ክፉ ጎረቤት እና ክፉ የጎረቤት መንግሥት ይመሳሰሉብኛል። ሁለቱም ከመሥራት ይልቅ መቅናት፤ ከመተባበር ይልቅ መነቋቆር፤ ከውይይት ይልቅ ሐሜት እና አሉባልታን ይወዳሉ። ከሁሉ በላይ ደግሞ የጎረቤታቸው እድገት እና ለውጥ ያንገበግባቸዋል፤ እንቅልፍ ይነሳቸዋል። ቅናታቸው በዝቶ ዓመድ ይነዛባቸዋል።
ከሁሉም የሚያስገርመው ደግሞ እኔም ሆንኩ ሀገሬ ክፉ ጎረቤት አጥቶን አያውቅም። ሁለታችንም ቢያንስ ቢያንስ አንድ ክፉ ጎረቤት አጥቶን አያውቅም። ታዲያ የእኔም ጎረቤት ሆነ የኢትዮጵያ ክፉ ጎረቤት ለአቅመ አዳም እና ለአቅመ መንግሥት ሳይደርሱ ጎጆ የወጡ ይመስለኛል። የእኔ ጉዳይ እንኳን እዳው ገብስ ነው። የወገብ ቅማል ሆኖ ከራሱ ይልቅ ስለኢትዮጵያ እንቅልፍ የነሳው የጎረቤት መንግሥት ጉዳይ ግን አግራሞትን ፈጥሮብኛል።
በተለይም ጎረቤታችን ሰሞኑን ተናገረው የተባለው ጉዳይ የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች የሚለውን ብሂል የሚያስታውስ ነው። ጎረቤታቸውን በዓለም ላይ ካሉ እጅግ ድሃ እና ምንም አይነት መሠረተ ልማት ከሌላቸው ሀገራት አንዱ ነው። ሰሞኑን ጎረቤታችንን የጐበኘ አንድ ግብፃዊ ጋዜጠኛ የተናገረውን ማስታወስ እዚህ ጋር ጠቃሚ ይመስለኛል።
ጎረቤቴን የጎበኘው ግብፃዊ ጋዜጠኛ ሀገሪቱን ተዘዋውሮ ይመለከታል። ቢዞር ቢዞር ጠብ የሚል ነገር ያጣል። የረባ መሠረተ ልማት የለም፤ ኢንዱስትሪዎች የሉም፤ ግብርናም ሆነ የቱሪዝም እንቅስቃሴም አልተመለከተም። በአጠቃላይ በአየው ነገር የተገረመው ጋዜጠኛ በአፍሪካ ውስጥ በዚህ ደረጃ ሀገር ለመባል ሳይበቁ ሀገር የተባሉ ሀገራት መኖራቸው እንዳስገረመው መጻፉ የሚታወስ ነው።
በጎረቤታችን ልማት ብቻ ሳይሆን ሕግ እና ሕገ መንግሥትም የለም። ጎረቤታችን ምንም ሕገ መንግሥት ከሌላቸው ጥቂት የዓለም ሀገራት አንዷ ነች። እነዚህም ሀገራት ሀገር ለመሆን ብቁ ያልሆኑ፤ ዘላለም ተሰቅለው የማይወርዱ መንግሥታት ያለባቸው እና ሁልጊዜም ስለጦርነት እና ዕልቂት ሲያሰላስሉ ውለው የሚያድሩ ናቸው። ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ደግሞ ጎረቤታችን ነው።
ጎረቤታችን ሕገ መንግሥት ሳይኖረው ሕገ መንግሥት የሚተች የመጀመሪያው መሪ ነው። የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ላለፉት 33 ዓመታት ሕዝቦችን ያስተዳደረ፤ በቀጣይም በተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ሊሻሻል የሚችል ዘመናዊ ሕገ መንግሥት ነው። ጎረቤታችን በ21ኛው ክፍለ ዘመን ያለሕገ መንግሥት ሕዝብን የሚገዛ መሆኑ ሳያንሰው ያለ ሐፍረት ሕገ መንግሥትን ለመተቸት መነሳቱ ይሉሽን ባልሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ የሚለውን ተረት የሚያስተርትበት ነው።
ጎረቤታችን ሕገ መንግሥት፤ ምርጫ፤ ዲሞክራሲ፤ የፖለቲካ ፓርቲ የሚሉትን ቃላት አያውቃቸውም። እርሱ የሚያውቀው መርጦ መሳደብ እና ማበጣበጥ ነው። ጎረቤታችን በ21ኛው ክፍለ ዘመን በንጉሣዊ እና አምባገነን አገዛዝ መንገድ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ መግዛት የሚፈልግ ሰው ነው። በሪከርድ ደረጃም በአፍሪካም ሥልጣን ላይ ረጅም ዘመን ካስቆጠሩ መንግሥታት የመጀመሪያው ረድፍ በመያዝ በአፍሪካ ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ለመስፈር በቅቷል።
