ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሰላም የኖቤል ሽልማት ማሸነፋቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ዝና በመላው አለም ናኝቷል። ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ይህን ታላቅ ዜና በየሀገሩ እና በየቤቱ አድርሰውታል።
ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኖርዌይ ኦስሎ በመገኘት ሜዳሊያውን በተቀበሉበት ወቅት ደግሞ ይህ የሀገሪቱ ዝና እና ታላቅነት ይበልጥ ተስተጋብቷል። የሽልማቱ አዘጋጆች እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለኢትዮጵያ ያደረጉት ንግግር ታሪካዊ ከመሆኑም በላይ የኢትዮጵያን ዘንተ ዓለምነት ሲያስተዋውቅ የሚኖር ነው።
ኢትዮጵያውያን በዚህ ታላቅ ክብር በእጅጉ ኮርተዋል። ሀገሪቱም በዚህ ሽልማት ገጽታዋ ይበልጥ ተገንብቷል። ይህ ደግሞ ለዘመናት ስሟ በተለያዩ ምክንያቶች ሲጠለሽ ለነበረች ሀገር ትልቅ ትርጉም አለው። እንደሚታወቀው ሀገሪቱ በድርቅ ፣ በርስ በርስ ጦርነት፣በአፈና ፣በሀገር ውስጥ መፈናቀል እና በመሳሰሉት ትታወቅ ነበር።
እነዚህ የቀድሞ ገጽታዎቿን ሰርታ መለወጥ ብትችልም የጠፋን ስም በሚገባ አድሶ ከስሙ ጋር ተያይዞ የታጣውን ጥቅም ማስመለስ ግን ብዙ ጊዜ ይወስዳል። አሁን በሽልማቱ ሀገሪቱ እንደ አዲስ መተዋወቋ በቀጣይ በቱሪዝም፣ በኢንቨስትመንት እና በመሳሰሉት ወደፊት ለመራመድ ለተያያዘቻቸው ተግባሮች ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል።
እንደሚታወቀው ሀገሪቱ በኢንቨስትመንቱ መስክ ብዙ እየተራመደች ትገኛለች። በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከአፍሪካ ቀደምት አምስት ሀገሮች አንዷ መሆን ችላለች። ይህ ማለት ግን በአለም አቀፍ ደረጃ ካለው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የሚገባትን ድርሻ አግኝታለች ማለት አይደለም። አሁንም ጠንክሮ በመስራት እነ አሜሪካ ቻይና እና የመሳሰሉት ሀገሮች ጭምር የሚረባረቡበትን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል።
ይህ ሽልማት ይህን ኢንቨስትመንት ለመሳብ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል። ኢትዮጵያ በሰላም የኖቤል ተሸላሚ መሆኗ በተለይ ሰላምና መረጋጋትን በጽኑ ለሚፈልገው ለዚህ ኢንቨስትመንት መጨመር የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም።
ሀገሪቱ በወጪ ንግድ ብዙ ርቀት መጓዝ ትፈልጋለች። ይህ ደግሞ የነበረውን ደንበኛ ለማቆየትም ሆነ አዳዲሶችን ለመሳብ ሰፊ የማስተዋወቅ ስራ ማድረግን ይፈልጋል፤ በቱሪዝም እና በሌሎች መስኮችም ተመሳሳይ ስራን ማከናወን ያስፈልጋል። ይህን ሽልማት በመጠቀምም የወጪ ንግዱን ከገባበት ማጥ ማውጣት ከቱሪዝሙም የሚፈለገውን ገቢ ለማግኘት መስራት ያስፈልጋል።
ሀገሪቱ በአለም አቀፍ ደረጃ ካለው ገበያና ከመሳሰለው ተጠቃሚ እንድትሆን አንዱ የሚያስፈልገው የማስተዋወቅ ስራ ነው። ማስተዋወቅ ደግሞ ከፍተኛ ሀብት ይጠይቃል። እንደ ኢትዮጵያ ያለ ድሃ ሀገር ደግሞ ይህን ለማድረግ ይቸገራል። ሽልማቱ የሰራው ማስታወቂያ በብዙ ሚሊዮን ብር የሚገመት እንደመሆኑ በሁሉም ዘርፍ ለመስራት ብረትን እንደ ጋለ ነው መቀጥቀጥ እንደሚባለው ይበልጥ የመንቀሳቀሻው ጊዜ አሁን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
ባለፉት ዘመናት የተሰሩ ታሪኮች ለሀገራችን እድገትና ሰላም የራሳቸውን ሚና እንደሚጫወቱ ይታመናል። ሽልማቱ የእዚህ ታሪክ አካል ሆኖ ይሄዳል፤ ዋናው ግን አሁን የምንሰራው እንደመሆኑ ሽልማቱን እየጠቀስን ብቻ የምናገኘው ውጤት ብዙም አያሻግረንም። ከሽልማቱ የሚጠቅመንን እየወሰደን መሰራት ላይ ማተኮር ይኖርብናል። ለእዚህም ሽልማቱን አንደ አንድ ካፒታል በመጠቀም ለመስራት ርብርብ ማድረግ ይኖርብናል።
ሽልማቱ የሚለግሰውን ለግሶ አልፏል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታይ ተመሳሳይ መድረኮች በየጊዜው ይደረጋሉ። ኢትዮጵያ ሽልማቱ ያመጣውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በየዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን በትኩረት መስራት ይጠበቅባታል። ከዚህ በኋላ ሽልማቱን እየጠቀስን መኩራራት አይኖርብንም። ይልቁኑ ሽልማቱን እንደ አንድ ካፒታል በመጠቀም ልማታችንን ማጠናከርና ሰላማችንን ዘላቂ ማድረግ ግድ ይለናል።
በእነዚህ ላይ አተኩረን በሰራን ቁጥር ሀገሪቱን ከማሳደግ በተጓዳኝ ሌሎች ተመሳሳይ ሽልማቶችን እናገኛለን። በመሰረቱ ሀገሪቱ ለዚህ ሽልማት የበቃችው በሀገር ውስጥ ባከናወነችው ተግባር ነው። አሁን ሀገር ውስጥ በሰላም ዘርፍ ማከናወን ያለብንን ማከናወን ይኖርብናል።
የህግ የበላይነት በማስከበር ሰርቶ ተጨባጭ ተግባር ማሳየት ያስፈልጋል። በኢትዮ ኤርትራ መካከል ለሁለት አስርት አመታት ዘልቆ የቆየውን የጦርነት ታሪክ መቀየር እንደተቻለው ሁሉ በሀገራችን እዚህም እዚያም እየተቀሰቀሰ የዜጎችን ህይወት ሲቀማ፣ሲያፈናቅል ለቆየው ግጭት ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት ይገባል። ሀገሪቱ በኢኮኖሚው መስክም በተለይ የወጪ ንግዷ ተቀዛቅዞ ቆይቷል። አሁን ሽልማቱ በራሱ የከፈተውን በር በመጠቀም በወጪ ንግዱ ላይ ለመስራት የዲፕሎማሲ ስራው ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 7/2012