መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራባቸው ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ ማድረግ ነው፡፡ እነዚህ መብቶች ህገመንግሥታዊ ነፃነቶች ሆነው የታወጁ ቢሆንም፤ባለፉት ጊዜያት ሲጣሱ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ጥሰቱ በህግ ማዕቀፍ ሳይቀር ተደግፎ መቆየቱም ሃቅ ነው፡፡
መንግሥት በዚህ ሂደት ውስጥ ቀደም ሲል የወጡትንና በሥራ ላይ ያሉትን የምርጫ ህግ፣ የጸረ ሽብር ህግ፣ የመረጃ ነጻነትና የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ፣ የበጎ አድራጎት ማህበራት አዋጅና ሌሎችንም ህጎችና አዋጆች ፈትሾና መርምሮ ለሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት የማሻሻያ ሃሳብ እንዲያቀርብ የህግና ፍትህ አማካሪ ጉባኤ በጠቅላይ አቃቢ ሕግ ተቋቁሟል፡፡
ጉባኤው በተመረጡ ባለሙያዎች ያለአንዳች ክፍያ ነጻ አገልግሎት እንዲሰጡ የተሰየሙበትና የተስማሙበት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ በሙያ መንግሥትንና ህዝብን በነጻ ማገልገል መልካም ጅምር ነው፡፡ ይህ በሌሎችም ስራዎች አርዓያ የሚሆን ተግባር ነው፡፡
ይህ ጉባኤ ሥራውን ከጀመረ እስካሁን ድረስ የበጎ አድራጎት ማህበራትን የሚመለከተውን ህግ ሙሉ በሙሉ አይቶና ፈትሾ፤ የማሻሻያ ሀሳብም አቅርቦ በጠቅላይ አቃቢ ህግ በኩል ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡ ካውንስሉ በቅድሚያ ያየው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ህግ በአገራችን ቀደም ሲል የነበሩትንም ሆነ አዲስ የሚቋቋሙትን የበጎ አደራጎት ድርጅቶች ከገንዘብ ጀምሮ በሁሉም አቅጣጫዎች አቅም የሚገድብና የማያሰራ እየተባለ የሚተች ነበር፡፡ ከዚህም አልፎ ድርጅቶቹ ከልማትና ከድጋፍ ውጪ በየትኛውም ህዝብን የማስተማርና የማሳወቅ ሥራ ላይ እንዳይሳተፉ ይደነግጋል፡፡ በዚህ ህግ ሰበብም የህዝቡ የማወቅ መብት በመገደቡ አሰራሩ እንደ አንድ የሰብዓዊ መብት ጥስት ሲታይ ቆይቷል፡፡ ስለሆነም መሻሻሉ ለፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ጠቃሚ ነው፡፡
በሌላ በኩል በጉባኤው ተፈትሸው የማሻሻያ ሃሳብ እንዲቀርብባቸው ከተያዙት ህጎች/አዋጆች መካከል የምርጫ ህጉ እና የመረጃ ነጻነትና መገናኛ ብዙኃን ህግ ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ህጎችም ባለፉት ዓመታት መንግሥት የህዝቡን መብት ለመገደብና የራሱን የስልጣን ጊዜ ለማራዘም ሆን ብሎ ያጸደቃቸው ህጎች ናቸው ተብለው ይጠቀሳሉ፡፡ በእነዚህ ህጎች መሰረትም ብዙዎች ተከስሰዋል፤ ታስረዋል፤ እልፍ ሲልም አገር ጥለው ተሰድደዋል፡፡ በአገር ውስጥ ከሚገኙ የፖለቲካ ተፎካካሪዎች አንስቶ በውጭ እስከሚገኙ የመብት ተሟጋቾች ድረስ በህጎቹ ላይ ተቃውሞ ሲሰነዘር ቆይቷል፡፡ በዚህም ህጎቹ ህገመንግሥታዊ ነጻነቶችን ገድበው የፖለቲካ ምህዳሩን አጥብበውታል፡፡ ማጥበብ ብቻ ሳይሆን በስልጣን ላይ ላለው መንግሥት ጥቅም ብቻ እንዲሆን ወስነውታል በሚልም ይተቻሉ፡፡ እነዚህም ህጎች ማሻሻል ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ከማስቻልም በተጨማሪ የፖለቲካ ምህዳሩ ለሁሉ እኩልና ምቹ እንዲሆን በማድረግ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የተሳካ እንዲሆን ይጠቅማሉ፡፡
መንግሥት ይህንን ጉባኤ ሲያቋቁምና ህጎችን ለማሻሻል ሲነሳ አላማው የህዝቦች ህገመንግሥታዊ መብት እንዲከበር ማድረግ ነውና ማሻሻያዎቹም የመንግሥትን የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት ፍላጎት የሚመልሱ፤ የህዝቡንም ነጻነት የሚያስከብሩ መሆን አለባቸው፡፡በተለይ መጪው ጊዜ አገራዊ ምርጫ የሚካሄድበት ወቅት በመሆኑ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለስጋት የሚንቀሳቀሱበት፤ የበጎ አድራጎትና የሲቪክ ማህበራት ህዝቡን የሚያነቁበትና የሚያስተምሩበት፤ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችም የሙያ ስነምግባርና ህገመንግሥቱን አክብረው ግዴታቸውን የሚወጡበትን ሁኔታ ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል፡፡
እነዚህ ማሻሻያ እንዲደረግባቸው የቀረቡት ህጎች ሁሉም በፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ ላይ ያላችው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡ በአንድ በኩል፤ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በሌላ በኩል ህብረተሰቡን አላላውስ ያሉ ህጎችን ፈትሾ ማሻሻል ደግሞ ትልቅ ጥቅም እንዳለው ይታሰባል፡፡ በመንግሥትም ሆነ በህዝቡ በኩል በትልቅ ተስፋም ይጠበቃል፡፡ እናም በጉባኤው ውስጥ የተሳተፉት ባለሙያዎች በነጻ በሚሰጡት ግልጋሎት የሚያቀርቧቸው የህግ ማሻሻያ ሀሳቦች የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ሁሉም ወገኖች እንደልብ የሚንቀሳቀሱበት እንዲሆን ይረዳሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ መሆንም አለበት፡፡
ማሻሻያው ቀደም ሲል መንግሥት የፖለቲካ ምህዳሩን አጥብቦ ለራሱ ብቻ አድርጎታል ተብሎ የሚታማበትን ከመሰረቱ ይቀይረዋል፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩ ሲሰፋም መሰረታዊው የዜጎች ህገመንግሥታዊ ነፃነትና መብት የማስከበሩ ጉዳይ እውን ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/20111