የሲኒማ ማህበርተኞች በብሪክስ

ኢትዮጵያ ብሪክስን ከተቀላቀለች ገና ፊርማዋ ያልደረቀ ቢሆንም ከልጆቿ የፈለቀው ሃሳብ ግን ለመላው ብሪክሳውያን መልካም መደላድልን የሚፈጥር ይሆናል። የዚህ ማህበርተኛ አባላት በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ፣ አልፎ አልፎም በጥቂት ማህበራዊ ጉዳዮቻቸው ቢተሳሰሩም መሃከላቸው የጎደለ ትልቅ ነገር ነበር። ግንኙነታቸው የሰመረ፣ ፍቅራቸውም የጸና ሊያደርግላቸው የሚችለውን ኪነ ጥበብ የዘነጉት ይመስላል።

እንደ ጅምር በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ሊደረግ የታሰበውም ይህንን ጉድለት ለመሙላት የምታግዛቸውን አንዲት ጠጠር ለሁለት መጣል ነው። የመጀመሪያው ጠጠርም በፊልም ፌስቲቫል እንዲሆን ወስነዋል። አሁን እነርሱ ይጀምሩታል። በቀጣይ ደግሞ ሙሉ አባላቱ ተግተልትለው መከተላቸው አይቀርም።

አባላቱን ከኋላ የተቀላቀለቻቸው ኢትዮጵያና ነባሯ ቻይና ለሁለት ሲመካከሩ ቆይተዋል። ከውስጥ ያሉት “ከኋላ የመጣ ቀንድ አወጣ” አይሉምና ቻይናም ብትሆን ሃሳቡ ተመችቷታል። “ሌሎቹንም እናካት ይሁን?” ብለው መከሩና “አይ ባይሆን ለአሁኑ ሁለታችን እንጀምረውና በቀጣይ እኛን አይተው እንዲቀላቀሉን ብናደርግ ይሻላል” ብለው ተስማሙ። ያሰቡትን ለመፈጸምም በየፊናቸው ደፋ ቀና ማለቱን ተያያዙት። በየጊዜው እየተገናኙም ውጥናቸውን ከዳር ለማድረስ ብዙ ተጉ። ለአንድ ዓመት ያህል ላይ ታች ሲሉ ከሰነበቱ በኋላም፤ ከሰሞኑ እውን ሆኖ ሃሳባቸውን ይፋ አድርገውታል።

በያዝነው ወር ታህሳስ ላይ፣ በቀጣዩ ሳምንት ለሁለት አብረው ሽር ይላሉ። ከታህሳስ 11 እስከ 14 ለአራት ቀናት አዲስ አበባ በኢትዮ-ቻይና የፊልም ፌስቲቫል ድምቅምቅ ትላለች። በአፍሪካዊቷ ኢትዮጵያና በኤዢያዊቷ ቻይና መካከል “ቺርስ ለጥበብ!” ለመባባል ቀነ ቀጠሯቸውን ቆርጠው ተሰናድተዋል። ቻይና ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት በቅርብ ርቀት አለሁ የምትል ወዳጅ ብትሆንም እስከዛሬ ድረስ ግን ይህን መሰሉን ጽዋ ከማናቸውም ጋር አንስታው አታውቅም። ፌስቲቫሉ ለብሪክስ ብቻም ሳይሆን በአፍሪካ ደረጃም የሚጀመሪያው ነው። ለብሪክስ ጎበዛዝትም ቢሆን ለአፍሪካውያኑ ሁሉ ያማረውን ደጅ፣ የተዋበውን በር የሚከፍት ነው። ከምንም በላይ ደግሞ በኢትዮ-ቻይና መካከል ላለው ወዳጅነት ጽኑ ማሰሪያ ይሆናል።

የኢትዮጵያና ቻይና ግንኙነት የጀመረው ዛሬ አይደለም። በቆየ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ክበብ ውስጥ ከገቡ ዘመናት አልፏል። ምናልባትም ደግሞ የሰመረ ግንኙነት አላቸው ከሚባሉ ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው። ይሁንናም ዛሬ ድረስ ያላቸው ግንኙነት በንግድና ኢንዱስትሪ ደግሞም በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ነው። በአጠቃላይም በኢኮኖሚውም ለሀገራችን አለሁልሽ የምትል ሆናለች። አብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት ጎተራ በሜድ ኢን ቻይና የታጨቀ ነው። የኛ ሀገርም ግንባር ቀደሟ ሳትሆን አትቀርም። መንገድ ቢሉ ቁሳቁሱ ሁሉ አርማው ሜድ ኢን ቻይና ነው። በቅርብ ጊዜ ደግሞ ከምዕራባውያኑ እርግጫ ለማምለጥ በብሪክስ ተሳስረው እህትማማች ሆነዋል። የግንኙነታቸውን መጠን ያሳየናል ለማለት ነው። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በብሪክስ ገበታ ላይ አብረው መቀመጣቸው ያረጋግጥልናል። ሆኖም መንግሥታቱስ በዚህና በዲፕሎማሲው ተገናኙ፤ ታዲያ ሕዝብ ለሕዝብስ በምን ይገናኝ?

