ዋልያዎቹ የቻን ማጣሪያ ዝግጅታቸውን ዛሬ ይጀምራሉ

በሀገር ውስጥ ሊጎች ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾች የሚሳተፉበት የቻን ዋንጫ ዘንድሮ ለ8ኛ ጊዜ ሶስት በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት (ኬንያ፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ) ጥምረት ይስተናገዳል። ኢትዮጵያም በመድረኩ ለአራተኛ ጊዜ ለመሳተፍ የሚያስችላትን የማጣሪያ ጨዋታ ዝግጅት ዛሬ ትጀምራለች። የዋልያዎቹ ጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ለ20 ተጫዋቾች ጥሪ ያደረጉ ሲሆን፤ ጨዋታዎቹ በሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሊቢያ ዋና ከተማ ቤንጋዚ ታህሳስ 13 እና 16/2017 ዓ.ም ይካሄዳሉ።

በአፍሪካ በትልቅነቱ ሁለተኛ ደረጃን በሚይዘው የቻን ዋንጫ በማጣሪያ ዋልያዎቹ ከሱዳን ጋር ሁለት የደርሶ መልስ ጨዋታዎችን ያደርጋሉ። ከዛሬ ጀምሮ ካሳንቺስ በሚገኘው ጁፒተር ሆቴል ተሰባስበውም የሜዳና የጂም ልምምዶችን የሚያደርጉ ይሆናል። ለዚህም እንዲረዳና ወደ ዝግጅት ለመግባት የቡድኑ ጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ለ20 ተጫዋቾች ጥሪ አድርገዋል። በጥሪው መሰረትም ሶስት ግብ ጠባቂዎች ሰይድ ሀብታሙ፣ ፍሬው ጌታሁን እና አቢዩ ካሳዬ ተካተዋል። በተከላካይ ክፍል ዘጠኝ ተጫዋቾች የተመረጡ ሲሆን፤ አስራት ቱንጆ፣ ብርሃኑ በቀለ፣ አህመድ ረሺድ፣ የሬድ ባዬ፣ ራምኬል ጀምስ፣ አማኑኤል ተረፈ፣ ሬድዋን ሸሪፍ፣ ያሬድ ካሳዬና አብዱሰላም የሱፍ ጥሪ ተደርጎላቸዋል።

በመሃል ሜዳው ስፍራ የተካተቱ ስድስት ተጫዋቾች ደግሞ በረከት ወልዴ፣ አማኑኤል ዮሐንስ፣ ብሩክ ማርቆስ፣ አብዱልከሪም ወርቁ፣ በረከት ግዛው እና አበባየሁ አጂሶ ናቸው። በረከት ደስታ፣ ቸርነት ጉግሳ፣ ስንታየሁ መንግስቱ፣ ተመስገን ብርሃኑ እና አማኑኤል ኢርቦ ደግሞ በአጥቂ መስመር ጥሪ ደርሷቸው በቡድኑ ውስጥ መካተት ችለዋል።

የቻን ዋንጫ የማጣሪያ ውድድር በሁሉም የአፍሪካ ዞኖች እአአ ከታኅሳስ 20-22 እና ከታኅሳስ 27-29/2024 ይከናወናሉ። ከሰሜን፣ ከደቡብ፣ ከምሥራቅ፣ ምዕራብ 1 እና ምዕራብ 2 ዞኖች እንዲሁም ከማዕከላዊ በአጠቃላይ ስድስት የአፍሪካ ዞኖች የማጣሪያ ውድድራቸውን አሸንፈው በውድድሩ ለመሳተፍ ሀገራት ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ። ኢትዮጵያም ምሥራቅ አፍሪካን ወክላ ለመሳተፍና ያላትን እድል ለመጠቀም ጠንካራ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባታል።

