ለመጪው ትውልድ የተሻለች አፍሪካን ለመፍጠር አሕጉራዊ አጋርነትን ማጠናከር ወሳኝ ጉዳይ ነው

አዲስ አበባ፡– ለመጪው ትውልድ የተሻለች አፍሪካን ለመፍጠር አሕጉራዊ አጋርነትን ማጠናከር ወሳኝ ነው ሲሉ የሠላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም ገለጹ፡፡

የአፍሪካ አሕጉራዊ የሠላም ኮንፈረንስ “የበለፀገችና ሠላማዊ አፍሪካን እንገንባ” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ትላንት መካሄድ ጀምሯል።

የሠላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ ለመጪው ትውልድ የተሻለች አፍሪካን ለመፍጠር አሕጉራዊ አጋርነትን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡

ሠላም በድንበር የማይገደብና የሁሉም መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ እኛ አፍሪካውያን በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ ለሠላም እጅ ለእጅ ተያይዘን ልንሠራ ይገባል ብለዋል፡፡

 

የአፍሪካውያንን ብዝኃነት በመጠቀም ጠንካራ አሕጉራዊ አንድነት መፍጠር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፣ ለችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎች በማበጀት ወደ ዘላቂ ሠላም የሚያደርሰውን መንገድ መቀየስና መጓዝ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር፤ የሽግግር ፍትሕንና የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ በማቋቋም ዘላቂ ሠላምን ለማረጋገጥ እየሠራች ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ በሀገራዊ አንድነትና ለኅብረ ብሔራዊ ትርክትን ለመገንባት እየሠራች ይገኛል ብለዋል፡፡

የሰሜኑን ጦርነት በሠላም ለመቋጨትና የፕሪቶሪያው የሠላም ስምምነት እውን እንዲሆን ጥረት መደረጉን ጠቅሰው፣ በስምምነቱ መሠረት ዘላቂ ሠላም ለማረጋገጥ በመልሶ ግንባታና ማቋቋም ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የተለያዩ እምነቶችና አመለካከቶች የሚንፀባረቁባት ሀገር መሆኗን በመግለጽ፣ በሀገሪቱ የወል ትርክት ተገንብቶ ኅብረ ብሔራዊነት እንዲሰፍን ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችው የሽግግር ፍትሕ፣ ሀገራዊ ምክክርና የብሔራዊ የተሐድሶ ለሠላም ያላትን ቁርጠኝነት ማሳያዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ በአሕጉሪቱ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በቁርጠኝነት እየሠራች ትገኛለች፡፡ የአፍሪካ ሀገራት ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎችን ተግባራዊ በማድረግ በትብብር ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን ተግባራዊ እያደረገች መሆኑን ገልጸው፤ ይህም አካባቢ ጥበቃ ከሠላም ግንባታ ጥረቶች ጋር የሚመጋገብ መሆኑን ገልጸዋል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ኅዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You