መግቢያ
ቀን የጣላቸው አሊያም ከጊዜ የተጣሉ የሚመስሉ በርካታ ሰዎች በእኚህ ሴት ዙሪያ ተኮልኩለው አንደበታቸው በመጠጥ ኃይል ተይዞ ‹‹ነይ ቅጂ›› ይላሉ። ሌሎች ደግሞ 50 ሣንቲም ጎድሎብኛል ነገ አመጣለሁ እባክሽ አንድ መለኪያ አረቄ ቅጂልኝ እያሉ በተማፅኖ ይጠይቃሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ ዓይናቸው እየተንከራተተ ቁጭ ብለው የሚጠጡ ሰዎችን ጋብዙን ስሜት ከወዲህ ወዲያ ይቀላውጣሉ። ጥቂቶች ደግሞ እስኪ ጠጡ እንያችሁ ከልኩ አታልፉ፤ ሰው እንደሆነ ቢበላ ቢጠጣ ነገም ያው ነው በሚል የትዝብት ዕይታ ከወዲህ ወዲያ ይንከላወሳሉ። አልፎ ሂያጁ ደግሞ አይ ኑሮ እያለ ገልመጥ እያደረገ ያልፋቸዋል።
ለነገሩ አዲስ የሆኑ ሰዎች ደግሞ ቆም ብለው ነገሩን በአንክሮ ይመለከታሉ። ጥቂቶቹ ደግሞ ከመንገዱ ዳር አረፍ ብለው ሁኔታውን ይቃኛሉ። ከሕይወቱም ሊቋደሱ አንድ መለኪያ አረቄ ቀመስ አድርገው ከሰዎቹ ዘንድ ይቀላቀላሉ። በመሠረቱ በእንዲህ ዓይነት ቦታ ሰዎች ለመተዋወቅ ቅርብ ናቸው። ለሃሜትና ምሬትም እንዲሁ። ጥርስ የማያስከድኑ ተጫዋቾች እንዳሉ ሁሉ፤ በቅፅበት በንግግራቸው አስቀያሚ ቃላትን ወርውረው ከስፍራው ሰዎችን የሚያርቁም በርካታ ናቸው።
መሰል ቦታዎች ሁሉም ዓለም፤ ሁሉም ቀለም ያለበት ስፍራ ነው- የመንገድ ዳር መሸታ። ይህን የመንገድ ዳር መሸታ ብዙም የተለመደ ባይሆንም በአሁኑ ወቅት ግን በርካቶች ሕይወታቸውን ለማሸነፍ ሲሉ እየተለማመዱት በሂደትም የኑሮ መሠረታቸው አድርገውታል። በዚህ የኑሮ ዘይቤ ሕይወታ ቸውንና ቤተሰባቸው ለ20 ዓመታት የመሩት ወይዘሮ ብዙነሽ ገብረመስቀል የዛሬ እንዲህም ይኖራል አምዳችሁ እንግዳ ናቸው።
ስንብት
ወይዘሮ ብዙነሽ ገብረመስቀል ዕድሜ ያቸውን የሚያሰሉት እቴጌ መነን በሞቱ ጊዜ ተወልጄ አራስ እንደነበርኩ እናቴ ነግራኛለች በማለት ነው። በዚህም አቆጣጠር 60 ዓመት ሞልቶኛል ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት የሚኖሩት ደብረሊባኖስ ገዳም ከፍ ብሎ ጫገል ከሚባለው ስፍራ ነው። ወደዚህ ከመምጣታቸው በፊት አቦቴ የሚባል ቦታ እየኖሩ ነበር። አግብተውም ወልደው በሰፈሩም ጥሩ ሕይወት ነበራቸው። ግን ከዕለታት በአንዱ ቀን ችግር ገጠማቸው። ጤናቸው ታወከ። የተለያዩ ባህላዊ ህክምናዎችንም ቢሞክሩ ጤናቸው በዋዛ ሊመለስ አልቻለም። ታዲያ በዚህ ጊዜ ወደ ፀበል ልሄድ ብለው ወደ ደብረሊባኖስ ገዳም አቀኑ። ጤናቸውም ወደ መደበኛ ስፍራው ተመለሰ። ከዚያ ወደ ሰፈራቸው ሲመለሱ ያማቸዋል። ወደ ጸበሉ ሲመጡ ግን ይሻላቸዋል። ከዚያ የኖሩበትን ቀዬ ትተውት በዚሁ ኑሮ መሰረቱ። በወቅቱ በጀርባቸው አዝለውት የመጡት ልጃቸው ዛሬ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነው። በመንገድ ዳር መሸታ አራት ወንድ ልጆች እና ሁለት የልጅ ልጆችንም ያስተዳድራሉ። እናም ኑሮ እንደ እሳት እየለበለበን እዚህ ደርሰናል ይላሉ ወይዘሮ ብዙነሽ የኑሮን ውጣ ውረድ እንዴት እንደፈተናቸው ሲናገሩ።