ይህ ድንቅ ጎረቤታችን ልማት ኋላቀርነት ነው ብሎ በመናገርም በቅርቡ በሌላ ጊነስ ሪከርድ ላይ እንደሚመዘገብ ይጠበቃል። ትምህርት፤ ጤና፤ ግብርና፤ መሠረተ ልማት፤ የኃይል አቅርቦት የሚሉት የልማት ጽንሰ ሃሳቦች አይስማሙትም። የከፍተኛ ትምህርት ተቋም አያስፈልግም ብሎ አንድ ለእናቱ የነበረውን ዩኒቨርሲቲ ከዘጋም ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል።
ጎረቤታችን የኃይል አቅርቦትንም አምርሮ ስለሚጠላ በጣት የሚቆጠሩት ፋብሪካዎችም የሚያመርቱት በፈረቃ ነው። ሕዝቡም የእለት ፍጆታዎችን የሚያገኘው በፈረቃ ነው። ውሃ በፈረቃ፤ ምግብ በፈረቃ፤ መጠጥ በፈረቃ፤ ትራንስፖርት በፈረቃ። በአጠቃላይ ኑሮ በፈረቃ ነው። ይህ ሰው ከሥልጣኑ በስተቀር ሁሉንም ነገር በፈረቃ አድርጎ ሕዝቡም ሀገሪቱም በጨለማ ውስጥ እየዳከሩ ይገኛሉ።
ታዲያ ይህ ሰው ከሰሞኑ የህዳሴ ግድብ አያስፈልግም ሲል የሰጠው መግለጫ የማይገባውን የሚናገር የማይወደውን ይሰማል የሚለውን የቆየ ብሂል እንዳስታውስ አድርጎኛል። ጎረቤታችን ሦስት ጄኔሬተሮችን ገዝቶ በሰበር ዜና አስነግሯል። የተገዙት ጄኔሬተሮች ከ24 ሜጋ ባይት በላይ የማምረት አቅም የላቸውም። ይህ ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ኢንዱስትሪ የሚጠቀምበት ኃይል መጠን ማለት ነው።
ስለዚህም ጎረቤታችን ስለህዳሴ ግድብ አምርሮ አስተያየት መስጠቱ የአዕምሮ ጤናውን እንድጠራጠር አድርጎኛል። መቼም ጎረቤታችን ነውና የጤናው ነገር ቢያሳስበን አይገርምም።
ይህ ጎረቤታችን ይሻሻላል ብለን እና የያዘውም ሰይጣን እንዲለቀው ተመኝተን የኢትዮጵያን የልማት ግስጋሴ እንዲያይና መንፈሳዊ ቅናት ተሰምቶት ፊቱን ከጥፋት ይልቅ ወደ ልማት እንዲያዞር ኢትዮጵያ ድረስ ጋብዘን አስጎብኝተናዋል። የሀዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክ፤ በአዲስ አበባ ያሉ የሪልስቴት ልማቶችን፣ የባሕር ዳር እና የጎንደር የልማት እንቅስቃሴዎችን በዓይኑ በብረቱ ተመልክቶ በኢትዮጵያ የሠላም እና የልማት ጎዳና እንዲጓዝ ብንመኝም ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስስ አይለቅምና ብዙም ሳይውል ሳያድር ምቀኝነቱ አገርሽቶበታል። በእልህ ተነሳስቶ እራስንም ሀገርንም ከመቀየር ይልቅ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ልማት እንድታቆም፤ በአፍሪካ ግዙፍ የሆነውን እና ከሀገር አልፎ ለምስራቅ አፍሪካ ተስፋ ሆነውን የህዳሴ ግድብን ያለኃፍረት ማጣጣል ጀመረ።
ሆኖም ጎረቤታችን ሊረዳው የሚገባው ነገር ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት ብቻ መንግሥት አያስብልም። ከዚያ ይልቅ የመሪነት ስብዕና ተላብሶ ሀገርንም ሕዝብንም ከድህነት አረንቋ ማውጣት ያስፈልጋል። ሀገሬ ኢትዮጵያ ደግሞ በጋዜጣዊ መግለጫ የምትበገር እና የምትበረግግ አይደለችም። ዛሬ የሀገሬ ታሪክ ከቀጣናው አልፎ በዓለም አደባባይ መሰማት ጀምሯል።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የስበት ማዕከል ናት። የቀጣናውን ሀገራት ከማስተሳሰር ጎን ለጎን በአካባቢው ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የበኩሏን ጥረት የምታደርግ ሀገር ነች።
በጎረቤት ሀገራት የሚነሱ አለመግባባቶች ቶሎ እንዲፈቱና ሀገራቱ በፍጥነት ፊታቸውን ወደ ልማት እንዲያዞሩ በማድረግ ረገድ ኢትዮጵያ እየተጫወተች ያለችው ሚና መተኪያ የሌለው ነው። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ማግስት ጀምሮ በሰሜን ሱዳን፤ በሱዳንና በሶማሊያ ወደ ግጭት የገቡ ኃይሎችን በመሸምገል ውጤታማ ተግባራትን አከናውነዋል።
ግጭት ባልቆመባቸው በሱዳን የአብዩ ግዛትና በሶማሊያ የሠላም አስከባሪ ኃይልን በመላክ ኢትዮጵያ ለአባል ሀገራቱ ጥላና ከለላ መሆን ችላለች። በቀውስ ውስጥ የምትገኘውን ሱዳንን ወደ ሠላም ለመመለስም በብቸኝነት የበኩሏን ጥረት በማድረግ ላይ የምትገኝ ሀገር ነች።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የመጀመሪያው ትኩረት የጎረቤት ሀገራት በመሆናቸው ኢትዮጵያ ከየትኛውም ዓለም አቀፋዊም ሆነ አሕጉራዊ ጉዳዮች በበለጠ ለጎረቤት ሀገራት የቅድሚያ ትኩረት ትሰጣለች። ይህንኑ መነሻ በማድረግም ግጭት እና ሁከት ውስጥ የሚገኙትን ሶማሊያ፤ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በመሪዎች መካከል ተደጋጋሚ ውይይት እንዲደረግ ኃላፊነትን በመውሰድና አልፎ ተርፎም የሠላም አስከባሪ በመላክ ሀገራቱ አንጻራዊ ሠላም እንዲኖራቸው አበክራ በመሥራት ላይ ትገኛለች።
ሶማሊያ መንግሥት አልባ ሆና ለዘመናት ቆይታለች። ኢትዮጵያ ባደረገችው ጥረት እኤአ ከ2008 ጀምሮ ሶማሊያ መንግሥት መሥርታ አንጻራዊ ሠላም አግኝታ ቆይታለች። ለሶማሊያ መረጋጋትና የሶማሊያን ሕዝብ ለመታደግ ሲባልም ኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን አጥታለች።
በፊት ‘AMISOM’ አሁን ደግሞ ‘ATMIS’ እየተባለ በሚጠራው የአፍረካ ኅብረት የሶማሊያ ሠላም ማስከበር ተልዕኮ በኩል ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሠላም ጉልህ አስተዋፅዖ ስታደርግ ቆይታለች። በዚህ ተልዕኮም አብዛኛውን የሶማሊያ መሬት በመሸፈንና ከጥቃት በመከላከል የሶማሊያ ሕዝብ በሠላም ወጥቶ እንዲገባ፤ የሶማሊያ መንግሥትም ተረጋግቶ መንግሥታዊ ሥራዎችን እንዲያከናውን በማድረግ ላይ ይገኛል።
በተመሳሳይም ሱዳን ግጭት ውስጥ በገባችበት ወቅት ሁሉ ከሕዝቡ ጎን በመቆም ሱዳን ወደ ተሻለ ሠላምና መረጋጋት እንድትመጣ ኢትዮጵያ የበኩሏን ጥረት ስታደርግ ቆይታለች። በሱዳን የሽግግር መንግሥት እንዲመሠረትም ግንባር ቀደም ሚናዋን መወጣቷ የሚታወስ ነው።
በግጭት አዙሪት ውስጥ የምትገኘውን ሱዳን ወደ ሠላሟ እንድትመለስ ማንም መሪ ባላደረገው መልኩ ፖርት ሱዳን ድረስ በመሄድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሱዳን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ አል ቡርሃን ጋር ተወያይተው ተመልሰዋል። ውይይታቸውን ካጠናቀቁ በኋላም ‹‹”የወንድም ሱዳን ሕዝብ ችግር የኛም ችግር፤ ሠላማቸውም ሠላማችን በመሆኑ ለሱዳን ሕዝብ እፎይታ እና የብልፅግና ጉዞ ዛሬም እንደ ትላንቱ ከልብ እንሠራለን።” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
አዲሲቷ ሀገር ደቡብ ሱዳንም እንደ ሀገር እንድትቆም ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ሚና ከመጫወቷም ባሻገር በሀገሪቱ የነበረው የእርስ በእርስ ግጭት እንዲያባራና አንጻራዊ ሠላም እንዲረጋገጥ የማይተካ ሚና ተጫውታለች።
በጎረቤት ሀገራት የሚታየውን ግጭትና ጦርነት እንዲያበቃ ከመሥራት ጎን ለጎንም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በልማት እንዲተሳሰሩ በማድረግ ረገድም የኢትዮጵያ ሚና የጎላ ነው።
ኢትዮጵያ በተለይም ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በየዓመቱ በበርካታ ቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል በቀጣናው የሚታየውን ድርቅ በዘላቂነት ለመቋቋም አበክራ በመሥራት ላይ ትገኛለች። ከዚያም ባሻገር የአካባቢ መራቆት የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ዋነኛ ችግር መሆኑን በመረዳት የአረጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩ ከኢትዮጵያ አልፎ በምሥራቅ አፍሪካ አባል ሀገራት ዘንድ እንዲተገበር የመሪነት ሚናውን ወስዳ በመንቀሳቀስ ላይ ትገኛለች።
ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሀገራት ልማት በማቀራረብ ረገድ እየተጫወተችው ያለችው ሚና በአካባቢ ጥበቃ ብቻ የተገታ አይደለም። በተለይም ከዓባይ ግድብና ከጊቤ ሦስት ግድቦች የሚመነጭ ኃይልን ለጎረቤት ሀገራት በተመጣጣኝ ዋጋ በማዳረስ ቀጣናው በኃይል እንዲተሳሰር በማድረግ ላይ ትገኛለች።
በድርቅና ረሃብ የምትታወቀው ኢትዮጵያ ዛሬ ስንዴን በማምረት ኤክስፖርት የማድረግ ደረጃ ላይ ደርሳለች። ይህ የአካባቢውን ሀገራት ከማነቃቃቱም ባሻገር አባል ሀገራቱ በቅርበት ስንዴን እንዲያገኙ ዕድል ፈጥሮላቸዋል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሀገራት ከማስተሳሰር ጎን ለጎን በአካባቢው ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የምታደርገው ጥረት እንደትላንትናና ዛሬ ሁሉ ነገም ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው።
ስለዚህም ኢትዮጵያን በጋዜጣዊ መግለጫ ማጣጣል እና ያልተገባ ስም መስጠት ሕሊና ላለው ሰው ከእውነት ጋር መጋጨት ነው። ሕገ መንግሥት ሳይኖር ስለ ሕገ መንግሥት መተቸት፤ በኃይል አቅርቦት እየተሰቃዩ ስለ ህዳሴ ግድብ ማብጠልጠል፤ ምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች በሌሉበት ሀገር ስለ መንግሥት ሥርዓት መተቸት የጤነኝነት አይመስልም። ስለዚህም የሚበጀው ራስን ማየት ነው። ወደ እራስ ሲታይ ብዙ ጉድ አለና!
አሊሴሮ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም