
የጥራትና ደረጃዎች አስፈላጊነት ለምርቶች እጅግ ወሳኝ መሆኑን አለም በአንድ ድምጽ የሚስማማበት ሀቅ ነው:: ጥራትና ደረጃ ማረጋገጥ ደግሞ ከምርት አመራረቱ የሚጀምር ሲሆን፤ አሰባሰብ፣ አቀማመጥ፣ አጫጫንና ወደ ገበያ የማውጣት ሂደትንም ታሳቢ የሚያደርግ ነው::በዚህ መካከል የሚፈጠሩ ችግሮች ደግሞ ምርቶች ከደረጃ በታች እንዲሆኑ ያደርጋሉ::
ምርቶች እንዲህ ባለው መልክ ተዘጋጅተው ለገበያ በሚቀርቡበት ወቅት ጥራታቸውን፣ ደረጃቸውን፣ እንዲሁም የሚይዙትን ግብዓትና የመጠቀሚያ ጊዜያቸውን አስመልክቶ ደረጃ የሚያወጣላቸው አካል በየአገራቱ ይገኛሉ::
በኢትዮጵያ “ የደረጃዎች ኤጀንሲ” የምርቶቹን ጥራት፣ የአገልግሎት ዘመናቸውን፣ የሚያካትቱትን ግብዓት፣ እየተከታተለና እየለካ ጥራት እያረጋገጠ ለገበያ ያቀርባል:: በሌላም በኩል ይህንን ደረጃ ለሚያወጡ ባለሙያዎች በውስን አቅሙ ስልጠናዎችን ይሰጣል:: ይህንን ቢያደርግም አሁንም የምርት ጥራት ጉድለት የአገሪቱ አንገብጋቢ ችግር ሆኖ ቀጥሏል::
ይህንን የምርት ጥራት ችግር እንዴት ማለፍ ይቻላል? አሁን ያለው ሁኔታ ምን ያህል ተስፋ ሰጪ ነው? ስንል ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳለ መኮንን ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል::
አዲስ ዘመን ፦ የኤጀንሲው የስራ ድርሻና ያለበት ሀላፊነት ምንድን ነው?
አቶ እንዳለ፦ ኤጀንሲው በዋናነት በሦስት ዋና ዋና ዘርፎችን መሰረት አድርጎ ይሰራል:: በዚህም በብሔራዊ ደረጃ፤ ደረጃ ማውጣት ፣ ደረጃዎች ተግባራዊ እንዲደረጉ የቴክኒክ ድጋፍና ስልጠና መስጠትና የደረጃዎች መረጃ መስጠትም ከስራ ሀላፊነቶቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው:: በዚህ መሰረት በአገሪቱ የሚመረቱና ከአገር ውጪ የሚመጡ የተለያዩ የምግብና የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ደረጃ በማረጋገጥ በገበያው ላይ እንዲሰራጩ ያደርጋል::
አዲስ ዘመን ፦ እነዚህን ዋና ብሎ ያስቀመጣቸውን ተግባራት በማከናወን በኩል ኤጀንሲው ስኬታማ ነኝ ብሎ ያምናል ?
አቶ እንዳለ፦ ደረጃ የሚዘጋጀው በቴክኒክ ኮሚቴዎች አማካይነት ነው:: እነዚህ ኮሚቴዎች የሚደራጁት ደግሞ ከተለያዩ ተቋማት ተውጣጥተው ነው:: በአንድ ኮሚቴ ላይ ቢያንስ አስር ተቋማት ይወከላሉ:: ከዚህ አንጻር የተሻለ ስራ መስራት አለብን ብለን በማሰብ 101 የነበሩትን የቴክኒክ ኮሚቴዎች ወደ 201 እንዲያድጉ ተደርጓል:: ወደፊትም የሚመጡ አዳዲስ ዘርፎች ካሉ እነሱንም በደንብ ሊያካትት በሚችል መልኩ እያዋቀርንና እየሰራን እንገኛለን::
በዋናነት የደረጃ መነሻ የሚሆነው ሁለት ነገር ነው፤ አንደኛው ከአለም አቀፍ ወይም አህጉራዊ የሆኑ ደረጃዎችን በቀጥታ የምንወስድበት ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ በምርምር የተደገፉ አገር በቀል ደረጃዎችን መስጠት ነው:: በተለይም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጡት ደረጃዎች በምርምር መደገፍ ስላለባቸው ከህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን ስምምነት በመፈራረምና በዚያ መሰረት ወደ ስራ እንዲገቡ የማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ ነው::
አዲስ ዘመን፦ በተለይም አገር አቀፍ ደረጃ ያላቸው ሆነው እንዲወሰኑ የተደረጉ ምርቶች ምን ዓይነት ይዘት ይኖራቸዋል?
