አዲስ አበባ፦ ብልጽግና ፓርቲ እውነተኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓት እውን የሚሆንበት መሆኑን የፌዴራል ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በምስረታ ሂደት ላይ በሚገኘው የብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራምና መሠረታዊ እሳቤዎች ላይ ባደረጉት ውይይት ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት በተሳተፉበት በዚሁ ውይይት ላይ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የውጭ ግንኙነት መስኮችን ምሰሶ ያደረገው አዲሱ ብልጽግና ፓርቲ፤ የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠልና ችግሮችን በማስተካከል እንዲሁም ህብረ ብሄራዊነት እና የሀገራዊ አንድነት ሚዛን በጠበቀ መልኩ እንዲሄዱ የብልጽግና ፓርቲ ጠንክሮ እንደሚሰራ በመድረኩ ላይ ተጠቁሟል።
በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር አለሙ ስሜ ኢህአዴግ ባለፉት ዓመታት በኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ እና ማህበራዊ ዘርፎች ለውጦችን ማምጣቱን በመግለፅ ሆኖም ውስንነቶች የነበሩበት ግንባር መሆኑን አንስተው ከእነዚህም መካከል እውነተኛ ፌዴራሊዝምን አለመገንባት፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አለመከበር እና ጥራት ያለው የኢኮኖሚ እድገት አለመኖር በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።
አዲሱ የብልጽግና ፓርቲም እነዚህን ችግሮች በማረም ጠንካራና ተቀባይነት ያለው ዘላቂ መንግሥታዊ መዋቅርና ተቋማት መገንባት፣ የብሔር ማንነትና ሀገራዊ አንድነት ሚዛን የጠበቀ ማድረግ እንዲሁም አንድ ጠንካራ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመፍጠር አላማ እንዳለው ዶ/ር አለሙ አስገንዝበዋል።
ፓርቲው በተለያዩ ቡድኖችና መደቦች መካከል የነበረውን ዋልታ ረገጥነት የሚረግብበት መንገድ ስለዘረጋ ህብረ ብሄራዊ አንድነት እንደሚመጣና በአገሪቱ ውስጥ በስፋት ተንሰራፍቶ የነበረውም ጽንፈኝነት በህብረ ብሄራዊ አንድነት ሚዛናዊ እንደሚሆን ዶ/ር አለሙ አብራርተዋል።
እንደ ዶክተር አለሙ ገለጻ፤ ዘላቂ ህብረ ብሄራዊት አገር መገንባት በፀጥታ ሃይል ሳይሆን ዜጎችን ፍትሃዊና ተጠቃሚ በማድረግ የሚመጣ ነው። የብልጽግና ፓርቲ ከዚህ በፊት አግላይ የነበረውን አሰራር በማስቀረት ሁሉም ዜጎች እኩል ተጠቃሚ የሆኑበትን አሰራር ይዘረጋል። የውህደቱ አስፈላጊነትም ከዚህ በፊት በቡድኖችና መደቦች መካከል የነበረውን ዋልታ ረገጥነት የሚያስቀር ነው ብለዋል።
ከዚህ በፊት በነበረው ኢህአዴግ ማዕከላዊነት እንዳልነበረ የገለጹት ዶክተር አለሙ፤ ኢህአዴግ ወደ ውህደት ካደረጉት አስገዳጅ ምክንያቶቹም ውስጥ በግንባር ፓርቲዎች መካከል የነበረው መጠራጠርና ሁሉም በአሻው መንገድ የመጓዝ ዝንባሌ ተጠቃሾች ናቸው ብለዋል።
ዶክተር አለሙ አክለው እንደገለጹት፤ ፓርቲው እንደ ግንባር ህልውናው አደጋ ውስጥ ነበር። የፓርቲው አመራሮች በአካል ይሰባሰባሉ እንጂ ማዕከላዊነት አልነበረም። ‹‹ስንገናኝ የምናወራው ሌላ፤ ወደ ክልላችን ስንገባ የምንሰጠው መግለጫ ሌላ ነው››
ብለዋል ዶክተር አለሙ። የህግ የበላይነትን ለማስከበር አስቸጋሪ ሁኔታዎች ነበሩ። እነዚህ ችግሮችም ኢህአዴግ መዋሃድ እንዳለበት አስገዳጅ ሆነዋል። ግንባሩ መዋሃድ እንዳለበትም በተለያዩ የድርጅቱ ጉባኤዎች ሲነገሩ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።
የብልጽግና ፓርቲን የኢኮኖሚ ፕሮግ ራምም በቀረበው ጽሑፍ፤ የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ይገነባል ተብሏል። ከግብርና በተጨማሪ በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎችም ትኩረት የሚሰጣቸው ሲሆን፤ ግብርናውም በቴክኖሎጂ እንዲታገዘ ይደረጋል።
ዘመናዊ አርብቶ አደር በመፍጠር በሁሉም የግብርና ዘርፎች የወጪ ንግድን መሰረት ያደረገ ኢኮኖሚ ይፈጠራል። የገጠርና ከተማ ልማትን በማቀናጀት ገበያን መሰረት ያደረገ የሰው ሃይል ለመፍጠር እንደሚሰራም ተብራርቷል።
የብልጽግና ፓርቲ መከላከልን ማዕከል አድርጎ በጤናው ዘርፍ ላይ እንደሚሰራም በጽሑፍ ተገልጿል። የውጭ ግንኙነቱም አገራዊ ክብርን ማዕከል ያደረገ እንደሚሆንም ተገልጿል።
በዚሁ ጊዜ የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የጸደቀውን የብልጽግና ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ አቅርበዋል። ወይዘሮ ዳግማዊት እንደገለጹት፤ ውህደቱ ፖለቲካዊና ህጋዊ መንገድን ተከትሎ የተከናወነ ነው። በ11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ በተላለፈው ውሳኔ ጥናት ተደርጎበት የተፈጸመ ውህደት ነው።
በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብና በውህደቱ አስፈላጊነት ላይ የተጀመረው ውይይት በቀ ጣይም ከሌሎች ባለድርሻ አካላትም ጋር እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን ህዳር 27/2012
ዋለልኝ አየለ