በዛሬው የኪነ ጥበብ አምዳችን ላይ አንጋፋውን የሙዚቃ ባለሙያ ኃይሉ መርጊያን አስ ታውሰን ጥቂት ለመጨዋወት ወደድን። በመሣሪያ ብቻ የሚቀናበር ሙዚቃ ተጫዋቹ አንጋፋ በኢትዮጵያውያን የጥበብ አፍቃሪዎች ዘንድ ክብርና ሞገስ ደርቦ ለዓመታት የቆየው ‹‹የዋሊያ ባንድ›› አባል ነበር። በአሜሪካ ቆይታውም ዓለም አቀፍ ሙዚቃን ከእውቅ ዩኒቨርሲቲ በማጥናት የገነነ ስምና ዝናን ማትረፍ ችሏል። ተወዳጅ የኢቲዮ ጃዝ ብሎም ኤሌክትሮ ጃዝ እንዲሁም ሌሎች እውቅ ስልቶች ተጫዋች ነው። በተለይ ኢትዮ ጃዝ ሲነሳ ከእውቅ ሙዚቀኞች ተርታ ይሰለፋል።
ሙዚቀኛ ሀይሉ መርጊያ በሙዚቃ ፍቅር የወደቀው በለጋ እድሜው መሆኑ ይነገራል። ገና ከአስር ዓመቱ ጀምሮ በአማረኛ ኦሮምኛና ሌሎች ቋንቋዎች የሚሰሩ ባህላዊ የኢትዮጵያ ሙዚቃዎችን እየሰማ ነው ያደገው። እድሜው 14 ዓመት ሲደርስ ደግሞ ‹‹አኮርዲዮን›› የሚባል ዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያ አቀላጥፎ መጫወት ጀመረ። ይህ ብቻ ሳይሆን በውጭው ዓለም ‹‹ፎልክ›› እና ‹‹ፈንኪየር›› የሚባሉ ጣዕመ ዜማዎችን በኪቦርድና በአኮርዲዮን መሣሪያዎች የመጫወት ክህሎቱን ማዳበር ችሏል።
ኃይሉ መርጊያ በ1970ዎቹ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ተጽዕኖ መፍጠር የጀመረበትና ተወዳጅነቱ እያየለ የመጣበት ጊዜ ነበር። በዚህም በኪቦርዲስትነት በዋሊያ፣ ኢቲዮ ጃዝና ፈንክ ባንድ ውስጥ የተለያዩ ማራኪ የአገር ውስጥና የምዕራባዊያን ተወዳጅ ሙዚቃዎቹን ከሙያ አጋሮቹ ጋር መጫወት ችሏል። በዘመኑ የነበሩ ቅንጡና አራዳ የሙዚቃ ወዳጆችም በጥበብ ሀሴት ተመስጦ ውስጥ እየከተተ የህይወትን ጣፋጭ ጎን ከሚያስኮመኩሙ ተወዳጅ ሰዎች ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ ያዘ።
በዘመኑ የደርግ ሥርዓት የሙዚቃ ሙያተኞች ህይወት ከባድ እንዲሆንና እንጀራቸውን በሚወዱት ሙያ እንዳይጋግሩ እንቅፋት ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ምሽት ክለቦች በሰዓት እላፊ ምክንያት በሚፈልጉት መንገድ እንዳይሠሩ ያስገደዱ ስለነበር ነው። ሆኖም ግን እነ ሀይሉን የመሰሉ ባለተሰጦ አርቲስቶች በርካታ ሥራዎችን ከመሥራትና ለአድናቂዎቻቸው ካሴቶችን እየቀዱ ከማሰራጨት አላገዳቸውም ነበር።
በጊዜው ሌላኛው ፈተና የነበረው እነ ኃይሉን የመሰሉ የሙዚቃ ተሰጦ ያላቸው ሰዎች በወታደራዊው መንግሥት የሚደርስባቸው የሳንሱር ጫና ነበር። ከዚህ ባለፈም በሙዚቃ ሥራዎቻቸው የሶሻሊስት ሥርዓትን የሚደግፍ ሙዚቃ እንዲሠሩ ይገደዱ ነበር። ይህን በማስመልከት በአንድ ወቅት አንጋፋው ሙዚቀኛ እንዲህ የሚል ትውስታውን አጋርቶ ነበር። ‹‹ድምፃዊም ሆንክ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋች በወቅቱ የደርግ ሥርዓትን መደገፍ ይኖርብሐል። ይሄን የማታደርግ ከሆነ ያው ችግር ውስጥ እንደምትገባ ግልፅ ነበር›› ብሏል።