ለመንግሥታቱም ቢሆን በሕዝብ መካከል የሚፈጠረው ትስስር ከፖለቲካው ባልተናነሰ መልኩ ወዳጅነትን የሚያጸና ነው። ከአንድ ለአንድ ግንኙነትም በተለይ እንደ ብሪክስ ባለ ማህበር ውስጥ ሲሆን ደግሞ ይበልጥ ወሳኝ ይሆናል። ያንን ሁሉ ስንመለከት ግን እስካሁን ድረስ በኪነ ጥበቡ ዘርፍ አልተቆራኙም። ነገሬ ብለው በቅጡ የተነጋገሩበትም አይመስልም። በደረቁ ያለ ኪነ ጥበብ የሚደረጉ ግንኙነቶች አይዛለቁም ባይባልም ወዝ ግን አይኖራቸውም። በየትኛውም ነገር ላይ ኪነ ጥበባዊውን ጨው ካልነሰነሱበት መምረር ማሰልቸቱ አይቀርም። በሀገራቱ ማዕድ ላይ ከጥበብ በተን ማድረጉ ለማጣፈጥና ላለመሰላቸት ብቻ ሳይሆን እንደ ልጥ ማሠሪያ መሆን ስለሚችልም ጭምር ነው። ምሰሶ አቁመው፣ ቋሚውን ለጠገጠጉለት ቤት ማገሩን ካላዞሩበት በጭቃ ሊለስኑት አይቻልም። ካለሰኑት የቤቱ ውበት አልባ መሆን ብቻ ሳይሆን ለብርድም መገላለጥ ነው።

በሀገራት የርስ በርስ ግንኙነት ውስጥ የኪነ ጥበብ አስፈላጊነት የዋዛ መስሎ ቢያቀሉትም፤ ሃይልና ጉልበቱን የሚያውቀው ተጠቅሞ ያየ ብቻ ነው። ብዙ ተዋዶ፣ ብዙ ተፋቅሮ፣ ረዥም መንገድ ስለመጓዝ ካሰቡ እንደ ኪነ ጥበብ ያለውን አዋዶ የሚያስታርቅ አይገኝም።

ይሁንናም እንዲሁ ዓይነቱ የፊልም ፌስቲቫል ለአዲስ አበባ ብርቅ አይደለም። ብዙ ጊዜ አስተናግዳ፣ በሌላ ጊዜም ተስተናግዳለች። በተለይ ደግሞ በምዕራባውያኑ መንደር ውላ አድራለች። በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ቆየት ያሉ ፊልሞቻችን ሳይቀሩ በከተሞቻቸው ሲንጎራደዱ ታይተዋል። ታዲያ የአሁኑ እንዲህ የሚያስወራ ምን አዲስ ነገር አለው? ማለት አይቀርም። አዲስ ነገርም አለውና እኛም መናገራችን አይቀርም። ከምዕራባውያኑ ጋር የነበሩን ፌስቲቫሎችና የልምድ ልውውጦች ለሀገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ አበርክቶ አልነበረውም ለማለት አይቻልም። ግን ደግሞ የኢንዱስትሪውን ገመና ገልጦ አላስነወረም ላለማለትም አይቻልም። በዚህ መልኩ በሦስትና አራት ቀናት ውስጥ የሚደረጉ ግንኙነቶች ጣጣቸውም በዚያው አያከትምም። ልክ እንደ ጉንፋን ነው፤ ጥሩም ይሁን መጥፎ አንዱ በሌላው የሚያጋባው አይጠፋም። እንግዲህ የተጋባብን ጥሩ ከሆነ ኢንዱስትሪውን ሽቅብ፣ መጥፎ ከሆነም ቁልቁል ያዘቅጠዋል። እኛ ግን ከሁለቱም ዓይነት ቀማምሰናል።

