አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች መካከል ለዘመናት የተገነባው አብሮነትና በብዝሃነት የሚገለጸው አንድነት በዘላቂ የህዝቦች ግንኙነት ላይ ተመስርቶ እንዲጠናከር የሚያስችል አሠራር ለመዘርጋት የህዝቦች ግንኙነት ሰነድ ሊዘጋጅ መሆኑ ተነገረ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል እና በምክር ቤቱ የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ዋና ፀሐፊ አቶ ኃይሉ ኢፋ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ፌዴሬሽኑ ለዘመናት የቆየውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል። ለዚህም በዘመናት የተገነባውን የህዝቦች አብሮነትና አንድነት ባልተቆራረጠ የህዝቦች ግንኙነት እንዲታገዝ የማድረግ ተግባር እየተከናወነ ሲሆን፤ ይህም በሰነድ የተደገፈ ወጥ አሠራር እንዲኖረው የህዝቦች ግንኙነት የሚመራበት ሰነድ ለማዘጋጀት እየተሠራ ይገኛል።
እንደ አቶ ኃያሉ ገለጻ፤ 14ኛው የብሔር ብሔረሰቦች በዓልን ለማክበር ሲታስብ የህዝቦችን የእርስ በእርስ ግንኙነት ማጠናከር ዋነኛው ማዕከል ተደርጎ ሲሠራ የቆየ ሲሆን በዚህም ህዝቦችን እንደየጉርብትናቸው በክልል፣ በዞንና በወረዳ የማገናኘት፤ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋርም የእርስ በእርስ ውይይት እንዲያደርጉ አራት መድረኮች ተዘጋጅተዋል።
በመጀመሪያውና አዲስ አበባ ላይ በተዘጋጀው መድረክ ከምዕራብ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች የተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት እንደነበርና ሁለተኛውና በአዳማ የተካሄደው መድረክ ደግሞ ከዞን እስከ ወረዳ ያሉ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የምሥራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች መድረክ እንደነበር አቶ ኃይሉ ተናግረዋል።
በሰመራ የተካሄደው ሦስተኛው መድረክ ደግሞ የሰሜን ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች የወከሏቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት ሲሆን አራተኛው የኦሮሚያና የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ተጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች ተወካይ የህብረተሰብ ክፍሎች የተገናኙበት መድረክ እንደሆነም ጠቁመዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ትልቁ ሚናም ክልሎችን ማገናኘት እንደመሆኑ፤ በቀጣይም እነዚህን መድረኮች ወደታች የማውረድ ተግባር እንደሚከናወን የገለጹት አቶ ኃይሉ በተካሄዱት አራት መድረኮች በህዝቦች መካከል የነበረውም ሆነ ያለው መስተጋብር ጠንካራ መሆኑን ከመረዳት ባለፈ፤ ይሄን ዓይነት የህዝቦችን ግንኙነት የሚያጠናክር መድረክ ዓመት እየጠበቀ የሚከናወንና በሁኔታዎች ላይ የሚመሰረት መሆን እንደሌለበት ይልቁንም ቀጣይነት ባለው መልኩ ህዝቦች እየተገናኙ በጋራ ጉዟቸው ላይ የሚመክሩበትን ዕድል መፍጠር እንዳለበት ያስገነዘበ ነው ብለዋል።
በመሆኑም እነዚህ መድረኮች በዚህ ሳያበቁ ክልሎች በራሳቸው ሥራውን ወስደው ዞኖችንና ወረዳዎችን የማገናኘት ሥራ እንዲያከናውኑ ይደረጋል ብለዋል። ይህ የህዝቦችን ግንኙነት የማጠናከር ሥራው ሳይቆራረጥና ወጥነት ባለው የአሠራር ስርዓት እንዲመራ የማድረግ ሥራው በምን አግባብ ይመራ የሚለው መታየት ያለበት ጉዳይ መሆኑ ተለይቷል ብለዋል።
አቶ ኃይሉ እንደገለጹት በተለይ በመድረኮቹ ሲደመጥና ከህዝቡም ሲነገር እንደነበረው በህዝቦች መካከል ችግር የለም፤ ይልቁንም ይነሳ የነበረው የህዝቦችን አንድነት ለማጠናከር የሚያስችል አሠራር አለመኖር ነው። በመሆኑም ይሄን የህዝብ ፍላጎት ከግምት በማስገባት በእነዚህ መድረኮችም ሆነ በእስከአሁን ጉዞ የተገኙ ልምዶችን በመቀመር የህዝቦች ግንኙነት የሚመራበት ሰነድ ለማዘጋጀትና አሠራርም ለመዘርጋት እየተሠራ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ህዳር 29/2012
ወንድወሰን ሽመልስ