ከ20 ዓመት በፊት ወደዚህ ስፍራ መጥተው ቤት ሲከራዩ አምስት ብር ይከፍሉ ነበር። ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ደግሞ ስድስት ብር ሆነ። ከዚያ ደግሞ አስር ብር ገባ። አምስት ዓመት ቆይቶ 20 ብር ገባ። እያለ እያለ 70 ብር ገባ። በአሁኑ ወቅት 400 ብር የቤት ኪራይ ይከፍላሉ። በዚህ ሁኔታ ውስጥም አንድም የሚያግዛቸው አካል አለመኖሩ ኑሮ ይፈትናቸዋል። ባለቤታቸውም የአልጋ ቁራኛ ከሆኑ ሰነባብተዋል።
ፈተናዎች
አረቄ ሲያወጡ እስከ ምሽት ሰባት ሰዓት ይቆያሉ። ጥዋት 11 ሰዓት ተነስተው ቤታቸውን ያዘገጃጃሉ። ጠዋት ቤት እየሰሩ ይቆዩና ስድስት ሰዓት ወደ መንገድ ዳር ይወጣሉ። ማታ ደግሞ እስከ አንድ ሰዓት በዚያው ይቆያሉ። ጥሩ ገበያ ያገኙ ቀን 50 ብር ይሸጣሉ። በዚህ 20 ዓመት ውስጥ በዚህ ሥራ ውስጥ ሆነው የማይረሱት ትዝታ አብሯቸው አለ። ከ20 ዓመት በፊት አንድ ሙሉ ጠርሙስ አረቄ ይሸጡ የነበረው በአንድ ብር ከሃያ ሳንቲም ነው። ከዚያ በኋላ ግን ዋጋው እየጨመረ ሲመጣ ሁለት ብር ገባ። ይህ እየጨመረ መጥቶ አሁን 60 ብር ገብቷል። የኑሮ ውድነቱን እያሰሉ እጃቸውን ከአፋቸው ላይ ጭነው በአግራሞት ከአንዱ ዘመን ወደ ሌላው ዘመን በትዝታ ይወረውራሉ- አይ ኑሮ እያሉ። በዚህ ሥራ ስድስት ቤተሰብ ይመራሉ። በዚህ ኑሮ ሠካራም እያንጓጠጠ፣ ኑሮ ወገባቸው እያጎበጠ ይኸው ከዛሬ ደርሰዋል። ግን አሁንም ቢሆን ፈተናውን ለማሸነፍ ሲሉ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። በዚህ ጥረት ውስጥ የኑሮ አስከፊነቱንና ውጣ ውረድ እየተመለከቱ ዛሬም እንዳለሁ አለሁ ይላሉ።
ደንበኛ ፍለጋ
ደንበኛ ለማግኘት በርካታ ውጣ ውረዶች እንዳሉት ነው የሚናገሩት። በአሁኑ ወቅት ይህ ነው የሚባል ቋሚ ደንበኛ የላቸውም። ግን አላፊ አግዳሚው ሆዱንም ሲያመው አንድ መለኪያ አረቄ በሶስት ብር ሸምቶ ቀምሶ ይሄዳል። ደንበኛ ኖሮኝ ልጆቼንና ቤተሰቦቼን እለውጣለሁ ብዬ ተስፋ አድርጌ አላውቅም። ግን ደግሞ ታሪክ እየተለወጠ ይኸው ከዛሬ ደረስን ይላሉ።
