ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአገራችንን ሰላምና ደህንነት እንዲሁም የህዝቦችን አብሮነት አደጋ ላይ እየጣሉ ካሉት ችግሮች መካከል የጥላቻ ንግግር እና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት ዋነኞቹ ናቸው:: በጥላቻ ንግግርና በሃሰተኛ መረጃ ስርጭት ምክንያት የዜጎች ህይወት አልፏል፣ ንብረት ወድሟል::
ለዘመናት አብረው የኖሩ ህዝቦች ላይ መጠራጠር እንዲሰፍን፣ አለመተማመን እንዲነግስ በማድረግ አንድነታቸውን የማላላት ሁኔታዎች ተከስተዋል:: ይህ በዚህ ከቀጠለ አደጋው ከፍተኛ በመሆኑ መንግስት ህግ አውጥቶ ለመከላከል ጥረት እያደረገ ነው::
በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው “የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ” ረቂቅ ሕግ ችግሩን ለመከላከል መንግስት ከሚያከናውነው ተግባር አንዱ ነው:: ስለሆነም ይህን ረቂቅ አዋጅ በሃሳብ በማዳበር በፍጥነት ጸድቆ ስራ ላይ እንዲውል ማድረግ ተገቢ ነው::
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በጥላቻ ንግግርና በሀሰተኛ መረጃ ምክንያት በአገራችን ሚሊዮኖች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል:: በርካቶች በብሔራቸው ተለይተው ግፍ ተፈጽሞባቸዋል:: ንብረታቸው ወድሟል፤ ተዘርፏል:: አብያተ-ክርስቲያናት እና መስጊዶች ተቃጥለዋል:: የአገልጋዮችና የምዕመናን ደም ፈሷል:: ይህ ድርጊት ድጋሚ መፈጸም ስለሌለበት ሁሉም ዜጎች ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል::
ይህ ሁሉ ጥፋት የደረሰው በማህበራዊ የትስስር ገጾችና በሚዲያዎች አማካይነት አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ የሚያደርጉ፣ ብሄርን፣ ሃይማኖትን ወይም የፖለቲካ አስተሳሰብን መሰረት ያደረጉ የጥላቻና የሃሰት ወሬዎች በመሰራጨታቸው ነው:: ከዚህ የምንረዳው አደጋው ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ ነው:: አገራችን በሃሰተኛ ወሬ ስጋት ውስጥ ወድቃለችና ይህንን አደጋ ለመቀነስ ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት አለብን::
በረቂቅ አዋጁ ላይ ከሚሰነዘሩ ትችቶች መካከል ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ሊጋፋ ይችላል የሚለው አንዱ ነው:: ይህ ስጋት ተገቢ ቢሆንም ለሰው ልጅ ህይወት መቀጠፍ እና ንብረት መውደም ስጋት የሆነ ሀሳብን መገደብ ተገቢ ነው:: መብት ሁሌም ገደብ አለው:: ገደቡን ሲያልፍ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል መገንዘብ አስፈላጊ ነው:: ስሆነም አሁን ሀገራችንን ለአደጋ እያጋለጠ ያለውን ሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግርን መከላከልና ማውገዝ የግድ ይለናል::
የተረቀቀው ሕግ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የሚጋፋ እንዳይሆን ጥንቃቄ ያስፈልገዋል:: ምክንያቱም ሃሳብን በነጻነት መግለጽ መሰረታዊ ከሚባሉት መብቶች ውስጥ አንዱ ነው:: ይሁንና የሕዝብንና የአገርን ደህንነት አደጋ ላይ እስከሚጥል ድረስ ተለጥጦ የሚተገበር ሳይሆን ልጓም የሚበጅለት መብት መሆኑ መታወቅ አለበት::
ረቂቅ አዋጁ ባለፈው ሳምንት ለፓርላማ ሲቀርብ “ሃሳብን በነፃነት በመግለፅ ሽፋን የሚከሰቱ ጥላቻን፣ ማግለልን፣ ግጭትን፣ ጥቃትንና መሰል በግለሰቦችና በማህበረሰቡ መካከል ያሉትን መልካም ግንኙነቶች የሚያሳሱና የሚጎዱ ንግግሮችንና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን በህግ መከላከል ያስፈልጋል” በሚል ከአስፈጻሚው የቀረበው ማብራሪያም መነሻው ይኸው ነው::
ኢትዮጵያ የፈረመችውና እ.ኤ.አ. በ1965 ዓ.ም. የወጣው ሁሉንም ዓይነት የዘር ልዩነቶችን ለማስወገድ የተደረገው ዓለም አቀፍ ስምምነት አገሮች ብሔራዊ የበላይነትን የሚሰብኩ ወይም የዘር ጥላቻንና ልዩነትን የሚያራምዱ ተቋማትንና ንግግሮችን ለማስወገድ ሕግ ማውጣት እንዳለባቸው ያስገነዝባል::
እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ኢጣሊያ፣ ዴንማርክና ሌሎችም የአውሮፓ አገራት ከናዚ መንኮታኮት ማግስት የጸረ-ጥላቻ ንግግር ሕግ አውጥተዋል:: በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል ሕግ መውጣቱ ካሳለፍነው ችግር አንጻር ሲታይ ዘግይቷል ከሚባል ውጭ አስፈላጊነቱ ላይ ጥርጣሬ ሊኖር አይገባም::
የፖለቲካ መሪዎች፣ አክቲቪስቶች፣ የሚዲያ ተቋማት ባለቤቶችና ባለሙያዎች፣ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እና መላው የአገራችን ህዝቦች ለአገር ሰላምና ደህንነት ጠንቅ፣ ለህዝቦች አብሮነት አሜከላ የሆነውን የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ሥርጭት በመከላከል ረገድ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል:: ራሳቸውንም ከዚሁ ተግባር አርቀው በሌሎች ሲፈጸምም ማውገዝ አለባቸው:: ረቂቅ ህጉን በማዳበር በኩልም የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል::
አዲስ ዘመን ህዳር 24/2012