የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ለሀገራዊ መግባባት

በኢትዮጵያ የሚገኙ ከ80 በላይ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በባሕላዊ አለባበስ ደምቀው፤ በተለያዩ ጌጦች አጊጠው፤ በባሕላዊ ሙዚቃቸውና ውዝዋዜያቸው እያዜሙና እያሳዩ፤ በየቋንቋቸው እየተናገሩ፣ እየተግባቡ በጉራማይሌ ውብት ኅዳር 29 ቀን ያከብራሉ፡፡

የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የብዙኃን እኩልነት ማለትም የቋንቋ፤ የባሕል፤ የኃይማኖት እኩልነትን ያረጋገጠው እና የሀገር ሀብትን በፍትሕዊነት የመጠቀም መብትን ያጎናጸፈውን ኅዳር 29 ቀን በየዓመቱ ያከብራሉ።

ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ኅዳር 29 ቀን ሲያከብሩ አለመግባባትን በሚፈታ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚገነባና በሚያፀና መልኩ ነው፡፡ የዘንድሮው 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል “ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ የፊታችን ኅዳር 29 በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአርባ ምንጭ ከተማ ይከበራል፡፡

ቀኑ ሁሉም የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነታቸው እንዲከበርና በቀጣይ ለፍትሕ፣ ነፃነትና ለዲሞክራሲ ሥርዓት መከበርና መረጋገጥ በጋራ ጠንክረው እንዲሠሩ በጋራ የሚነሱበትን መሠረት የጣለ ነው፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶች፣ ትስስርና አንድነት የሚያጠናክሩ እንዲሁም የብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቱባ ባሕሎቻቸው፤ እሴቶቻቸው የሚያስተዋውቁበት ዕድልንም የፈጠረ ነው፡፡

የቦሌ ክፍለ ከተማ ሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ቡድን መሪ ፍሬሕይወት ለገሠ ለኢፕድ በሰጡት አስተያየት፤ የኅዳር 29 መከበር የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ሀገራዊ አንድነትንና መግባባት የሚያጸና ነው፤ እንደሀገር እያጋጠሙ ያሉ አለመግባባቶችን በመቻቻልና በመከባበር መፍትሔ እንዲያገኙና ሕዝቦች በሠላም እንዲኖሩ የሚያደርግ ነው ይላሉ፡፡

በየዓመቱ የሚከበረው ኅዳር 29 የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በኢትዮጵያ የሚኖር ሁሉም ዜጋ በዘር፤ በሃይማኖት፣ በብሔር ሳይለያይ ሰው በመሆኑ ተከባብሮ በእኩልነት እንዲኖር የሚያደርግ ነው፤ ዜጎች በእኩልነት መኖራቸውም ሠላምና አንድነትን ያስቀጥላል ሲሉ አስተያየታቸው ሰጥተውናል፡፡

ኅዳር 29 ቀን የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ልዩነታችን ድምቀታችን፤ ለአንድነታችን ውበት መሆኑን የሚያሳይ ነው፤ በዘር፣ በሃይማኖትና በቋንቋ ሳንለያይ ተባብረን በአንድነት እንድንኖር የሚያደርግ ነው፤ ይህም ሀገራዊ መግባባትን የሚያፀና ነው ሲሉ ያብራራሉ፡፡

በሀገራዊ መግባባት ላይ የሴቶች ሚና ትልቅ ነው፤ ሴቶች በልማት፤ በበጎ ፍቃድና በሠላም ግንባታ ላይ እየተጫወቱት ያለው ፋይዳ ትልቅ ነው፡፡ በልዩነት ጉራማይሌ ውበት፤ በጉራማይሌ ውበት ድምቀት፤ በልዩነት አንድነት የሚስተዋልበት የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ኅዳር 29 መከበሩ ኢትዮጵያዊነትን ያስተምራል፤ ይሰብካልም ነው ያሉት፡፡

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ሴቶች ማኅበር ሰብሳቢ ወይዘሮ መቅደስ ተክሉ በበኩላቸው፤ ኅዳር 29 የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበሩ ሠላምና አንድነትን የሚያረጋግጥ፤ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን የሚያዳብር ነው ብለዋል፡፡

ልዩነታችን የሚያጣላንና የሚያጋጨን ሳይሆን ውበታችን ነው፤ ውበታችን የሆነውን ልዩነታችንን በማቻቻል፤ በአንድነት እንድንኖር እሴቶቻችን፤ ባሕላችን መከበር አለባቸው፤ ጠብና ንትርክን ትተን በሠላምና በአንድነት መኖር አለብን ይላሉ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ደስ የሚልና የሚያኮራ ማንነት አላቸው፤ በሚያኮራ ማንነት በሠላምና በፍቅር መኖር አስፈላጊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች ውቅር ናት፤ አንዱ የአንዱን ባሕል፤ ቋንቋ፤ ሃይማኖት አክብሮ በፍቅርና በአንድነት መኖር አለበት ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

በመመካከር፤ በመከባበር አብሮ መኖርን ከአባቶቻችን ተምረናል፤ አሁን ግን አባቶቻችን ያስተማሩንን አክብሮት ጥለን ብሔርን አንስተናል፤ ያነሳነው ጽንፍ የወጣ ብሔርተኝነት አይጠቅመንም፤ እንደ ሰው ተከባብረን፤ ያለንን አቃፊነት፤ ሰብሳቢነት በማስቀጠል በፍቅርና በሠላም መኖር ይገባናል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ብሔር የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን በተፈጥሮ የሚሰጥ ነው፤ በተፈጥሮ በተሰጠ ነገር መጋጨት አስፈላጊ አይደለም፤ በሰውነታችን ተባብረን መኖር ነው አስፈላጊው ነገር ይላሉ፡፡

ኅዳር 29 የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ያሉብንን ችግሮች ቀርፎ አንድነትን የሚያስተምር ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የፊታችን ኅዳር 29 ቀን የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል አንድነትን ለማምጣት ትልቅ አስተዋፅዖ አለው ሲሉ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ እቴነሽ ለገሠ ይናገራሉ፡፡

ኅዳር 29 ቀን የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ኅብረ ብሔራዊነትን፤ አንድነትንና መቻቻልን የሚያስተምር በመሆኑ ሀገራዊ መግባባትን የሚያመጣ ነው ይላሉ፡፡

‹‹እኔ አማራም ኦሮሞም ነኝ፤ ከሁለቱም ብሔሮች ነው የተወለድኩት፤ ከሁሉም ብሔሮች መፈጠሬን ምርጫዬ ሳይሆን በተፈጥሮ ያገኘሁት ነው፤ በተፈጥሮ የተገኘ ብሔር ሊያጣላም ሆነ ሊያጋጭ አይችልም፤ በሰውነት ተከባብሮና ተዋዶ መኖር ዘላቂ ሠላም የሚያስገኘው›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡

ችግሮችን በውይይትና በሠላም በመፍታት፣ በፍቅርና አብሮነት መኖር ያስፈልጋል፤ ወጣቱ መንግሥትና ራሱ በፈጠረው የሥራ ዕድል በመሰማራት ራሱንና ሀገሩን ማሳደግ እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

ኅዳር 29 ቀን የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን የድምቀታቸው፤ የውበታቸው፤ የአብሮነታቸው መገለጫ ነው፡፡ በዓሉ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት የፀደቀበትን ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም ለመዘከር የሚከበር በዓል ነው። የበዓሉ መከበር ዋነኛ ፋይዳ በአገራችን ሕገ መንግሥትና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ኅብረተሰቡ የተሻለ ግንዛቤ እንዲያገኝ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያለመ ነው፡፡

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን  ኅዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You