በክልሉ ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥማቸውን የመሠረተ ልማት ክፍተቶች የማስተካከል ሥራ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡- በአማራ ክልል ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥማቸውን የመሠረተ ልማትና የፋይናንስ ክፍተቶች የማስተካከል ሥራ እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ከተሞችና መሠረተ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላት በወረታ ከተማ የሚገኙ የኢንዱስትሪ መንደሮችን ጎብኝተዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የከተሞች እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የግብርና ምርትን ከኢንዱስትሪዎች ጋር የማስተሳሰር ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው።

ለዚህም በወረታ ከተማ ለኢንዱስትሪው በተሰጠው ትኩረት የተገነባና በግንባታ ላይ የሚገኝ የኢንዱስትሪ መንደርን መመልከታቸውን ገልጸዋል።

ኢንዱስትሪዎቹ ከግብዓት አቅርቦት ችግር ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማስተካከል በከተማ አስተዳደሩ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች መኖራቸውን አመልክተዋል።

የክልሉ ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥማቸውን የመሠረተ ልማትና የፋይናንስ ችግሮች መፍታት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይም የ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ዘርፈ ብዙ እያሳየ የመጣው ለውጥ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል።

ከወረታ ከተማ በቅርብ ርቀት የወረታ ደረቅ ወደብ የሚገኝ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም በአካባቢው የሚመረተውን የግብርና ምርት ከኢንዱስትሪዎች ጋር የማስተሳሰሩ ተግባር እንደሚጠናከር ገልጸዋል።

የወረታ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጌትነት ፈረደ በበኩላቸው፤ በኢንዱስትሪ መንደሩ በመጀመሪያው ምዕራፍ ባለሀብቶች ግንባታ አጠናቀው ማሽን ተከላ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በግንባታ ላይ የሚገኙት ኢንዱስትሪዎች በፍጥነት አጠናቀው ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩም አስተዳደሩ ድጋፍና ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ባለሀብቶቹ የሚያቀርቧቸውን የመንገድና ሌሎች የመሠረተ ልማት ችግሮች ደረጃ በደረጃ እየተፈቱ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ከተማዋ ካላት ብዝኃ ፀጋ ጋር ተያይዞ 22 ባለሀብቶች ቦታ ተረክበው በዱቄትና በዓሣ ማቀነባበር፤ በቺፑድ ማምረትና ሌሎች የሥራ ዘርፎች ወደ ሥራ ለመግባት እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

በአካባቢው ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ የሩዝ፣ የስንዴና የዓሣ ምርት በስፋት የሚገኝ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በእነዚህ ዘርፎች መሰማራት ፍላጎት ላላቸው ባለሀብቶች 114 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

በጉብኝቱ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ፤ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር)፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎች አመራር አባላት መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ህዳር 17/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You