አቶ እንዳለ ፦ አገር አቀፍ ይዘት ያላቸው ደረጃዎች ሆነው እንዲቀጥሉ እየተሰራባቸው ያሉ ምርቶች እንደ ሽሮ፣ በርበሬ፣ በሶ፣ የገብስ ቆሎ፣ የአበሻ አረቄና ጠጅ ናቸው:: የእነዚህን ምርቶች ደረጃ አገር አቀፋዊ አደርጎ ለመቀጠል ዝርዝር የሆነ ምርምር ያስፈልጋል:: ምርምሩ ካለቀ በኋላ እነዚህ ስድስት አገር በቀል ምርቶች መለያ እንዲኖራቸው ይደረጋሉ ማለት ነው:: ይህ መለያቸው ደግሞ ከውጭ በሚመጡት ምርቶች ላይ እንደምናየው ምን ያህል የአልኮል፣ የፕሮቲን ወይም ሌላ ያላቸው ይዘት ይገልጻል:: እስከ መቼ መጠቀም ይቻላል? በምን ዓይነት ቦታ ላይ መቀመጥ አለባቸው? የሚሉና ሌሎች መሰረታዊ የደረጃ መመዘኛዎችን ይይዛሉ ማለት ነው::
አለም አቀፍ ወይም አህጉራዊ ሆነው ከውጭ የምናመጣቸው ደረጃዎችም ሙሉ በሙሉ ባንወስዳቸውም ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እያናበብን እንጠቀምባቸዋለን:: ይህ የማጣጣም ስራ የሚሰራው የአገሪቱ የአየር ጸባይ፣ ሙቀቱ፣ ብርዱ እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን አይተን ነው:: ለምሳሌ በውጭው ዓለም ላለው ከፍተኛ ቅዝቃዜ የተሰራ ደረጃ ለእኛ አይሆንም ፤ ስለዚህ ከእኛ ሁኔታ ጋር እንዲጣጣም ተደርጎ ነው ደረጃው የሚዘጋጀው::አዲስ ዘመን፦ ኤጀንሲው በዓለም አቀፍም ሆነ አህጉራዊ ከሆኑ መሰል ተቋማት ጋር ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል?
አቶ እንዳለ፦ ደረጃ እንደ አገር ይዘጋጃል፤ በአህጉር ደረጃ ደግሞ የማጣጣም ስራ ይሰራል ፤ ይህ ሲባል ደግሞ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ “የአፍሪካ ሪጅናል ስታንዳርድ ኦርጋናይዜሽን” አባልን መስራች ነው፤ የውሳኔ ሰጪው ካውንስልም አባል ነው ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በአለም አቀፍ ደረጃ የአይሶ ሙሉ አባል ሲሆን አይ ኢሲ፣ ኮዴክስ ሙሉ አባል ነው::
በመሆኑም ከእነዚህ ተቋማት ጋር የነቃ ተሳትፎን እናደርጋለን:: በእነርሱ አማካይነት የሚዘጋጁ ደረጃዎች ደግሞ አገር ውስጥ መጥተው እኛም ምርቶቻችንን በእዛ መሰረት የምንገመግምበት አግባብ እንዲፈጠር እናደርጋለን::አዲስ ዘመን፦ አገር አቀፍ ይዘት ያላቸው እንደ ሽሮ፣ በርበሬ፣ በሶ፣ ቆሎ፣ ጠጅና አረቄ ለበርካታ ዓመታት ስንጠቀምባቸው የቆዩ ናቸው፤ ለእነዚህ ደረጃ ማውጣት ለምን አስፈለገ?
አቶ እንዳለ፦ እዚህ ላይ ደረጃ ማለት የንግድ ቋንቋ ነው:: ማንም ምንም ይናገር ምን በንግድ አለም መግባቢያው ደረጃዎችን የያዙ ወረቀቶች ናቸው:: ስለዚህ ጠጁ የሚሸጠው ከወረቀት ጋር ነው::ምን ዓይነት ወረቀት የተባለ እንደሆነ ደግሞ የአልኮል መጠኑን፣ ለጤና ጠንቅ የሆኑ ነገሮች አለመኖራቸውን የአገልግሎት ጊዜው እስከዚህ ድረስ ነው፤ እንዲሁም በዚህ መጠን ሙቀት ወይም ቅዝቃዜ መቀመጥ አለበት ማለት መቻል ይኖርበታል::
ሁል ጊዜ አገር በቀል ደረጃዎች ሲዘጋጁ ሻጭና ገዢ ሊግባቡበት የሚችሉበት ደረጃ ሊኖረው ይገባል::ለምሳሌ ጠጅን ወደ ውጭ ስንልክ ዝም ብለን መረጃ የሌለውን ጠርሙሱን ብቻ መላክ አንችልም:: ምክንያቱም ያ ተጠቃሚ የአልኮል መጠኑ ስንት ነው ብሎ ሲጠይቅ መናገር መቻል ያስፈልጋል:: ሽሮን ብንወስድ በውስጡ ያሉ ጠቃሚ ይዘቶቹ ምንድን ናቸው? ተብሎ ለሚጠይቅ በቂ መልስ መኖር አለበት:: ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ወጥ የሆነና የራሱ መስፈርት ሊኖር ሲችል ነው::
በጠቅላላው ግን ደረጃ ሲባል ምንም ሰው ሳይኖር ምርቱ የትም ቦታ ሄዶ እራሱን ሊገልጽ የሚችል ማለት
ነው:: ዝም ብሎ ምርትን በባዶ መላክ ግን በገበያው ላይ ተፈላጊነትን የሚያሳጣ ነው::
አዲስ ዘመን፦ አሁን በተደጋጋሚ ተቋማት የአይሶ ተሸላሚ ነን እያሉ ማስታወቂያ ያስነግራሉ፤ ምንም እንኳን አይሶ ሽልማት ባይሆንም፤ የእነዚህ ተቋማት ማስታወቂያ በእናንተ በኩል ያለው ተቀባይነት ምን ያህል ነው?
አቶ እንዳለ፦ መጀመሪያ እኛ የማንስማማው የአይሶ ተሸላሚ ነን ማለታቸው ላይ ነው:: ምክንያቱም አይሶ አይሸልምም :: ምንም ዓይነት የሽልማት ስርዓትም የለውም:: አይሶ አለም አቀፍ ደረጃ ነው የሚያወጣው፤ በዚያ መሰረት ያመረተ ተቋም ደግሞ የሶስተኛ ወገን የማረጋገጫ ሂደትን አልፎ በአይሶ 9001/ 2015 መሰረት አሟልተዋል ብሎ ሰርተፍኬት ይሰጠዋል::
አዲስ ዘመን፦ በዚህ የጥራት ማረጋገጫ ሂደት ላይ ግን የኤጀንሲው ተሳትፎ የለም ማለት ነው?
