አዲስ አበባ፡- በኮሪደር ልማት የሀዋሳ ከተማን ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የከተማዋ ምክትል ከንቲባና ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አጋና ነቶ አስታወቁ።
ምክትል ከንቲባው አቶ አጋና ነቶ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ በከተማዋ በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት ሀዋሳን ፅዱ፣ አረንጓዴ፣ ውብና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ ሌት ተቀን እየሰራን ነው። ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ ተመድቦለት እየተከናወነ ያለው ይኸው የልማት ስራ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ የከተማዋን የቱሪዝም ፍሰት በእጅጉ የሚያሳድግና ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን በማድረግ ረገድ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።
ሀዋሳ የክልላችን ዋና ከተማ ፣ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን አቅፋ የያዘች እንዲሁም ፈጣን እድገት እያስመዘገበች ያለች ከተማ ናት ያሉት ኃላፊው፤ እንደ ሀገር የተያዘው የኮሪደር ልማት አካል እንድትሆን በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት በሁለት ምዕራፍ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱ በተለየ መልኩ ትልልቅ መሰረተ ልማቶችንና ማራኪ ዲዛይን እንዲኖረው ተደርጎ መቀረፁን አቶ አጋና ተናግረው፤ ይህም ሀዋሳን በቱሪዝም በምሥራቅ አፍሪካ ተመራጭ የሚያደርጋት እንደሚሆን አስረድተዋል።
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ ሁለት ነጥብ አራት ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውና ከሜምቦ መብራት ላይት እስከ ሪፈራል አደባባይ ድረስ ያለውን የልማት ስራ ከሶስት ወር በፊት የተጀመረ ነው። በውስጡ የተለያዩ ገፅታዎችን እንዲይዝ ተደርጓል። ከእነዚህም መካከል የእግረኛ መንገድ፣ የሳይክል መንገድና አረንጓዴ ስፍራዎች ተጠቃሽ ሲሆኑ ላለፉት ሶስት ወራት በተቀናጀ ጥረት ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል።
የዚሁ ምዕራፍ አካል የሆነውና ከሳውዝ ስፕሪንግ እስከ ኃይሌ ሪዞርት፤ ከኃይሌ ሪዞርት እስከ ሸዋ በር፤ ከሸዋ በር እስከ ሻፌታ ታወር ድረስ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ አምስት ነጥብ ስድስት ኪሎ ሜትር ይሸፍናል። ይህም የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን የያዘ ሲሆን፤ በተለይም በጣም ሰፋፊና ማራኪ ዲዛይን ያላቸው አረንጓዴ ስፍራዎች ፣ የእግረኛ መንገዶች፣ የአስፋልት ግንባታ አሉት።
‹‹የመጀመሪያው ምዕራፍ ተጠናቆ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትራችን ተመርቆ ወደ ስራ ገብቷል›› ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ በተለይም የእግረኛ መንገዱ ከሌሎች ከተሞች በተለየ ሰፊና ማራኪ ተደርጎ በመሰራቱ ነዋሪው ደስታውን እንደገለጸ ጠቁመዋል። የልማት ስራው በተለያዩ ሎቶች ተከፋፍሎ የግንባታ ማሰሪያዎች ገብተው ቀን ከሌሊት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት የአፈር ስራ እየተከናወነ ሲሆን፤ አጠቃላይ የምዕራፍ አንድ የኮሪደር ስራ በአምስት ወራት ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ ርብርቡ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀው ፤ለዚህም የከተማው አስተዳደር በቂ በጀት መመደቡን፤ ሥራውንም ከከንቲባ ጀምሮ ያሉ የከተማዋ ቁልፍ አመራሮች በአምስት ቡድን ተከፋፍለው እየተከታተሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ወሰን የማስከበር ስራ ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን አቶ አጋና አመልክተው፤ በሚነሱ ቤቶች ዙሪያ ቅሬታ እንዳይፈጠር አስቀድሞ ከሕዝቡ ጋር በመነጋገር መግባባት ላይ መድረስ መቻሉን አስገንዝበዋል። ‹‹ከሰውዝ ስፕሪንግ እስከ ሻፊታ ታወር ድረስ ያለው ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦለት ነው እየተከናወነ ያለው›› ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ ይህም ስራ የከተማዋን፤ የነዋሪውን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድግ እንደሆነ አመልክተዋል።
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ በሁለተኛው ምዕራፍ የሐዋሳ ከተማ የኮሪደር ስራ የከተማዋ ማስፋፊያ አካቢዎች ላይ ያተኮረ ነው። ከዚህ ቀደም የከተማነት ይዘት እምብዛም ያልነበራቸው እንደ ጨፌ እና ዳቶ የመሳሰሉ አካባቢዎችን ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ እንዲከናወኑ ትኩረት ተሰጥቷል። በዚህም እስከ 50 ሜትር ስፋት ያላቸው አስር መንገዶች የተለዩ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ ለሶስቱ መንገዶች ቅድሚያ በመስጠት የዲዛይን ስራ ተጠናቆ ወደ ስራ ለመግባት እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል።
በሌላ በኩል በከተማዋ ፒያሳ ወይም የቀድሞ ማዘጋጃ በሚባለው አካባቢ የሚጀምርና እስከ ስሙዳ የተባለ ስፍራ እንዲሁም ከሱሙዳ እስከ ሳውዝስታር ፣ ከሳውዝ ስታር እስከ መኩሪዬ ሆቴል እንዲሁም ፈጣን መንገድና ኢንዱስትሪ ፓርክ ድረስ ያለው የኮሪደር ስራ በምዕራፍ ሁለት የተካተተ መሆኑን አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት ዲዛይኑ ተጠናቆ ወሰን የማስከበር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል። በአጠቃላይ በመጀመሪያው ምዕራፍ ወደ 13 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን፤ በምዕራፍ ሁለት ጨፌና ዳቶ አካባቢን ሳይጨምር 11 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚዘልቅ የኮሪደር ልማት ለማከናወን እየተሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በሁለቱም ምዕራፍ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ የከተማዋን የቱሪዝም ፍሰት ከማሳደግ በዘለለ የነዋሪውን ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማጎልበት፣ የልማት ጥያቄዎችን በመመለስ ረገድ ፋይዳው የጎላ እንደሆነም አመልክተዋል። በተጨማሪም ለግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታ የሚፈጠር በመሆኑ በከተማዋ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም