የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስቴር ዶክተር አብይ አህመድ ላደረጉት የሰላም አበርክቶ የዘንድሮው የሰላም ኖቤል ተሸላሚ መሆናቸውን ተከትሎ ባሳለፍነው ሳምንት ማክሰኞ የኖቤል ሽልማት ድርጅት ዋና ፅህፈት ቤት መገኛ በሆነችው የኖርዌ ርእሰ መዲና ኦስሎ በማቅናት የተዋጣለት በተባለና ባማረ ዝግጅት ሽልማታቸውን ተረክበዋል።ሽልማታቸውን ከተቀበሉ በኋላም ለሰላም ሊከፈል ስለሚገባ ዋጋ ስሜት ኮርኳሪ ንግግር አድርገዋል።በተለይም “ሰላም እንደ ዛፍ ችግኝ ነው፤ ችግኝን ተክሎ ለማሳደግ እንክብካቤ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ሰላምም ጥሩ ልብ እና እንክብካቤ ያስፈልገዋል” ሲሉ የተናገሩት ንግግር የአብዛኛዎቹን ታዳሚ ቀልብ ስቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማቱን የተቀበሉት በሀገራቱ መካከል ሰላም እንዲመጣ ዋጋ በከፈሉ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ስም እንዲሁም ለኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ስምምነት ቁርጠኛ በነበሩት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ስም መሆኑን ሲገልፁም የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ለሰላም መረጋገጥ ያሳዩትን ቁርጠኝነት ባከበረ መልኩ ነበር።ታዲያ ጠቅላይ ሚንስትሩ በዚህ ቀልብ ሳቢ ንግግራቸው የመላው ኢትዮጵያውያንን ቀልብ ብቻ ሳይሆን የዓለምን ትኩረትም ለመሳብ ችለዋል።
በኖርዌ የተካሄደው ይህ የሽልማት ሥነሥርዓት በረሃብና ድርቅ፣ በስደትና መፈናቀል፣ በግጭትና ጦርነት ጋር የምትታወቀውን ኢትዮጵያ ዓለም በሌላ ገፅታዋ እንዲመለከታት አድርጓል።ኢትዮጵያ የጀግና ሀገር፣ ለቅኝ ገዢዎች እጅ ያልሰጠች የጥቁር ህዝብ መናገሻ፣ የሰው ልጅ ዱካ ለመጀመሪያ ጊዜ ያረፈባት ምድር መሆኗን የዓለም ህዝብ እንዲያውቀው የተደረገበት ታሪካዊ መድረክም ሆኗል።በአጭሩ መድረኩ ኢትዮጵያ በዓለም ዙሪያ ስሟ እንዲገን አስተዋፅኦ አበርክቷል።
ከመነሻውም በጠቅላይ ሚንስትሩ የኖቤል ሽልማት ተገቢነት ላይ አንዳንድ ክርክሮች የነበሩ ቢሆንም አብዛኛዎቹ ግን በሽልማቱ ተገቢነት ላይ አመዝነው ቆይተዋል ማለት ይቻላል።በመጨረሻው የሽልማት መርሃግብርም በዶክተር አብይ የኖቤል ሽልማት ተገቢነት ዙሪያ ኦስሎ ሁለት ገፅታን አስተናግዳለች።አንዱ የዶክተር አብይ የኖቤል ሽልማት ተገቢ ነው የሚል ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ሽልማቱ አይገባቸውም የሚል ነበር።ይህም በድጋፍና የተቃውሞ ሰልፎች ታጅቦ አምሽቷል።
በኦስሎ ማምሻውን በርካታ ኢትዮጵያውያን የዶክተር አብይን የኖቤል አሸናፊነት ተገቢ ነው በሚል ደስታቸው እርሳቸው ባረፉበት ሆቴል ፊትለፊት በመገኘት ገልፀዋል።ድጋፉ በኤርትራውያንም ጭምር ታጅቧል።በሌላ በኩል ደግሞ ጥቂት ኤርትራውያን ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ሰላም አመጡ እንጂ በኤርትራ በኩል ያለውን ሰላም ስላልፈቱ ሽልማቱ ለእርሳቸው አይገባም በሚል የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል።ይሁንና የጠቅላይ ሚንስትሩን መሸለም ለመደገፍ የወጡትን በርካታ ኤርትራውያንን መዝንጋት የማይገባ በመሆኑ ተቃውሞው መላው የኤርትራ ህዝብን ይወክላል ማለት አይደለም።በተመሳሳይ ጥቂት ኢትዮጵያውያንም ‹‹በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ የለም ሽልማቱም ለጠቅላይ ሚንስትሩ አይገባም›› ሲሉ ተቃውሟቸውን ገልፀዋል።