በየዞኑ ለውድድሩ ለማለፍ ትልልቅ የማጣሪያ ፍልሚያዎች የሚያስተናገዱ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል፣ በምዕራብ ዞን የመድረኩ አሸናፊ ሴኔጋል ከላይቤሪያ እና ጋና ከናይጄሪያ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠቀሳሉ። በማዕከላዊ አፍሪካ፣ በምሥራቅና በደቡባዊ የአፍሪካ ዞኖችም በተመሳሳይ ጠንካራ ጨዋታዎች ሲስተናገዱ፤ ኢኳቶሪያል ጊኒ ከኮንጎ እና ቡሩንዲ ከኡጋንዳ የሚጠበቁ ናቸው። ከምሥራቁ ዞን በስተቀርም ከሁሉም ዞኖች ሶስት ሀገራት የማጣሪያ ጨዋታዎችን አሸንፈው ለውድድሩ የሚያልፉ ይሆናል።

የመጀመሪያው የቻን ዋንጫ እአአ በ2009 በኮትዲቯር አስተናጋጅነት የተካሄደ ሲሆን፤ ስምንት ሀገራት ተሳትፈው ዴሞክራቲክ ኮንጎ ዋንጫውን ወስዳለች። ውድድሩ ከአፍሪካ ዋንጫና ከዓለም ዋንጫ ጋር እንዳይጋጭ በጎዶሎ ቁጥር እየተካሄደ የተሳታፊዎቹ ሀገራት ቁጥርም በእጥፍ ጨምሮ 18 በማድረስ መካሄዱን ቀጥሏል። ኢትዮጵያም በውድድሩ የመጀመሪያ ተሳትፎዋን እአአ 2014 ደቡብ አፍሪካ ማድረጓ የሚታወስ ነው። በወቅቱ ሶስት ሀገራት ምሥራቅ አፍሪካን ወክለው ሲሳተፉ፣ ብሩንዲ ሱዳንን፣ ኡጋንዳ ታንዛኒያን እንዲሁም ኢትዮጵያ ርዋንዳን አሸንፈው መሳተፍ ችለዋል።

ኢትዮጵያ በመጀመሪያው የመድረኩ ተሳትፎ የምድብ ማጣሪያ ሶስት ጨዋታዎችን አድርጋ ያለምንም ነጥብ በአራት የጎል እዳዎች ነበር የተሰናበተችው። በ2016 ርዋንዳ አስተናጋጅ በነበረችበት ውድድር ዴሞክራቲክ ኮንጎ ለሁለተኛ ጊዜ ቻምፒዮን ስትሆን፤ የኢትዮጵያ ተሳትፎ በአንድ ነጥብ ከምድቧ በመሰናበት ነበር ያጠናቀቀችው። ከሁለት ዓመት በፊት በአልጄሪያ በተስተናገደው የቻን ውድድር ሶስተኛ ተሳትፎዋን ያደረገችው ኢትዮጵያ በተመሳሳይ አንድ ነጥብ ይዛ ከምድቡ ተሰናብታለች።

ከምድብ ማጣሪያ ያልዘለለው የኢትዮጵያ የመድረኩ ተሳትፎ፣ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ ለመሳተፍ በሚደረገው የማጣሪያ ጨዋታ ከዞኑ ጠንካራ ሀገራት መካከል አንዷ በሆነችው ሱዳን ይፈተናል። ውድድሩ ምንም እንኳን የሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት ቢሆን ሱዳንም በአብዛኛው ሀገር በቀል ተጫዋቾችን ይዛ የአፍሪካ ትልልቅ ሀገራት የሆኑትን ጋናን ጭምር ጥላ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፏ ይታወሳል።

ውድድሩን ኬንያ፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ በጣምራ ሆነው የሚያስተናግዱት ሲሆን፤ ለዚህም ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ። ዴሞክራቲክ ኮንጎ እና ሞሮኮ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ጊዜ ሲያሸንፉ፣ ሊቢያ፣ ሴኔጋል እና ቱኒዚያ አንድ ጊዜ ማሳካት ችለዋል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You