አቶ እንዳለ፦ እኛ እንደ ተቋም የቴክኒክ ድጋፍና ስልጠና እንሰጣለን:: ይህ ሲባል ደግሞ የኤጀንሲው ሁለት ባለሙያዎች ወደ ኢንደስትሪው በመሄድ የአሰራር ስርዓቱ የአይሶ 9001 ወይም ሌላ ሊሆን ይችላል ግን ተቋማችሁ እነዚህን ነገሮች ማሟላት ከቻለ የብቃት ማረጋገጫው ይሰጠዋል በማለት የተለያዩ እንደ ተቋሙ የስራ ባህርይ የሚያስፈልጉ ሲስተሞችን ይዘረጋሉ፤ እነዚህ ሙሉ በሙሉ መስራት ሲጀምሩ ባለሙያዎቹ ይወጣሉ:: ከዚያም ሶስተኛ ወገን መጥቶ እያንዳንዱን ስራ ከመስፈርቱ ጋር በማስተያየት ትክክል መሆኑን ያረጋግጣል:: ማሟላታቸው ሲረጋገጥ የብቃት ማረጋገጫውን ይሰጣቸዋል:: ካላሟሉ ደግሞ የሚቀሩት ነገሮች ተገልጸውላቸው ለቀጣይ ዓመት እንዲሰሩበት ይደረጋሉ::
አዲስ ዘመን፦ ስለዚህ ኤጀንሲው ቴክኒካል ድጋፍ ማድረግና ስልጠና መስጠት ነው ተቀዳሚ ሃላፊነቱ፤ ስልጠናው ተደራሽና በቂ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ እንዳለ ፦ አዎ ኤጀንሲው በተለይ ስልጠናውን በእያንዳንዱ ማኔጅመንት አሰራር ዙሪያ ይሰጣል፤ ሆኖም ባለው የቦታ ውስንነት ምክንያት በበቂ ሁኔታ መስጠት አልቻለም:: እንደ አገርም በጣም ውስንነት ያለበት አገልግሎት ነው በመስጠት ላይ ያለነው:: ለምሳሌ ከተለያዩ ክልሎች ለአምስትና ከዚያ በላይ ቀናት ስልጠና ሊወስዱ የሚመጡ አካላት አሉ፤ በቂ የሆነ ማረፊያ ቦታ ስለሌለ በተገቢው ሁኔታ ስልጠናውን መውሰድ አልቻሉም::
አዲስ ዘመን፦ ስልጠናው መሰረታዊ ከመሆኑ አንጻር ችግሩን ለሚመለከተው አካላት አላቀረባችሁም በምንስ ልትፈቱት አቅዳችኋል?
አቶ እንዳለ ፦ ኤጀንሲው የሚሰጠው ስልጠና እንደ አገር የምንፈልገውን ደረጃ ለማምጣት ወሳኝ በመሆኑም ችግሩን ይዘን ቁጭ አላልንም፤ በግቢው ውስጥ ባለው ቦታ ላይ “አገራዊ የደረጃዎች አካዳሚ” እየገነባን ነው:: በውስጡም 40 ያህል አልጋዎች በተሟላ ሁኔታ የያዘ ነው:: ይህ ማለት ደግሞ ከአገር ብቻ ሳይሆን ከጎረቤት አገራትም እየመጡ አገልግሎቱን የሚያገኙበት ቦታ እንደሚሆን እርግጠኛ ነን:: በቀጣዩ ሚያዝያ ወር ተመርቆ ወደ ስራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል::
ህንጻው ከተጠናቀቀ በኋላም ከመላው አገሪቱ የሚመለከታቸውን አካላት እየጠራን በማሰልጠን ጥሩ የደረጃዎች ባለሙያን ለማውጣት እንሰራለን::
አዲስ ዘመን፦ የደረጃዎች ኤጀንሲ በስልጠና ያበቃል እንጂ ሰርተፍኬት አይሰጥም ማለት ነው?
አቶ እንዳለ ፦ ሰርተፍኬት የሚሰጠው አካል እኮ ሶስት ቀን ነው ለኦዲት ስራ የሚመጣው፣ ኤጀንሲው ግን በትንሹ ከስድስት ወር እስከ ሁለት አመት ድረስ በየተቋማቱ ሲስተሙን ለመዘርጋት ይሰራል:: በመሆኑም ትልቁ ስራ የስልጠናና ቴክኒክ ድጋፉ ነው::
በሌላ በኩል ደግሞ ኤጀንሲው በ 9001፣ 14 ሺ፣ 22ሺ፣ 50ሺ፣ 27ሺና በሌሎችም የማኔጅመንት አካሄዶች ላይ ስልጠና በመስጠት ሰርተፍኬት ይሰጣል:: ለምሳሌ አይሶ 9001 ሰርቲፋይ ለማድረግ ስልጠናው የሚፈጀው አምስት ቀን ነው:: ፈተናው ከታለፈ ይሰጣል ማለት ነው::
አዲስ ዘመን፦ ተቋማት በዚህ ረገድ ሰልጥነው ራሳቸውን ለማብቃት ምን ያህል ፍቃደኛ ናቸው?
አቶ እንዳለ ፦ አሁን ላይ ከአቅም በላይ ነው እየመጡና ፍቃደኛነታቸውን እያሳዩ ያሉት፤ በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ የኮንስትራክሽን ካምፓኒዎች፣ አምራቾች፣ አገልግሎት ሰጪዎች፣ ስልጠና የሚሰጡ ተቋማት (ካይዘንናና ስራ አመራር ኢንስቲትዩት) ይመጣሉ::
ሰልጣኞች ይመጣሉ ግን የተመቻቸ የስልጠና መስጫ ቦታ አለመኖሩ አስቸጋሪ ሁኔታን ፈጥሯል:: በቡድን ሆነው ለመወያየት፣ የቤት ስራ ለመስራት፣ መድረክ ላይ ሊያቀርቡት የሚችሉ ጽሁፎችን ለማዘጋጀት በጣም አስቸጋሪ ነው:: ወደፊት ግን ህንጻው ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ችግሩ ሙሉ በሙሉ ስለሚፈታ ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን እናወጣለን::
አዲስ ዘመን ፦ ይህንን ያህል ቢሰራም አሁንም የምግብ ግብዓቶችን ጨምሮ የኢንዱስትሪ ምርቶች፣ የኮንስትራክሽን እቃዎች ከደረጃ በታች እየሆኑ በሰው ጤና ላይ ጉዳት እያደረሱ በኢኮኖሚው ላይም ትልቅ ጫና እያሳደሩ ነው፤ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ እንዳለ፦ ይህ ሁኔታ ወደፊትም የሚቀጥል ነው:: ምክንያቱም ጥራትን ማረጋገጥ የአንድ ተቋም ሀላፊነት ወይም እርሱ ብቻውን የሚወጣው ተግባር አይደለም:: እዚህ ላይ የመገናኛ ብዙኃን በማሳወቅ በማስገንዘብ በኩል ሀላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው:: ሌላውና ዋናው ደግሞ ተጠቃሚው እራሱ ይህንን ችግር መቆጣጠር መቻል አለበት ፤ በሌላው ዓለም ያለ አሰራር በመሆኑ፣ ስለዚህ ጥራት ማረጋገጥ የብዙ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ የሚጠይቅ ብዙ ሊሰራበት የሚገባ ወደፊትም ቢሆን ምርቶች እየበዙ ተቋማት እየጨመሩ ኢንዱስትሪውም በዚያው ልክ አቅሙን እያጎለበተ ሲሄድ ተቆጣጣሪ አካላትም እየጠነከሩ የደረጃ አረጋጋጭ አካሉም ከችግሮቹ እየቀደመ መሄድ አለበት::
አዲስ ዘመን፦ በተለይም አሁን ላይ እየታዩ ያሉ የጥራት ችግሮች ገና የሚቀጥሉ ናቸው እያሉ ነው?
አቶ እንዳለ፦ በየሰፈሩ ባዕድ ነገሮችን ቀላቅለው የሚያበሉን እኮ ኤጀንሲው ስለሰራ ስላልሰራ ወይም ሌላ ተቆጣጣሪ አካል ዝም ስላለ አይደለም፤ የእነሱ የሞራል ውድቀት የፈጠረውና ገበያን ብቻ ታሳቢ አድርጎ የመስራት ችግር ነው:: ይህም ቢሆን ግን ማህበረሰቡን በማስተማር ግንዛቤውን በማሳደግ ጠያቂ እንዲሆን በማድረግ ችግሩን ማቃለል ይቻል ይሆናል:: የእኛም ተቋም ደግሞ መስራት ያለበት ብዙ ስራዎች እንዳሉ አመላካች ነው::
ግን ጥራትን ከማረጋገጥ አንጻር ሸማቹ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል:: ማምረቻ ተቋሙ የሚቀጣው ወይም መስመር የሚይዘው፣ ተቆጣጣሪ አካላትም ጥቆማን የሚያገኙት ከሸማቹ ሲሆን ነው::
ለምሳሌ መድሃኒትን ብንወስድ የመቀመጫ ቦታው ምናልባት ቅዝቃዜው በተጠበቀ አልያም ሌላ ትዕዛዝ ይኖረዋል፤ ግን ይህንን ማነው ተግባራዊ የሚያደርገው? ስለዚህ ጥራት ሲባል ሁሉን አቀፍ ሆኖ እናገኘዋለን::
አዲስ ዘመን ፦የህብረተሰቡን ግንዛቤን በማሳደግ በኩል ኤጀንሲው የሰራው ስራ አለ?
አቶ እንዳለ፦ የኤጀንሲው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት በርካታ ስራዎችን ይሰራል፤ ለምሳሌ በመገናኛ ብዙኃን በቋሚነት ዓመቱን ሙሉ የምናስተላልፋቸው መልዕክቶች አሉ፤ የተለያዩ ብሮሸሮች ይበተናሉ፤ ሴክተር መስሪያ ቤቶችንና ክልሎችን በመሰብሰብ እንወያያለን፤ በጠቅላላው አቅም በፈቀደ መጠን ብዙ ስራዎችን ለመስራት ይሞከራል::
አገሪቱ የደረጃዎችን ቋንቋ የሚናገሩ ባለሙያዎች በጣም ያስፈልጓታል:: ምክንያቱም ፖሊሲ አውጪዎች ስለ ደረጃዎች ሳያውቁ ነው ቁጥጥር የሚያደርጉት:: ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዘንድ ያለው ግንዛቤ በጣም ያሳፍራል፤ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሩ ስለ ደረጃዎች የሚያውቀው ነገር የለም:: ኢንደስትሪ ባለሙያው ያውቃል ግን ተግባራዊ ማድረግ ላይ ወስንነቶች አሉበት:: በመሆኑም ሁሉም አንድ የደረጃዎች ቋንቋን ነው ማወቅ የሚጠበቅባቸው::
እኛ እኮ ወደ አረብ አገራት፣ አውሮፓና አሜሪካ ምርቶችን እንልካለን እዛ የላክናቸው እቃዎች መግባቢያ መንገዳቸው የደረጃዎች ቋንቋ ነው:: ይህንን ግን አቀላጥፈው የሚናገሩ ባለሙያዎች ያስፈልጉናል:: ይህንን ከአገር አልፎ እንደ አህጉርም ያመጣልናል ብለን የምናስበው ደግሞ እየገነባነው ያለነው የስልጠና ማዕከል ነው::
አዲስ ዘመን፦ ኤጀንሲው የመቅጣትስ ሀላፊነት ተሰጥቶታል?
አቶ እንዳለ፦ የመቅጣት ሀላፊነት የለውም:: ለምሳሌ የደረጃ ምልክት የሚሰራ አስተዳደራዊ ክፍል አለው:: በዚህም ማንም ፍቃድ ሳይሰጠው በምርቶቹ ላይ ምልክት የሚለጥፍ አካልን ይቆጣጠራል:: በዚህ የቁጥጥር ስራ ውስጥም ምልክቱን እንዲለጥፍ ማነው ፍቃድ የሰጠው የሚለውን በማጣራትና የሚመለከታቸው ተቋማትም ያልሰጡት ከሆነ ድርጅቱን የመጠየቅ ስራ ይሰራል::
በሌላ በኩል ደግሞ ሸማቹ ጥቆማ በሚያመጣበት ወቅት “ እንዲህ ዓይነት ምልክት ያለው ምርት ወደ ገበያ የገባ በመሆኑ ቁጥጥርና ክትትል ተደርጎ ሪፖርት እንዲደረግ” ብለን የመጻፍ መብት አለን::
አዲስ ዘመን ፦ በዚህ መልኩ እርምጃ የተወሰደባቸው ተቋማት ይኖሩ ይሆን?
አቶ እንዳለ፦ ብዙ አሉ፤ ለምሳሌ አስፈላጊውን ምልክት ያልለጠፈ ቆርቆሮ፣ መጠጥ ተይዘው ፋብሪካቸው ታሽጎ እርምጃ ተወስዷል::
አዲስ ዘመን፦ ደረጃዎች ኤጀንሲ ባይኖር ኖሮ እነዚህ ችግሮች ይፈጠሩ ነበር፤ መኖሩ ይህንን አድኗል የሚሉት ነገር አለ?