በሰላማዊ ሰልፍ ሃሳብን በነፃነት መግለፅና ተቃውሞ ማሰማት የሁሉም ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብት በመሆኑ ሁሉም ሀገራት ይህን መብት በህገ መንግስታቸው ውስጥ በማካተት ዜጎቻቸው ይህንን መብት እንዲጠቀሙበት አድርገዋል።ይህንኑ መብት በመጠቀምም ጥቂት የማይባሉ የዓለም ሀገራት ህዝቦች የመንግሥታቶቻቸውን ህግና ፖሊሲዎች ከማስቀየር አንስቶ መሪዎቻቸውን ከስልጣን እስከማውረድ ደርሰዋል።
ይህን መብት ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ታዲያ ሁሉም ልብ ሊለውና ሊያጤነው የሚገባው ጉዳይ ቢኖር ተቃውሞ ሁሉ የፈለጉትን ከማድረግ ወደኋላ አይጎትትም ማለት አይደለም።ይልቁንም በመቃወም ሂደት ውስጥ ሰላማዊነትን፣ ምክንያታዊነትንና እውነተኛነትን መከተል የግድ ይላል።ሰዎች በምክንያታዊነት፣ በሰላማዊና በእውነት መንገድ ያልተስማማቸውን ጉዳይ ሲቃወሙ ማሸነፍ ይችላሉ።ማሸነፍ ባይችሉም እንኳን ለሌሎች አሸናፊዎች በር የመክፈት እድል ያገኛሉ።ከዚህ በተቃራኒ ግን ሰዎች ያለ በቂ ምክኒያትና ተጨባጭ ማረጋገጫ በሰላማዊ መንገድም ቢሆን አንድን ጉዳይ ቢቃወሙ ውጤቱ ትርጉም አልባና ፍሬ ቢስ ይሆናል።እንደው ለይስሙላ ካልሆነ በስተቀር ሰው ያደረገው ሁሉ አይቅርብን ከሚል ምክንያት በዘለለ ተቃውሞው ውሃ የሚቋጥር አይደለም።እንዲህ አይነቱ ተቃውሞ ብዙ ግዜ የሚደረገውም የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ለመሳብና ተቃውሞ የደረሰበት የመንግስት አካል ክብሪት እንዲጭር ለማድረግ ካልሆነ በስተቀር ተቃውሞው ቋሚ መሰረት የለውም።ወይንም ደግሞ የተወሰነ አካል ተላላኪ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም።
እንዲህ አይነቱ ምክንያት የሌለው ተቃውሞ በተለይም የማህበራዊ ድረገፆችን በመጠቀምና ልክ የእነሱ ወገን የተነካ አድርጎ በማቅረብ ህዝብ በተሳሳተ አቅጣጫ በመንግስት ላይ እንዲነሳሳና እምነቱም እንዲሸረሸር የማድረጊያ አንዱ ስልት ተደርጎም ይቆጠራል።ይኸው ክስተትም ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኖቤል ሽልማታቸውን በኦስሎ በተቀበሉበት ወቅት ታይቷል።ከዚሁ ጎን ለጎንም ለተቃውሞው አፀፋ የድጋፍ ሰልፍ በተመሳሳይ ተደርጓል።
ሌላውና ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ቢኖር ተቃውሞ በምክንያት እንደሚደረግ ሁሉ ድጋፍም በምክንያት ሊሆን ይገባል።ማንም ሰው አንድን ጉዳይ የመደገፍ መብት እንዳለው ሁሉ አንድ የህብረተሰብ ክፍል የሆነ መሪውን ወይም የመንግስትን ውሳኔን በመደገፍ በደስታ ጦዞ አደባባይ ስለወጣ ብቻ ሁሉም በግብታዊነትና በመከተል የድጋፉን መቀላቀል አይጠበቅበትም።ምንም የማያወላደው ጉዳይ ግን ብዙሃኑን የሚያግባባ፣ ሁሉም የሚያውቀውና ምክንያታዊ በሆነ ጉዳይ ላይ ግን ድጋፍ ማድረግ ተገቢና እንደውም ሊበረታታ የሚጋባ ነው።
የጠቅላይ ሚንስትሩን የኖቤል ሽልማት አስመልክቶ በኖርዌ የድጋፍ ሰልፍ እንደተደረገ ሁሉ ጠቅላይ ሚንስትሩን በመቃወም የወጡ ሰልፈኞችንም ለመቃወም የተደረጉ ሰልፎች ታይተዋል።ዞሮ ዞሮ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ግን የድጋፍ ሰልፎች እንዳሉ ሁሉ የተቃውሞ ሰልፎችም ይኖራሉ።ይህ ደግሞ ሁሌም የሚጠበቅና የሚደረግ ተግባር ነው።ይሁን እንጂ ሰልፎች በድጋፍም ሆነ በተቃውሞ ሲደረጉ በምክንያት ሊሆኑ ይገባል።አንዱ የስልጣኔ መለኪያ ነገሮችን በአመክንዮ መደገፍና መቃውም ነውና!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 4/12
አስናቀ ፀጋዬ