አሁን አሁን ሁሉም ነገር ፖለቲካ እየሆነ በተቸገርንባት “አፍቃሬ ፖለቲካዋ” ኢትዮጵያችን ከፖለቲካ ውጪ ሌላ ህይወት የሌለ እስኪመስል ድረስ በጓዳም፣ በጎዳናም፣ በቤትም፣ በመስሪያ ቤትም፣ በተናጠልም በሚዲያም አየሩን ሁሉ የተቆጣጠረው ፖለቲካው ነው። በተለይም በዋናውም ይሁን በማህበራዊ (ፖለቲካዊ ሚዲያ ቢባል ይቀላል) ሚዲያው ሰፊውን ቦታ የያዙት ፖለቲካዊ አለያም በግዴታም ቢሆን ፖለቲካ እንዲሆኑ የተደረጉ ጉዳዮች ናቸው።
የሚወራውም የሚጻፈውም ከፖለቲካዊ አንድምታው አኳያ እየታየ ነው ማለት ይቻላል። በእርግጥ ይህ ለምን እንደሆነ “ሆነ” ከማለት ባሻገር ሁሉም ነገር ፖለቲካ እየሆነ የመጣበትንና ሁሉም ፖለቲከኛ የሆነበትን ምክንያት ቀደም ሲል በዚህ አምድ ላይ ባቀረብኩት ጽሑፍ ለማሳየት ሞክሬያለሁ። ዛሬ በድጋሜ ያነሳሁት በጉዳዩ ላይ ልጽፍበት ሳይሆን ከፖለቲካው ባሻገር ልናወራላቸውና ልንጽፍላቸው የሚገቡ ሌሎችም በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን ለማስታወስና የበኩሌን በተግባር ለማሳየት ነው።
የፖለቲካውን ያህል ባይሆንም ከሰሞኑ አነጋጋሪ ሆነው ከሰነበቱ ጉዳዮች መካከል ከሁለት ሳምንታት በኋላ ታኅሣሥ 7 ቀን 2012 ዓ.ም (በአየር ጠባይ ምቹ አለመሆን ምክንያት ሳተላይቷ የምትመጥቅበት ቀን ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ተገልጿል) ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋን ሳተላይት ወደ ጠፈር እንደምታመጥቅ መገለጹ አንደኛው ነው። ሆኖም ከርዕሰ ጉዳዩ ትልቅነት እና ታሪካዊነት አኳያ በቂ የሚዲያ ሽፋን አለማግኘቱና ሰፊ የመወያያ አጀንዳ አለመሆኑ በእጅጉ እንድገረም አድርጎኛል።
ፖለቲካው ምን ያህል እንደተጫነንና ሌላ ነገር እንዳናስብ አዕምሯችንን በቁጥጥሩ ስር አውሎ በእኛ ሳይሆን በእነርሱ ፍላጎት እየመራን(እየነዳን ቢባል ይቀላል) መሆኑን እንድታዘብ አድርጎኛል። በጣም የሚገርመው ነገር ደግሞ ጉዳዩ ፖለቲካ ነክ ከሆነ ትንሿን ነገር ሳይቀር እያጋነነ፣ የማይገናኘውን በግድ አገናኝቶ ፖለቲካ እያደረገ፣ እየጮኸና እያስጮኸ አገር ምድሩን ሲያዳርሰው የሚውለው “ማህበራዊ ሚዲያ” ተብዬው ኢትዮጵያ ሳተላይት ልታመጥቅ ነው ስለሚለው ዜና ያን ያህል ሲጨነቅ አለመታየቱ ነው። ሰው ማባላት ሲሆን ናይጀሪያ ውስጥ የሆነውን ኢትዮጵያ ውስጥ የሆነ ለማስመሰል ዓይኑ እስኪፈዝ ድረስ “አዶቤ” ላይ አፍጥጦ የሚውለውና አገር ምድሩን በ“ፎቶ በተደገፈ ዜና” የሚያጥለቀልቀው ማህበራዊ ሚዲያ በዚህ ጊዜ መናገር ተስኖት ዓይጥ የዋጠች ድመት ሆኖ ጥጉን ይዞ ሲቁለጨለጭ መሰንበቱ አጃኢብ የሚያስብል ነው።
ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ የሆነውን ሳተላይት ወደ ህዋ እንደምታመጥቅ የሚያበስረው ዜና መሰማቱን ተከትሎ በጥቂቱም ቢሆን በተሰወኑ አካላት ዘንድ የመወያያ ርዕስ ሆኖ ቢነሳ እንኳን የሚነሱት ጉዳዮች በአብዛኛው ትችትን ያዘሉ መሆናቸው ደግሞ የበለጠ ግርምትን ስለፈጠረብኝ “ግን ለምን?” የሚል ጥያቄን አጭሮብኛል። እናም ጉዳዩን በሚመለከት እኔም የራሴን ምልከታ እንዳቀርብ ምክንያት ሆኖኛል።
ዕውቀት ጎደል ትችቶች