ከዚህ ባለፈ በጊዜው በነበረው የሙዚቃ ሂደት የመሪነቱን ስፍራ የሚይዙት ድምፃዊያን ነበሩ። ክላሲካል አሊያም በሙዚቃ መሣሪያ የተቀነባበረ ሥራ የሚሠሩ ተጫዋቾች በጣም ጥቂት ነበሩ። በአድማጭ ዘንድ የሚሰጣቸው ስፍራም ያን ያክል የገነነ አልነበረም። በዚህ የተነሳ በ70ዎቹ ከአምስት የማያንሱ የክላሲካል አልበሞች ብቻ ነበሩ ለሙዚቃ አፍቃሪዎች መውጣት የቻሉት። ከዚህ ውስጥ ደግሞ በወርቃማው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘመን ተወዳጅነትን ያተረፈው ሀይሉ መርጊያ ከዋሊያ ባንድ ጋር በጋራ በ1977 የወጣው ‹‹ቼ በለው›› የሚል ስያሜ ያለው ሥራ ነበር። ይህ ሥራ የአንጋፋው አርቲስት ምልክት ተደርጎም በብዙዎች ዘንድ ይነሳል።
ኃይሉ የሙዚቃ ሥራውን መሥራቱን ሳያቆም በዚያው ቀጣይ ዓመት አዲስ በመሣሪያ ብቻ የተቀነባበረ ሥራውን በዘመኑ በሙዚቃ ፍቅር ለተሸፈኑ አራዳዎች አበረከተ። ሥራው ‹‹ወደ አገር ቤት ጉዞ›› የሚል ስያሜም ነበረው። ታዲያ ይህን ሥራ የሠራው ‹‹ዳህላክ ባንድን›› ከተቀላቀለ በኋላ ነበር። በዚህ ሥራው ላይ ‹‹jazz-infused›› ወይም በድንገት በሚቀናበሩ ሥራዎች ‹‹improvisation›› ተጽዕኖ የሚበዛባቸው ነበሩ። የዋሊያ ባንድ በነበረበት ወቅት በኪቦርዲስት ተጫዋችነቱ የቡድኑ ቀዳሚ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንደነበረም በተለያዩ አጋጣሚዎች ይነገራል።
አዲስ መንገድ
አንጋፋው ኪቦርዲስት ኃይሉ መርጊያ በ80ዎቹ በሙዚቃ ጎዳናው ላይ አዲስ መንገድ የጠረገበት ነበር። እርሱና የባንድ አባላቱ የሙዚቃ ጉዞ ወደ አሜሪካ ባደረጉበት ወቅት በህይወታቸው ላይ ቀጣይ አሻራ ማሳረፍ የቻለ ውሳኔ የወሰኑበት ነበር። እርሱን ጨምሮ ግማሾቹ የሙዚቃው ባንድ አባላት በአሜሪካን አገር ለመቅረት ወሰኑ። በኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው የሙዚቃ ቆይታቸው ለወዳጆቻቸው ያቀበሉት ሥራ ታሪካዊ አሻራውን ትቶ አለፈ። በተለይ ኃይሉ ከባንዱ ጋር ያበረከተው ‹‹የሙዚቃ ስሌት›› የሚለው ክላሲካል ሥራ ትውስታን በማጫር መግነጢሳዊ ኃይሉ ተጠቃሽ ነው።
