በ19ኛው ክፍለ ዘመን አውሮፓዊያን አፍሪካን በቅኝ በተቀራመቱበት ወቅት ነጻ የነበረችው አገር ኢትዮጵያ ደግሞ በተማከለ የፖለቲካ አገዛዝ ስር ስለመግባቷ፤ በዚህም ህዝቦቿ ወደውና ፈቅደው ሳይሆን በግዴታና በሀይል በአንድነት ስም በዘመናዊ የፖለቲካ ስርዓት ስር ስለመውደቃቸው የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያውና የትምህርት ሚንስትር ዴኤታ ዶክተር ገረመው ሁሉቃ ይናገራሉ::
14ኛውን የብሔር ብሔረሰቦች በዓል አስመልክቶ ትናንት በአዳማ በተካሄደው ሲምፖዚዬም ላይ ‹‹የኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ሥርዓት እና የህዝቦች ግንኙነት›› የሚል ጥናታዊ ጽሁፍ ለውይይት ያቀረቡት ዶክተር ገረመው፤ ዘመናዊ አስተዳደርን መመስረት በኢትዮጵያ ብቻ የተጀመረ አለመሆኑን፤ የኢትዮጵያ የዘመናዊ አስተዳደርና አንድነት ምስረታ ጉዞ በውህደት ሂደቱና ውጤቱ ላይ ችግር እንደነበረበት ይገልጻሉ::
‹‹ ይህ ሂደት ምንም እንኳን ህዝቡ ውህደትና አንድነቱን የማይጠላ ቢሆንም፤ ውህደቱ በሃይል ስለነበረ ውጤቱ ከፍተኛ ጭቆናና ብዝበዛ መሆኑ በህዝቦች ላይ ቅሬታን አሳድሯል:: ይህ የሆነውም አንድነቱ ህዝቦቹን ያሳተፈና ያማከለ ሣይሆን በገዢዎች ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ነው፤ አንድነቱ የህዝቦችን ማንነት ያማከለ ሳይሆን፤ መሬታቸውን፣ጋራውንና ሸንተረሩን ያማከለ ስለነበር፤ ህዝቦች በገዛ ቀያቸው ማንነታቸውን ተነጥቀው እንደሁለተኛ ዜጋ እንዲቆጠሩ ስላደረጋቸው ነው›› ብለዋል::
ዶክተር ገረመው፤ ህዝቦች የባህልና የቋንቋ ማንነታቸውን፣ የእምነትና የኢኮኖሚ ነጻነታቸውን፣ እራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸውን ያሳጣቸው፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ የተሳሳቱ የበላይነትና የበታችነት ትርክቶች መኖራቸው በህዝቦች ግንኙነት ላይ መጥፎ አሻራ አስቀምጦ ማለፉን አብራርተዋል::
የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎችም ይህን ሀሳብ ይጋራሉ:: ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ብርሃን ደሳለኝ እንደሚሉት፤ የኦሮሞ ህዝብ አቃፊና አሳታፊ ብቻ ሳይሆን የሰላምና የፍቅር ህዝብ ነው:: ዛሬ አንተ አማራ፣ ትግሬ፣ ሶማሌ፣ ወዘተ… መባባል ሳይጀመር በፊት ቀድሞ ከሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በአንድነትና በፍቅር የኖረ ህዝብ ነው::
ይህ ህዝብ ባለው የአቃፊነትና የሰላም ብሎም የፍቅር እሴት ታግዞ ለኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነት ሊሰራ፤ የሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን በአንድነት እውን የማድረግ ጉዞው እንዲሳካ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል:: ከቤተሰብ ጀምሮ ህዝብ እንደ ህዝብ መንግስትም እንደ መንግስት ሃላፊነቱን ወስዶ ሊሰራ፤ የታሪክ ነጋሪዎችን እውነቱ ላይ አተኩረው በወጉ ሊተርኩና ሊያሳውቁ ያስፈልጋል::
ዶክተር ገረመውም በጽሑፋቸው ይህንኑ ያጠናክራሉ:: እርሳቸው እንደሚያብራሩት፤ በዘመናት ውስጥ የአንዱ ብሔር ቋንቋ ከሌላው የሚበልጥ አስመስለው ማቅረብ፤ አንዱ ብሄር ከሌላው በላይ የሰለጠነ በማስመሰል በህዝቦች መካከል ጥርጣሬን ማስፈን፤ አንዱ ብሄር ከሌላው በላይ ኢትዮጵያዊ የሆነ አስመስሎ ማስቀመጥ፤ የህዝቦችን ታሪክ ማዛባት፣ የውሸት ታሪክ መጻፍና ማስተማርን የመሳሰሉ አደገኛ አስተሳሰቦች ሲራመዱ ቆይተዋል::
ይህ ደግሞ በህዝቦች መካከል ጥርጣሬን ከመፍጠሩ ባለፈ ሕዝቦች በዜግነታቸው ላይ እምነት እንዲያጡ፤ ሕዝቦች በአንድነት ብሎም በአንድ ልብ በሀገራቸው ሁለንተናዊ ልማትና ሠላም ላይ እንዳይሳተፉ የሚያደርግ፤ አገርንም የሚጎዳ ተግባር ነው::
እንደ ዶክተር ገረመው ገለጻ፤ በመሬት ላይ ያለው እውነታ ከሚነገረውና ከሚጻፈው የተዛባ ታሪክ የተለየ ነው:: ኢትዮጵያ አንዱ የበላይ አንዱ የበታች የሆነባት ሳትሆን የሁሉም የእኩልነት ምድር ናት:: ከምንም በላይ የኢትዮጵያ አንድነት የሁሉም ህዝቦችዋ የረዥም ጊዜ ግንኙነት ውጤት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል::
ይህ በብዝሃነት እሴት የተገነባ የህዝቦች አንድነት እንዲጠናከርም የተለያዩ እሴቶች፣ አመለካከቶች እና አስተሳሰቦች መኖራቸውን አምኖ መቀበል እና ዕውቅናም መስጠት፤ ልዩነትን ማክበር፤ በመርህ ላይ የተመሠረተ ግንኙነትን ማጠናከር፤ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ልማቶችን ማስፋፋትና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልን ማስፈን ያስፈልጋል::
ዶክተር ገረመው በግጭቶች ላይ አተኩሮ የሚከናወኑ ጥናቶችና በህዝቦች አንድነት ላይ የተንጠለጠሉ የዘርፉ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች ትረካ በሚዛኑ ሊቃኝና አገራዊ አንድነትን በሚያጎሉ የበዙ እሴቶች ላይ ሊያተኩር እንደሚገባው መክረዋል::
የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የቋንቋ፣ የባህል፣ የሃይማኖትና የማንነት ብዝሃነት ያለባት አገር ናት:: ላለፉት በርካታ ዓመታት የአንድ ቋንቋ የበላይነት ነግሶ የቆየበት፤ የተወሰኑ ህዝቦች ታሪክና የተዛቡ ትርክቶች ሲነገሩባት ቆይተዋል::
ነገር ግን ኢትዮጵያ በሁሉም ህዝቦች እዚህ የደረሰች፤ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አገር መሆኗን ማወቅ፤ በዚያው ልክ እነዚህ ህዝቦች በኢትዮጵያ እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት ኖሯቸው በአንድነት የበለጸገች ኢትዮጵያን የሚገነቡበት እድልን ለመፍጠር መስራት ይገባል::
አፈ ጉባኤዋ ‹‹በዓሉ በጭፈራና በባህል ትዕይንት ታጅቦ እንዲከበር ከማድረግ ባለፈ፤ ልዩነታችን ውበታችን እንደሆነ፣ በልዩነት ውስጥ ጠንካራ አንድነት እንዳለ፣ በጋራ የመስራትና ተቻችሎ የመኖር እሴቶች ጎልተው የሚታዩበት መሆኑን መገንዘብ ይገባል::
ነገር ግን ይህ በዓል የሚከበረው አገሪቱ በለውጥ ጉዞ ውስጥ ባለችበትና ለውጡም በብዙ መልኩ እየተፈተነ ባለበት ወቅት እንደመሆኑ፤ ለውጡ ቀጣይነት እንዳይኖረው የሚፈልጉና ለዚሁም የሚሰሩ ሃይሎች ከውስጥም ከውጭም መኖራቸውን ተገንዝቦ የህዝቦችን በጋራ ቆሞ መስራት የሚጠይቅ ነው›› ብለዋል::
እንደ አፈ ጉባኤዋ ማብራሪያ፤ የኦሮሞ ህዝብም ሆነ መላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አንድነታቸውን በማጠናከር በጋራ ጥረታቸው ያመጡትን ለውጥ ለማስቀጠል ተናብበው ሊሰሩ ይገባል:: ምክንያቱም ኢትዮጵያ የብዙ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ ማንነቶችና ሃይማኖቶች ያላቸው ህዝቦች ብትሆንም ይህ ብዝሃነት ግን ተጠላልፎ አንድነትን በሚያጠፋ ልዩነት የታጠረ ሳይሆን፤ በብዝሃነት ደምቆ አንድነትን የሚያጸና እንደ ጠንካራ ድር መሆኑን መገንዘብ ይገባል::
ህዝቦች በዚህ በዓል ሲገናኙ እነዚህን ባህሎች የማወቅ፣ እያወቀም የመቀራረብ፣ በመቀራረብ ውስጥም ተቻችሎ የመኖር እሴቶቹን ተወራርሶ የሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን የመፍጠር ሂደትን የማሳካት ይሆናል::
አዲስ ዘመን ህዳር 24/2012
ወንድወሰን ሽመልስ