ከሚቀርቡ ትችቶች መካከልም “ብዙ ችግር ባለባት አገር ውስጥ(የአገሪቱን ፖለቲካ ሁኔታ በዋነኝነት ያነሳሉ) በተጨማሪም በልቶ ማደር እንኳን አስቸጋሪ በሆነባት ድሃ አገር የህዋ ሳይንስ ያን ያህል አስፈላጊ ነገር ነውን? “ስንት መቅደም የሚገባቸው ነገሮች እያሉ በአሁኑ ሰዓት ሳተላይት ማምጠቅ ይህን ያህል ትኩረት ማግኘት ያለበት ጉዳይ ነውን? “ሳይንሱ ውድ ከመሆኑ የተነሳ ከሚያስወጣው ወጪ አኳያ እንደ አገር የሚያስገኘው ጥቅም፣ አጠቃላይ ፋይዳውስ ምንድነው? ”የሚሉት ከሚቀርቡ ትችቶች መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
ትችቶቹ የህዋ ሳይንስን ሁለንተናዊ ፋይዳ ያልተገነዘቡና ዕውቀት የጎደላቸው መሆናቸውን ማስገንዘብ ይገባል። ምክንያቱም እዚህ ላይ የሚቀርበው ትችት ለአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገት ከፖለቲካ በተጨማሪ ሳይንስና ቴክኖሎጂም እጅግ ወሳኝ ነገር መሆኑን ግምት ውስጥ ያላስገባ በመሆኑ ነው። የዘርፉ ምሁራንና ባለሙያዎች እንደሚያስገነዝቡት የህዋ ሳይንስ በማንኛውም የልማት ዓይነት ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልና በትልቁ ከሰው ህይወት ጋር የተቆራኘ ሁለንተናዊ ፋይዳ ያለው ሳይንስ ነው።
የእኛን አገር ጨምሮ በሌሎችም የሳይንሱ ፋይዳ ባልተገለጸላቸው ታዳጊ አገራት ዘንድ የህዋ ሳይንስ ለድሃ አገራት አያስፈልግም የሚል የተሳሳተ አመለካከት አለ። በዚህ ረገድ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት እንደ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ እና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የመሳሰሉ ተቋማት ለዓመታት ያደረጉት ጥረት ፍሬ ማፍራት የጀመረ ይመስላል። በአመለካከት ላይ ትኩረት ተደርጎ በመሠራቱ መንግሥትም ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት ጀምሯል።በዘርፉ አበረታች ጅምር ለውጦች መታየትም ጀምረዋል።
አንድ መቶ ሚሊዮን ብር የወጣበት የእንጦጦ ስፔስ ኦብዘርቫቶሪ የህዋ የምርምርና ስልጠና ተቋምን በማሳያነት ማንሳት ይቻላል። ሁለት ዘመናዊ ሳይንቲፊክ ቴሌስኮፖች ተገዝተውለት የምርምር ሥራውን እያከናወነ ይገኛል። ከጥናትና ምርምር ሥራው ጎን ለጎን በዘርፉ ባለሙያዎችን ለማፍራትና ሳይንሱን ለማስፋፋት ተቋሙ በአሁኑ ሰዓት በአምስት የትምህርት ዘርፎች በመስኩ ትምህርትና ስልጠና እየሰጠ ይገኛል። በተጨማሪም ማህበሩ ባደረገው ከፍተኛ ጥረት የህዋ ሳይንስ በመደበኛው የአገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ተካትቶ የሚሰጥበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ለአብነትም በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ፣ በጅማ ዩኒቨርሲቲና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህዋ ሳይንስ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ድረስ ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል። እንዲህ እንዲህ እያለ የመጣው የኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስ ዛሬ ላይ ባለታሪኳ አገራችን የመጀመሪያ የሆነውን ሳተላይት ወደ ጠፈር ለማምጠቅና ሌላ አዲስ አኩሪ ታሪክ ለመጻፍ ቀጠሮ ይዟል።
ከኃያላኑ ምን እንማራለን?
ለልማትም ባይሆን የህዋ ሳይንስ ፋይዳ ቀድሞ የገባት አገር ጀርመን ነበረች። የሁለቱም የዓለም ጦርነቶች ቀስቃሽ ጀርመን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጨረሻ አካባቢ በመከላከያ መስሪያ ቤቷ አማካኝነት የመጀመሪያውን ሰው ሠራሽ ሮኬት ወደ ጠፈር በማስወንጨፍ ተቀናቃኟን ለማጥቃት ሞክራ ነበር። ሙከራም ብቻ ሳይሆን ለጊዜውም ቢሆን በጠላቶቿ ዘንድ የበላይ መሆን ችላ ነበር።
የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃቱን ተከትሎ ግን አውሮፓውያንን ተክታ ብቅ ያለችው አዲሲቷ ኃያል አገር አሜሪካ በበኩሏ ለኃያልነቷ መሰረት የጣለችው በህዋ ሳይንስና በሳተላይት ቴክኖሎጂ ነበር። ይህንንም ለማድረግ ያኔ እንደለመችው ህልሟ ተሳክቶ ዓለም በቁጥጥሯ ስር የሆነላት ኃያል እየተባለች የምትጠራው ብልጧ አገር አሜሪካ 500 ሚሊዮን ዶላር የሚሆን ግዙፍ ገንዘብ መድባ የህዋ ሳይንስ ምርምርን ጀመረች። ምርምሩን ለመጀመር የሚያስችል የተማረ የሰው ኃይል ያልነበራት ብትሆንም እንደ እኛ “ሳይንሱ ለድሃ አገር አይሆንም” ብላ እጅና እግሯን አጣጥፋ አልተቀመጠችም ነበር። የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲያበቃና ጀርመን ስትሸነፍ ሥራውን ቀድመው ጀምረው ሮኬት ማስወንጨፍ ጀምረው የነበሩ የጀርመን ሳይንቲስቶችን ማርካ ወደ አገሯ ወስዳ ስለነበር በጠላት ዕውቀት የሳተላይት ሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምርን አስጀመረች።
እንደ አውሮፓውኑ አቆጣጠር ጥቅምት አራት ቀን 1957 ሌላኛዋ ኃያል አገር ሩስያ ከአሜሪካ ቀድማ የመጀመሪያውን ሰው አልባ መንኮራኩር(ስፑትኒክ ዋን) ወደህዋ በማምጠቅ ጠፈር ላይ አሳረፈች። ጠፈር ላይ በማረፍ ሩስያውያን ፈር ቀዳጅ ቢሆኑም አሜሪካውያኑ ደግሞ ጨረቃ ላይ ቀድመው በመውጣት በአጭር ጊዜ ውስጥ በዘርፉ የፈጠሩትን ትልቅ አቅም ለዓለም አሳይተዋል። እነሆ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ለኃያላኑ ብቻ የሚያስፈልግ እስኪመስል ድረስ የህዋ ሳይንስ የሁለቱ አገራት ዋነኛ መፎካከሪያ መድረክ ሆኖ ቀጥሏል። ለመሆኑ እነዚህ ሁለቱ የዓለማችን ኃያላን ለህዋ ሳይንስ ይህን ያህል ትኩረት የሰጡበት ምክንያቱ ምን ይሆን?
ከስፔስ ሳይንስ ተፈላጊነት ጀርባ ያሉ ምስጢሮች
የህዋ ሳይንስ ተመንዝሮ የማያልቅ ፋይዳ ያለው ተግባራዊ ሳይንስ መሆኑን ዘርፉን በሚገባ ያጠኑ ምሁራን ይመሰክራሉ። በዚህ ረገድ ላለፉት አርባ ዓመታት በአገር ውስጥና በውጭ አገር በዘርፉ በግላቸው ምርምር ሲያካሂዱ የቆዩትና በአሁኑ ሰዓት “ያዝሚ” የተባለ የግል ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ኖህ ሳማራ የተባሉ ኢትዮጵያዊ የጠፈር ሳይንስ ተመራማሪ ከህዋ ሳይንስ ተፈላጊነት ጀርባ ያለውን ምስጢር በአንድ መድረክ ላይ እንዲህ ገልጸውት ነበር።
‹‹አሁን በከፍተኛ የብልጽግና ደረጃ ላይ የሚገኙት እንደነ አሜሪካና ሩስያ የመሳሰሉ አገሮች ሥር ነቀል ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ያካሄዱትና ሁለንተናዊ ዕድገት ያመጡት ለህዋ ሳይንስ በሰጡት ከፍተኛ ትኩረት ነው። ለአገሬ ዕድገት በምን በኩል አስተዋፅኦ ማድረግ እንዳለብኝ ብዙ ጊዜ ሳስብ መልሱ የህዋ ሳይንስን መሆኑ ገባኝ። በተለይም በዘርፉ ሊቃውንት ዘንድ ‹የህዋ ሳይንስ ልብ› እየተባለ የሚጠራው የሳተላይት ሳይንስና ቴክኖሎጂ በአገር ዕድገት ላይ አብዮታዊ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ተገንዝበው በአሁኑ ሰዓት በርካታ የዓለማችን አገራት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ ይገኛሉ። እናም የህዋ ሳይንስ የብልጽግና ምልክት ብቻ ሳይሆን የብልጽግና ጎዳናም ነውና በእኛም አገር የታየው መልካም ጅምር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል እንላለን።››
በእርግጥ የህዋ ሳይንስ ለድሃ አገራት አያስፈልግምን?
ምንነቱ ያልገባቸው፣ ፋይዳው ያልተገለጸላቸው ወይንም ገብቷቸውም ቢሆን ከለመዱት የፖለቲካ ንግግር ሌላ መናገርና መስማት የማይፈልጉ ባለ አንድ አቅጣጫ(Uni-directional) መንገደኞች እንደሚሉት የህዋ ሳይንስ ለበለጸጉ አገራት ብቻ የሚያስፈልግ የቅንጦት ሳይንስ አይደለም። እንዲያውም ነገሩን ጠልቆ ለመረመረ ሰው ካደጉትና የብልጽግና ማማ ላይ ከደረሱት አገራት ይልቅ የህዋ ሳይንስ በጣም የሚያስፈልገው ለድሃና ለታዳጊ አገራት እንደሆነ ይገባዋል። ምክንያቱም የህዋ ሳይንስ በተለይም ደግሞ አሁን አገራችን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የምትሞክረውና በዘርፉ ምሁራን ዘንድ “የህዋ ሳይንስ ልብ” በመባል የሚወደሰው የህዋ ሳይንስ በማንኛው ዘርፍ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልና በአገር ሁለንተናዊ ዕድገት ውስጥ ቁልፍ ሚና ሊጫወት የሚችል ተመንዝሮ የማያልቅ ፋይዳ ያለው ተግባራዊ ሳይንስ በመሆኑ ነው። የሳተላይት ቴክኖሎጂ በአየር ትንበያ መረጃና በግብርና፣ በምህንድስና፣ በመረጃና በቴሌ ኮሙኒኬሽን፣ በከተማ ልማት፣ በኢንዱስትሪ፣ በውትድርና ሳይንስና በአገር ደህንነት፣ በህክምናና በጤና፣ በትምህርትና ማህበራዊ ለውጥ፣ በአየር ንብረት ብክለት ቁጥጥርና በአካባቢ ጥበቃ…በአጠቃላይ በሁሉም የልማት መስኮች ውስጥ ከፍተኛ ጥቅም ያላቸው ዕውቀቶች የሚገኙበት ከሁሉም በላይ ከፍ ያለ ፋይዳ ያለው የተግባር ሳይንስ ነው። ይህም በአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሁለንተናዊ ዕድገት ቁልፍ ሚናን ይጫወታል።
