አዲስ አበባ፡- ለአዲስ አበባ ከተማ የቀላል ባቡር ትራንስፖርት ድጎማ ለማድረግ ቃል በተገባው መሰረት ተግባራዊ አለመደረጉን ኮርፖሬሽኑ ገለጸ፡፡ የኮርፖሬሽኑ ድጎማ ይከፈለኝ ጥያቄ ተጠንቶ ለሚመለከተው የውሳኔ ሀሳብ መቅረቡን ባለሥልጣኑ አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተፈራ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ የአዲስ አበባ ከተማ የቀላል ባቡር ትራንስፖርት ታሪፍ ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጸር በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ መንግሥት የህብረተሰቡን የመክፈል አቅም በማገናዘብ ታሪፉን ሁለት፣አራት እና ስድስት ብር ያደረገው የከተማውን የትራንስፖርት ተጠቃሚ ህብረተሰብ ለመደጎም በማሰብ ነው፡፡
ታሪፍ ዝቅተኛ ሆኖ ከተተመነባቸው ምክንያቶች አንዱ ከአዲስ አበባ መስተዳድር ጋር የተደረሰው የድጎማ ስምምነት መሆኑን ጠቅሰው፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት በየዓመቱ 1.5 ቢሊዮን ብር መክፈል ቢጠበቅበትም እስካሁን አልከፈለም፡፡
አቶ ደረጀ እንደገለፁት፤ የቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱ ወደ ሥራ ሲገባ 41 ባቡሮችን ይዞ ነበር፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን አገልግሎት የሚሰጡት ከ22 እስከ 26 የሚሆኑት ሲሆኑ፤ ሌሎቹ ቆመዋል፡፡
የከተማው መስተዳድር የቀላል ባቡር ትራንስፖርት ዘርፉ ወደሥራ ከመግባቱ በፊት በየዓመቱ 1.5 ሚሊዮን ብር ኮርፖሬሽኑን ሊደጉመው ስምምነት ላይ የተደረሰ ቢሆንም እስካሁን አንድም የተደረገ ድጎማ የለም፤ ይህም በሥራው ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል፤ በማለት የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ የቀላል ባቡር ትራንስፖርቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ በመለዋወጫ እጥረት የቆሙት ባቡሮች ወደሥራ እንዲገቡ፣ የባቡሮቹ ቁጥር እንዲጨምርና መስመሩም እንዲራዘም ገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የመንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ምክትል ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ፤ ኮርፖሬሽኑ ድጎማው ይከፈለኝ ብሎ ጥያቄ አቅርቧል፤ እኛም ምን ያህል መከፈል እንዳለበት ከነልዩነቱ አጥንተን የውሳኔ ሀሳብ ለሚመለከተው አካል አቅርበናል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አቶ ምትኩ እንዳስረዱት፤ ኮርፖሬሽኑ የይከፈለኝ ጥያቄውን ያቀረበው ባለፈው ዓመት ነው፤ ይሁን እንጂ ችግሮች ሳይለዩ፣ ምን የማን ኃላፊነት እንደሆነ፣ ትርፍና ኪሳራው ሳይታወቅ መክፈል ስለማይቻል ይህን ለማጣራት ሲጠና ነው የቆየው፤ በዚሁ ጥናት መሰረት የውሳኔ ሀሳብም ለበላይ አካል ተልኳል፡፡
ሌሎች በኮርፖሬሽኑ በኩል ያሉ ችግሮችን ለመለየት ይቻል ዘንድ ቡድን ተቋቁሞ የማጣራት ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ምክትል የቢሮ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የቀላል ባቡር ትራንስፖርት በሁለት መስመሮች በመሰማራት በየቀኑ በአማካይ እስከ 120 ሺህ መንገደኞችን የሚያጓጉዝ ሲሆን፤ የእለት ገቢውም በአማካይ ከብር 330 ሺህ እስከ 350 ሺህ እንደሚደርስ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊው አቶ ደረጀ ተፈራ አስታውቀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/20111
ግርማ መንግሥቴ