አብሮነትን የሚያፀኑና በጋራ መኖርን የሚሰብኩ መድረኮች ማዘጋጀት ህዝቦችን ለማቀራረብ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል። አንዱ የሌላውን ማንነት እንዲረዳ፣ ባህሉን እንዲያውቅና የራሱን ሌሎች ዘንድ በማድረስ ያለውን ግንኙነት እንዲያጠነክርም ጥሩ መደላድል ይሆናል። ኢትዮጵያ የብዙ ባህል ባለቤት እንደመሆንዋ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህል፣ቋንቋና እሴት ተጠብቆ እንዲቆይና ያላቸውን ለሌላ ለማስተዋወቅና ማጋራት እንዲችሉም ዕድል ይፈጥራል።
የብሔር ብሔረሰብ ቀንን የመሰሉ ክብረ በዓላት ደግሞ የህዝቦችን አንድነት የማጠናከር ዕድል ከሚፈጥሩ ሁነቶች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው። የብሄረ ብሄረሰብ ቀን በድምቀት የመከበሩ አንድምታም አንድም ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቅርርባቸው እንዲጠናከር ብሎም ለፌዴራላዊ ሰርዓቱ ዋስትና የሰጠው የኢፌዴሪ ህገ መንግስትን ለመጠበቅ በአንድነት ቃል ለመግባት ነው።
ለማናችንም ግልጽ እንደሆነው ከዛሬ 28 ዓመት በፊት ኢትዮጵያ የብሄረሰቦች አስር ቤት ነበረች። ኢትዮጵያን የገነቡ ብሄር ብሄረሰቦች ማንታቸው ተዋርዶ፣ ባህልና ቋንቋቸው ተንቆ የመከራን ዘመን ሲገፉ መኖራቸውም አሌ የማይባል ሀቅ ነው።
ይህም የህዝቦችን ብሶት ወልዶ ለርስ በርስ ግጭትና ጦርነት ዳርጎን ኖሯል። ግጭቱና ጦርነቱም ለአሰከፊ ድህነት አጋልጦን ዛሬም ድረስ ብንገፋው ብንገፋው አልነቃነቅ ላለ የኢኮኖሚ ቸግር ዳርጎናል። ብዝሃነት በሞላባት አገር አሀዳዊነትን ማስፈን ምን ያህል ለከፋ ችግር እንደሚያጋልጥም ከራሳችን ታሪክ ብዙ ተምረናል።
የብሄር ብሄረሰቦች መብት ረገጣና አፈናን በመቃወምም ኢትዮጵያውያን በአንድነት ታግለውና ክቡር የአካልና የህይወት መስዋዕትነትን ከፍለው ፌዴራለዊት ኢትዮጵያ እውን ማድረግ ችለዋል። ይሁንና ይህ ውድ መስዋእትነት የተከፈለለት ሥርዓት በጥቂቶቸ ፈሩን እንዲሰት ተደርጎ በስመ ፌዴራሊዝም የአጅ አዙር አነሃዳዊነት በህዝባችን ላይ ተጭኖ ቆይቷል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር ዓብይ አህመድ 14ኛውን የብሄር ብሄረሰቦች ቀን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክትም ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ሲገልጹ “የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ለእኩልነት፣ ለነጻነትና ለፍትሐዊነት ታግለዋል። ራስን በራስ የማስተዳደር፣ ባህልንና ቋንቋን የማበልጸግ መብት ለማግኘት መሥዋዕትነት ከፍለዋል።
ኢትዮጵያ ሁሉም እኩል መሥዋዕትነት ሲከፍሉባት የኖረች ሀገራቸው በመሆኗ ሁሉም እኩል የሚጠቀሙባት ሀገር እንድትሆን ከገዥዎች ጋር ተናንቀዋል።
ይህ የዘመናት ትግላቸው በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና አግኝቶ ራስን የማስተዳደር መብታቸው ተረጋግጧል። በተግባር ሲፈተሽ ግን የዘረጋነው ሥርዓት ትግላቸውን በተሟላ ሁኔታ የሚመልስ፣ መብታቸውንም በእኩልነት የሚያስከብር አልነበረም። አሐዳዊነት በፌዴራላዊነት ሳይሆን በእጅ አዙር አሐዳዊነት ተተካ።
ብሔረሰቦችን ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር እንዲችሉ የተመሠረቱት አብዛኞቹ ክልሎች በጡት አባቶች እንዲተዳደሩ ተደረጉ።
ክልሎች በተፈጥሮና ሰው በሠራሽ ሀብቶቻቸው የበዪ ተመልካቾች ሆኑ። ሀገር ለመምራት የሚፈቀድላቸውና የማይፈቀድላቸው ብሔረሰቦች ተፈጠሩ። የተወሰኑት ከበሮውን ሲመቱ ሌሎች አጋሮች ሆነው እንዲያጨበጭቡ ብቻ ተፈቀደላቸው።
በሕዝብ መራራ ትግል የሕዝቡን ሉዓላዊነትና መብት ለማስከበር የወጣው ሕገ መንግሥት እየተሻረ የጥቂቶች አገዛዝ መስፈን ጀመረ። ሰብአዊ መብቶች ተጣሱ፣ የዜጎች ክብር ጠፍቶ ኢትዮጵያ የጨለማ እሥር ቤቶችና የማሰቃያ ሥፍራዎች መናኸሪያ ሆነች።
የክልሎች መሬት ያለ እነርሱ ፈቃድ ለእጅ አዙር አሃዳውያን ተሸነሸነ። ሀብታቸውና ንብረታቸው ተመዘበረ፤ በየክልሉ የተዘረጉት ታላላቅ ፕሮጀክቶች የእጅ አዙር አሃዳውያን የምዝበራ ማዕከላት ሆኑ። ለምን? ብለው የጠየቁ ሁሉ ከአራዊት ጋር ታሠሩ፤ ተኮላሹ፤ እግርና እጃቸው ተቆረጠ፤ ከሀገር ተሰደዱ” ብለዋል።
ከዚህ አባባል የምንረዳው ሀቅ ቢኖር በኢትዮጵያ ህዝቦች መራራ ትግል የለውጥ አመራሩ ሥልጣኑን አስከያዘበት ጊዜ ድረስ ፌዴራሊዝም በስም አንጂ አካል ነስቶ በስጋ ኢትዮጵያ ውስጥ አለመኖሩን ነው።
ስለሆነም ዘንድሮ የተከበረው 14ኛው የብር ብሄረሰቦች ቀን እውነተኛ ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ የማስፈን ጅማሮ ላይ የተከበረ የመጀመሪያው በዓል ነው ብለን አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን።
አውነታው እንዲህ ባለበት ሁኔታ ጥቂት የፖለቲካ ቁማርተኞች የህዝቦች የትግል ውጤትን ቀምተው ፌዴራሊዝምን ለህዝቦች መጨቆኛና ለራሳቸው ስግብግብ ፍላጎት መጠቀሚያ ሲያደርጉት መቆየታቸውን ረስተው አሁን እውነተኛ ፌዴራሊዝም እውን በሆነበትና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከእንጀራ ልጅነት ወደልጅነት በተሸጋረበት ወቅት ፌዴራሊዝሙ ሊፈርስ ነው፤ አሃዳዊነት ሊነግስ ብለው ለማደናገር ሲሞክሩ ስናይ ይሉሽን በሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ የሚለውን ምሳሌያዊ ንግግር እንድናስታውስ ያደርጉናል።
መልካሙ ነገር መላ ኢትዮጵያውያን አገራችን ቀድማ የነበረችበትን እና አሁን በለውጡ አመራሩ የመጣውን ለውጥ ጠንቅቀው የተገነዘቡ መሆናቸው ነው። ለዚህም ነው ንፋስ አመጣሹን የውሸት ወሬ ወደጎን በመተው የበለጸገች እና አውነተኛ ፌዴራሊዝም የሰፈነባትን አገር እውን ለማድረግ ከለውጥ አመራሩ ጎን በመቆም ርብርባቸውን የቀጠሉት። ይህ አኩሪ ተግባራቸውም ጅምሩ ለውጥ ፍሬ እሰኪያፈራ ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አይጠረጠርም!
አዲስ ዘመን ህዳር 30/2012