ጊዜ አንዱን ሲያመጣ፤ ሌላውን ይወስዳል። አንዱ ሲወለድ ሌላው ይሞታል። ይህ የማይታበልና የማይለዋወጥ የተፈጥሮ ሕግ ነው። በዚህ የጊዜ ዥዋዥዌ ውስጥ በበጎም ይሁኑ በመጥፎ ታሪክ ይጻፋል። በጎ ሥራ ያስወድሳል፤ መጥፎው ያስወቅሳል። ይህ የታሪክ ሐቅ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሚገዛበት ሕግ ነው።
ለዛሬ ኢህአዴግን በዚህ መነፅር ለመመልከት ወደድኩ ። ሀገር ከማስተዳደር በፊት ሁለት ዓመት ሀገርን በማስተዳደር 29 ዓመታትን የቆየው ኢህአዴግም ከውልደቱ እስከ ፍፃሜው በቆየባቸው 31 ዓመታት የሚወደስበትም የሚወቀስበትም ታሪክ አለው።
የኢህአዴግ ጥንስስ 1960 ዎቹ ላይ ይጀምራል። ከቀዳማዊ ወያኔ በኋላ ትግራይ ውስጥ ከረር ያለና ውል ያለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ የተጀመረው በስልሳዎቹ መጀመሪያ ላይ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በተለይም ከዩኒቨርሲቲ የኮበለሉና በዘመኑ የነበረውን የአፄ ኃይለሥላሴን አገዛዝ በመቃወም የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ወጣቶች በየአካባቢው በድብቅ መሰባሰብ የጀመሩበት ወቅትም ነበር። ሉአላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ አቶ ገብሩ አሥራት ለንባብ ባበቁት መጽሐፍ ላይ በግልፅ እንዳሠፈሩት ከ1966 በፊት ማህበረ ገስገስቲ ብሔረ ትግራይ (ማገብት) የተባለ ህቡዕ ደርጅት በትግራይ ተቋቁሞ ነበር። ቆየት ብሎም የዚሁ ደርጅት ዓባላት የሆኑ 11 ሰዎች ወደ ደደቢት በርሃ በማቅናት የትግራይ ህዝብ አርነት ትግራይ (ተሓህት) ተመሥርቷል። በቀጣይም ስሙን ወደ ህወሓት ቀይሯል።
በ19/ 73 ከኢህአፓ ተገንጥለው በቀሩ ጥቂት ዓባላት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢህዴን) ከህውሓት ጋር በመሆን ኢህአዴግን ከመሰረቱ ድርጅቶች አንዱ ነው። ሁለቱ ድርጅቶች በ1981 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ግንባር (ኢህአዴግን) መሥርተዋል።
ክህውሓትና ከኢህዴን በመቀጠል ኦህዴድና ደኢህዴን ኢህአዴግን በመቀላቀል የኢህአዴግን ጉልበት አፈርጥመዋል። በተለይም በ1983 ኢህአዴግ የደርግን መንግሥት ገርስሶ መንበረ ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ አራቱ ድርጅቶች እስከ ያዝነው ወር አጋማሽ ድረስ ግንባር መሥርተው ለ29 ዓመታት ኢትዮጵያን አስተዳድረዋል። ምናልባትም በግንባርነት አንዲትን ሀገር ለረጅም ዓመታት ያስተዳደሩ ብቸኛ ፓርቲዎች ሳይሆኑ እንደ ማይቀሩ እገምታለሁ።
ከ1981 ጀምሮ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ሚና የነበረውና በኋላም ሀገሪቱን የማስተዳደር ዕድል ያገኘው ኢህአዴግ በቆየባቸው 31 ዓመታት እንደማንኛውም ሀገርን እንደመራ ፓርቲ በበጎም ሆነ በክፉ የሚነሱለት ታሪኮች አሉት። ኢህአዴግ አምባገነን የነበረውን የደርግ አገዛዝ በመገርሰስ ህዝቦች የነፃነት አየር እንዲተነፍሱ አድርጓል። በአፍሪካ ግዙፍ ጦር እንዳለው የሚነገርለትንና ሀገሪቱን በአምባገነናዊና ወታደራዊ አመራር ጠርንፎ ለአስራ ሰባት ዓመታት የገዛውን የደርግ ሥርዓት በትግል መጣሉ ኢህአዴግ ከሚወደስባቸውና ከሠራቸው አኩሪ ገድሎች አንዱ ነው።
የደርግን አገዛዝ ጥሎ ሀገሪቱን ማስተዳደር ከጀመረበት ከግንቦት 1983 ጀምሮም በሀገሪቱ ታሪክ አዲስ ሊባል በሚችል መልኩ በግልፅ ለብሔር ብሔረሰቦች ዕውቅና የሰጠና በ1987 በፀደቀውም ሕገ መንግሥት ይህንኑ ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና እንዲገኝ ያደረገ ፓርቲ ሲሆን ይህም ለዘመናት በማንነት ጥያቄ ስትናጥ ለነበረችው ኢትዮጵያ አንፃራዊ መረጋጋት እንዲፈጠር ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።
በአሐዳዊ አገዛዝ ዘመናትን ላሳለፈችውም ኢትዮጵያ አዲስ የፌዴራላዊ ሥርዓት እንዲዘረጋና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ኢህአዴግ በር ከፍቷል። ዜጎችም በማንነታቸው ሳይሸማቀቁ፤ ባህልና ቋንቋቸውን እንዲያበለፅጉ ዕድሉን ከፍቷል።
በሌላም በኩል ሀገሪቱን ከዕዝ ኢኮኖሚ በማላቀቅ ና የነፃ ገበያ ኢኮኖሚን በማወጅ አዲስ የኢኮኖሚ አስተሳሰብ እንዲሰርፅ ኢህአዴግ በርካታ መንገዶችን ተጉዟል። በዚህም ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት ሀገሪቱ እንድታስመዘግብ እና አንፃራዊ በሆነ መልኩ የዜጎች ህይወት እንዲሻሻል አድርጓል። የትምህርትና የጤና ማህበራዊ አገልግሎቶች በከተማና በገጠር እንዲስፋፉና ህብረተሰቡም ተጠቃሚ እንዲሆን ኢህአዴግ ብዙ ርቀት ተጉዟል። በከተሞች ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ የሄደባቸው መንገዶች ከነችግሩም ቢሆን ለበርካታ አፍሪካ አገራት ምሳሌ የሚሆን ነው።
ኢህአዴግ መሰረተ ልማትን በማስፋፋት የሚጠቀሱለት መልካም ሥራዎች አሉት። በአፍሪካ ደረጃ እንኳን ሲነፃፀር እጅግ ውስን የነበረውን የመንገድ መሰረተ ልማት እምርታዊ በሆነ መልኩ በማስፋፋት ተጠቃሽ ተግባራትን አከናውኗል። የኃይል አቅርቦትና የቴሌኮሙኒኬሽን ሥራዎቹም በኢህአዴግ ወቅት ለውጥ ካሳዩ ተቋማት ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው። እነዚህና መሰል መልካም ሥራዎች ያሉት ኢህአዴግ በ31 ዓመት ቆይታው የሚወቀስባቸውም በርካታ ህፀፆች አሉት።
ኢህአዴግ በሀገሪቱ የፌዴራል ሥርዓት ቢያነብርም የፌዴራል ሥርዓቱ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን የሚሰብክ፤ በህዝቦች መካከል መቀራረብን ከመፍጠር ይልቅ መጠራጠርና ጥላቻ እንዲነግሥ አድርጓል የሚሉ ወቀሳዎች የበዙ ናቸው። ብሔርተኝነት ፅንፍ እንዲይዝና ወጣቶችም ሥር በሰደደ ዘረኝነት እርስ በእርስ እንዲገዳደሉ ፤ ብሎም ሀገሪቱ በሰላም እጦት እንደትናጥ አሉታዊ ሚና ተጫውቷል ብለው የሚከሱት የትየለሌ ናቸው። ሌላው 29 ዓመታት ሙሉ አጋር ፓርቲዎች በሚል ሽፋን ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ባይተዋር እንዲሆኑ ማድረጉ ኢህአዴግ ከሄደባቸው ስሁት መንገዶች አንዱ ነው። ሀገሪቱን ከግማሽ በላይ የሚሸፍኑ ክልሎችን አጋር በሚል ብሂል ዜጎች በሕገ መንግሥቱ ከተሰጣቸው እራስን በእራስ የማስተዳደር መብት በተፃራሪ የሞግዚት አስተዳደር ሥር እንዲሰድ አድርጓል የሚለው ወቀሳም እስካሁን ድረስ ኢህአዴግ ነጥብ የጣለበት ክፍተቱ ነው።
የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም ከኢህአዴግ ድክመቶች ውስጥ አንዱ ነው። ኢህአዴግ ሰብአዊ መብት አረጋግጣለሁ በሚል በርካታ ቃል ኪዳኖችን ቢገባም ከቃል የዘለለ ተግባር ካለማከናወኑም ባሻገር በእሥር ቤቶች ሳይቀር ታራሚዎችን በማሰቃየትና በማንገላታት የአካልና የሥነ ልቦና ቀውስ ውስጥ እንዲገቡ ማድረጉ በርካታ እማኞች ቀርበውበታል።
ሌላኛው የኢህአዴግ ድክመት ደግሞ ሙስናና ብልሹ አሠራር ነው። ኢህአዴግ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመዘገብ የድርሻውን ቢወጣም ከዛ በከፋ መልኩ ሙስናና ብልሹ አሠራር እንዲስፋፋ መንገዱን ጠርጓል። የኢህአዴግ ፖለቲካ ለብዙዎችም የሀብት ማካበቻ ምንጭም ሆኗል። በርካቶች ወደ ኢህአዴግ ፖለቲካ ጠጋ በማለት በአንድ ጀንበር ሚሊየነር የሆኑበት አጋጣሚ ብዙ ነው። በሙስናና ብልሹ አሠራርም መንሠራፋት የተነሳ የሀገሪቱን ዕድገት የገቱ ምዝበራዎች ተፈፅመዋል። እስከ 30 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብም ከሀገር እንዲወጣ ተደርጓል። በዚህም አገሪቱ በዕዳ ቅርቃር ውስጥ እንድትገባ ምክንያት ሆኗል።
በአጠቃላይ የ31 ዓመቱ ጎልማሳ ኢህአዴግ በበጎም በክፉም የሚነሱ ታሪኮቹን ይዞ ከያዝነው ወር አጋማሽ ጀምሮ ከኢትዮጵያ መድረክ ተሰናብቷል። የሠራቸው በጎ ተግባራት ዘላለም ሲያስወድሱት እንደሚኖሩ ሁሉ ድክመቶቹም እንዲሁ እንደ ታሪክ መዝገብ እየተገለጡ ሲዘከሩ መኖራቸው አይቀሬ ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ህዳር 27/2012
ከእስማኤል አረቦ