አዲስ አበባ፡- ለ10 ዓመታት ይጀመራል እየተባለ በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተት የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ህንፃ ግንባታ ጥር 15 ቀን 2011 ዓ.ም ከተቋራጩ ጋር ውል ታስሮ ወደ ሥራ ሊገባ መሆኑን ቴአትር ቤቱ አስታወቀ፡፡
የቴአትር ቤቱ የግዥ፣ ፋይናንስና ንብረት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ እዮብ ታምሩ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ዘመናዊው ባለአራት ፎቅ የቴአትር ቤት ህንጻ ግንባታ ጨረታውን ካሸነፈው አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ድርጅት ጋር ውል በመግባት ግንባታው እንደሚጀመር አስታውቀዋል፡፡
የሚገነባው ህንፃ ዘመናዊ ቴአትር ቤት የሚያሟላውን ሁሉንም ነገር የያዘ ሲሆን፤ በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ይሆናል፡፡ የቴአትር መመልከቻ አዳራሹ ዘመናዊ የድምጽና የመብራት ሥርዓት ይኖረዋል፡፡ ከወጥ ቤት እስከ ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያ ድረስ እንደሚይዝም ዳይሬክተሩ አመላክተዋል፡፡
እንደ አቶ እዮብ ገለጻ፤ ግንባታው የሚካሄደው በአሁኑ ወቅት እንደ ቢሮ በሚጠቀሙበት ቦታ ላይ ስለሆነ ሌላ ቢሮ ተከራይተው ለግንባታው ለቀዋል፡፡ የኮንትራክተር መረጣና የግንባታ ፈቃድ ቀደም ሲል ተጠናቅቋል፡፡ ከበጀት ጋር ተያይዞ ለሚቀጥለው ዓመት ይተላለፍ አይተላለፍ የሚባለው ታይቶ በዘንድሮ ዓመት ግንባታው እንዲካሄድም የገንዘብ ሚኒስቴር ፈቅዷል፡፡
ግንባታውን በበላይነት የሚቆጣጠረው የቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ግንባታው 1.4 ቢሊዮን ብር የሚፈጅ ሲሆን፤ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥም ይጠናቀቃል፡፡ ህንፃው ዘመናዊ ቴአትር ቤት የሚያስፈልገውን ሁኔታዎች ሁሉ የያዘ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት የተገነባው ከ64 ዓመት በፊት ሲሆን፤ 1ሺ200 አካባቢ ተመልካች የመያዝ አቅምም አለው፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ጣራው የማፍሰስ ችግር ስላለበት ዝግጅቶችን በአግባቡ ለማካሄድ እያስቸገረ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/20111
በአጎናፍር ገዛኽኝ