በመሃከል ግን ቆም ብለን ልናጤነው የሚገባ አንድ ነገር አለ። ሙያዊ ከሆኑ ክህሎቶች ጀምሮ የተሻለ በረከት የምናገኝባቸው ቢሆኑም ከእኛ የፊልም ኢንዱስትሪ ጋር ሆድና ጀርባ የሆነና አብሮ የማይሄድ ጉዳይ እንዳላቸውም ልንገነዘብ ይገባል። ይሄውም በፊልሞቻቸው ውስጥ የሚንጸባረቁት ባህሎቻቸው ፈጽሞ ከኛ ባህል ጋር የማይጣጣም ነው። በግንኙነቶቻችን ወቅት ይህን ሳናጠራ እንደወረደ ተቀብለን ለፊልሞቻችን ማህበረሰቡ ጥሩ የሆነ ምላሽ እንዳይኖረው ያደረጉ ነገሮችም አሉ። እነዚህን በመሰሉ መድረኮች ስለፊልም የልምድ ልውውጥ ስናደርግ አስቀድመን ከማን ጋር ነው እያደረግን ያለነው የሚለውን ማሰብ ያስፈልጋል።

አሁን በኢትዮጵያና ቻይና መካከል የተጀመረውና ወደ ብሪክስ እየታሰበለት ያለው የፊልም ፌስቲቫል አዲስ ነገር አለውና የተለየ ነው የምንለውም እዚህ ጋር ነው። የፊልም ኢንዱስትሪያችን ማንነት ከባህላችን ጋር እንዳይጋጭ የተሻለውን የራሱን መስመር ይዞ እንዲሄድ ያግዘዋል። “ከአህያ ጋር የዋለች ጊደር …” እንደሚሉት አዋዋላችንን ያሳምርልናል። እንዴት? ከተባለ፤ ቻይናን ጨምሮ በብሪክስ ውስጥ ያሉ አብዛኛዎቹ ሀገራት የፊልም ኢንዱስትሪዎቻቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ መበልጸግ ከመድረሱም በላይ ቱባ በሆነ ባህልና እሴቶቻቸው ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ከዘመኑ ንፋስ ጋር መንፈስን ብቻ ሳይሆን፤ የራስን ማንነት ሳይለቁ ታላቅ የፊልም ኢንዱስትሪ እንዴት መገንባት እንደምንችል ሚስጥሮቻቸውን ሹክ ይሉናል።

አሁን የመጀመሪያ የሆነችውን ቻይናን ብንመለከት ለባህሏ ሟች ከመሆኗም በቀደምት ኪናዊ ሥልጣኔ ውስጥ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያመሳስል ነገር ያላት ሀገር ናት። የፊልም ኢንዱስትሪዋም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅነትን ማትረፍ የቻለ ነው። ቀጥሎ በብሪክስ ውስጥ የምናገኛት ሌላኛዋ ሀገር ህንድ ናት። ይህቺም ሀገር ልክ እንደ ኢትዮጵያ በብዝሃነት ውስጥ ያለች ናት። ሕዝቦቿ በማህበራዊ መስተጋብሮቻቸው የተሳሰሩና እንደኛው በልዩነት ውስጥ የጋራ እሴቶቻቸውን በአንድነት ያጸኑ ናቸው። ከባህላዊ የተፈጥሮ ቁርኝት ጋር ባላቸው ውሕደት ለእኛ ከቻይናውያኑም በላይ የሚያመሳስል የአኗኗር ዘዬ አላቸው። ትንሽ ወደኋላ ዞር ብለን ካስታወስን የዛሬን አያድርገውና አብዛኛው የሀገራችን የፊልም አፍቃሪ በህንድ ፊልሞች ፍቅር የወደቀ ነበር። ዛሬ ላይ የምንመለከታቸው የፊልም ባለሙያዎቻችንም መነሻቸው በህንድ ፊልሞች ስለመሆኑ ሲናገሩት እንሰማለን። በዚያ ልክ የነበረን ፍቅር ከኛ ጋር አብሮ የሚሄድ አንድ ነገር እንዳለው ማሳያ ነው።

ህንዶች ሆሊውድን የሚገዳደረው ትልቁ የፊልም ኢንዱስትሪ፤ የቦሊውድ ባለቤት ናቸው። ታዲያ ከቻይና ጋር የጀመርነው ኪነ ጥበባዊ ዝምድና በብሪክስ እውን ሆኖ ከህንድ ጋር ተዛመድን ማለት ከምንጊዜውም በላይ ምርጡንና ትክክለኛውን ቦታ አገኘን ማለት ነው።

ከማይመስሉን ጋር ውለን የቱንም ያህል ጣፋጭ ጉርሻ ቢያጎርሱን መጨረሻው ላይ መጎርበጡ አይቀርም። አገኘን ብለን የበላነው ሁሉ ዛሬ ላይ ውጤቱን እየተመለከትን ነው። ባህልና እሴቶቻችንን ገሸሽ አድርገን የፊልም ኢንዱስትሪያችንን በዓለም ተወዳዳሪ እንዲሆን ብናደርገው እንኳን ዋጋ ቢስ ነው። ባፍ ባፍ ያልነው ነገር መልሶ በአፍጢም ይደፋናል። እስከዛሬ ድረስ በነበረው ሂደት የሀገራችን ሲኒማ መሪጌታው ያደረገው የሆሊውድን ሲኒማ ነው።

ካነሳናቸው ነጥቦች አንጻር ገፍቶ እንዳይሄድ ጅብራ መስሎ የቆመበትም አንደኛው ምክንያት ይህ በመሆኑ ነው። ከሆሊውድ ይልቅ ለኛ ተምሳሌት ቦሊውድ ለመሆን ይችላል። ፊልሞቻችን እኛን አንመስል ብለዋል ለሚለው በጥሩ የመስተካከያ መንገድ ለመግባት አጋጣሚውን ከዚህ አናጣለትም። የሚመስለንን ለማግኘት ከሚመስሉን ጋር መዛመዱ መልካም ይሆናል።

ለጊዜው ፖለቲካዊውን ሽታ ማሽተታችንን ወዲያ እንበልና በኪነ ጥበባዊ እሳቤ እስቲ ደግሞ ሌላኛዋን የብሪክስ ክፋይ ራሺያን ጥቂት ከኛ እናመሳስላት። ካሏት ነገሮች ሁሉ በሥነ ጽሁፍ ዘርፍ በዓለም ላይ ያላት የቆየ ሃያልነት አላት። በአንደኛው ዘመን ላይ ልክ እንደኛው ነበረች ብንልም አሁን እንደርሷ ነን ለማለት የሚያስችል አቅም ላይ ግን አይደለንም። እሱንም እንተወውና ወርቃማ የኪነ ጥበብና ሥነ ጥበብ ጊዜ የምንለውን ዘመን ብቻ እናስብ። ያ ዘመን ማለት የሀገራችን ኪነ ጥበብ ከራሺያ ጥበብ ጋር ጫጉላ ሽርሽር የጉቡበት ጊዜ ነው።

በተለይ ቲያትርና ሥነ ጽሁፍ። ለዚህ እንደ ምክንያት የሆነው ደግሞ አብዛኛዎቹ የሀገራችን ጠቢባን ተምረው የመጡት ራሺያ መሆኑ ነው። የኛዎቹ ደራሲያን ከራሳቸው ሥራዎች ባሻገር የራሺያ ጸሀፊያንን ሥራዎች በመተርጎም ተጠምደው ነበር። ከአንድሬ ዶስኮቭስኪ እስከ ሰርጌ ኤንሽታይንና አንቶቫን ቼኮቭ ድረስ የእነርሱን ልቦለዶችና ተውኔቶች በመተርጎም ሕዝቡን አስኮምኩመውታል። የተማረው ብቻ ሳይሆን ቀሪው ማህበረሰብም በራሺያውያኑ ሥራዎች ልቡ ተለክፏል። ይህ ሁሉ የሆነውም የባህላዊ ደም ስራቸው ከኛ ጋር ተመሳስሎሽ ስላለው ነው። ባለሙያዎቹን በእነርሱ ስለተገሩ ብንል እንኳን ጥበብ አፍቃሪው ማህበረሰብ በዚያ ልክ ወዶ መቀበሉ፤ አሁንም የሚነግረን ነገር አለው።

ሌላዋን ብናክል እሷም ኢራን ናት። ሲንቋትም ከየት መጣሽ ሳይሏት፣ በራሷ ቀለም ሽክ ብላ መታየት የቻለች ናት። ታዲያ ከእኚህ በላይ ለኛ መድኃኒት ማን ይሆናል?

ማህበርተኛው ከእልፍኝ ገብቶ ደጋሽ ማነው እንዳይል ማወቅ በጊዜ ነው። ለዚህ የፊልም ፌስቲቫል በርከት ያሉ አካላት እጅ ለእጅ ተጣምረዋል። ይህን ድንኳን ለማቆም ከዛፉ ግንድ ወጥረውታል፤ ከብሪክስ ማለት ነው። በመጀመሪያ ሃሳቡ ብቅ ያለው ስሩ ከሀገራችን ከሆነውና ልዩ ልዩ ሁነቶችን በማዘጋጀት ከሚታወቀው ጎፍ ኢንተርቴይንመንት ነው። ከተመሠረተ 5 ዓመታትን አስቆጥሯል። በእነዚህ ዓመታትም ከ150 በላይ በሆኑ ሥራዎች ውስጥ በኢትዮጵያና በተለያዩ የውጭ ሀገራት መካከል ድልድይ ሆኖ ሠርቷል። ይህን የፊልም ፌስቲቫል ሃሳብ ይዞ በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ነበር ያመራው።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኪነ ጥበቡ ዘርፍ መንግሥትን ተክቶ እያደረገው ባለው ሩጫ አሁን ላይ ከፊት አስከትሎ እየመራ ያለ ይመስላል። በዘንድሮው ዓመት ብቻ በግሉም በቡድንም በርካታ ዝግጅቶችን ማሰናዳቱ አይዘነጋም። ከጎፍ በተነሳው ሃሳብም ሁለቱ ተያይዘው በተራ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ቀጥሎም በኢትዮጵያ ወደ ቻይና ኤምባሲ ደርሰው ከባዱን ጥምረት ፈጥረዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የባህል ዘርፍ አማካሪ የሆኑት ወይዘሮ ዛንግ ያ ዌይ ከወደ ቻይና በኩል መልካም የሆኑ ነገሮች እንደሚፈጸሙ ቃል የመግባት ያህል የተናገሩት አለ። አሰናባሪ አካላቱ ተሰባስበው ስለጉዳዩ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅትም አማካሪዋ እንዲህ ነበር ያሉት፤ “…የቻይና መንግሥት ኢትዮጵያ ያላትን የኪነ ጥበብና ሥነ ጥበብ እምቅ አቅም ለማሳደግ ቁሳቁን ጨምሮ የሥልጠና ድጋፍም ያደርጋል። ባለሙያዎችም ከቻይና ልምድ እንዲቀስሙ በማድረጉ እንሠራለን። የጠነከረ ግንኙነት እንዲኖርም ከዚህ በኋላ ትኩረታችንን በእነዚህ ዘርፎች ላይ አድርገን እንቀሳቀሳለን” ። “…ኢትዮጵያም ሁል ጊዜ ከሌላው ቀጂ አይደለችም። የራሷ ታሪክ፣ ባህልና ወግ ያላት ሀገር ናት። እንደ ተቀባይ ብቻ አድርገን መቁጠር የለብንም። እኛም የምንሰጠው አለን” ያሉት ደግሞ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነ ጥበብ፣ ሥነ ጥበብና ፈጠራ ልማት ዘርፍ ሃላፊዋ ወይዘሮ ነፊሳ አልማህዲ ናቸው። በእርግጥም ያለንን ካወቅን የምንሰጠውን አናጣም። ምንም ነገር እንደሌለን ቆጥረን እጃችንን የምንዘረጋው ለመቀበል ብቻ ሳይሆን ለመስጠትም መሆን አለበት።

የፌስቲቫሉ መቆያ በሆኑት አራቱ ቀናት ማህበርተኛው ከእድምተኛው ተሰባስቦ የዚያኔም ቺርስ ለጥበብ! ነው። የፊልም ፌስቲቫል እንደመሆኑ የመጀመሪያው ነገር ፊልሞች ይታያሉ። ከኢትዮጵያ የተመረጡት “ሂሩት አባቷ ማነው” እና “ዶቃ” ፊልም ናቸው። ከወደ ቻይናም ጓዛቸውን አንጠልጥለው ከሚመጡት ፊልሞች መካከል “ዘ ሆም ኢን ዘ ትሪ” እና “ራኒግ ላይክ ዊንድ” ይገኙበታል። በእነዚህ ሳያበቃ ሌሎች ዘጋቢ ፊልሞችም ተራ በተራ ይከታተሉበታል። የሁለቱም ሀገራት የፊልም ባለሙያዎች ጠጋ ብለው ባግባባቸው ቋንቋ ሁሉ ልምዶቻቸውን ይለዋወጡበታል። ትውውቅ በመፍጠር ቀጣይ በግልም በጋራም ለመገናኘት ይቃጠሩበታል። ስለቀጣዩ ጉዞ፣ ስለብሪክሱ መዳረሻ በቁም በጨዋታው ይወጋበታል። በፊልሞች እየተዝናኑ፣ ሃሳቦች ይንሸራሸራሉ። ብቻ ብዙ ብዙ…መንገድ ጠቋሚው መንገዱን እንጂ ወንበሩን አያሳይምና ከታህሳስ 11 እስከ 14 ስድስት ኪሎ ወደሚገኘው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (መኮንን አዳራሽ) በነጻው መግቢያ በር ብለን ጠቁመናል።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You