ስለሆነም በእኛ አገር የሳተላይት ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ መዋል መጀመረ ወጣቱ ትውልድ የሚያጋጥሙትን ችግሮች በአግባቡ መፍታት እንዲችልና አገሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከኋላ ቀርነት አላቅቆ ዘመኑ የደረሰበት የዕድገት ደረጃ ላይ ለማድረስ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል። ከሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያውያንና ቻይናውያን ኢንጅነሮች በትብብር የተፈበረከችውና ታኅሣሥ ወር ከቻይና ምድር ወደ ጠፈር የምትመጥቀው ታሪካዊቷ የኢትዮጵያ ሳተላይት “የምድር ምልከታ” ከሚባሉት የሳተላይት ዓይነቶች የምትመደብ ሲሆን፤ ዋነኛ ተልዕኮዋም የአገሪቱ የጀርባ አጥንት የሆነውን የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማዘመን የሚያግዙ መረጃዎችን መሰብሰብ ነው።
በእስከአሁኑ ሙከራ ያልተሳካውን ግብርናውን የማዘመንና የዘርፉን ትራንስፎርሜሽን ሂደት ዕውን ለማድረግ በሚደረገው ርብርብ ውስጥ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል የሚል ተስፋ ፈጥሯል። የግብርናው መዘመንና የኢኮኖሚ ሽግግሩ ዕውን መሆን በበኩሉ ዜጎችን ከድህነትና ከኋላቀርነት ለማላቀቅና የሚፈለገውን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማምጣት የሚያስችል አቅም ይፈጥራል።
ከዚህ ድንቅ የሳይንስ በረከት ለመካፈልና ለአገር ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያበረክተውን ፈርጀ ብዙ ፋይዳ በተግባር ለመጠቀም ሳይንሱ እንዳያድግ የዘርፉ የዘመናት ማነቆ ሆኖ የቆየውን “ምግብ ሳይጠገብ ምን የሚሉት የህዋ ምርምር ነው” በሚል የተሳሳተ አመለካከት ሳይደናቀፉ ጅምሩን አጠናክሮ መቀጠል ከሁሉም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ለማስታወስ እንወዳለን።
እንደ ስፔስ ሳይንስ ዓይነት ሳይንሶችና ቴክኖሎጂዎች ለአደጉ አገራት ብቻ የተፈቀዱ የቅንጦት ዕውቀቶች ሳይሆኑ ለድሃና ለታዳጊ አገራትም አስፈላጊ መሆናቸውን መተንተን ያስፈልጋል።
አገር በፖለቲካ ብቻ አትኖርም
በአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገት ውስጥ ፍልስፍና፣ ዕውቀት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ያላቸው አስተዋፅኦ ለማይታያችሁና አገር በፖለቲካ ብቻ የምትኖር ለምትመስላችሁ ወገኖቼ አውዱ የተለያየ ቢሆንም የኢየሱስን ቃል ተውሼ በኢየሱስኛ የንግግር ዘዬ አንድ ነገር ልበላችሁ፤ “ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ በሚወጣ ኃይል ጭምር እንጅ አገር በፖለቲካ ብቻ አትኖርም”። ታዋቂው የኢንተርፕርነር ምሁር አሰልጣኝና ደራሲ ዶክተር ወሮታው በዛብህ በአንድ ወቅት ለተማሪዎች የምረቃ ሥነ ሥርዓት በተዘጋጀ መድረክ ላይ አሜሪካ የምትባለውን ኃያል አገር በመገንባት ሂደት ውስጥ ከፖለቲከኞች በላይ ሳይንቲስቶች፣ ምሁራንና ኢንተርፕርነሮች የነበራቸው ሚና የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። እንዲያውም ኃያሏን አሜሪካ የፈጠሯት እንደ ቬንደር ቬልት፣ ጀ.ኬ ሞርጋንና አንድሬው ካርኒጌ የመሳሰሉ በከፍተኛ ደረጃ በሥራ ፈጠራ የተካኑ ጥቂት ግለሰቦች መሆናቸውን “ሜን ሁ ቢዩልት አሜሪካ” የሚል የፊልም ሥራን በማስረጃነት በመጥቀስ በአንድ ግንባታ ሂደት ውስጥ ከፖለቲካ ውጪ የሆኑ ዕውቀቶች ያላቸውን ከፍተኛ ዋጋ አስረድተዋል። የእኔ አመለካከትም ከዚሁ ብዙ የሚርቅ ስላልሆነ ነው ይህን ጽሑፍ የምጽፈው። ምናልባት ከዶክተር ወረታው የምለየበት ምክንያት ለአገር ግንባታ ፖለቲከኞችም ምሁራንም እኩል ሚና አላቸው ብዬ የማምን በመሆኔ ነው። ሁሉም ሰው በያለበት ሙያ ለአገሩ ትልቅ ሥራ መሥራት ይችላል ብዬ አስባለሁ።
ከፖለቲካው ባሻገር ሳይንስና ቴክኖሎጂን ሌሎችም ዕውቀቶች ለአገር ዕድገት ያላቸውን ሚና አስመልክቶ የሃሳብ ተጋሪዬ በሆኑት የዶክተር በፍቃዱ ኃይሉ ምልከታ ልሰናበታችሁ።
“….እንደሚታወቀው አገራችን ላለችበት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበረሰባዊ፣ የስነ-ልቦናና የባህል ችግር፣ እንዲሁም የፖለቲካና የርዕይ ችግር የብሄረሰብ መብትን በማወቅ የሚፈታ ነገር አይደለም። የአገራችን ችግሮች ፖለቲካዊ፣ መንግሥታዊ፣ ስነ-ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ የአካባቢ መውደም ወይም መቆሸሽ ጉዳይና፣ እንዲሁም የሳይንስና የቴክኖሎጂ ጥያቄዎች እንደመሆናቸው መጠን ጠቅላላውን በዛች ምድር የሚኖረውን ህዝብ የሚመለከቱ ናቸው። ይህም ማለት ያሉት ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት፣ በፍልስፍና፣ በሶስዮሎጂ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ብቻ ነው።
‹‹በሌላ አነጋገር፣ በአገራችን ምድር አፍጠውና አግጠው የሚታዩት ችግሮች፣ ማለትም የከተማዎች በስነ-ስርዓት አለመገንባትና ህዝባችንም ባልባሌ ቦታዎች እየተሰቃየ መኖር፣ የሚጠጣው፣ የሚቀቅልበትና የሚታጠብበት ንጹህ ውሃ አለማግኘት፣ አስፈላጊው ለሰውነት ገንቢ የሆኑ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን በብዛትም ሆነ በጥራት አለማግኘት፣ ለማሞቂያ፣ ለመቀቀያና ለመብራት የሚያገለግል የኃይል ጉዳይ፣ የህክምናና የትምህርት ጉዳይ፣ ለወጣቱ የሙያ ማሰልጠኛ ቦታ አለማግኘት፣ በየቦታው የሥራ መስክ የሚከፍቱ ትናንሽና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች አለመኖር ወዘተ… እነዚህ ጥያቄዎች በሙሉ ህብረተሰባዊ እንደመሆናቸው መጠን የብሄረሰብን መብት በማወቅ የሚፈቱ ሳይሆኑ፣ በጠለቀና ተከታታይነት ባለው የሳይንስ ምርምር ብቻ ነው።
‹‹ሊያሠራ የሚችል፣ ኃይልን የሚሰበስብና በአገር ውስጥ ያለንን የተፈጥሮ ሀብት በስነስርዓት አውጥተን በቴክኖሎጂ አማካይነት ለመለወጥና የህዝባችንን ፍላጎቶች ለመመለስ የምንችለው አንዳች ዓይነት ርዕይ ሲኖረን ብቻ ነው።” እኛም ፖለቲካንም ሳይንስንም ማናቸውም ነገሮች ቢሆኑ አገርን የሚጠቅሙ እስከሆኑ ድረስ እኩል እንውደድ፣ እኩል ትኩረት እንስጣቸው፣ እናውራላቸው፣ እንጻፍላቸው! ኢትዮጵያ ለዘመናት ትኑር!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ህዳር 24/2012
ይበል ካሳ