አዲስ አበባ፡– አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጋር በትብብር በመሥራት ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታወቀ። ኮሚሽኑ አሁንም ለቀሩት ለተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የትጥቅ ትግል ለሚያደርጉ አካላት ሁሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጋር በትብብር እየሠሩ እንደሚገኙና ጥቂቶች ግን ወደ ኮሚሽኑ መቅረብ እንዳልፈለጉ ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ ሥራ በጀመረ ሰሞን ጥሪውን ተቀብለው በጋራ ለመሥራት ፍላጎት ያሳዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አነስተኛ ነበሩ ያሉት ኮሚሽነሯ፤ በአሁኑ ጊዜ አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኮሚሽኑ ጋር በትብብር እየሠሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ተሳትፎ ሊያድግ የቻለው የኮሚሽኑን ገለልተኝነትና አካታችነት እየተረዱ በመምጣታቸው እንደሆነም የጠቀሱት ኮሚሽነሯ፤ ራሳቸውን ያገለሉት ጥቂት የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቀረብ ብለው ሂደቱን ቢመለከቱ፣ አካሄዱን ቢፈትሹና ወደ መጨረሻው ውሳኔ ላይ ቢደርሱ እንደሚሻል መክረዋል፤
ሠላማዊ የፖለቲካ ትግል ማድረግን ዓላማው አድርጎ ለተቋቋመ የፖለቲካ ፓርቲ ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ጥሩ አጋጣሚ ነው ያሉት ኮሚሽነር ሂሩት፤ ዕድሉን አለመጠቀም በራሱ የሚያስቆጭ ይሆናል ነው ያሉት፡፡
ኮሚሽኑ ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ በተደጋጋሚ ጊዜ ጥሪ ሲያቀርብ እንደነበረ እና በአካልም እንዳነጋገራቸው ገልጸው፤ አሁንም በሀገራዊ ምክክሩ መሳተፍ ለሚፈልጉ ሁሉ ኮሚሽኑ በሩን ክፍት አድርጎ እየጠበቃቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የትጥቅ ትግል ውስጥ የገቡ አካላት ተወካዮችም ምንም አይነት የስጋትና የደኅንነት ጥርጣሬ ሳይኖራቸው መጥተው በሀገራዊ ምክክሩ ላይ እንዲሳተፉ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የደኅንነት ስጋት እንዳይፈጠርባቸው ዋስትና የሚሰጡና ሁኔታውን የሚያመቻቹ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መኖራቸውን ጠቁመው፤ መንግሥትም በጉዳዩ ላይ ፍቃደኝነቱን እንደገለጸ ተናግረዋል፡፡
‹‹አለመግባባት በጦርነት አይፈታም፤ ችግሮችን በውይይት መፍታት እየቻልን ብዙ ምሑራንና ወጣቶችን ያጣንባቸው መጥፎ አጋጣሚዎች ሊያስቆጩን ይገባል›› ያሉት ኮሚሽነር ሂሩት፤ በከፍተኛ ልፋትና ድካም ተምረው ለጥሩ ውጤት የበቁ ብርቅና ውድ ዜጎች ተነጋግረን መፍታት ስንችል ግጭት ውስጥ መግባት ለሀገርም የከፋ ጉዳት ያስከትላል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
እንደ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገለጻ፤ ወደ ትጥቅ ትግል አስገብቶናል፤ እንዳንግባባ አድርጎናል የሚባሉ ጉዳዮች ካሉ ቁጭ ብለው በመመካከር ሊፈቱ የማይችሉበት ምንም አይነት ምክንያት የለም፡፡
ኢትዮጵያውያን ትልቁ ችግራችን አንዱ አካል ሲሠራ ሌሎቻችን ተመልካች፣ ታዛቢ እና ተቺ መሆናችን ነው ያሉት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ፤ ይህ አስተሳሰባችን ወደ ችግር እየከተተን መሆኑን መረዳት አያዳግትም፡፡ እውነትን መፈለግ፣ የሌላውን የማኅበረሰብ ክፍል ወይም የሀገራችንን ዜጋ ቁስል ማዳመጥ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት እና የሲቪክ ማኅበራትም የሩቅ ተመልካች ከመሆን ይልቅ ቀረብ ብለው የሚጠበቅባቸውን እንዲሠሩ ኮሚሽነሯ አሳስበው፤ ሁሉም ሚናውን ሲወጣ ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ የማይሆንበት ምንም ዓይነት ምክንያት አይኖርም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ኅዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም