«ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው»
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
“ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” የሚሉት አባባል አለ። የቀደሙቱ አባት እናቶቻችን ይህንን አባባል ሲናገሩ ያለምክንያት አልነበረም። ጦርነት ሕዝብ አስጨራሽ፣ አገር አፍራሽ ስለሆነ፤ ከጦርነት በሚብስ ሁኔታ ደግሞ ወሬ አስከፊ ውጤት ስለሚያስከትል ነው።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በምድረ-ኢትዮጵያ ሚሊዮኖች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። በርካቶች በብሔራቸው ተለይተው ግፍ ተፈጽሞባቸዋል። ንብረታቸው ወድሟል፤ ተዘርፏልም። አብያተ-ክርስቲያናት እና መስኪዶች ተቃጥለዋል። የአገልጋዮችና የምዕመናን ደም ፈሷል።
ይህ ሁሉ የሆነው በጦርነት አልነበረም፤ በወሬ እንጂ። በማህበራዊ የትስስር ገጾችና በሚዲያዎች አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ የሚያደርጉ፣ ብሄርን፣ ሃይማኖትን ወይም የፖለቲካ አስተሳሰብን መሰረት ያደረጉ ወሬዎች በመሰራጨታቸው አገሪቱ ለዚህ ሁሉ ችግር ተጋልጣለች።
ከዚህ ሁሉ በኋላ “የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ” በሚል ረቂቅ ሕግ ተዘጋጅቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሰሞኑ ቀርቧል።
የጥላቻ ንግግር ሕግ ወሰን እና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሚዛናዊነት
የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ራሱን የቻለ ሕግ መውጣቱን ተከትሎ አንዳንዶች መንግስት የተቺዎቹን አፍ ለማዘጋት የሚያወጣው በመሆኑ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ይናገራሉ። ገሚሶቹ ደግሞ የሕጉን መውጣት በመርህ ደረጃ ቢደግፉም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን እንዳይጋፋ ይሰጋሉ።
ያም ሆነ ይህ ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ፣ ከሌሎች አገራት ተሞክሮና ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሥምምነቶች አንጻር ሲታይ የሕጉ አስፈላጊነት ክርክር አይነሳበትም። አገራችን በወሬ ልትፈታ ስጋት ውስጥ ወድቃለች። በናዚ የአይሁዶች ጭፍጨፋና የርዋንዳው የዘር ፍጅት፤ በአሁኑ ወቅትም በማይንማር የሮሂንጊያ ሙስሊሞች ወደ ባንግላዴሽ መሰደድ ለእኛም የማንቂያ ደወል ነው።
ኢትዮጵያ የፈረመችውና እኤአ በ1965 ዓ.ም. የወጣው ሁሉንም ዓይነት የዘር ልዩነቶችን ለማስወገድ የተደረገው ዓለም አቀፍ ሥምምነት አገሮች ብሔራዊ የበላይነትን የሚሰብኩ ወይም የዘር ጥላቻንና ልዩነትን የሚያራምዱ ተቋማትንና ንግግሮችን ለማስወገድ ሕግ ማውጣት እንዳለባቸው ያስገነዝባል። እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ኢጣሊያ፣ ዴንማርክና ሌሎችም የአውሮፓ አገራት ከናዚ መንኮታኮት ማግስት የጸረ-ጥላቻ ንግግር ሕግ አውጥተዋል። ከዚህ መነሻ ታዲያ በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግር ለመከላከል ሕግ መውጣቱ ካሳለፍነው ችግር አንጻር ሲታይ ዘግይቷል ከሚባል ውጭ አስፈላጊነቱ ላይ ጥርጣሬ አይኖርም።
ይልቁንም ሕጉ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የሚጋፋ እንዳይሆን ነው ጥንቃቄ የሚያስፈልገው። እርግጥ ነው ሃሳብን በነጻነት መግለጽ መሰረታዊ ከሚባሉት መብቶች ውስጥ አንዱ ነው። ይሁንና የሕዝብንና የአገርን ደህንነት አደጋ ላይ እስከሚጥል ድረስ ተለጥጦ የሚተገበር ሳይሆን ልጓም የሚበጅለት መብት ነው። ረቂቅ አዋጁ ባለፈው ሳምንት ለፓርላማ ሲቀርብ “ሀሳብን በነፃነት በመግለፅ ሽፋን የሚከሰቱ ጥላቻን፣ ማግለልን፣ ግጭትን፣ ጥቃትንና መሰል በግለሰቦችና በማህበረሰቡ መካከል ያለውን መልካም ግንኙነትን የሚያሳሱና የሚጎዱ ንግግሮችንና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን በህግ መከላከል ያስፈልጋል” በሚል ከአስፈጻሚው የቀረበው ማብራሪያም መነሻው ይኸው ነው።
እናም የጥላቻ ንግግር መከላከያ ሕጉ ወሰንና የያዛቸው ድንጋጌዎች ሃሳብን በነጻነት ከመግለጽ መብት ጋር ሚዛናቸውን የጠበቁ መሆን አለባቸው። ከሁሉም በላይ ሕጉ ግልጽ መሆን አለበት። ለዴሞክራሲ መሰረት የሆነውን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በማይጋፋ መልኩ በጠባቡ የሚተረጎምና ለመንግስት አካላት የተለጠጠ ሥልጣን የማይሰጥ መሆን አለበት። ስለዚህ በመብቱ ላይ የሚጣል ገደብ ተመጣጣኝ ከሆነና በጥንቃቄ ተግባራዊ የሚደረግ እስከሆነ ድረስ ሕጉ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተቀባይነት ያለው ነው።
በእነዚህ መሰረታዊ ሃሳቦች መነጽርነት ታዲያ ረቂቅ አዋጁን እንደሚከተለው እንቃኘው።
የጥላቻ ንግግርና ሃሰተኛ መረጃ
በአዋጁ መሰረት የጥላቻ ንግግር ማለት በአንድ ሰው (የተወሰነ ቡድን) ላይ ያነጣጠረ፣ ብሄርን፣ ብሄረሰብንና ህዝብን፣ ሃይማኖትን፣ ዘርን፣ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ ጥላቻን፣ መድሎን ወይም ጥቃትን የሚያበረታታ ንግግር ነው።
ሃሰተኛ መረጃ የሚባለው ደግሞ ውሸት የሆነና የመረጃውን ውሸት መሆን በሚያውቅ ወይም መረጃውን የሚያሰራጨው ሰው ካለበት አጠቃላይ ሁኔታ አንጻር የመረጃውን ሃሰተኝነት ሊያውቅ ይገባ ነበር የሚያስብል በቂ ምክንያት እያለ የሚሰራጭ ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ እድሉ ከፍ ያለ ንግግር ነው። በዚሁ መነሻ የጥላቻ ንግግርን ወይም ሃሰተኛ መረጃን በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማህበራዊ ሚድያ በጽሁፍ፣ በምስል፣ በድምጽ ወይም በቪድዮ ማሰራጨት ወንጀል ነው።
ሕጉ ሃሰተኛ መረጃን ሲተረጉም “… ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ እድሉ ከፍ ያለ ንግግር ነው” የሚል አገላለጽ መጠቀሙ ግልጽነት ስለሚጎድለውና ለትርጉም ስለሚጋለጥ “… ጥቃት እንዲደርስ የሚያደርግ ንግግር ነው” በሚል መስተካከል ይኖርበታል።
ከዚህ ሌላ በግለሰብ ላይ ያነጣጠረ የጥላቻ ንግግርን ማሰራጨት የተከለከለ ቢሆንም ግለሰብን የተመለከተ ሃሰተኛ መረጃን ማሰራጨት ስለመከልከሉ አዋጁ በግልጽ አያሳይም። ያም ሆኖ አንቀጽ 7(5) “…ሃሰተኛ መረጃ በመሰራጨቱ ምክንያት በግለሰብ (በቡድን) ላይ ጥቃት የተፈጸመ ወይም…” በሚል የተገለጸው ድንጋጌ ግለሰብን የተመለከተ መረጃን ማሰራጨትም በሕጉ ሊከለከል እንደሚገባ አመላካች በመሆኑ ይኸው በግልጽ መቀመጥ ይኖርበታል።
የአንቀጽ 6 እና የሕጉ ዓላማ ተቃርኖ
ረቂቅ አዋጁ የጥላቻ ንግግርን ወይም ሃሰተኛ መረጃን በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማህበራዊ ሚዲያ ማሰራጨትን በመከልከል ወንጀል አድርጓቸዋል። አንቀጽ 6 ደግሞ አንድ ንግግር እንደ ጥላቻ ንግግር ወይም እንደ ሃሰት መረጃ ተወስዶ ለማሰራጨት የማይከለከልባቸውን ልዩ ሁኔታዎች አስቀምጧል። እነዚህም ንግግሩ (መረጃው) የትምህርታዊ ወይም ሳይንሳዊ ምርምር አካል፤ የዜና ዘገባ፣ የትንታኔ ወይም የፖለቲካ ትችት አካል፤ የኪነጥበብ፣ የትወና ወይም መሰል የስነጥበብ ውጤት እንዲሁም የሃይማኖታዊ አስተምህሮ አካል እንደሆነ ነው።
መንግስት ለዚህ ያቀረበው ምክንያት “ህጉ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ ሊኖረው የሚችለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ ነው” የሚል ነው። ይሁንና የሕጉ ዓላማ የጥላቻ ንግግርንና የሃሰት መረጃዎችን መከልከል እስከሆነ ድረስ ሊተኮርበት የሚገባው ጉዳይ የንግግሩ ወይም የመረጃው ይዘት የጥላቻ ወይም የሃሰት መሆን/ያለመሆኑ ነው። ስለዚህ በየትኛውም መልኩ የሚተላለፍ የጥላቻ ንግግርም ሆነ የሃሰት መረጃ በሕጉ የሚያስቀጣ መሆን አለበት። ይህ መሆኑ ደግሞ የዜጎችን መብት የሚገድብ ሳይሆን በማንኛውም መንገድ ሃሳባቸውን በነጻነት ሲገልጹ ከጥላቻ ንግግርና ከሃሰት መረጃ እንዲቆጠቡ ያደርጋቸዋል።
የብሮድካስትና የማህበራዊ ሚዲያዎች መደበላለቅ
የአዋጁ መሰረተ ሃሳብ የጥላቻ ንግግርን ወይም ሃሰተኛ መረጃን በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማህበራዊ ሚድያ ማሰራጨትን መከልከል ነው። ይሁንና የብሮድካስትና የማህበራዊ ሚዲያዎች በየራሳቸው ያላቸውን ልዩና ነባራዊ ሁኔታ ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ አይመስልም።
የብሮድካስት ሚዲያዎች (በአዋጅ ቁጥር 590/2000 መሰረት መገናኛ ብዙሃን በሚል የሚጠሩትን የህትመት ሚዲያዎችን ጨምሮ) ስለአመዘጋገባቸው፣ ሥለአሰራራቸው፣ ሥለ አደረጃጀታቸውና ስለኤዲቶሪያል ጉዳዮቻቸው በሕግ በተቀመጠ ሥርዓት የሚመሩ ናቸው። በአንጻሩ በአብዛኛው ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚባሉት ተቀማጭነታቸውን በውጭ አገራት ያደረጉና ከአገራችን የሕግ የግዛት ወሰን ውጭ ናቸው። የማህበራዊ ሚዲያ የሕግ ማዕቀፍም የለንም። በመሆኑም በእነዚህ በሁለቱ የሚዲያ ዘውጎች የሚሰራጩ መረጃዎችን ለመቆጣጠር ተመሳሳይ የሕግ ማዕቀፍ መቅረጽ ለአፈጻጸም አስቸጋሪ መሆኑ አይቀርም።
ከዚህ በተጨማሪ ረቂቅ ሕጉ የጥላቻ ንግግርን ወይም ሃሰተኛ መረጃን በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማህበራዊ ሚዲያ ማሰራጨትን የሚከለክል ሆኖ ሳለ “የአገልግሎት ሰጪዎች ግዴታ” በሚል ባስቀመጠው ድንጋጌ ውስጥ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ግዴታን በመጣል የብሮድካስትና የሕትመት ሚዲያዎችን ከግዴታ ውጭ አድርጓቸዋል።
በማህበራዊ ሚዲያዎቹ ላይ ብቻ የተጣለው ይህ ግዴታ በይዘቱም ሆነ ከአፈጻጸም አንጻር ሲታይ መሰረታዊ ሕጸጾች አሉበት። በይዘት ረገድ ማንኛውም የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመቆጣጠርና ለመግታት ጥረት ማድረግ እንዳለበት መደንገጉ በራሱ “ምን ዓይነት ጥረት?” ኢትዮጵያ ውስጥ ሕጋዊ ሰውነት ተሰጥቶት የሚንቀሳቀስ የማህበራዊ ሚዲያ ድርጅትስ አለ ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችን ስለሚያስነሳ ግልጽነት ይጎድለዋል።
በተጨማሪም “ማንኛውም የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት የጥላቻ ንግግርን ወይም የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን የተመለከተ ጥቆማ ሲደርሰው በፍጥነት ይህን መሰል መልዕክቶችን ወይም ንግግሮችን ከአገልግሎት አውታሩ ሊያስወግድ ይገባል” ይላል። ይህ በእርግጥም የመፈጸሙ ነገር ጥያቄ ምልክት ውስጥ የገባ ድንጋጌ ነው።
“በፍጥነት” የሚለው ለትርጉም የተጋለጠ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በሕጉ ውስጥ ማህበራዊ ሚዲያዎችን ሕጋዊ ሰውነት እንዳለው አካል የሚመለከት፤ መስራቾቻቸውን ወይም ባለቤትና የተለያዩ የስራ ኃላፊዎቻቸውንም የተመለከተ ድንጋጌ የለም። “በፍጥነት” መረጃው ስለመጥፋቱ የሚከታተል አካልስ ማን ነው? “በፍጥነት” በማያስወግድ ማህበራዊ ሚዲያ ላይስ ምን ዓይነት ርምጃ ይወሰዳል? ጥቆማውስ ከማን ነው መቅረብ ያለበት? የሚሉት መሰረታዊ ጥያቄዎችም በሕጉ ምላሽ የላቸውም።
በጣም የሚያስገርመው ድንጋጌ ደግሞ ማንኛውም የማህበራዊ ሚዲያ ግዴታውን ለመወጣት የሚያስችለው አሰራርና ፖሊሲ ሊኖረው እንደሚገባ የሚደነግገው ነው። በዚህ ሳይበቃ ሕጉ አሰራርና ፖሊሲ ባልዘረጉት ላይ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን እየተከታተለ ለህዝብ ይፋ የሚሆን ሪፖርት እንደሚያዘጋጅ ይገልጻል። ባለኝ መረጃ እስካሁን በኢትዮጵያ ውስጥ “የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ድርጅት” የሚል ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው ድርጅቶች ስለመኖራቸው እርግጠኛ አይደለሁም። ነገር ግን የምንጠቀማቸው አብዛኞቹ ማህበራዊ ሚዲያዎች ተቀማጭነታቸውን በውጭ አገራት ያደረጉና ከአገራችን የሕግ የግዛት ወሰን ውጭ ስለመሆናቸው እርግጠኛ ነኝ። ነባራዊው እውነታ ይህ ሆኖ ሳለ ሕጉ እንዲህ ያለ ድንጋጌ መያዙ አስገራሚ ሆኗል።
ሌላው ሳይጠቀስ ሊታለፍ የማይገባው ጉዳይ አዋጁ የብሮድካስት ባለስልጣንና የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሃሰት መረጃ ስርጭትና ጉዳትን ለመከላከል የሚረዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮችን የማዘጋጀት ኃላፊነት የጣለባቸው መሆኑ ነው። በተቋማት ላይ የኃላፊነት መደራረብን የሚያመጣ ከመሆኑም በላይ የሀብትና የሰው ኃይል ብክነትን የሚያስከትል ብሎም ለተጠያቂነት አሰራር እንቅፋት እንደሚሆን ግልጽ ነው።
የወንጀል ድንጋጌዎቹ ሕጸጾች
በአገራችን ከባድ አደጋን ጋርጧል የተባለውን ችግር ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተቀረጸው ይህ አዋጅ አስር አንቀጾች ብቻ ናቸው ያሉት። ከእነዚህ ውስጥ የወንጀል ተጠያቂነትን የደነገገው አንቀጽ 7 መሰረታዊ የሚባሉ ሕጸጾች አሉበት። የመጀመሪያው ለየድርጊቶቹ የተቀመጡት ቅጣቶች አነስተኛ መሆናቸው ነው። እርግጥ ነው የወንጀል ቅጣት ተቀዳሚ አላማው ፈጻሚውንና ማህበረሰቡን ማስተማር ቢሆንም ቅሉ፤ ከድርጊቶቹ አደገኛነት አንጻር በአጥፊዎች ላይ ተመጣጣኝ ቅጣት ሊጣል ይገባል። በመሆኑም በወንጀል ሕጉና በኮምፒውተር ወንጀሎች አዋጅ በሌሎች የማነሳሳት አድራጎቶች ላይ ከሚጣለው ቅጣት ያልተናነሰ፤ እንዲያውም ከፍ ያለ ቅጣት ሊቀመጥ ይገባል።
ሌላው ጉዳይ የወንጀል ተጠያቂነቶቹ የሚያጠነጥኑት የጥላቻ ንግግሩን ማድረግ ወይም የሃሰት መረጃውን ማሰራጨት ላይ ሲሆን፤ የሚቀጡትም እነዚህን ድርጊቶች የፈጸሙትን ሰዎች ነው። ከዚህ ውጭ ግን ኮሜንት፣ ሼር፣ ላይክ፣ ሪትዊትና መሰል የስርጭት ተሳትፎዎችን በተመለከተ ሕጉ ምንም የሚገልጸው ነገር የለም።
የአዋጁ አንቀጽ 7(4) የጥላቻ ንግግሩ ወይም ሃሰተኛ መረጃው የተሰራጨው ከአምስት ሺ በላይ ተከታይ ባለው የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ከሆነ ቅጣቱን በማክበድ አስቀምጧል። ይሁንና ይህ “ከ5ሺ በላይ ተከታይ” የሚለው መለኪያ በሕጉ የተቀመጠበት አመክንዮ ግልጽ አይደለም። ይሁንና በርካታ ተከታዮች ባሉት ማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨ የጥላቻ ንግግር ወይም ሃሰተኛ መረጃ ለበርካቶች ስለሚደርስ ከባድነቱን ለማመልከት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።
ያም ሆነ ይህ ግን የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ ወይም ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑ ከግምት ውስጥ እንዲገባ ባልተደረገበት ሁኔታ 5ሺ ተከታዮች ባሉት ማህበራዊ ሚዲያ ገጽ የተሰራጨን መረጃ 4999 ተከታዮች ካሉት ማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ለይቶ በማክበድ ቅጣት ማስቀመጥ በዘፈቀደ የተገመደለ እንጂ ቅቡልነት ባለው አመክንዮ የተቀረጸ አይመስልም። ይህ ብቻ ሳይሆን በርካታ ተከታይ ያላቸው ገጾች ባለቤት የሆኑ ተጠቃሚዎችስ በተከታዮቻቸው ወይም በሃሰተኛ ስም የጥላቻ ንግግር ወይም ሃሰተኛ መረጃ በገጻቸው ላይ ቢሰራጭ የሚኖርባቸው ተጠያቂነት ምንድን ነው የሚለውን ሕጉ በዝምታ አልፎታል።
ከወንጀል ተጠያቂነት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ቁልፍ ጉዳይ የወንጀል አድራጊዎቹን የመለየት ፈተና ነው። በተለይም በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮችና የሃሰት መረጃዎች የሚፈበረኩት በሃሰተኛ ስሞች ወይም ማንነታቸው ባልተለዩ ተዋንያን ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ ወንጀል ፈጻሚዎቹን በትክክል ለይቶ ለሕግ እንዳይቀርቡ እንቅፋት ነው።
