ከወር በፊት የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን(ሉሲዎቹ) ዋና አሰልጣኝ በመሆን ለአጭር ጊዜ ኮንትራት ወደ ኃላፊነት የመጣው አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው አጭር ጊዜዝግጅት በመካከለኛውና ምስራቅ አፍሪካ ዋንጫ(ሴካፋ) ተሳትፎ ከአስር ቀን በፊት ተመልሷል። አሰልጣኙ በሴካፋ ቆይታው ቡድኑን እየመራ በምድብ ጨዋታዎች በኬንያ ሁለት ለዜሮ፣ በዩጋንዳ አንድ ለዜሮ ሽንፈት ገጥሞት ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ሳይችል ቀርቷል። ያም ሆኖ በምድቡ እጅግ ደካማ የሆነችውና በርካታ ግቦችን ያስተናገደችው ጅቡቲን በሦስተኛው የምድብ ጨዋታ ስምንት ለዜሮ በመርታት የሴካፋ ጉዞው ተቋጭቷል። አሰልጣኝ ብርሃኑ ወደ ሴካፋ ሲያመራ ካደረገው የአጭር ጊዜ ዝግጅት አኳያ ከውድድሩ ብዙም ውጤት ለማምጣት እንዳላሰበ ቀደም ብሎ ተናግሮ ነበር። ያም ሆኖ በቀጣይ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ስኬታማ ቡድን ገንብቶ ሉሲዎቹን ለአፍሪካ ዋንጫ ካላበቃ በራሱ ፍቃድ ስራውን እንደሚለቅ ቃል ገብቷል። አሰልጣኙ በሴካፋ ቆይታውና ስለቡድኑ ቀጣይ ሁኔታዎች ከአዲስ ዘመን ጋር ያደረገው አጭር ቃለ ምልልስ የሚከተለውን ይመስላል።
አዲስ ዘመን፡- አሰልጣኝ ብርሃኑ የሴካፋ ቆይታ እንዴት ነበር፣ ቡድኑንስ እንዴት ገመገምከው?
አሰልጣኝ ብርሃኑ፡- በሴካፋ ውድድር ትልቁ ነገር ተሳትፎ ነው፣ መወዳደር በራሱ ጥሩ ነው፣ ወደ ወድድድሩ ከመሄዴ በፊት እቅዴን አስቀምጬ ነበር፣ በተሰጠኝ አስር ቀን ውስጥ የመጀመሪያ እቅዴ የአገር ግዴታና አገርን ማገልገል ስለሚያስደስትና ከዚህ በፊትም ስላገለገልኩኝ እምቢ ማለትን አልመረጥኩም፣ ፌዴሬሽኑ ኃላፊነቱን ሲሰጠኝ ገብቼበታለሁ፣ መጀመሪያ ሴካፋ ላይ ልጆቹ ምን አይነት አቅም ላይ እንዳሉ ለማየት በማሰብ ነው ወደ ውድድሩ ያቀናነው። ተጫዋቾቹ አራት ወራት ያህል እረፍት ላይ የቆዩ እንደመሆናቸው በውድድሩ የሚችሉትን አድርገዋል፣ ነገር ግን በእግር ኳስ የሚያስፈልገው ብዙ ነገር በመሆኑ መቋቋም አልቻሉም፣ ውድድሩ ከብዶን ወጥተናል፣ ይሄን ውድድር ዝም ብለን ማየት ሳይሆን በቀጣይ ውድድሮችን አጠንክረን ይዘን ለአፍሪካ ዋንጫ መብቃት ነው፣ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ የማንችል ከሆነ ደግሞ በገባሁት ቃል መሰረት ራሴን አገላለሁ፣ ሴካፋ ብዙ ነገር አሳይቶናል፣ በጣም እንችላለን፣በጣም ጎበዞች ነን ብለን የምናስበውን በምስራቅ አፍሪካ እንኳን እንደማንችል አይተናል፣ ሴካፋ ራሱ ደካማ ነው፣ ከኛ በታች የነበሩት እነ ኬንያ የተሻለ ሆነዋል፣ ምክንያቱም እነሱ አልቆሙም እኛ ቆመናል፣ የቆምንበት ትልቁ ችግር በውስን ተጫዋች ላይ ሁልጊዜ መንጠልጠላችን ነው፣ እነ ኬንያ ዛሬ አንድ ተጫዋች ቢኖራቸው ነገ ሌላ ለማፍራት ነው የሚሰሩት፣ እኛ ለአፍሪካ ዋንጫ ስናልፍ 5ለ0 አሸንፈናቸው ነበር፣ አሁን ግን እነሱን ማሸነፍ ችግር ሆኖብናል። ለአፍሪካ ዋንጫ ከማለፍ ባለፈ ሴካፋ ላይ አንድም ግብ ሳይቆጠርባቸው ዋንጫ አንስተዋል። አሁንም ጊዜ አለን እንስራ ግን ለምን እንደምንሰራ ማወቅ አለብን። ብሔራዊ ቡድኖቻችን ተመጋጋቢ መሆን አለባቸው፣ ከ17ዓመት በታች የምንመርጠው ከፕሪሚየር ሊግ ከሆነ፣ ከ20 ዓመት በታችም እንደዚሁ ከሆነ አስቸጋሪ ስለሚሆን ተመጋጋቢነቱ ከ17 ዓመት በታች በዚያው የእድሜ ክልል ባለ ጨዋታ ሌላውም እንደዚያው ሊሆን ይገባል። አሁን በማንም ለማሳበብ አይደለም፣ሙያተኛው ስራውን መስራት አለበት።ፌዴሬሽኑም አቅጣጫ መስጠት አለበት። እንደዚህ ከሰራን ከቆምንበት መነሳት እንችላለን። እነ ኬንያ አልቆሙም ነገር ግን ሴካፋ በራሱ ደካማ በመሆኑ ከደካማው ጠንካራ እንደመምረጥ ነው፤እኛ ደግሞ ከዚሁ ደካማ የባሰበት ደካማ ሆነናል፤ይሄ ምንም ጥያቄ የለውም፤ ስለዚህ እኔን በአስር ቀን ውስጥ ቡድን ሰርተህ ውጤታማ ሁን ብትለኝ አስቸጋሪ ነው፤ ውጤታማ ብሆን እንኳን ዘራፍ ካልኩኝ እንዳልሰራሁ ነው መታወቅ ያለበት፤ ውድድሩም የሰጠን የራሱ ነገር ስላለ እንደገና ተመልክቼ የተወሰነ ማሻሻያ በማድረግ የአፍሪካ ዋንጫ ከፊት በቅርባችን አለ ውጤታማ ለመሆን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ቀጣዩ ትልቁ የቤት ስራህ ቡድኑን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያና በኦሊምፒክ ማጣሪያ ውጤታማ ማድረግ ቢሆንም ፌዴሬሽኑ በሰጠህ እጅግ አጭር ሊባል በሚችል የሦስት ወር ኮንትራት ማሳካት እንዴት ይቻላል?
አሰልጣኝ ብርሃኑ፡- ኮንትራቱ ያጥራል፣እንግሊዝም ሂድ አፍሪካ አንድ አሰልጣኝ ኮንትራት በወራት ሳይሆን በዓመታት ነው የሚሰጠው፤እኛ ጋር እንደ ቢሮ ስራ የአርባ አምስት ቀናት የሙከራ ጊዜ ዘጠና ቀን ተደረገልህ እንደማለት ነው፤ምናልባት እኔን የማያሳስበኝ ክለብ ውስጥም እዚሁ ስራ ላይ ስላለሁበት ከስራ እጦት ወደ ስራ ሳይሆን ከስራ ወደ ስራ ነው እየተሸጋገርኩኝ ያለሁት፤ስለዚህ ያ ነገር ስላላሳሰበኝ በየቀኑ የሚሰራ ሰው ደግሞ ራሱን በየጊዜው ያሻሽላል፣ ለአፍሪካ ዋንጫ ፈጣሪ ብሎ ቡድኑን ማሳለፍ ከቻልኩ እንደዚህ አይነት አሰራሮችና አመለካከቶች ላይ የራስን አቋም ለመያዝ ይመቻል። ምክንያቱም በወር ውስጥ የምታደርገው ነገር ስለሌለ፣ አንዳንድ ጊዜ አይተህ ከሆነ ዋና አሰልጣኝ ይፈልጉና ጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝ እንኳን ሲቀጥሩ የወራት ሳይሆን የዓመት ኮንትራት ነው የሚሰጠው፤እነ ሮቤርቶ ዲማቲዮን መመልከት ይቻላል፣ የኦሊምፒክ ሲዝን የሚሰጠው ፍልስፍናህ ተጫዋች ላይ አርፎ እንዲሰራ በሂደት ነው እንጂ ዛሬውኑ የሚሆን ነገር የለም። ኳስ ከገበያ ገዝተህ የምታመጣው ወይም እንደ ብር ከባንክ የምታወጣው ነገር አይደለም፣ ሰው ላይ አእምሮ ላይ ነው የምትሰራው፣ አንድ ቦታ ቀብተህ ሌላው ቀረኝ የምትለው አይነት አይደለም፤ ብዙ ስህተት የሚፈጠርበት በጊዜ እያየህ የምታስተካክለው ነው ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለሴቶች እግር ኳስ በክለቦችም ይሁን እንደ አገር የሚሰጠው አነስተኛ ትኩረት የሴቶችን ብሔራዊ ቡድን ከማሰልጠን የወንዶች ይቀላል ለማለት ያስደፍራል?
አሰልጣኝ ብርሃኑ፡- የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጉዳይ አሁን ላይ ለሚይዘው አሰልጣኝም ለባለሙያም አስቸጋሪ የሆነበት ጊዜ ነው፣ እንዲያው ትንሽ ተስፋ የሚሰጠው አካዳሚዎች ተጫዋቾችን እያወጡ መምጣታቸው ነው፤ እነ አረጋሽንና እነ ሴናፍን፣ ናርዶስን ስትመለከት ብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ አራትና አምስት ሆነዋል፤ ይሄ ተስፋ ይሰጣል እንጂ ክለቦች ለይምሰል ነው የሚሰሩት፣ እጅግ በጣም ጥቂት ክለቦች ብቻ ናቸው ለሴቶች እግር ኳስ የቆሙት፤ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውስጥ ስንት ክለቦች ጠንካራ የሴት ቡድን አላቸው? ዋና የሚጨበጨብላቸው ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና ቅዱስ ጊዮርጊስ እንኳን የሴት ቡድናቸውን የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሚያወዳድረው ላይ እናሳትፋለን ሲሉ ትሰማለህ፣ ይሄ ማለት ቤትህ ሙሉ ሆኖ ራቁትህን እንደመቅረት ነው፤ ወንዱን አልብሰህ ሴቱን እንደመተው ነው፣ ጥሩ የሴት ቡድን ደጋፊዎች በየክለቦቹ አሉ፤ ወንድ ብቻ የወንዶቹን ቡድን ደግፎ እዚህ አላደረሳቸውም፣ የቡናንም ይሁን የጊዮርጊስን ሴት ቡድኖች ስትመለከት ያሳዝኑሃል ፤ አምና ከከፍተኛ ዲቪዚዮን አውጥተው እንዲወዳደሩ አድርገዋል፤ የሚፍጨረጨሩት እንደ አዳማ፣መከላከያ፣ድሬዳዋ እነ ጌዲዮ ዲላ፣ አርባምንጭ ምሳሌ ቢሆኑም በቂ አይደሉም። ስለዚህ በፊት የነበሩትንና የአሁኖቹን ለማዋቀር ከባድ ነው፣ ክለቦች ለተጫዋቾቻቸው እየሰጡ ያሉት ነገር ፣ የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ለአፍሪካ ዋንጫ ስናልፍ በወቅቱ የነበረው ስራ አስፈፃሚ ለሴቶች አንድ ነገር መስራት አለብን ብሎ በመጀመሪያ ክለቦች የሴት ቡድን መያዝ አለባቸው፣ ክለቦች ተጫዋቾችን ሲይዙ ያደረጉት የ ቢና ሲ ቡድንን ነው ያፈረሱት፤ እስካሁን በስምንት ዓመት ውስጥ መሻሻል ነበረብን፤ ከ17 ዓመት በታች ጀምሮ በየደረጃው ማቋቋም አለብን፣ እነዚህ ወጪም አያስወጡም፣ የትኛው ትልቅ ወጪ ነው የሚወጣባቸው?አሁን ክለቦች ላይ እየተደረገ ያለው ነገር የይምሰል ነው፤ ፌዴሬሽኑም እዚህ ላይ የግል አቋም ሊኖረው ይገባል፤ ክለቦችም ክረምቱን በሙሉ በመግለጫ ሲያሰለቹን የነበሩ አንዳቸውም ስለ ሴቶች ሲያወሩ አልተመለከትናቸውም።ቀደም ሲል የነበሩት የስፖርት አመራሮች የተማሩት እዚህችው አገር ሆነው ነው፤ እነ ይድነቃቸው ተሰማን ስናነሳ ዓለምን የዞሩት ዝም ብለው ሳይሆን በእውቀት ነው።ከዚህ አልፎ ሌሎች አገራት ላይ ስታድየም በስማቸው የተገነባላቸው፤ አሁን ያሉትም መሪዎች ወንዱን መገንባት ሴቱን የማፍረስ ችግሮች አሉባቸው።
አዲስ ዘመን፡- አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ለሰጠኸን ጊዜ ከልብ እናመሰግናለን።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ህዳር 27/2012
ቦጋለ አበበ