አዲስ አበባ፡- በ2016/17 የመኸር እርሻ ለመሰብሰብ ከታቀደው 337 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ውስጥ እስካሁን ድረስ ከ100 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ በሪሶ ፈይሳ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በ2016/17 የመኸር እርሻ ለመሰብሰብ ከታቀደው 337 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እስካሁን ድረስም ከ100 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል ።
በክልሉ በ2016/17 የመኸር እርሻ በዘር ከተሸፈነው 11 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ሰብል ውስጥ ስድስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታሩ ለመሰብሰብ ደርሷል ያሉት አቶ በሪሶ፤ ከዚህ ውስጥ ሦስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የለማው ሰብል በመሰብሰብ መውቃት ተችሏል። በዚህም ከ100 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ጠቁመዋል።
በክልሉ ያለው የአየር ሁኔታ ምርት ለመሰብሰብ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቅሰው፤ ያልተሰበሰቡ ሰብሎች ወቅቱን ጠብቆ ለመሰብሰብ እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።
ከመኸር እርሻ የታቀደውን ምርት ለማግኘት የሰብል እንክብካቤ ሥራው በተጠናከረ መልኩ ሲከናወን መቆየቱን አስታውሰው፤ አብዛኛው አካባቢ እየደረሰ ያለው ሰብል በቀጣይነት የሚሰበሰብ ስለሆነ እስካሁን የተገኘው የታቀደውን እቅድ በአግባቡ ማሳካት እንደሚቻል የሚያመላክት ነው ብለዋል።
የግብርና ሥራ በትብብር የሚሠራ ሥራ ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ ቢሮው ሕዝብን የማነቃቃት፣ እቅዶችን የማቀድና ወደታች ማውረድ፣ አስፈላጊ ሙያዊ ስልጠናዎችን በመስጠት እንዲሁም የአቅም ግንባታ የሚፈጥሩ ግብዓቶችን የማቅረብ ሥራዎችን ያከናውናል ነው ያሉት።
ሌሎችም የልማት አጋር የሆኑ ባለድርሻዎችም አርሶ አደሩን በመደገፍ ውጤታማ እንዲሆን የሚሠሩት ሥራ ትልቅ አቅም ይፈጥራል። አሁንም ይህን እገዛቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የሥራው ዋና ተዋናይ የሆኑት አርሶ አደሮችም ከየአቅጣጫቸው የሚያገኙትን ሙያዊና ሌሎችም አስፈላጊ እገዛዎች ተጠቅመው እና ቤተሰባቸውን አስተባብረው መሥራት እንደሚገባቸው ጠቁመው፤ ለአርሶ አደሩ በቅርበት እግዛ የሚያደርጉ ባለሙያዎችም ተገቢው ድጋፍና ክትትል እያደረጉ መሟላት የሚገባቸው ነገሮች እንዲሟላ ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል በ2016/17 መኸር እርሻ 11 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ፣ በቦቆሎ፣ በገብስ፣ በሩዝ እና በተለያዩ ሰብሎች የለማ መሆኑ መገለጹ ይታወሳል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም