አዲስ አበባ፡- በኅዳር ወር የመጨረሻዎቹ አስር ቀናት በደቡብ ምዕራብና በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ ዝናብ እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በላከው ሪፖረት፤ በኅዳር ወር የመጨረሻዎቹ አስር ቀናት በደቡብ ምዕራብና በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ ዝናብ ይኖራቸዋል፡፡
በኅዳር ወር መጨረሻ አስር ቀናት ወይም በፈረንጆቹ የዲሴምበር የመጀመሪያዎቹ አስር ቀናት በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት በደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ለዝናብ መኖር አመቺ ሁኔታ የሚፈጥሩ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች እንዳሉም ጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም በመካከለኛው፣ በምሥራቅ፤ በሰሜን ምሥራቅ፣ በሰሜንና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ከሚጠናከሩት የአየር ሁኔታ ክስተቶች አልፎ አልፎ በሚኖሩት ቀናት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደሚኖር ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
በሚቀጥሉት ቀናት በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት በደቡብና ደቡብ ምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ለዝናብ መፈጠር አመቺ ሁኔታ የሚፈጥሩ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ቀጣይነት እንደሚኖራቸው ያመላከተው ኢንስቲትዩቱ፤ በፀሐይ ኃይል ታግዞ ከሚጠናከሩት የአየር ሁኔታ በደቡብ ምዕራብና በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ይዘንባል፡፡
እንደ ኢንስቲትዩቱ ገለጻ፤ በሚቀጥሉት አስር ቀናት በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት ኦሮሚያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ሲዳማ፣ ሱማሌ፣ ሐረሪ ክልሎችና ድሬዳዋ ዞኖች ላይ በብዙ ቦታዎቻቸው ላይ ከቀላል መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ፡፡
ከሚጠናከሩት የአየር ሁኔታ ክስተቶች ላይ በመነሳት አልፎ አልፎ በሚኖሩት ቀናት ከአማራ፣ ትግራይ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ አዲስ አበባ፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ሐረሪ ክልሎችና ድሬዳዋ ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ቀላል መጠን ያለው ዝናብ ሊኖር እንደሚችል አኃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ ብሏል፡፡
በሰሜን፣ በመካከለኛውና በምሥራቅ የሀገሪቱ የመኸር ሰብል አብቃይ አካባቢዎች ላይ የሚጠበቀው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል የሚመለከታቸው አካላት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን ህዳር 17/2017 ዓ.ም