“ላለው ይጨምርለታል” እንዲል ፣ አዲስ አበቤ ሰልፍ ተጨምሮለታል:: ለታክሲ ፣ ለዳቦ ፣ ለዘይት ፣ ለስኳርና ለድጋፍ ነጋ ጠባ መሰለፉ አማርሮት የማያውቀው ጨዋ ህዝብ ፣ አሁን ደግሞ መታወቂያ ለማሳደስ ሳይነጋ በየወረዳው መሰለፍ ይዟል::
ከሁለት ሳምንት በፊት ጉዳይ ጥሎኝ ቦሌ ክፍለ ከተማ በሚገኝ አንድ ወረዳ ተገኝቼ ነበር:: በርካታ ሰዎች ወፍራም ሹራብ ፣ ኮትና ካፖርት ለብሰው አንዳንዶቹም ጋቢና ፎጣ ተከናንበው ሰልፍ ይዘዋል:: ከሁኔታቸው ሰልፉ ሌሊት እንደተጀመረ መረዳት ይቻላል:: ካፖርት ወደ ለበሱ አንድ አባት ጠጋ አልኩና ለምን እንደ ተሰለፉ ጠየቅኳቸሁ:: “መታወቂያ ለማሳደስ ነው ፤ ገረመህ አይደል” አሉኝ:: ሰዓቴን ተመለከትኩ ፣ ለሶስት አምስት ጉዳይ ይላል:: ወረዳው ምንም አይነት አገልግሎት መስጠት አልጀመረም:: አጠገባቸው ቁጢጥ አልኩ:: ቀጠል አድርገው “ትናንት እንዲሁ ልጄ በጠዋት መጥታ ወረፋ ይዛልኝ ነበር ፤ ሳይደርሰኝ ቀረ:: ዛሬ እርሷ ሳትሰማ ማልጄ ተነስቼ 12 ሰዓት ሳይሞላ እዚህ ደረስኩ:: ይገርምሃል ሰባት ሰው ቀድሞ ጠበቀኝ” እርሳቸው የተገረምክ ግብዣ ስላቀረቡልኝ ሳይሆን የምር መታወቂያ ማሳደስና ማውጣት ይህን ያህል ደጅ ማስጠናቱ ደንቆኝ ተገረምኩ::
ሶስት ሰአት ከሩብ ገደማ ወረዳው አገልግሎት መስጠት ጀመረ:: ከተሰላፊዎቹ ፈንጠር ብለው ግቢ ውስጥ ጸሐይ ሲሞቁ ከነበሩ ሰራተኞች መካከል የነበረች አንድ ወጣት ወደ ተሰለፉት ሰዎች ጠጋ ብላ “40 ሰው ብቻ ነው የምናስተናግደው” አለች:: ከተጠቀሰው ቁጥር የሚርቁት ተሰላፊዎች ቁጣቸውን ገለጹ:: በአንዳንዶቹ ሁኔታ የተበሳጨችው ተናጋሪ “ነግሬያችኋለሁ ስትፈልጉ ተገትራችሁ ዋሉ የራሳችሁ ጉዳይ ነው” ብላ ወደ ውስጥ ገባች::
አገልግሎቱ የሚሰጥበትን መንገድ ለመመልከት ወደ ውስጥ ገባሁ:: እስከ አያት ያለን ስም ሶስት ጊዜ ጭንቅላታቸውን ጎንበስ ቀና እያደረጉ ጠይቀው ፣ ከሰሌዳ ላይ እንደሚገለብጥ የአንደኛ ክፍል ተማሪ “በፍጥነት” የመታወቂያ ቅጹ ላይ የሚጽፉ “የልብ አድርሶች” የሞሉበት ወረዳ ነው:: ባየሁት ነገር አዘንኩ:: ወረዳው ሁለት ሰዓት ከሰላሳ ላይ አገልግሎት መስጠት ቢጀምርና አገልግሎት ሰጪዎቹ ባይንቀራፈፉ ጠዋት ብርድ ጠብሶት ሲያበቃ ጸሐይ የሚቆላው ነዋሪ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተስተናግዶ ወደ ጉዳዩ ያመራ ነበር::
በሌሎች ወረዳዎችም ተመሳሳይ ሰልፎች ይስተዋላሉ:: በየወረዳው ምን አይነት አገልግሎት እንደሚሰጥ ፣ የሚሰጥበት መንገድ፣ የሚወስደው ጊዜና መቼ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚቻል የሚገልጽ መረጃ ተለጥፏል:: ግን ይህ ብቻውን በቂ አይደለም:: አገልግሎት ፣ አገልግሎቱን ከሚሰጠው ባለሙያ ተጽዕኖ ሊላቀቅ አይችልም:: በፈገግታ መቀበል ፣ ለደንበኛ ንግግርና ጥያቄዎች ሙሉ ትኩረትን መስጠት ፣ እርጋታን መላበስ ፣ ጥሩ አቀባበል ማድረግና ቅሬታን ለመቀበል መፍቀድ የሚቀናቸው አገልግሎት ሰጪዎች ያስፈልጋሉ:: አገልግሎት ሰጪዎች ደንበኛን በዕኩል ዓይን ማየት ፤ ታማኝ መሆን ፤ ቀጠሮን ማክበር፣ ቃላቸውን መጠበቅና ደንበኞቻቸውን ማክበር አለባቸው::
ከኃላፊነታቸውና ከሚጠበቅባቸው እላፊ እርምጃዎችን ተጉዘው ደንበኞቻቸውን ለማርካት የሚታትሩ አገልግሎት ሰጪዎች የሉም ማለቴ አይደለም:: ደውሉ ወይም በዚህ ጊዜ ኑ በማለት ፈንታ “እኔ ደውዬ አሳውቃችኋለሁ” የሚሉ ትሁት አገልግሎት ሰጪዎችም በርካታ ናቸው::
ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ይኖር ዘንድ አገልግሎት ሰጪው ተቋም ፣ ሰራተኞቹና ደንበኞች በየበኩላቸው የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው ግልጽ ነው:: ደንበኞች ተበሳጭተው ከበር በመመለስ አገልግሎት የማግኘት መብታቸውን ከማስከበር ወደኋላ ከማለት ይልቅ ለምን ? ብለው መጠየቅና አቤት ማለት አለባቸው:: አገልግሎት ሰጪዎች ደግሞ ስራቸው እንጀራቸው መሆኑን አስበው ኃላፊነታቸውን ለመወጣት መታተር ይገባቸዋል:: ወረዳዎችም በሰራተኞቻቸው መካከል ጤናማ የውድድር መንፈስን በመፍጠር ማበረታቻዎችን ቢያደርጉ ለኗሪዎች የተሻለ አገልግሎት በመስጠት ውጤታማ መሆን ይችላሉ::
በዋነኝነት ግን የአዲስ አበባ ከተማ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻል የደንበኞቹን አስተያየቶች በመቀበል ፣ አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ ማድረግ አለበት:: ኤጀንሲው ለከተማዋ ነዋሪዎች ዲጂታል መታወቂያ ለመስጠት የሙከራ አገልግሎት መጀመሩን ከገለጸ ቢሰነባብትም ጠብ ያለ ነገር የለም:: በወቅቱ አየሩን ይዞ የከረመው ዜና እንዲህ ይነበባል፡-
“አዲስ አበባ ዲጂታል የነዋሪዎች መታወቂያ በሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ መስጠት እንደምትጀምር የከተማዋ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ አስታወቀ። አዲሱ የዲጂታል መታወቂያ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አገልግሎቱ የሚጀመር ሲሆን፤ ለዚህም በቂ መታወቂያ ካርዶች መዘጋጀታቸውን በኤጀንሲው የነዋሪዎች አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ገለጹ። በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የአዲሱ መታወቂያ አሰጣጥ ጥንካሬና ድክመት ታይቶ በቀጣይ በሁሉም ክፍለ ከተማ ወረዳዎች መስጠት ይጀመራል። አዲሱ መታወቂያ የብሔር ማንነትና የትውልድ ቦታ የሚገልጽ ይዘት የሌለው ሲሆን፤ በአንጻሩ የደም ዓይነት እንዲጠቀስ መደረጉም ተገልጿል።”
አዲስ አበቤ አዲሱን ዲጅታል መታወቂያ በጉጉት ሲጠብቅ የአዲስ አበባ ነዋሪ ላልሆኑ ሰዎች “መታወቂያ ታድሏል ፤ አልታደለም” የሚል ሙግት ቀጠለ:: ነዋሪው የመርሳት ጸጋውን ተጠቅሞ የተባለውን እንዳልተባለ ቆጥሮ ለወረቀት መሰለፉን ሙጥኝ አለ:: ቀጠሮና ምክንያት ደርዳሪው ኤጀንሲ ግን በተደጋጋሚ “በቅርቡ ለሁሉም ነዋሪዎች አገልግሎቱን መስጠት እጀምራለሁ” እያለ መግለጫ ሲያወጣ አመት ሞላው::
እኔ የምለው … እንዴት ነው ይህን ዲጂታል መታወቂያ የምርጫ ቅስቀሳው አካል ሊያደርጉት አሰቡ እንዴ ? ብቻ ለስንተኛ ጊዜ እንደሆነ እንጃ ባሳለፍነው ሳምንትም ይሄው “በቅርቡ የመታወቂያው እደላ ይጀመራል” የሚል ዲስኩር ሲነገር ሰምተናል:: አመቱን ሙሉ በየቴሌቪዥን ጣቢያው በሚደጋገሙት አሰልቺ ማስታወቂያዎች መደንዘዛችን ሳያንስ ምን አድርጉ ይሉናል ?
ከሰሞኑ ደግሞ የከተማዋ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ ዲጅታል መታወቂያው ሳይለይለት፣ “ከመታወቂያ በተጨማሪም በቅርብ ጊዜ የልደት ምስክር ወረቀት በዲጅታል መልኩ እሰጣለሁ” ብሏል:: ለዚህም የከተማዋ ነዋሪዎች መረጃና አሻራ ከሰጡ በኋላ የቀጠሮ ቀናቸው በእጅ ስልካቸው እንዲደርሳቸው የሚያደርግ ቴክኖሎጂ እየተዘረጋ መሆኑን ጠቁሟል:: እሰየው ! ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘትን የሚጠላ ማን አለ? እንደ እኔ ኤጀንሲው “በቅርብ ጊዜ” እያለ የሚለቀውን ጨረር እርግፍ አድርጎ ስራውን ቢሰራ ይሻለዋል ፤ ከወቀሳም ይድናል::
ነባሩን የወረቀት መታወቂያ ለማደስ መከራውን የሚያይ ተቋም ገና ምኑንም ባልጨበጠው ሙከራ ላይ ባለ አሰራር እንዲህ መመጻደቁ ያስገርማል:: ከሰሞኑ የከተማዋ ከንቲባ የመታወቂያ አገልግሎት አሰጣጡን በወረዳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ተገኝተው ጎብኝተዋል:: በሚኖሩበት ወረዳም አሻራ በመስጠት የዲጅታል መታወቂያው መውሰዳቸው ተነግሯል:: ባሳለፍነው ሳምንት ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጄንሲ ከስራ ቀናት በተጨማሪ ቅዳሜ አገልግሎት መሰጠት መጀመሩን ያስታወቀው ከንቲባው በአንዳንድ ወረዳዎች የችግሩን ስፋት ከተመለከቱ በኋላ በሠጡት አቅጣጫ ይመስለኛል:: ኤጀንሲው በራሱ አድርጎትም ከሆነ እርምጃው የሚያስመሰግን ነው:: ነገር ግን ቀን ከመጨመር ባለፈ አገልግሎቱ የሚሰጥበት መንገድ ቢቀለጥፍ የአዲስ አበቤዎችን አዲስ ሰልፍ ማስቀረት ይቻላል::
አዲስ ዘመን ረቡዕ ህዳር 24/2012
የትናየት ፈሩ