ወይዘሮ ብዙነሽ ዱሮ ጥጥ እየፈተሉ ኑሯቸውን ለማሸነፍ ብዙ ጥረት አድርገዋል። አሁን ግን ሁሉ ነገር ተለውጦ ሽመናው ሁሉ በማሽን የሚሰራ በመሆኑና ሥራውም ስለዘመነ ፈትላቸውን የሚገዛ ሰው አላገኙም። ታዲያ በዚህ የተነሳ ጥጥ መፍተሉን እርግፍ አድርገው ትተውታል። ወዲህ ደግሞ ቋሚ ደንበኛ ባለመኖሩ የዕለት ገቢያቸው በሚገባ መገመት አይችሉም። ግን ተጠቃሚ እንዲመጣላቸው ማለዳ ከመኝታቸው ሲነሱ ቀዳሚ ፀሎታቸው አምላኬ አንተ ታውቃለህ የሚለው ነው።
የሆነው ሆኖ አንዳንድ ተጠቃሚዎች አረቄ መንገድ ዳር በማግኘታችን ደስተኛ ነን፤ ምግብ ብትሰሩ እንበላ ነበር ይሏቸዋል። ሌሎች ደግሞ እንዴት ከመንገድ ዳር አረቄ ትሸጣላችሁ፤ይህ ፀሐይ ላይ የሚሸጥ መጠጥ አይደለም። ልጆችም ይህን መጠጥ ይለምዱታል አዕምሯው ያቃውሳል ብለው ይገስፃሉ። ወይዘሮ ብዙነሽ ግን ደንበኛ ፍለጋ ሁሉንም ነገር እሺ ብለው በትዕግስት ያልፉታል።
የዘመድ ነገር
እርሳቸውን ሥራዬ ብሎ የሚጠይቃቸው ሰው የለም። ምናልባት ከሌላ ቦታ ታመው የሚመጡ ሰዎች ወደ እርሳቸው ዘንድ ጎራ ብሎ የችግር ጊዜው ያሳልፉ ይሆናል እንጂ ዘመድ አለኝ ብሎ የሚመጣ ሰው እምብዛም እንደሌለ በትካዜ ይናገራሉ። በዚህም የተነሳ ከሰዎች ጋር ያላቸው ማህበራዊ ህይወት የተገደበ መሆኑን ይናገራሉ። አንድም ከእጃቸው ላይ በቂ ገንዘብ ስለማይኖር በሚፈልጉት ጊዜ ወደፈለጉት ቦታ መንቀሳቀስ ይከብዳቸዋል። ወዲህ ደግሞ የአልጋ ቁራኛ የሆነው ባለቤታቸውን ትተው ወደየትም ርቀው መሄድ አይችሉም። በዚህ ደግሞ እናት አባታቸው የሌሉ ሁለት የልጅ ልጆችን እያሳደጉ ነው። በሌላ ጎኑ ደግሞ የቤተሰቡን ጣጣ ለመሸፈንና የዕለት ጉርስ ለማዳረስ በየቀኑ ከመንገድ ዳር ሆነ የኑሯቸው መሰረት የሆነውን አረቄ መሸጥ ይጠበቅባቸዋል። ታዲያ የእነዚህ ነገሮች መደራራብ ማህበራዊ ሕይወታቸው የተገደበ እንዲሆን አድርጎታል። የሆነው ሆኖ ፈጣሪ እንደፈቀደው እያኖረኝ ነው ይላሉ።
ተስፋ
እኚህ እናት የጤና መታወክ ገጥሟቸው ጥለውት የመጡት ደጅ ይናፍቃቸዋል። ተድረው፤ ተኩለው ያደጉበት መንደር በት ዝታ ውል ይልባቸዋል። ግን እነዚህ ሁሉ ችግ ሮች አልፈው ወደ ቤቴ ተመልሼ ከጎረቤቴ ጋር ቡና ጠጥቼ፣ ሸጋ ጨዋታ ተጫውቼ እኖ ራለሁ የሚለውን በሙሉ እርግፍ አድርገው ትተውታል።
ወይዘሮ ብዙነሽ ገብረመስቀል አሁን ተስፋ የሚደርጉት ነገር አንድ እና አንድ ነገር ብቻ ነው። ይህም ልጆቻቸው ከተሻለ ቦታ ደርሰው ከመንገድ ዳር ወደ ቤት ገብተው ኑሯቸው የተቃና የሚሆንበት ጊዜ እንዲመጣ ይመኛሉ። ተስፋውን ከፈጣሪ ቀጥሎ በልጆቻቸው ላይ ጥለዋል። እኛም ‹‹እንዲህም ይኖራል›› ብለን ስናበቃ ምኞታቸው እውን ይሆን ዘንድ ምኞ ታችን ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 4/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር