። ከወር በኋላ በደማስቆ ከተማ ዳርቻዎች የኬሚካል መሣሪያዎች ጥቃት ተካሄደ። በዚህም ቀንደኛ ወኪል ሆኖ የተሳተፈው ሳሪን ከ1ሺህ 400 በላይ ሰዎች ገድሎ ነበር። የተጎጂዎቹ አሳዛኝ ምስሎችና በስቃይ ላይ ሆነው በጭንቀት ሲንቀጠቀጡ መታየቱ ዓለምን ያስደነገጠ ክስተት ነበር። በወቅቱ የምዕራብ ኃይሎች “ጥቃቱ ሊካሄድ የሚችለው በመንግሥት ብቻ ነው” ቢሉም አሳድ ግን በወቅቱ ተቃዋሚዎችን ሲወቅሱ ነበር።
የኬሚካል መሣሪያዎች ተከላካይ ድርጅት እና ተመድ 1ሺህ 300 ቶን የሚሆን ኬሚካል እንዳስወገዱ የሶሪያ መንግሥት ቢያሳውቅም በሀገሪቱ የኬሚካል መሣሪያዎች ጥቃት አሁንም እንደቀጠለ መሆኑ ተዘግቧል።
ባለፈው ሰኞ የኬሚካል መሣሪያዎች ተከላካይ ድርጅት እንዳለው ከሶሪያ ጋር መገናኘቱንና በሀገሪቱ ‹‹ ከሁሉም የኬሚካል መሣሪያዎች ተዛማጅነት ካላቸው ቁሳቁሶችና መገልገያዎች ለመጠበቅ ትኩረት እንዲሰጡና የሰዎችን ደህንነትና ፀጥታ ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን›› ገልጿል።
በተያያዘ ዜናም፣ የእሥራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዴዎን ሳር ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ የእስራኤል መከላከያ ኃይል በፀጥታ ምክንያት በጣም የተወሰነ እርምጃ ብቻ መውሰዱን ገልጸዋል። ሚኒስትሩ አክለው እንደተናገሩት፤ እሥራኤል በሶሪያ ውስጣዊ ጉዳይ የመግባት ፍላጎት እንደሌላትና የሚጨነቁት ዜጎቻቸውን ብቻ ለመከላከል እንደሆነ አስታውቀዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ መከላከያ ሚኒስትሩ ካትዝ እንዳሉት የእሥራኤል ጦር ከባድ ስትራቴጂክ መሣሪያዎች፣ ሚሳይሎችን እና አየር መከላከያ ሲስተሞችን ጨምሮ ማውደሙን ተናግረዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም