አዳማ:- የግብርና ስራ በማዘመን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ማሽነሪዎች ከውጭ ለሚያሥገቡ ከቀረጥ ነጻ አሰራር መፈቀዱ የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።በዋና ዋና ሰብሎች ከ382 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኝት መታቀዱንም አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ የሩብ ዓመቱን የዕቅድ አፈጻጸም ከክልሎች ጋር በገመገሙበት ወቅት ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን እንደተናገሩት፤ በቀጣይ የግብርናውን ስራ ለማዘመን፣ የምርት አሰባሰቡን ቀልጣፋ ለማድረግ እና ወደ ሜካናይዜሽን ግብርና ለመግባት ከውጪ ማሽነሪዎችን የሚያስገቡ አካላት ከቀረጥ ነጻ አሰራር ተፈቅዷል።
የማሽነሪዎቹ ከቀረጥ ነጻ መግባት ለቀጣዩ የምርት ዘመን ጥሩ ሁኔታን እንደሚፈጥር የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣በዘንድሮው የመኸር እርሻ በዋና ዋና ሰብሎች 382 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱንም አስታውቀዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት ከደረሱ ሰብሎች መካከል 50 በመቶ ያህሉ ተሰብስቧል። ከዚህ በኋላም ባለን የትንበያ መረጃ መሰረት ዝናቡ በመጪዎቹ ሁለት ሳምንት የማይጥል በመሆኑ፤ በነዚህ ጊዜያት ምርቶችን ሙሉ በሙሉ እንዲሰበሰብ ይደረጋል ብለዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መለሰ መኮንን በበኩላቸው፤ ዘንድሮ በክልሉ በተደረገ የምርት ጉብኝት የተሻለና ከፍተኛ ምርት የሚገኝበት ሁኔታ እንዳለ ተገንዝበናል ብለዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት ከ2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የሚሆን መሬት በሰብል በተለይም በስንዴ ተሸፍኗል። ከሄክታርም ከ50 ኩንታል በላይ ምርት እየተገኘ ነው። ይህ ደግሞ የመኸር እርሻን ውጤታማ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
የኦሮሚያ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የእቅድ ዝግጅትና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ጸጋዬ ታደሰ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በክልሉ በዓመቱ 6 ሚሊዮን 64 ሺ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ፤ በዘር የተሸፈነው 6 ሚሊዮን 100 ሺ ነው። ይህ ደግሞ ከዕቅድ በላይ ነው።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በመኸር ለነዚህ መሬቶች የሚያስፈልጉ ኬሚካሎች፣ መድሀኒቶች፣ ዘርና ሌሎችንም ግብዓቶች በማሟላት በኩል ሰፊ ስራ እንደተሰራ ጠቁመዋል።
ከመጠን በላይ የሆነ ዝናብና የቆላ አንበጣ በግብርና ስራው ላይ ጫና አሳድሮ እንደነበር ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፤ ችግሮቹን ለመፍታትም ከፍተኛ ርብርብ መደረጉን አብራርተዋል። የደረሱ ሰብሎችን በተለይም ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ጉዳት እንዳይደርስባቸው በቅንጅት እንዲሰበሰቡ እየተደረገ መሆኑን አመልክተ ዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 25/2012
እፀገነት አክሊሉ