የኅዳር ወር መጨረሻ የሆነው የትናንትናው ዕለት ለኢትዮጵያ፣ ለህዝቦቿና ለመሪዋ እንደማንኛውም ቀን ተራ ቀን አልነበሩም።
ይልቁኑ ለአገራቸውና ለጎረቤቶቻቸው ሰላም ላበረከቱት አስተዋጽኦ በዓለም መድረክ የከፍታን ማዕረግ የተጎናጸፉባት
ልዩ ቀን እንጂ! በዚህች ታሪካዊ ቀን የአፍሪካ ቀንድን ሰላም ለማረጋገጥ ኢትዮጵያውያኑ ላበረከቱት ጉልህ አስተዋጽኦ
በመሪያቸው በኩል የኖቤል ሽልማትን በዓለም ህዝብ ፊት በክብር ተረክበዋል!
እውነት ነው ለውስጥ ጉዳያችን ሁነኛ መፍትሄ ማስቀመጥ ተስኖን በዓለም ህዝብ ፊት የርስ በርስ ጦርነትና ግጭት መገለጫችን ሆኖ ብዙ ዘመን ገፍተናል።
ለፍትህና ዴሞክራሲ ታግለናል ብለን ስናበቃ በሰብዓዊ መብት ረገጣ የዓለም መዘባበቻ ሆነንም መቆየታችንም የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። መብታቸው በጠየቁና ልዩነትን ባንጸባረቁ ብዙዎች ለአሰቃቂ ግፍ ተዳርገው ጥፍራቸው ተነቅሏል፤ በገፍ ታስረዋል፤ ለአውሬ ተጥለውም ለመናገር የሚቀፍ የግፍ ቀንበርን ተሸክመው በብርሃናማዋ ኢትዮጵያ በጨለማ ኖረዋል።
የግፉ ጽዋ ሲሞላ ግን መላ ኢትዮጵያ ለነጻነትና ለፍትህ በሚደረጉ ትግሎች ዳር እስከዳር ተቀጣጥላ ቆይታለች። በዚህም ብዙ ኢትዮጵያውያን በተለይም ለጋ ወጣቶች አጅግ አስከፊ የሕይወትና የአካል መስዋዕትነት ከፍለዋል። መስዋዕትነታቸው ሜዳ ላይ ፈሶ ሳይቀርም በክቡር ደማቸው የለውጥ አመራርን ወልደው ለፍሬ አብቅተዋል። በትናትናው ዕለትም ለኖቤል ሽልማት የበቁት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድም የዚህ ትግል ፍሬ ናቸው።
የለውጥ አመራሩም አገሪቱን የመምራት ከፍተኛ ኃላፊነት ከተረከበበት ማግስት አንስቶ በአገር ወስጥ ለጎረቤት አገራትና ለአፍሪካ ሰላም፣ መረጋጋትና ዕድገት የሚበጁ በርካታ ሥራዎችን ለማከናወን ችሏል።
በርካታ እስረኞችን ከማጎሪያዎች ነጻ ማውጣት፣ የሰላም እና የህዝብ ለህዝብ መድረኮች ማካሄድ፣ አሳሪ ህጎችን ማሻሻል፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ተዓማኒ በሆኑ ግለሰቦች እንዲመሩ ማድረግና መገናኛ ብዙሃን ያለምንም አፈናና ጭቆና የሚሰሩበትን ሁኔታ ማመቻቸትን የመሳሰሉ ክንውኖች በአገር ውስጥ ከተሰሩ ጉልህ የለውጥ ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
ከጎረቤት ኤርትራ ጋር ለዘመናት የዘለቀውን ቁርሾና ግጭት ለማስቆምም የለውጥ አመራሩ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ዋነኛ ተዋናይነት የወሰደው ቁርጠኛ እርምጃ ለሁለቱ አገራት ህዝቦች ሰላምና እፎይታን ያጎናጸፈና የዓለምን ህዝብ ያስደመመ ታላቅ ክንውን ነበር።
ጎረቤት ሱዳን በሰላም እጦት በከፍተኛ ችግር ውስጥ በነበረችበት ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የወሰደው ግንባር ቀደም እርምጃና ይህንንም ተከትሎ የተገኙ ውጤቶች የለውጡ አመራር ከአገር አልፎ ለጎረቤት አገራት የተረፈ ስለመሆኑ የሚመሰክሩ ሁነኛ ማስረጃዎች ናቸው።
ትናንት በዓለም አቀፍ መድረክ ኢትዮጵያና መሪዋ ከፍ ያሉባቸው ዋና ዋና ምክንያቶችም ከላይ የተጠቃቀሱት ናቸው። ኢትዮጵያና መሪዋ ለሰላምና ለዕድገት ሰርተው እንዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ መሞገስና መሸለማቸው የአገራችንን ገጽታ በአዎንታዊ መልኩ ለመቀየር አስተዋጽዎ የጎላ ነውና ሽልማቱ አገራችንንና መሪዎቿን በከፍታ ሰገነት ላይ ያስቀመጠ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 1/2012