አቶ እንዳለ፦ ደረጃ ባይኖር ብለን ብናስብ ይገርማል፤ በምን ላስመስልልሽ አዎ አብዮት አደባባይ ያለ ትራፊክ መብራትና ትራፊክ ፖሊስ ዝም ብለሽ አስቢው:: የመኪኖች እንቅስቃሴ ምን ሊመስል እንደሚችል በአገሪቱ ደረጃዎች ባይኖር የሚፈጠረውም ተመሳሳይ ትርምስምስ ነበር::
ደረጃዎች ባይኖር ገበያው ላይ ከሶኬት አቅም እንኳን 50 ዓይነት ሊኖር ይችላል ፤ የእስያ አገራት “ የአንድ አገር መገለጫ የደረጃዎች መስፈርት ነው” ይላሉ:: ደረጃዎችን በትክክል ተግባራዊ ያደረጉ አገራት መንገዶቻቸው ምቹና ገልጽ ናቸው:: የመንገድ ዳር ምልክቶቻቸው ግልጽና በስነ ስርዓት ቦታቸውን ጠብቀው የተተከሉ ናቸው:: እያንዳንዱ ነገር ልቅም ያለ በመሆኑ ሁሉም ነገር በተረጋጋ ሁኔታ ይሰራል::
ባንኮች፣ የትራንስፖርት አገልግሎታቸው ሁሉ ከሰው ንክኪ ነጻና በሲስተም የበለጸጉ ናቸው፤ እኛ ዘንድ ደግሞ ደረጃዎች ባይኖር ብለን ስናስብ ሁልጊዜ መርዛማ ነገሮች እንበላለን፣ የተበከሉ መጫወቻዎች ለልጆቻችን እንገዛለን፣ ጊዜያቸው ያለፉ የመዋቢያና ሌሎች ምርቶች እንጠቀማለን ብሔራዊ ደህንነትን ሁሉ የሚፈታተንበት አጋጣሚ ይፈጠር ነበር፣ በመሆኑም ያለ መለኪያ ምንም ነገር መቆጣጠር አይቻልም::
ለምሳሌ የደም ግፊት የጤነኛ ሰው 120 በ 80 ነው ይህንን ያወቅነው መለኪያ ስላለ ነው:: ባይኖርስ ኖሮ ሰዎች ጤንነታቸውን አይቆጣጠሩም፤ ዝም ብለው ይኖራሉ፤ ችግርም ሲያጋጥማቸው ምን እንደሆኑ ሳያውቁ ያልፋሉ ማለት ነው::
አዲስ ዘመን ፦በደረጃዎች ቋንቋ ለመናገር ምን ይቀረናል?
አቶ እንዳለ፦ የበቁ የነቁ ባለሙያዎችን በየጊዜው ማውጣትና ወደ ኢንዱስትሪው ማስገባት፣ ለሸማቹ በቂ ግንዛቤ መፍጠር፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደረጃዎችን በደንብ ተረድተው ምርምር ማድረግ ይቀረናል::
አዲስ ዘመን፦ በቀጣይ ይህንን ዓይነት ስራ ሰርተን ደረጃዎችን በማረጋገጥ በኩል ለውጥ እናመጣለን የሚሉኝ ነገር ካለ?
አቶ እንዳለ፦ የመጀመሪያ እቅዳችን እያገባደድነው ያለነውን አካዳሚ ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቅና ወደ ስራ ማስገባት ነው:: ሌላው የአነስተኛና ጥቃቅን ፕሮግራሞችን መስራት፣ ስልጠናዎችን ማዘጋጀት በርካታ ያዘጋጀናቸውን ደረጃዎች ወደ ተግባር መቀየር የተለያዩ የግንዛቤ ማስፊያ ፕሮግራሞችን ወደ ከክልሎች ጋር የመስራት እቅድ አለ::እነዚህን አሳክተን ደግሞ በቀጣይ አገሪቱ ላይ በደረጃዎች ቋንቋ የሚናገሩ ብቁ ባለሙያዎችን እናፈራለን ብለን እናስባለን::
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ
አቶ እንዳለ፦ እኔም አመሰግናለሁ::
አዲስ ዘመን ረቡዕ ህዳር 24/2012
እፀገነት አክሊሉ