ከዚህ መነሻ ታዲያ ረቂቅ አዋጁ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የማስረጃ አሰባሰብም ሆነ የሥነ-ሥርዓት ማዕቀፍ አልዘረጋም። በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የጥላቻ ንግግሩን “ወዲያውኑ” እንዲያስወግዱ ግዴታ ሲያስቀምጥ የወንጀሉ ማስረጃ እየጠፋ መሆኑንም የዘነጋው ይመስላል። አዋጁ በኮምፒውተር ወንጀሎች አዋጁና በማቋቋሚያ አዋጁ ውስጥ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በተለይም የኦንላይን መረጃ ሥርጭቶችን በተመለከተ ቀጥተኛ ኃላፊነት ሊሰጠው የሚገባውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲን ገሸሽ ማድረጉ ደግሞ የሕጉን ተፈጻሚነት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ያደርገዋል።
የአዋጁ አንቀጽ 7(7) የተከለከሉት ተግባራት የተፈጸሙት በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ከሆነ የወንጀል ሕጉ ድንጋጌዎች ተፈጻሚ እንደሚሆኑ ይገልጻል። ከጅምሩ ይህ ድንጋጌ ወንጀሉ የተፈጸመው ከአምስት ሺ በላይ ተከታይ ባለው የማህበራዊ ሚድያ ገጽ ከሆነ ወይም በብሮድካስት አገልግሎት ወይም በየጊዜው በሚወጣ የህትመት ውጤት ከሆነ ቅጣቱን ከሚያከብደው ከአንቀጽ 7(4) ጋር ሲነጻጸር ድግግሞሽ ነው።
ያም ሆኖ ወደ ወንጀል ሕጉ መምራቱ በራሱ ችግር አለበት። ምክንያቱም በወንጀል ሕጉ ከአንቀጽ 42 እስከ 47 ያሉት በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት በሚደረጉ ወንጀሎች ተካፋይ መሆንን የሚመለከቱ የመርህ ድንጋጌዎች እንጂ ዝርዝር የወንጀል አንቀጾች አይደሉም። በመሆኑም በመገናኛ ብዙሃን ውስጥ የተቋሙን ሕጋዊ ሰውነት ጨምሮ የተለያየ ድርሻ ያላቸው አካላት (ዋና አዘጋጅ፣ ሪፖርተር፣ ብሮድካስተር፣ አሳታሚ፣ አታሚ፣ አከፋፋይ ወዘተ) በመኖራቸው የትኛው አካል የትኛውን የአዋጁን ድርጊት ሲፈጽም ምን ዓይነት የወንጀል ተጠያቂነት አለበት የሚለውን ሕጉ በግልጽ ማሳየት አለበት።
የወንጀል ተጠያቂነትን በሚደነግገው የአዋጁ አንቀጽ ውስጥ ያልተካተቱ ነገር ግን መካተት ያለባቸው ጉዳዮች ከሚባሉት ውስጥ የጥላቻ ንግግሩን ወይም የሃሰት መረጃውን ያሰራጨው የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ በሚሆንበት ጊዜ ቅጣቱ ከብዶ እንዲጣል የሚያደርግ ድንጋጌ አንዱ ነው። በተጨማሪም የመገናኛ ብዙሃን ለሚፈጽሙት ወንጀል ማረሚያ የማውጣት፣ ተጎጂዎች ካሉ ሃሳባቸውን ያለክፍያ እንዲያቀርቡ የማድረግና እና ሌሎች ግዴታዎችም በተጨማሪነት ሊጣልባቸው ይገባል። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ሌሎች ወንጀል ደንጋጊ አዋጆች እንደሚያደርጉት የወንጀል ክሶቹ የሚቀርቡበትንና የመዳኘት ሥልጣን ያለውን ፍርድ ቤት ሕጉ ሊያመለክት ይገባል።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ህዳር 24/2012
በገብረ ክርስቶስ