በአሜሪካ ውስጥ ሥራውን ለማቅረብ ሄዶ ኑሮውን በዚያው ያደረገው አንጋፋው የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋች አዲስ በሙዚቃ የተቀነባበረ ሥራ በአልበም መልክ ሠርቶ ለአድማጮች ለማድረስ ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም። ‹‹መርጊያና የመሣሪያ ቅንብሮቹ›› በሚል በ1985 ለቀቀ። ይህን ሲያወጣ ‹‹ዙላ›› የተሰኘ ባንድ ውስጥ እየሠራ የነበረ ቢሆንም አልበሙን ግን በትንሽ ስቱዲዮ ውስጥ ብቻውን ነበር የቀረፀው። አልበሙን በሚሠራበት ተመሳሳይ ጊዜ የሙዚቃ ትምህርት በሆዋርድ ዩኒቨርሲቲ ሙዚቃ ያጠና ነበር። ጠባቧን ስቱዲዮ ያገኛትም የሙዚቃ ጭውውት ከሚያደርገው እና በአጋጣሚ ከተገናኘው ጓደኛው ተበድሮ ነበር።
አንጋፋው የሙዚቃ ቅንብር ባለሙያ ሀይሉ መርጊያ አስራ አንድ ሥራዎችን ያካተተውን አልበም በአጋጣሚ ነበር የለቀቀው። በተለይ በዚህ ሥራ ላይ ለዓመታት ተራርቆ የቆየውን የአኮርዲዮን የሙዚቃ መሣሪያ ጋር የተገናኘበት ነበር። እርሱ እንደሚለው ‹‹አልበሙን ለአድማጭ ለማድረስ አስቤ አልነበረም። በአጋጣሚ ለራሴ ለመስማት የምፈልገውን በአኮርዲዮን የተቀናበረ ሙዚቃ ለመቅረፅ ነበር ሐሳቤ። ከዚያ ነው ሐሳቡ አድጎ በሦስት ቀናት ውስጥ አልበም ሆኖ መውጣት የቻለው›› ሥራውን በሚሠራበት ወቅት በዋናነት አኮርዲዮን የተጠቀመ ሲሆን ፒያኖ፤ ሞግ ሲንተሳይዘር እና ድራም ይጠቀሳሉ።
‹‹መርጊያና የመሣሪያ ቅንብሮቹ›› በሚል ስያሜ የተለቀቀው አልበም ላይ ልዩ ጣዕመ ዜማዎችን እጅግ ዘመናዊ በሆኑ የሙዚቃ መሣሪያዎች ተጫውቷል። በተለይ በአፍላ የወጣትነት ዘመኑ የተጫወታቸውን ኢትዮጵያዊ ቃና የተጎዳኛቸው ሥራዎቹን ከምዕራቡ ዓለም ስልትና የሙዚቃ መሣሪያ ጋር ለማዋሐድ ያደረገው ሙከራ ስኬታማ አድርጎታል። በጊዜውም በአሜሪካን አገር ተደማጭ ለመሆን አብቅቶታል። የተለያዩ የሙዚቃ ሂስ የሚሰጡ ጋዜጠኞችም የመርጊያን ሥራ ትኩረት ሰጥተው ዘገባቸውን መሥራት ችለዋል። በተለይ የሙዚቃ ሐያሲው ሮበርት ክርሲታጉዋ ‹‹በዘመናዊው የሙዚቃ ስልት ያለፈውን የወጣትነት ሥራዎቹን በድንቅ ሁኔታ የሠራበት›› በማለት አሞካሽቶታል።
አኮርዲዮን እና አዲሱ አልበም
ኃይሉ በልጅነቱ ከአኮርዲዮን የሙዚቃ መሣሪያ ጋር ነው ያደገው። ለረጅም ጊዜያትም ሲጫወት እና መንፈሱን ሲያረካበት ቆይቷል። እርሱ ብቻ ሳይሆን በዘመኑ የነበሩ አድማጮቹ ከአኮርዲዮን ጋር ልዩ ትዝታ አላቸው። አሜሪካን አገር ከገባ በኋላ ያወጣው አልበሙም የዚሁ ተወዳጅ መሣሪያ ተጽዕኖ በእጅጉ ያረፈበት ነው። ከሌሎች የኤክትኖኒክ መሣሪያዎች ጋር በማዋሐድም የ1950ዎቹ ትዝታን ለመጫር ጥረት አድርጓል።
ዘመናዊ ሙዚቃን በራሱ መንገድ ለአድማጮች በማቅረብ ይታወቃል። ለምሳሌ ያህል የተለየ ኢትዮጵያዊ ቃና ያለው እንዲሁም ዓለም አቀፍ ስልትን ያዋሀደ ሥራ ለመሥራት በዋናነት አኮርዲዮን እና ኪቦርድን ይጠቀማል። የተለያዩ አውድ ያላቸው ቃናዎችን ለመፍጠርም ‹‹ሮድስ ፒያኖ›› እንዲሁም ‹‹ድራም ማሽን›› በመጫወት የአድማጭን መንፈስ ጭልጥ አድርጎ ይወስዳል። አብዛኛው የሙዚቃ ሥራው የተቀመሙት ከባህላዊውና ከዘመናዊው የኢትዮጵያ ሙዚቃ መሆኑም በሌላው ዓለም ላይ ላለ አድማጭ አዲስ ቃና መፍጠር ችሏል። ለአገሩ ልጆችም ትዝታን እየጫረ ትውስታን እየኮረኮረ በሙዚቃ ስሌት ውስጥ እንዲንሳፈፉ የማድረግ አቅሙ ልዩ እንደሆነ ይነገርለታል።
የኢትዮ ጃዝ ምልክት
በአሁን ወቅት የኢትዮጵያ የጃዝ ሙዚቃ ትኩረትን እየሳቡ ከመጡ ቀዳሚ ሙዚቀኞች መካከል ነው። እንደ ሀይሉ መርጊያ ያሉ ሙዚቀኞች ኢትዮ ጃዝ ተወዳጅ ስለመሆኑ ምስክሮች ናቸው። የጃዝ ሙዚቀኛው ሀይሉ መርጊያ ለ20 ዓመታት ያህል ከሙዚቃው ዓለም ርቆ ዳግሞ ወደ ሙዚቃው ዓለም ለመመለስ እንደቻለም በተለያየ አጋጣሚ የሚወጡ ዘገባዎች ጠቁመዋል። ዳግም ወደ ሥራው እንዲመለስ የረዳውም የአሁኑ ማናጀሩ ብሪያን ሺሞኮቪትዝ እንደሆነ ይነገራል።
የአሁኑ ማናጀሩ ወደ ኢትዮጵያ በመጣበት ወቅት ሙዚቃውን ሰምቶ ዳግም አልበሙ እንዲወጣ ማድረጉን ሀይሉ እራሱ ከዋሽንግተን ፖስት ጋር በነበረው ቃለምልልስ ላይ ከዓመታት በፊት ገልፆ ነበር። ለፒያኖ ልዩ ፍቅር እንዳለው የሚናገረው ኃይሉ ከሙዚቃው የራቀውም በግል ሥራ ምክንያት እንደሆነም በወቅቱ አስረድቷል።
ኃይሉ ገና በ14 ዓመቱ ጦር ሠራዊት በመቀጠር ለ2 ዓመት የሙዚቃ ትምህር ተምሮ ከጨረሰ በኋላ በምሽት ክለብ በሙዚቀኛነት በኋላም የአኮርዲዮ፣ የኦርጋን ተጨዋች በመሆን የሠራ ተወዳጅ ሙዚቀኛ ነው። በ1962 ዓ.ም አካባቢ የቀድሞ ዋሊያስ ባንድ በማቋቋም ከሂልተን ሆቴል እስከ አሜሪካን አገር ሥራዎቹን ማቅረብ ችሏል። ወደ አሜሪካ ከሄደ በኋላም ወደ ሌላ ሥራ በመሰማራት ከመድረክ ላይ ራቅ ብሎ ቆይቷል። ነገር ግን ሙዚቃውን ጨርሶ አልተወም ነበር። በተለይ ለራሱ ያለውን ፍቅር ለማርካት የሚወዳቸውን መሣሪያዎች ይጫወት ነበር። ኃይሉ ‹‹ኤርፖርት ውስጥ በታክሲ ሾፌርነት ይሠራ እንደነበር ከተለያዩ መረጃዎች ላይ ማግኘት ችለናል። በአንድ ወቅትም በመገናኛ ብዙሃን ተጠይቆ ‹‹በየቀኑ ልምምድ አደርጋለሁ፤ እቤት ስገባም የሙዚቃ መሣሪያዎች ስላሉኝ ማጥናት መቻሌ ዳግም ወደ ሙዚቃው ስመለስ ውጤታማ እንድሆን አድርጎኛል›› በማለት ከሁለት አስርት ዓመታት ቆይታ በኋላም የቀድሞ ተወዳጅነቱ ያለመቀነስ ሚስጥር ምን እንደሆነ ለማስረዳት ሞክሮ ነበር።
ይህ ደግሞ እንደ አዲስ ብዙ አድናቂዎችንን እንዲያፈራ ከማድረግ አልፎ ተርፎ የተለያዩ አገሮች ጀርመን ፣ ፈረንሳይ፣ ስዊድን፣ ካናዳ እና አሜሪካን ጨምሮ ሥራውን ዳግም እንዲያስተዋውቅ አግዞታል። ወደ ሙዚቃው ዓለም ከተመለሰ በኋላ ‹‹ላላ በሉ›› የሚል አዲስ በመሣሪያ የተቀነባበረ የሙዘቃ አልበም አሳትሟል። ለወደፊትም ቢሆን የተለያዩ አገሮች ላይ ተዘዋውሮ ለመሥራት እና አዳዲስ አልበሞችን ለማሳታም ፍላጎት እና ዕቅድ እንዳለውም ለዋሽንግተን ፖስት ገልፆ ነበር። ዛሬም ኑሮውን አሜሪካ የሙዚቃ ሥራውና ስሜቱ ኢትዮጵያን አድርጓል።
አዲስ ዘመን ህዳር 28/2012
ዳግም ከበደ